በፈረንሳይ በጽንስ ማቋረጥ ለሞቱ ሴቶች ሐውልት እንዲቆም የምትታገለው ታዋቂ ደራሲ

"የዚያ ፅንስ ማቋረጥ እያንዳንዱ ቅጽበት ለእኔ አስገራሚ ነበር" ትላለች አኒ ኤርናክስ።
የፈረንሳዩ የኖቤል ሥነ ጽሑፍ ተሸላሚ በአውሮፓውያኑ 1963 ሕይወቷን ሊቀጥፍ ስለተቃረበ ሕገወጥ ጽንስ ማቋረጥ እያወራች ነው።
የ23 ዓመት ተማሪ ነበረች፤ ፀሐፊ የመሆን ምኞትም ነበራት። ነገር ግን በቀን ሠራተኝነት እና በመደብር ጠባቂነት በሚተዳደረው ቤተሰብ ውስጥ ወደ ዩኒቨርሲቲ የገባች የመጀመሪያዋ ልጅ እንደመሆኗ መጠን የወደፊት ሕይወቷ ከእጇ እያመለጠ እንደሆነ ይሰማት ነበር።
"የፍቅር ግንኙነት ጠለፈኝ። እናም በውስጤ እያደገ የመጣው ነገር የማኅበራዊ ውድቀት የሆነው መገለል እንደሆነ ተመለከትኩት" ስትል በኋላ ላይ ጽፋለች።
የወር አበባዋ የሚመጣበትን ቀን እየጠበቀች የጻፈችው የዕለት ማስታወሻ መዝገቧ መግቢያ 'ምንም የለም' በሚል ቃል የሰፈረበት ነበር።
የነበሯት አማራጮች ራሷ ጽንስ ማቋረጥ ወይም ዶክተር መፈለግ ወይም በየስርቻው ጽንስ የሚያቋርጥ ባለሙያ ማግኘት ነበሩ። የመጨረሻው አማራጭ ብዙውን ጊዜ ሴቶች፣ "የክፉ ቀን ደራሽ" እያሉ የሚጠሯቸው ናቸው።
ነገር ግን ምንም ዓይነት መረጃ ማግኘት አይቻልም። ጽንስ ማቋረጥ ሕገወጥ ስለነበር ማንኛውም ሰው ነፍሰ ጡሯን ጨምሮ ወደ እስር ቤት ልትወረወር ትችላለች።
የ85 ዓመቷ አዛውንት በወቅቱ "ምሥጢር ነበር፣ ማንም ስለዚህ ጉዳይ አያወራም" ትላለች። "የዘመኑ ልጃገረዶችም ጽንስ ማቋረጥ እንዴት እንደሚፈጸም በጭራሽ አያውቁም ነበር።"
ዝምታን መስበር
ኤርናክስ እንደተተወች ቢሰማትም ቆራጥ ግን ነበረች። ስለዚያ ጊዜ ስትጽፍ፣ ይህንን ችግር ለመቋቋም ምን ያህል ጥንካሬ እንደሚያስፈልግ ማሳየት ነበር የፈለገችው።
"በእርግጥ የሕይወት እና የሞት ግብግብ ነበር" ትላለች።
ኤርናክስ በቀላል እና በግልጽ ምሥል ከሳች ቋንቋ "ሃፕኒንግ" በተሰኘው መጽሐፏ ውስጥ ክስተቶቹን በዝርዝር ገልጻቸዋለች።
የሕክምና ባለሙያዎች ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው እና ራሷ ማድረግ ባለመቻሏ በመጨረሻ በሕገወጥ መንገድ ጽንስ የሚያቋርጥ ሰው አገኘች።
"ዝርዝሩ ነው የሚያስፈልገው" ትላለች።
"ከወላጆቼ ቤት ያመጣሁት የሹራብ መሥሪያ ነበር። በመጨረሻም ጽንሱ ሲወርድ፣ የእንግዴ ልጁ መውጣት እንዳለበት አላውቅም ነበር።"
በሕገወጥ መንገድ ጽንሱ ከተቋረጠ በኋላ በዩኒቨርስቲው በሚገኘው የመኝታ ክፍሏ ብትደርስም ብዙ ደም ስለፈሰሳት ወደ ሆስፒታል ተወሰደች።
"በሴት ላይ ሊደርስ የሚችለው እጅግ የከፋው ጥቃት ነበር። ሴቶች በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዴት እንዲያልፉ መፍቀድ ቻልን?" ትላለች።
"ይህን ሁሉ ለመግለጽ አላፍርም። በታሪክ ውስጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር እያደረግኩ እንደሆነ በሚሰማ ስሜት ነው የተነሳሳሁት።"
"ሕገወጥ ጽንስ ማቋረጥ ላይ የነገሰው ዝምታ ወደ ሕጋዊ ጽንስ ማቋረጥም እንደተሸጋገረ ተገነዘብኩ። ስለዚህ ለራሴ 'ይህ ሁሉ ይረሳል' አልኩ።"
በአውሮፓውያኑ 2000 የታተመው ሃፕኒንግ አሁን በፈረንሳይ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የተካተተ ሲሆን፣ በብዙ ሽልማቶች አሸናፊ መሆን የቻለ ፊልምም ተሠርቶለታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኤርናክስ ወጣቶች ስለ ሕገ ወጥ የጽንስ ማቋረጥ አደጋዎች ማወቅ እንዳለባቸው ተናግራለች።
ምክንያቱም ፖለቲከኞች አንዳንድ ጊዜ ሕጋዊ የጽንስ ማቋረጫ መዳረሻዎችን ለመገደብ ስለሚፈልጉ ነው።
በቅርቡ በአንዳንድ የአሜሪካ ግዛቶች እና ፖላንድ ያጋጠሙትን ክስተቶች ለዚህ በማሳያነት ትጠቅሳለች።
"አካልን መቆጣጠር እና በዚህም ምክንያት የመውለድን መብት መቆጣጠር መሠረታዊ ነፃነት ነው" ትላለች።
ጽንስ ማቋረጥ አሁን በፈረንሳይ ሕጋዊ መብት ነው።
በዓለም ላይ ይህንን ዋስትና የሰጠች የመጀመሪያዋም አገር ነች።
ነገር ግን ኤርናክስ ሕገ ወጥ ጽንስ ማቋረጥን ተከትሎ ለሞቱት ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ሴቶች እውቅና እንዲሰጣቸው ትፈልጋለች።
የሞታቸው መንስኤ ብዙ ጊዜ ተደብቆ ስለሚቀር የሞቱት ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ በትክክል ማንም አያውቅም።
በ1975 ፈረንሳይ ጽንስ ማቋረጥን ከመፍቀዷ በፊት በየዓመቱ ከ300 ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ሴቶች በሕገ ወጥ መንገድ ጽንስ እንደሚያቋርጡ ይገመታል።
"በፈረንሳይ ውስጥ ለማይታወቀው ወታደር እንደተሠራለት ሁሉ የመታሰቢያ ሐውልት ሊኖራቸው እንደሚገባ አስባለሁ" ትላለች።
ኤርናክስ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ለፓሪስ ከንቲባ እንዲህ ዓይነቱን የመታሰቢያ ሐውልት እንዲሠራ ለማሳመን የተቋቋመው ቡድን አካል ነበረች።
ነገር ግን ማንኛውም እርምጃ መወሰድ አለመወሰዱ የሚወሰነው በመጋቢት ወር በሚካሄደው ምርጫ ውጤት ላይ ነው።
ርዕሰ ጉዳዩ አሁንም የማስደንገጥ ኃይል አለው።
የኤርናክስ "ዘ ይርስ" የተሰኘው መጽሐፍ ወደ ቴአትር ተቀይሮ ለመድረክ ሲበቃ ተመልካቾች የጽንስ ማቋረጥ ትዕይንቱ ሲታይ የተወሰኑት ተደግፈው ይወጣሉ።
ኤርናክስ አንድ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር "እኔ ልሆን እኮ እችላለሁ!" እንዳላት በመግለጽ አንዳንድ አስቂኝ ምላሾች እንዳጋጠሟት ትናገራለች።
"ይህ የሴቶችን ኃይል በተመለከተ ያለውን ያልተለመደ ፍርሃት ያሳያል" ትላለች።
ኤርናክስ በሥ���ዋ ውስጥ የራሷን ሕይወት በድፍረት ትበረብራለች።
መጽሐፎቿ ብዙዎች ያጋጠሟቸውን አሳፋሪ ርዕሰ ጉዳዮች ይዳስሳሉ፣ ነገር ግን ጥቂቶች ብቻ ስለ ወሲባዊ ጥቃት፣ ስለ ጨለማ የቤተሰብ ምሥጢሮች፣ እናትን በአልዛይመር በሽታ ስለ ማጣት ለመናገር ይደፍራሉ።
"እነዚህ ነገሮች እኔ ላይ ደርሰውብኛል፤ ደግሜ ልተርካቸው እችላለሁ" በማለት "ሃፕኒንግ"ን መጻፏን ትገልጻለች።
በ"ኤ ገርልስ ስቶሪ" በሚለው መጽሐፏ ደግሞ፣ አንድ በዕድሜ የገፋ የካምፕ ኃላፊ ጥቃት እንደሰነዘረባት በመጥቀስ የመጀመሪያ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ልምዷን ትተርካለች።
በወቅቱ ምን እየተከናወነ እንዳለ አልገባትም ነበር።
እና "ምን ማድረግ እንዳለባት የማታውቅ እባብ ፊት እንዳለች አይጥ" እመስል ነበር ትላለች።
አሁን አስገድዶ መድፈር እንደሆነ ታውቃለች፤ ነገር ግን መጽሐፏ ይህንን ቃል እንደማያካትት ትናገራለች።
"ምክንያቱም ለእኔ አስፈላጊ የሆነው ነገር ያለ ፍርድ የሆነውን በትክክል መግለጽ ነው።"

የፎቶው ባለመብት, Gamma-Rapho via Getty Images
እነዚህ ክስተቶች ኤርናክስ ከ16 ዓመቷ ጀምሮ ትጽፋቸው በነበሩ በግል ማስታወሻ ደብተሮቿ ውስጥ ተመዝግበዋል። ካገባች በኋላ፣ እነዚህ ውድ ዕቃዎች በእናቷ ቤት በሚገኝ ሣጥን ውስጥ ከጓደኞቿ ጋር ከተጻፈቻቸው ደብዳቤዎች ጋር ተቀምጠዋል።
ነገር ግን በ1970 የኤርናክስ እናት ከእሷና ከቤተሰቧ ጋር ለመኖር ሲመጡ፣ ከሳጥኑ በስተቀር ሌላውን ነገር ሁሉ ይዘው መጡ።
"እሷ እንዳነበበቻቸው እና መጥፋት እንዳለባቸው እንዳሰበች ተረድቻለሁ" ትላለች ኤርናክስ። "ሙሉ በሙሉ ተጸይፋው መሆን አለበት።"
ሊቆጠር የማይችል ኪሳራ ነበር፣ ነገር ግን ኤርናክስ ግንኙነታቸውን በከንቱ ክርክር ማበላሸት አልፈለገችም። እናቷ ያለፈውን ለማጥፋት ያደረጉት ሙከራ፣ አልተሳካም።
ኤርናክስ በ"ኤ ገርልስ ስቶሪ" መፅሐፍ ላይ "እውነት ከእሳት ላንቃ ተረፈች" ስትል ጽፋለች።
ማስታወሻ ደብተሮቿን ሳታገላብጥ፣ በትዝታዎቿ ላይ ብቻ መተማመንን በቂ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ትላለች።
"እንደምፈልገው ያለፈውን ጊዜዬን ማየት እችላለሁ። ልክ ፊልም እንደማየት ነው።"
ከጦርነቱ በኋላ በነበረው ትውልድ የጋራ ታሪክ ላይ የሚያተኩረውን 'ዘ ይርስ" የተሰኘውን መጽሐፏን የጻፈችውም በዚህ መንገድ ነው።
"'ከጦርነቱ በኋላ ምን ይመስል ነበር?' ብዬ ራሴን መጠየቅ ነበረብኝ። እናም በዐይነ ሕሊናዬ ማየትና መስማት እችላለሁ" ትላለች።
እነዚህ ትዝታዎች የራሷ ብቻ ሳይሆኑ በዙሪያዋ ያሉ ሰዎች የሚጋሩዋቸው ጭምር ናቸው። ኤርናክስ ያደገችው በኖርማንዲ በሚገኘው የወላጆቿ ካፌ ውስጥ ሲሆን፣ ቤቱ ከጠዋት እስከ ማታ ድረስ በደንበኞች ይከበብ ነበር።
ይህ ማለት ደግሞ ከልጅነቷ ጀምሮ ስለ አዋቂ ሰዎች ችግር መስማት ነበረባት ማለት ነው፤ ይህም ያሳፍራታል።
"የክፍል ጓደኞቼ ስለ ዓለም እኔ የማውቀውን ያህል ማወቃቸውን እርግጠኛ አልነበርኩም" ትላለች።
"ስለ ሰከሩ ሰዎች፤ ከመጠን በላይ ስለሚጠጡ ወንዶች ማወቄ አስጠልቶኝ ነበር። ስለዚህ በብዙ ነገሮች አፍር ነበር።"

የፎቶው ባለመብት, Hulton Archive via Getty Images
"ሕዝቤን ለመበቀል እጽፋለሁ"
ኤርናክስ በተቆራረጠ እና ባልተሸላለመ መልኩ ትጽፋለች።
በአንድ ወቅት ስለ አባቷ መጻፍ ስትጀምር እንዳዳበረችው ትናገራለች። ከሠራተኛው መደብ የተገኘ የዘወትር ቋንቋ በቂው የሆነ ሰው ነው አባቷ።
በ22 ዓመቷ፣ በማስታወሻ ደብተሯ ላይ "ሕዝቤን ለመበቀል እጽፋለሁ" ስትል ጽፋለች።
ይህ ዓረፍተ ነገር መሪ ብርሃኗ ሆኖ አገልግሏታል።
ዓላማዋ "በተወለደችበት ጊዜ ከማኅበራዊ ደረጃ ጋር የተያያዘውን ማኅበራዊ ኢፍትሃዊነት ማስተካከል" እንደ ነበር በ2022 በኖቤል ሽልማቷ ወቅት ባደረገችው ንግግር ላይ ገልጸዋለች።
ከገጠር የሠራተኛው መደብ ሕይወት ወደ መካከለኛ ደረጃ ወዳለው የከተማ ሕይወት ያደረገችውን ሽግግር 'የአገር ውስጥ ስደተኛ' ብላ ትጠራዋለች።
ባለፉት 50 ዓመታት በፓሪስ ዙሪያ ከተገነቡት አምስት "አዲስ ከተሞች" አንዷ በሆነችው በሰርጊ ትኖር ነበር።
እዚያም ከባለቤቷ እና ከልጆቿ ጋር ነው የኖረችው።
በ1975 በግንባታ ላይ የነበረው ከተማ እየሰፋ መምጣቱን ስትመለከት ቆይታለች።
"በዚህ ቦታ ሁላችንም እኩል ነን፤ ከፈረንሳይ ውስጥም ሆነ ከውጭ የመጡ ስደተኞች የሚገኙበት" ትላለች።
"በማዕከላዊ ፓሪስ ብኖር ኖሮ በፈረንሳይ ማኅበረሰብ ላይ ተመሳሳይ አመለካከት ይኖረኝ ነበር ብዬ አላስብም።"
አሁን የምትኖርበትን ቤት የገዛችው ለመጀመሪያ ጊዜ ካገኘችው የሥነ ጽሑፍ ሽልማት ገንዘብ ነው።
ከተደራሲዎቿ ጋር ያላት ግንኙነት ለኤርናክስ አስፈላጊ ነው።
ባለትዳር ከሆነው የሶቪየት ዲፕሎማት ጋር የነበራት የፍቅር ግንኙነት በአውሮፓውያኑ 1989 ሲያበቃ፣ ስለሱ መጽሐፍ መጻፏ መልሳ እንድታገግም ረድቷታል።
"ኤ ሲምፕል ፓሽን" የተሰኘው መጽሐፍ ከታተመ በኋላ፣ መጽናኛ ቃሎች እና አስተያየቶች ከአንባቢዎቿ አግኝታለች።
"ድንገት ከሴቶችም ከወንዶችም ብዙ መልዕክቶችን መቀበል ጀመርኩ፤ እነሱም ስለራሳቸው የፍቅር ግንኙነት ነግረውኛል። ሰዎች ስለ ምሥጢራቸው እንዲገልጹ የፈቀድኩ ያህል ተሰማኝ" ትላለች።
ሁሉንም ጊዜ የሚወስድ የፍቅር ግንኙነት ውስጥ መግባቱ የተወሰነ ሃፍረት እንደሚያስከትል አክላ ተናግራለች።
"ግን በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ ይህ በሕይወቴ ውስጥ እጅግ አስደናቂ ትዝታዬ ነው ማለት እፈልጋለሁ" ብላለች።















