እስራኤል በፈፀመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 32 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ

በጋዛ ሰርጥ የተፈፀመ ጥቃት ፍንዳታ የሚያሳይ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኻን ዩኒስን ጨምሮ በጋዛ ሰርጥ በርካታ ጥቃቶች መፈፀማቸው ተዘግቧል

እስራኤል ቅዳሜ ዕለት በጋዛ ሰርጥ በፈፀመቻቸው ተከታታይ የአየር ጥቃቶች ቢያንስ 32 ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናገሩ።

በሐማስ የሚመራው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ እንዳለው በጥቃቱ ከተገደሉት ሰዎች መካከል ሕፃናት እና ሴቶች ይገኙበታል።

ኤጀንሲው ጨምሮ በአንደኛው ጥቃት መሳሪያ የታጠቀ ሄሊኮፕተር በደቡባዊ የጋዛ ከተማ ኻን ዩኒስ ተፈናቃዮች የተጠለሉበትን ድንኳን መትቷል ብሏል።

ፍልስጤማውያን የአሁኑ ጥቃት በአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አደራዳሪነት ስምምነት ላይ የተደረሰው የተኩስ አቁም ሁለተኛው ምዕራፍ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ "የተፈፀመ ከባዱ ጥቃት" ሲሉ ገልጸውታል።

የእስራኤል ጦርም "ሐማስ አርብ ዕለት ስምምነቱን ጥሷል" ሲል ምላሽ ለመስጠት በርካታ ጥቃቶችን እንደፈፀመ አረጋግጧል።

እስራኤል እና ሐማስ ስምምነቱ ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ የተኩስ አቁሙን በመጣስ እርስ በእርስ ይካሰሳሉ።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል በሰጠው መግለጫ እንዳለው በጥቅምቱ ስምምነት መሠረት የእስራኤል ኃይሎች ተሰማርተው በሚገኙበት "ምሥራቅ ራፋህ ከመሬት ሥር ባለ የሽብር መሠረተ ልማት ስምንት አሸባሪዎችን" ለይቷል።

በመሆኑም ከእስራኤል የፀጥታ ተቋም ጋር በመሆን በሰርጡ ሐማስ ይገለገልባቸዋል ያላቸውን "አራት ወታደራዊ አዛዦች እና ሌሎች ተጨማሪ አሸባሪዎችን እንዲሁም የጦር መሣሪያ ማከማቻዎችን፣ ማምረቻዎችን እና መተኮሻ ጣቢያዎችን" ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ኢላማዎችን መምታቱን መከላከያ ኃይሉ ገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሐማስ በበኩሉ ጥቃቱን አውግዞ አሜሪካ አስቸኳይ እርምጃ እንድትወስድ አሳስቧል።

" እነዚህ በተደጋጋሚ የሚፈፀሙ ጥሰቶች" የእስራኤል መንግሥት "በሰርጡ ላይ ጭካኔ የተሞላባት የዘር ማጥፋት መፈፀሙን እንደቀጠለ ያረጋግጣሉ" ብሏል።

በጥቃቱ የተገደሉት የኻን ዩኒስ ተፈናቃዮች እንደሆኑም ጠቅሷል። የሲቪል መከላከያ ቃል አቀባይም ጥቃቱ የመኖሪያ ሕንፃዎችን ፣ ድንኳኖችን ፣ መጠለያዎችን እና የፖሊስ ጣቢያዎችን መምታቱን ጨምሮ ገልጿል።

በጋዛ ከተማ የሚገኛው ሺፋ ሆስፒታል በመኖሪያ ሕንፃ ላይ የተፈፀመው ጥቃት ሦስት ሕፃናት እና ሁለት ሴቶችን መግደሉን ገልጿል።

ከጋዛ የወጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎችም ከሕንፃ ፍርስራሽ ውስጥ በርካታ አስከሬኖች ሲወጡ አሳይተዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመው የእስራኤል መከላከያ ኃይል በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የመጨረሻውን የእስራኤል ታጋች አስክሬን ማግኘቱን ተከትሎ እሁድ ዕለት በግብፅ በኩል ያለው የራፋህ ድንበር ከተከፈተ በኋላ ነው።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥቃቱን ማውገዙ የተዘገበ ሲሆን ሁሉም አካላት ከመሰል ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል።

አንደኛዋ የተኩስ አቁሙ አሸማጋይ የሆነችው ኳታር በበኩሏ "እስራኤል በተደጋጋሚ የምትፈፅመውን ጥሰት" አውግዛለች።

በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ጦርነት የተጀመረው በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7፣ 2023 በሐማስ በተመራ ጥቃት በደቡባዊ እስራኤል ክፍል 1 ሺህ 200 ሰዎች መገደላቸውን እና 251 ሰዎች መታገታቸውን ተከትሎ ነበር።

በዚህም እስራኤል በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ የከፈተች ሲሆን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንዳለው ከ71 ሺህ 660 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል። ከእነዚህ መካከል ቢያንስ 509 የሚሆኑት የተገደሉት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተጀመረ በኋላ ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ እንደሆነ ገልጿል።