በብርሌ ፍቅር የወደቁት ፈረንጅ 'ብርሌ ውስጥ የኢትዮጵያ ታሪክ አለ' ይላሉ

"የደብረ ሊባኖስ ጭፍጨፋ" የሚለውን መጽሐፋቸውን በስመረቁ ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, Ian Campbell

የምስሉ መግለጫ, ኢየን ካምብል "የደብረ ሊባኖስ ጭፍጨፋ" የሚለውን መጽሐፋቸውን ባስመረቁ ጊዜ

ሰሞኑን አረቄ ብሔራዊ አጀንዳ ሆና የማኅበራዊ ሚዲያ አናት ላይ ወጥታ ነበር።

ጠጅ ቢሆን አናት ላይ አይወጣም፤ ወደ ጉልበት ነው የሚወርደው።

ጠጅ ለመጨረሻ ጊዜ ጉዳይ ሆኖ የሥነ መንግሥቱ አናት ላይ ወጥቶ፣ 'ብሔራዊ አጀንዳ' የነበረው በዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ዘመን ነው።

ጌታሁን ገሰሰ የተባለ ምስኪን የመቄት ጭሰኛ ድንገት ነሽጦት፣ ምናልባትም ሞቅ ብሎት ይሆናል፣ ሳያስፈቅድ ድግስ ደገሰ። መደገሱንስ ይደግስ። ፍሪዳ ጣለ። ፍሪዳስ ይጣል። ጠጅ ይጥላል?!

በዮሐንስ ዘመን አንድ ገበሬ ጠጅ ከሚጥል ራሱን ቢጥል ይቀለዋል። ሰይጣን አሳስቶት መሆን አለበት። ለመሆኑ ገንዘቡንስ ከየት አመጣው?

ጠጅ ለዘመኑ የ'አይሪሽ ብሉ ሌብል' ማለት ነው።የመሳፍንቱ መጠጥ ነው። እንጂ ማንም ጭሰኛ በጉሮሮው የሚያንቆረቁረው ተራ መጠጥ አልነበረም። ነገሥታት በእነርሱ ዙሪያ ያሉ ብቻ ነበር የሚያንደቀድቁት።

ጌታሁን ጉዱ ፈላ።

የአካባቢ ሹማምንት በድግሱ ተገኝተው በልተው ጠጥተው ሲያበቁ በነገታው ይህን ምስኪን አያዳፉ ንጉሡ ዘንድ አቀረቡት።

"ጌታሁን ተልከሰከሰ - ወግና ባሕል አረከሰ" አሉት።

ጭሰኛው ጌታሁን 'የፍርድ ማቅለያ አለህ?' ተባለ።

"አልሰረቅኩ፤ ለራሴ አልጠጣሁት። ለእመቤቴ ንግሥ ድሃ ባበላሁ፣ ባጠጣሁ…ንጉሥ ሆይ! ምን አጠፋሁ?'' አለ።

የአካባቢው ሹማምንት ይበልጥ ተቆጡ፤ፍርድ ማክበጃ አመጡ።

"ጌታሁን ጠጅን አረከሳት- አረቄ አስመሰላት'' ሳይሉ አልቀሩም።

ንጉሥ ዮሐንስ ፍርድ ሰጡ፤ "ይህ ምስኪን ከብት ሰርቆ ነው ፍሪዳ የጣለ? ጠጅስ የጣለው ለእመቤታችን ክብር አይደለምን? ድሃ ባበላ ባጠጣ ምን አድርግ ነው የምትሉ? እናንተስ ከድግሱ ተቋድሳችሁ ስታበቁ በዚህ ሰው ላይ ፍርድ መስጠት ግፍ አይሆንባችሁምን?"

ያቺ ቅጽበት የታሪክ ማርሽ ቀየረች።

ያቺ ቅጽበት ለዘመኑ የመደብ ጭቆና የ'መሬት ላራሹ' ያህል ግዝፈትና ትርጉም ነበራት።

ለአብረሃም ሊንከን 'ኢማኑስፔሽን ፕሮክላሜሽን' እንላለን። ለአፄ ዮሐንስ አንድ ነገር ማለት ካለብን 'ኢማኑስፔሽን ኦፍ ብርሌ'' ማለት ነው የሚኖርብን።

ድሃ ቀን ወጣለት። "ከሰው እኩል ነህ- ጠጅም ትጠጣለህ" ተባለ።

በዚያች ቀን ጠጅ ብቻ ሳትሆን ብርሌም ከመሳፍንት እጅ አፍትልካ ወጣች።

ኢየን ካምብል የብርሌ ዐውደ ርዕይን በማስጎብኘት ላይ ሳሉ

የፎቶው ባለመብት, Ian Campbell

የምስሉ መግለጫ, ኢየን ካምብል የብርሌ ዐውደ ርዕይን በማስጎብኘት ላይ ሳሉ

የብርሌ ጉሮሮ ያነቁት ጋሽ ኢየን ካምብል

ወዳጆቻቸው 'ጋሽ ኢየን' ይሏቸዋል። የዋዛ ሰው አይደሉም።

በብርሌ ፍቅር ወድቀው የቆራሌው ደንበኛ ከመሆናቸው በፊት የኢትዮጵያን አንዳንድ ደንበኛ ታሪኮች ጽፈዋል።

ለዐሥርታት ተመራምረው አራት ዕፁብ ድንቅ መጽሐፍ ጽፈዋል።

ብዙ አንባቢ "The Massacre of Debre Libanos" በሚለው ሥራቸው ያውቃቸዋል።

ከዚያ የበለጠ አንባቢ ደግሞ "The Plot to kill Graziani" በሚለው መጽሐፋቸው ያወድሳቸዋል።

ይህ ሁለተኛው መጽሐፍ ሕዝብ የማያውቀውን አዲስ መረጃ ያቀረቡበት ሰነድ ነው።

ለምሳሌ በግራዚያኒ ግድያ እኛ እናውቅ የነበረው አብረሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶምን ብቻ ነበር።

የግራዚያኒን አናት በእጅ ቦምብ ለማደባየት በተደረገው ሙከራ ስምኦን አደፍርስ የሚባል ባለታክሲ ጉልህ ሚና እንደነበረው እሳቸው ባይነግሩን የት እናውቅ ነበር?

በዚያ ዘመን በአዲስ አበባ 8 ታክሲዎች ብቻ ነበሩ። ሁለቱ የስምኦን አደፍርስ ናቸው።

የ23 ዓመቱ ስምኦን የውስጥ አርበኛ ነበር። ግራዚያኒ ላይ ቦምብ ለወረወሩት ለነ ሞገስ ሽፋን ሰጥቶ በታክሲ ለማስመለጥ ሕይወቱን ሰጠ።

ስምኦን አደፍርስ እስከ ዛሬ አንዲት ፊልም እንኳ አልተሠራለትም። ሐውልትም አልቆመለትም። በስሙ ወላ ታክሲ ማቆምያ አልተሰየመም። ለጊዜው ጋሽ ኢየን ካምብል ናቸው ከመረሳት ያተረፉት።

አሁን ደግሞ ጠጅ ቤት እየተመናመነ ሲሄድ፣ የብርሌን ታሪክ አድምቀው እየጻፉት ይመስላል።

ደግሞ ስለ ብርሌ ተጻፈ አልተጻፈ የሚል የዋህ አንባቢ አይኖርም አይባልም።

ጋሽ ካምብል ለዚህ ፈጣን ምላሽ አላቸው። "የብርሌ ታሪክ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው" ይላሉ። "More or less" ይነስም ይብዛ ማለታቸው ነው።

ነገር በምሳሌ አገር በብርሌ

የፎቶው ባለመብት, YIMTU BEZINA FB

የምስሉ መግለጫ, ይህ ዐውደ ርዕይ ለአራት ወራት ይዘልቃል።አራት የዘመናችን አርቲስቶች በብርሌዎች ላይ ሥዕሎቻቸውን አኑረዋል።

የብርሌ ታሪክ እንዴት የኢትዮጵያ ታሪክ ይባላል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይ��� ያድርጉ

End of podcast promotion

ጋሽ ኢየን ከብርሌ ጋር በፍቅር የወደቁት ሳያስቡት ነው። ለነገሩ ሰው አቅዶ በፍቅር አይወድቅ።

ድሮ፣ በ80ዎቹ መባቻ በአዲስ አበባ ዞር ዞር ሲሉ አንድ መናኛ ዕቃ መሸጫ ሱቅ ይመለከታሉ። ብዙ ብርሌ ተደርድሮበታል።

ቆም ብለው ተመለከቱ። ረስተውት ይሆናል እንጂ የብርሌው አንገት ይበልጥ ሳይስባቸው አልቀረም።

ይበልጥ የገረማቸው ግን ያ ሁሉ ብርሌ ከየት መጣ? ለምንስ ይሸጣል? ሰውስ ምን ሊፈይድለት ይገዛዋል? የሚለው ነበር።

ከየት መጣ ያስባላቸው አንድም አገራችን ብርጭቆ እንደማታመርት ከማወቅ ነው።ሁለትም እንደ ታሪክ ፀሐፊ ቢገረሙ አይገርምም።

አንድ ሐበሻ ከሎንዶን ወደ ማንቺስተር ሲጓዝ የጤፍ ማሳ ቢያይ እንደሚገረመው ዓይነት።(ነገር በምሳሌ ጠጅ በብርሌ ማለት ይኸው ነው።)

ጋሽ ኢየን በዚያ ቅጽበት 'አስቂኝ ቅርጽ' ካለው ጠርሙስ ጋር በፍቅር ወደቁ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለ35 ዓመታት ብርሌ እየገዙ ያስቀምጡ ጀመር።

ቆራሌው ለየት ያለ ብርሌ ካገኘ ሰተት ብሎ ቤታቸው ይገባል።

በአጭር ጊዜ የብርሌዎች ቁጥር ተመነደገ።

ባለፉት ዓመታት የተሰበሰቡት ብርሌዎች ሚሊየንየም አዳራሽን የሚያህል ጠጅ ቤት ያስከፍታሉ። እርግጥ ነው ይህ ዐረፍተ ነገር የጠጅ ተጽእኖ ያለበት ይመስላል። በሞቅታ ተጋኖም ይሆናል።

ብቻ ጋሽ ኢየን በመቶዎች የሚቆጠሩ ብርሌዎችን በዓይነት በዓይነቱ ሲሰበስቡ ኖሩ።ቢያንስ መቶዎቹ ብርሌዎች በዓይነትም በዘመንም አይመሳሰሉም።

'ለምንድነው ግን የብርሌ ታሪክ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው የሚሉት?' ለሚለው የቢቢሲ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ እንዲህ አሉ።

"ምክንያቱም አንደኛ ጥንታዊ ነው። በዘመን ውስጥ ያደረገው የቅርጽ እና የዲዛይን ለውጥ ስለያንዳንዱ ዘመን ይናገራል። በዚያ ላይ ብርሌ ውስጥ ኢኮኖሚ አለ፣ ማኅበራዊ ለውጥ፣ ኅብረተሰባዊ እርከን አለ። ፖለቲካ አለ። በብርሌ ሌንስ የኢትዮጵያን ታሪክ ማየት ይቻላል፣ አይመስልህም?"

ጋሽ ኢየን ለ35 ዓመታት የለቃቀሟቸውን ብርሌዎች አሁን ለሕዝብ ዐውደ ርዕይ አቅርበዋቸዋል። ዲፕሎማቶች እና የአገሬው ሰው በየዕለቱ እየተመለከታቸው ነው።

የጋሽ ኢየን ዝናም ከፍ እያለ ነው። ዕድሜ ለ'ይምጡበዝና'።

ይምጡ በዝና የባሕል ማዕከል

የፎቶው ባለመብት, yimitu Bezina

የምስሉ መግለጫ, ይምጡ በዝና ቤተ መዘክር እና የባሕል ማዕከል

ወጣቱ አቤል እና ጋሽ ኢየን

አቤል አሰፋ የዝነኛው የ 'ይምጡ በዝና' ዳይሬክተር እና አጋፋሪ ነው።

"ይምጡ በዝና" ማነውና? የሚል ይኖራል። ለአዲስ አበባ የሚመጥናት የኪነ ጥበብ ቤት ነው።

ቤተ መዘክር እና የባሕል አዳራሽ ነው።

ከቤተ መንግሥቱ ማዶ፣ ከ4 ኪሎ ቁልቁለቱን ይዞ፣ የድሮው ቄራን ታኮ እስከ ሸራተን ደጅ ድረስ ለወዳጅነት ፓርክ ተፈልጎ ሲጠረግ፣ ይህ ውብ ታሪካዊ ቤት በሆነ ተአምር ተረፈ።

አሁን አዲስ አበባ ካሏት ሦስት የግል ሙዚየሞች አንዱ ነው። ውስጡም ውጪም ውብ ነው።

ባተሌው አቤል አሰፋ ይህን ቤት ያስተዳድረዋል። እስከ ዛሬ 11 ድንቅ ዐውደ ርዕዮችን በአጋፋሪነት ለሕዝብ አቅርቧል።

ለመሆኑ ከጋሽ ኢየን ካምብል ጋር የተዋወቁት መቼ ነው? የትስ ነው? ጠጅ ቤት ይሆን?

አይደለም።

በአውሮፓውያኑ 2023፣ ኅዳር ወር ላይ እሳቸው ለአንድ ዐውድ ርዕይ 'ይምጡበዝና' መጡ።

ከዚያ በፊት አቤል እሳቸውን በአካል አያውቅም። በመጽሐፎቻቸው ግን ያውቃቸዋል።

ያን ቀን በአካል ተዋወቁ። ትውውቁ ወደ ጥሩ ወዳጅነት እና የሥራ ትብብር አደገ።

የሆነ ቀን ቤ��ቸው ጋበዙት። አቤል የጋሽ ኢየን ቤት በብርሌ ተሞልቶ ቢያይ ጊዜ ተደነቀ።

ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ በኢትዮጵያ የነበሩ ብርሌዎችን በወግ በወጉ ሰድረዋል። ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል?

19ኛው አጋማሽ ማለት እኮ ገና መይሳው ካሳ ሰይፍም አላነሳ።1840 ማለት እኮ የዘመነ መሳፍንት የመጨረሻ ዘመን ማለት ነው።

በምኒልክ አያት በሳሕለሥላሴ ጊዜ የነበረ ብርሌ ጋሽ ኢየን ቤት አለ። አቤል ተደነቀ።

ይህን ተአምር ከጋሽ ኢየን ቤት አውጥቼ ለአደባባይ ማብቃት አለብኝ ብሎ ያመነው ያኔ ነው።

"ለምን ታላቅ የብርሌ ዐውድ ርዕይ አናሰናዳም?" ተባባሉ።የብርሌ አንገት አንቀው ቺርስ ተባብለውም ይሆናል። ለጤናችን! ለዐውደ ርዕያችን!

ጋሽ ኢየን ካምብል ቤታቸውን ለእንግዶች እያስጎበኙ

የፎቶው ባለመብት, Ian Campbell

የምስሉ መግለጫ, ጋሽ ኢየን ካምብል ቤታቸውን ለእንግዶች እያስጎበኙ

ሼክስፒር ብርሌ ያውቃል? አርተር ራንቦ ግን ያውቃል

ጋሽ ኢየን ብዙ የብርሌ ስብስብ ብቻ አይደለም ያላቸው። ጽሑፎችንም አሳትመዋል።

ለምሳሌ አርተር ራንቦ ከብርሌ ጋር የነበረውን ግንኙነት አጥንተው በፈረንሳይ አገር በዕውቅ ጆርናል አሳትመዋል።

ራንቦ ደግሞ ለፈረንሳዮች ሼክስፒር እንደማለት ነው። ባለቅኔ ነው። ከሼክስፒር ቢለይ በሁለት ነገር ነው። ሼክስፒር ብርሌ አያውቅም - አልነቃማ፡)

አርተር ራንቦ ግን ብርሌ ነፍሱ ነበረች።ስለባለቅኔዎቹ እያወራን ይህን ጥያቄ ጣል ብናደርግ አይከፋም። "ብርሌ ከነቃ አይሆንም ዕቃ" የሚባለው ምን ለማለት ተፈልጎ ነው?

መልሱን ታላቁ ራንቦ ሊያውቀው ይችላል።

የተወሰነ ዘመኑን ሐረር ኖሯል። ነገር ዓለሙን ጥሎ ሐረር በኖረበት የምነና ዘመኑ ታዲያ በብርሌ ፍቅር ወድቆ ነበር። ከቡና እና ከጠመንጃ ጋር የብርሌ ሸቀጥ ሱቅ ጀማምሮ ነበር።

ከአገሩ ፈረንሳይ እያስመጣ ለመሳፍንቱ ይሸጣል። ይክሰር ያትርፍ በቂ መረጃ የለም።

በዚህ ረገድ ነው ጋሽ ኢየን ጥናታዊ ጽሑፍ ነው ያሳተሙት።

"ጋሽ ኢየን ብርሌውን እንደ እቃ ከመሰብሰብ ባሻገር ጥንቅቅ ያለ ጥናት ያደረገ ሰው ነው" ይላል አቤል።

"እኔ ባለኝ የሥራ ልምድ ከ10 በላይ የብርሌ ዓይነት አይቼ አላውቅም። እሳቸው ጋር ከ90 ዓይነት በላይ ነበራቸው። ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ አሁን ቻይና ተመርቶ እስከሚገባው ብርሌ ድረስ።"

ዐውደ ርዕዩ መስከረም 10 ተከፍቷል። ገና ለአራት ወራት ይዘልቃል።

እነ አቤል ግን ነገሩ በወራት ዐውደ ርዕይ ብቻ እንዲዘጋ አልፈለጉም። ታሪኩን ለትውልድ ለማኖር ደረጃውን የጠበቀ የ1 ሰዓት ከ20 ዘጋቢ ፊልም እያሰናዱ ነው።

ምናልባት ዘጋቢ ፊልሙ የትልልቅ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ትኩረት አግኝቶ ብርሌ ለዓለም አቀፍ ዕይታ ትበቃ ይሆናል።

ብርሌ

የፎቶው ባለመብት, Yimitu Bezina

የምስሉ መግለጫ, ብርሌ

ቆራሌው እና ፈረንጁ ኢየን ካምብል

በደርግ መጨረሻ ዘመናት ቲቪ ውድ ንብረት ነበር። ከቡዳ ለመጠበቅ በሚመስል ሁኔታ ዳንቴል ለብሷል።

ከኢህአዴግ ዘመን መባቻ ፍሪጅ ያለው ቤተሰብ ይከበር - ይታፈር ነበር። ፍሪጅ የሳሎን እንጂ የማዕድ ቤት ዕቃ አልነበረም።

ቲቪም ሆነ ፍሪጅ ግን እንደ ብርሌ ለብዙ ዘመናት የክብር ዕቃ ሆነው በአገር አልነገሡም።

"አንድ በተለየ መንገድ የማናውቀው ዕለታዊ ዕቃ 700 ዓመት ታሪክ ሲኖረው ይገርማል" ይላል አቤል።

ብርሌ በገፍ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ስዊዝ ካናል የተከፈተ ሰሞን ነው።ያን ጊዜ ዐፄ ዮሐንስ አገር ያስተዳድሩ ነበር።

16ኛው የጎንደር ዘመን የብርሌ ወርቃማ ዘመን ሳይሆን አይቀርም። የንጉሥ ፋሲለደስ ወዳጅ የነበረው ነጋዴ አርመናዊው ጎሲያ ሙራድ ብዙ ብርሌ ከሕንድ እንዳስገባ ይነገራል።

ስኮትላንዳዊው ተጓዥ ጀምስ ብሩስ በ1769 ጎንደር በደረሰ ጊዜ የንጉሣዊያን ቤተሰብ ጠጅ ''አፉ ጠበብ ባለ" ብርጭቆ ሲጠጡ መመልከቱን ጽፏል።

ብርሌ በቀላሉ ምንም ጠንካራ ቢሆን ተሰባሪ በመሆኑ በልዩ ጥንቃቄ እና በክብር የሚጠበቅ ውድ ዕቃ ነበር።

አቤል እንደሚለው ድሮ ብርሌ በበቅሎ ሲሄድ እንዳይሰበር የሚደረግለት እንክብካቤ ልዩ ነበር።

እንደ 80ዎቹ ቴሌቪዥን ብርሌም ዳንቴል ለብሷል።

"በስንደዶ የብርሌ ማስቀመጫ ይሠራ ነበር" ይላል አቤል።

ከአፉ ቆምጨጭ- ከሆዱ ዘርፈጭ ያለበትስ ምክንያት ምን ይሆን?

በአፉ መጥበብ አንደኛ መአዛው ይሰነብታል፤ ሁለተኛ ድሮ 'ዴሊቨሪ' በአጋሰስ ነበር። አጋሰስ እነ ፈረስ ናቸው። አቧራ ይለብሳሉ፣ብርሌ ግን ዝንብ እና አቧራ በቀላሉ አይዘልቀውም።

ብርሌ ክርክሩ ላይ ማሰሪያ ነበረው።የጠጅ ማቅረቢያ ከመሆኑ በፊት ደግሞ የጠጅ ማስቀመጫ ነበር።

ለመሆኑ ጋሽ ኢየን እነዚህን የዘመን ብርሌዎች ከየት ነው የሰበሰቧቸው?

ዋናዎቹ አቅራቢዎቻቸው ቆራሌዎች እንደሆኑ ይናገራሉ።

ምናለሽ ተራ ዘልቀው በአሰሳ የገዟቸውም አሉ። የገጸ በረከት ሱቆች ለየት ያለ ነገር ሲያገኙ ይደውሉላቸዋል።

በስጦታ ያገኟቸውም አሉ፤ከሐረር የገዟቸውም አሉ።

በ35 ዓመታት ውስጥ ለብርሌ ስንት ብር ከሰከሱ የሚል ቀጥተኛ ጥያቄ ከቢቢሲ ቀርቦላቸው ነበር - ኢየን ካምብል።

እርሳቸው እርግጡን የገንዘብ መጠን ከመግለጽ ተቆጥበዋል። ግን ደግሞ የዋዛ ብር እንደማይሆን ጠቆም አድርገዋል።

ከብርሌ ጎብኚዎች መካከል

የፎቶው ባለመብት, YIMITU BEZINA FACEBOOK

የምስሉ መግለጫ, ከብርሌ ጎብኚዎች መካከል

ጠባብ የብርሌ ታሪክ

ብርሌ ከአክሱማዊያን ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እንነበረ ይገመታል። የማያወላዳ መረጃ የተገኘው ግን ከ14ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ ነው።

"ለምሳሌ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ የብራና ጽሑፎች እና ሥዕሎች መረጃ ያቀርባሉ። በቃና ዘገሊላ ኢየሱስ ክርስቶስ ውሃውን ወደ ወይን በቀየረበት ታሪክ ላይ ይታያል" ይላል አቤል።

ለመሆኑ ኢትዮጵያ ብርሌን አምርታ ታውቃለች?

ሞክራለች።ግን አልተሳካላትም።

ብርሌን አገር ውስጥ በማስገባት ግን ብዙ ገንዘብ ከስክሳለች።

በዚህ የውስኪ ዘመን የብሔራዊ ባንክን የውጭ ምንዛሬ የሚያጥበው ነዳጅ ነው። ቀጥሎ ማዳበሪያ።

በድሮ ዘመን ግን ብርሌ ነበር የነገሥታቱ ትልቅ ወጪ። መጀመሪያ አካባቢ ከሶሪያ ይመጣ ነበር።

ቀጥሎ ከቬኑስ መምጣት ጀመረ። ከኦስትሮ ሐንጋሪ የሚመጣበት ጊዜም ነበር። ከዚያ በኋላ ቤልጂየም።

በዘውዲቱ የንግሥና በዓል ድግስ ላይ አገልግሎት የዋሉ 'ስፔሻል' ብርሌዎች በትዕዛዝ ስለመመረታቸው የተመዘገበ መረጃ አለ።

ብቻ ታሪኩ እንደ ብርሌ አንገት ዘለግ ያለ ነው።

አቤል እንዲህ ይላል፦ "ከብዙ አገራት ይመጣ ነበር። ከቦሂሚያ ሳይቀር፤ ቦሂሚያ አገር ነበረች፤ አሁን የለችም፤ ብርሌ ግን አለ።"

ብርሌን በአገር ለማምረት የተደረጉ ሙከራዎች ጥቂት ናቸው።

ዋንኛው ከነጻነት በኋላ ጃንሆይ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ በተመኙ ጊዜ ነበር። የኮልፌ የሥልጠና ማዕከል ሲቋቋም እዚያ ብርሌ ይመረት ነበር።

ምን ዋጋ አለው የአዲስ አበባ አሸዋ ለብርጭቆ ጥሩ አልነበረምና ተተወ።

ከዚያ በኋላ ኤርትራ በፌዴሬሽን ወደ ኢትዮጵያ ስትገባ ሳባ ከሚባል ፋብሪካ ብርሌ እየተመረተ ይመጣ ነበር።

በደርግ ዘመን ደግሞ ከሶሻሊስቶቹ ሃንጋሪ እና ከምዕራብ ጀርመን ወደ ኢትዮጵያ ይገባ ነበር።

ኮሎኔል መንግሥቱ የመሳፍነቱ ኑሮ እና ቅንጦት ያበሳጫቸው ስለነበር በብርሌ ጠጅ ይጠጣሉ ተብሎ አይጠበቅም። እንዲያውም በብርሌ ላይ የነበሩ የአንበሳ ምልክቶችን አስፍቀዋል ይባላል።

በኢህአዴግ የመጀመሪያ ዓመታት ይባስ የብርሌ ገበያው ተዘጋ።

የኢትዮጵያ ሚሊንየም ጊዜ ደግሞ ያልተጠበቀ ማንሰራራት አሳየ።

ብዙ ሰዎች ኑሮ መወደድ የጀመረው በኢትዮጵያ ሚሊየነሙ መባቻ ነው ብለው ያምናሉ።

ብርሌ በይፋ ጌጥ መሆን የጀመረችውም ያን ሰሞን ነበር።ዳያስፖራን ለማማለል ይመስላል ከጠጅ መጠጫነት ወደ ሸራነት ወረደች።

ብርሌዎች እንደ ሸራ ብዙ ምሥል እየተሳለባቸው የጓሮ ማስዋቢያ መሆን ጀመሩ።

ይህ ዘመን ብርሌ ከሳሎን ወጥቶ ወደ ጓሮ የሄደበት ዘመን ሊባል ይችላል።

በመለስ ዜናዊ አስተዳደር የመጀመሪያ ዓመታት ባዲሳባ ጠጅ ቤቶች ጀንበራቸው ሲያዘቀዘቅ- በራቸው ሲዘጋ፣ ብርሌም ጉሮሮው አብሮ ተዘጋ።

ጋሽ ኢየን ካምብል ከሰበሰቧቸው ብርሌዎች አንድ ሁለቱ በሸዋው ንጉሥ ሣህለሥላሴ ዘመን (የዳግማዊ የምንሊክ አያት) ጊዜ የነበሩ ናቸው።

"ብዙዎቹን ብርሌዎች ያገኘኋቸው ግን በመለስ ዘመን ጠጅ ቤቶች በአዲስ አበባ በፈረሱበት ወቅት ነው።"

የብርሌ ዐውደ ርዕይ ባለፉት ሳምንታ የበርካታ ጎብኚዎችን ቀልብ ስቦ ሰንብቷል።

የፎቶው ባለመብት, YimituBezina

የምስሉ መግለጫ, የብርሌ ዐውደ ርዕይ ባለፉት ሳምንታ የበርካታ ጎብኚዎችን ቀልብ ስቦ ሰንብቷል

ፈረንጁ ጋሽ ኢየን ጠጅ ይጠጣሉ?

ለመሆኑ ስለ ብርሌ ይህን ሁሉ የነገሩን ፈረንጁ ጋሽ ኢየን እና አጋፋሪው አቤል አሰፋ ጠጅ ይጠጣሉ?

መሠረታዊ ጥያቄ ይመስላል።

አቤል የጠርሙሱ እንጂ የጠጁ አድናቂ አይመስልም።

"በሕይወት ዘመኔ አንዴ ነው የጠጣሁት፤ እንዳለመታደል ሆኖ ጠጅ አይስማማኝም"ይላል።

ጋሽ ኢየን ግን "ካገኘሁ አልምርም" የሚሉ ይመስላሉ።

"ሰርግ ላይ እቀማምሳለሁ። ብርሌን ወድጄ ጠጅን እንዴት ላልወድ እችላለሁ?"