ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትራምፕ አስተዳደር ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ሱዳንን ጨምሮ የ19 አገራት ዜጎችን የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ ሊመረምር ነው
የትራምፕ አስተዳደር ኤርትራን ጨምሮ ከ19 አገራት ወደ አሜሪካ የገቡ በሁሉም ዜጎች የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ ላይ እንደገና ምርመራ ሊያደርግ ነው።
የዩናይትድ ስቴትስ የዜግነት እና የኢሚግሬሽን አገልግሎት ኃላፊ ጆሴፍ ኤድሎው እንዳሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ "አሳሳቢ ከሆኑ አገራት የመጡ ስደተኞች በሙሉ የእያንዳንዳቸው የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ፣ በጥብቅ እንደገና እንዲመረምር" መመሪያ ሰጥተዋል።
ቢቢሲ እነዚህ አገራት እነማንን እንደሚያካትት ሲጠይቅ ኤጀንሲው ዋይት ሐውስ በሰኔ ወር ያወጣውን አዋጅ ተጠቅሷል። እነዚህም አገራት ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ሊቢያ እና ዴሞክራቲክ ኮንጎን ጨምሮ አፍጋኒስታን፣ የመን፣ ኩባ፣ ሄይቲ፣ ኢራን እና ቬንዙዌላን የሚያካትት ነው።
ይህ ትዕዛዝ የተሰማው አንድ አፍጋኒስታናዊ ረቡዕ ዕለት በዋሽንግተን ዲሲ ሁለት የብሔራዊ ዘብ አባላት ላይ ተኩሶ ከባድ ጉዳት ካደረሰ በኋላ ነው።
ተጠርጣሪው ራህማኑላህ ላካንዋል ወደ አሜሪካ በአውሮፓውያኑ 2021 የገባው ዩናይትድ ስቴትስ ከአፍጋኒስታን መውጣቷን ተከትሎ ለአፍጋኒስታን ልዩ የኢሚግሬሽን ጥበቃ በሚሰጥ ፕሮግራም ነው።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዋይ ሐውስ የብሔራዊ ዘብ አባላት ላይ የተፈጸመው ጥቃት ትልቅ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት መሆኑን ተናግረዋል።
ኤድሎው ሐሙስ ዕለት ባጋሩት የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው ላይ የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃዱ እንደገና መታየት የሚጀምረው ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ስለመሆኑ ምንም ያሉት ነገር የለም።
ኤድሎው "የዚህች አገር እና የአሜሪካ ሕዝብ ደኅንነት ከምንም በላይ ነው፤ እናም የአሜሪካ ሕዝብ ቀደም ሲል የነበረው አስተዳደር ግዴለሽነት የተሞላበት የሰፈራ ፖሊሲ ጦስን አይሸከምም" ሲሉ ተናግረዋል።
ዳግም የሚደረገው ምርመራ ምን እንደሚመስል ተጨማሪ ዝርዝሮች አልተገለጹም።
ኤጀንሲው ለቢቢሲ የጠቀሰው በሰኔ ወር የወጣው አዋጅ አሜሪካን "ከውጭ አሸባሪዎች እና ከሌሎች የብሔራዊ እና የሕዝብ ደኅንነት ስጋቶች" ለመጠበቅ የውጭ አገር ዜጎች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ የሚከለክል ነው።
የትራምፕ አስተዳደር አገራቱን የዘረዘረበትን ምከንያትም ሲገልጽ የፀጥታ ችግሮች እንዲሁም የቢዝነስ፣ የተማሪ እና የቱሪስት ቪዛ ያላቸው ግለሰቦች ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ በመቆየታቸው ምክንያት መሆኑን አስፍሯል።
"ታሊባን፣ በልዩ ሁኔታ የተፈረጀ ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን አፍጋኒስታንን ይቆጣጠራል" የሚለው ይህ አዋጅ "አፍጋኒስታን ፓስፖርቶችን ወይም የሲቪል ሰነዶችን ለመስጠት ብቃት ያለው ወይም ተባባሪ የሆነ አስተዳደር ስለሌላት ተገቢ የማጣራት እና የመለየት እርምጃዎች አታከናውንም" ብሏል።
የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃዳቸው ዳግም ከሚመረመሩ አገራት መካከል በርማ፣ ቻድ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ እና ሊቢያ ይገኙበታል።
ረቡዕ ዕለት በአሜሪካ ጦር አባላት ላይ የተፈፀመው ጥቃት ትራምፕ ጠንካራ ምላሽ እንዲሰጡ አድርጓል።
"ይህ ጥቃት በአገራችን ላይ የተጋረጠውን ትልቁን የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት አጉልቶ ያሳያል" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
"የባለፈው አስተዳደር 20 ሚሊዮን ያልታወቁ እና በሚገባ ምርመራ ያልተደረገባቸው የውጭ አገር ዜጎች ከመላው ዓለም፣ ለማወቅ እንኳን ከማትፈልጓቸው ቦታዎች እንዲገቡ አድርጓል። ማንኛውም አገር ለኅልውናችን አደጋ የሆነውን ይህንን ስጋት አይታገስም።"
ባለፈው ሳምንት ከመኖሪያ እና ከሥራ ፈቃድ ዳግም ምርመራ የሚያደርገው የአሜሪካ የዜግነት እና የኢሚግሬሽን አገልግሎት፣ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ስር የገቡትን ስደተኞች በሙሉ መገምገሙን አስታውቆ ነበር።
ረቡዕ ዕለት አሜሪካ ከአፍጋኒስታን የሚመጡትን ሁሉንም የኢሚግሬሽን ጥያቄዎች ማስተናገድ ማቆሟን ገልጻለች።
የዜግነት እና የኢሚግሬሽን አገልግሎት ውሳኔው ያሳለፈው "የደኅንነት እና የማጣራት አሠራሮች" እስኪፈተሹ ድረስ ነው ብለዋል።
ለዚህ የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ ምክንያት የሆነው የቀድሞ የሲአይኤ ሠራተኛ እንደነበር በተነገረው አፍጋናዊ ጥቃት ከባድ ጉዳት ከደረሰባቸው ሁለት የብሐራዊ ዘብ አባላት መካከል የአንደኛዋ ሕይወት ማለፉ ተዘግቧል።