ቻይ��� ድምጿን አጥፍታ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ውድድሩን እየመራች ነው?

የዲፕሲክ እና የኩዌን መተግበሪያ አርማዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በየወሩ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች ፒንተረስት የተባለውን ድረ-ገፅ እና መተግበሪያ ይጠቀማሉ።

ፒንተረስት በሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ/ኤአይ) በሚሠሩ ምሥሎች የተሞላ ሆኗል።

ምንም እንኳ ፒንተረስት የአሜሪካ ኩባንያ ይሁን እንጂ ድርጅቲ ከቻይና ኤአይ ሞዴሎችን በመጠቀም የተጠቃሚዎችን ፍላጎት ለሟሟላት እየሞከረ ነው።

"ፒንተረስትን በኤአይ የሚታገዝ የመገበያያ እርዳታ ሰጭ አድርገነዋል" ይላሉ የኩባንያው ኃላፊ ቢል ሬዲ።

መቀመጫውን ሳን ፍራንሲስኮ ያደረገው ፒንተረስት የአሜሪካ የኤአይ ኩባንያዎችን መጠቀም ይችላል።

ነገር ግን የቻይናው ዲፕሲክ አር-1 ሞዴል ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት መባቻ ይፋ ከተደረገ በኋላ የቻይና ኤአይ ቴክኖለጂ የፒንተረስት አካል መሆን ጀምሯል።

ሬዲ 'የዲፕሲክን መምጣት' ሁኔታዎችን የቀየረ ነው ይላሉ።

"ለሁሉም ክፍት እንዲሆን (ኦፕን ሶርስ) አድርገውታል። በዚህ ምክንያት ሌሎችም የእነሱን ሞዴል ተከትለዋል" ይላሉ።

ሌሎችም ቻይናዊያን ኤአይ ሞዴሎች ተከታትለው መጥተዋል። የአሊባባው ኩዌን፣ የሙንሹት ሞዴል የሆነው ኪሚ የሚጠቀሱ ሲሆኑ፣ የቲክቶክ ፈጣሪ የሆነው ባይትዳንስም ተመሳሳይ ቴክኖሎጂ ይዞ ለመምጣት እየሞከረ ነው።

የፒንተረስት የቴክኖሎጂ ኦፊሰር የሆኑት ማት ማድሪጋል እንደሚሉት የእነዚህ ሞዴሎች ጥንካሬ የትኛውም ኩባንያ አውርዷቸው እንደፍላጎቱ ሊጠቀማቸው መቻሉ ነው።

የቻትጂፒቲ ባለቤት የሆነው ኦፕንኤአይ እና ሌሎች የአሜሪካ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ኩባንያዎች ግን ይህን አገልግሎት በነፃ አይሰጡም።

'ፈጣን እና ርካሽ'

የቻይና የኤአይ ሞዴሎችን የሚጠቀመው ፒንተረስት ብቻ አይደለም።

የፎርቹን 500 ኩባንያ የሚባሉ በርካታ ድርጅቶች የቻይና ሰው ሰራሽ አስተውሎቶችን ይጠቀማሉ።

የኤርቢኤንቢ ጥምር መሥራች የሆነው ብራያን ቼስኪ ኩባንያው ለደንበኞች ግንኙነት አገልግሎት የአሊባባው ኩዌን ላይ "ጥገኛ" እንደሆነ ባለፈው ጥቅምት ለብሉምበርግር ተናግሮ ነበር።

ለዚህ ደግሞ ሦስት ምክንያቶች ይሰጣል - "በጣም አሪፍ" ነው "ፈጣን እና ርካሽ" ነው ይላል።

ሀጊንግ ፌስ የተባለው ተሠርተው የተቀመጡ የኤአይ ሞዴሎች ማውረጃ የሆነው ድረ-ገፅ ከሜታ እና ከአሊባባ ሳይቀር የኤአይ ሞዴሎችን ይሸጣል።

የድርጅቱ ሠራተኛ የሆነው ጄፍ ቦድዬር ወጣት የቢዝነስ ፈጣሪዎች ከአሜሪካ ይልቅ የቻይና ኤአይ የሚጠቀሙት ዋጋው ርካሽ በመሆኑ ነው ይላል።

ባለፈው መስከረም ኩዌን የሜታውን ላማ በመብለጥ ሀጊንግ ፌስ ላይ በርካታ ሰዎች ያወረዱት የኤአይ ሞደል መሆን ችሏል።

ሜታ፤ ላማ 4 የተባለ ለሁሉም ክፍት የሆነው የኤአይ ሞዴል ባለፈው ዓመት ይፋ ደያረገ ሲሆን በአሊባባ፣ በጉግል እና በኦፕንኤአይ አማካይነት የሠለጠነ አዲስ ሞዴል በቅርቡ ለአገልግሎት እንደሚውል ይጠበቃል።

ኤርቢንቢ ከቻይና በተጨማሪ የአሜሪካ ኤአይ እንደሚጠቀም ይናገራል። የደንበኞች መረጃ ለእነዚህ የኤአይ ኩባንያዎች ተላልፎ አይሰጥም ይላል።

የቻይና ስኬት

በ2025 ምንም እንኳ የአሜሪካ ቴክኖሎጂዎች በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች ቢመድቡም የቻይና ኩባንያዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል።

"አሁን ምርጥ የሚባለው ሞዴል ለሁሉም ክፍት የሆነ (ኦፕን ሶርስ) ነው" ይላል ቦዲዬር።

ባለፈው ወር የስታንፈርድ ዩኒቨርሲቲ ያወጣው መረጃ የቻይና ኤአይ ኩባንያዎች "የአሜሪካዎቹን ደርሰዋል፤ ኧረ እንደውም ሳይቀድም አይቀርም" ይላል። ብልጫው በአቅማቸው እና የሚጠቀማቸው ሰው ብዛትን ጨምሮ ነው።

የሜታ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኒክ ክሌግ የአሜሪካ ኤአይ ኩባንያዎች ትኩረታቸው ኤአይ አንድ ቀን ከሰዎች በበለጠ ማሰብ ይጀምር ይሆን የሚለው ጥያቄ ነው ይላሉ።

የሜታው ባለቤት ማርክ ዛከርበርግ 'ሱፐርኢንተለጀንስ' ያለውን ሐሳብ እውን ለማድረግ ቢሊዮን ዶላሮች እንደሚያፈስ ቃል ገብቷል።

ባለሙያዎች ይህ የተለጠጠ ዕቅድ ነው በማለት ቻይና የኦፕን ሶርስ ኤአይ ሜዳውን እንድትቆጣጠረው አስችሏታል ይላሉ።

"ቻይና የቴክኖሎጂ ውድድሩን ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ብዙ እያደረገች ነው" ይላሉ ኒክ።

የስታንፈርድ ትንታኔ የቻይና ኩባንያዎች በኦፕን ሶርስ ኤአይ የላቁ የሆኑት የመንግሥት ድጋፍ ስላላቸው ነው ይላል።

በሌላ በኩል እንደ ኦፕንኤአይ ያሉት የአሜሪካ ኩባንያዎች ገቢ እንዲያመጡ እና ትርፋማ እንዲሆኑ ጫና ይደርስባቸዋል።