ወጣቶች ፊታቸውን ለምን ወደ ውበት ቀዶ ሕክምና አዞሩ? ወጪው እና የሚያስከትለው ውስበስብ መዘዝ

ቀዶ ሕክምና

ፊት ላይ የሚደረግ ቀዶ ሕክምና ከመቼውም በላይ ተበራክቷል።

የፊት ቆዳን የመሰብሰብ ቀዶ ሕክምና (facelift) የተለመደው በዕድሜ በገፉ ሰዎች ዘንድ ነበር። ከፍተኛ ገንዘብም ያስወጣል።

አሁን ግን በ20ዎቹና በ30ዎቹ ዕድሜ ክልል ያሉትም ሳይቀሩ ፊታቸውን እያሠሩ ነው።

አንዳንዶቹ ወጣቶች ከቀዶ ሕክምና በፊት እና በኋላ ያላቸውን ገጽታ የሚያሳዩ ምሥሎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያጋራሉ።

ከቀዶ ሕክምና የማገገም ሒደቱ ቀላል ባይሆንም ለማኅበራዊ ሚዲያ ተከታዮቻቸው ያስቃኛሉ።

የፊት ቀዶ ሕክምና በምሥጢር የሚያዝ መሆኑም አብቅቶለታል። እንደ ክሪስ ጀነር፣ ካት ሳድለር እና ማርክ ጃኮብስ ያሉ ታዋቂ ግለሰቦች ቀዶ ሕክምና ማድረጋቸውን በይፋ ተናግረዋል።

ከፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ዓይነቶች የመጨረሻው ደረጃ ላይ ያለው የፊት ቀዶ ሕክምና ነው።

ታዲያ ብዙዎች ቀዶ ሕክምናን አማራጭ የሚያደርጉት ለምን ይሆን? በሺዎችን የሚቆጠር ገንዘብ ለምን ያወጣሉ?

እንደ ቦቶክስ እና ፊለር ያሉ ከቀዶ ሕክምና ውጪ ያሉ አማራጮች የተሻሉ ናቸው?

ኤምሊ የፊት ቀዶ ሕክምና ያደረገችው በ28 ዓመቷ ነው።

ሹል የሆነ አገጭና መንጋጋ እንዲኖራት አድርጓል። ዐይኗ ወደ ግራና ወደ ቀኝ እንዲሾል ያደረገችውም በቀዶ ሕክምናው ነው።

በቱርክ ያደረገችው ቀዶ ሕክምና "ሕይወቴን ለውጦታል" ትላለች፤ አይጸጽታትም።

"ስድስት ቀዶ ሕክምና ነው በአንድ ጊዜ ያደረግኩት። ፊቴና ከንፈሬ ከፍ እንዲል ተደርጓል። አፍንጫዬም ተስተካክሏል" ትላለች።

በካናዳ ቶሮንቶ ነጋዴ የሆነችው ኤምሊ፤ ቀዶ ሕክምናው ሲደረግላት የምትወደው ሙዚቃ ተከፍቶ ነው።

ሙሉ ማደንዘዣ ተደርጎላት ነበር። "ተኝቼ ስነቃ አስመለሰኝ። ፊቴን ሳየው አዲስ ፊትና አዲስ አፍንጫ አየሁ" ስትል ታስታውሳለች።

ኤምሊ

የፎቶው ባለመብት, @hotgirlenhancements

የምስሉ መግለጫ, ኤምሊ

ለማገገም ረዥም ጊዜ ወስዶባታል። በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ቁስል መውጣት ጀመረ። ጉንጯን ስትነካው ሰሜቱ ይሰማት የጀመረው ከስድስት ወራት በኋላ ነበር።

"ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ሕይወቴን ለወጥኩ። ጤናማ ነኝ። ብዙ መጠጥ አልጠጣም። ቆዳዬን እንከባከባለሁ። እተኛለሁ። አሁን የማውቀውን ያኔ ባውቅ ኖሮ ቀዶ ሕክምናውን አላደርግም ነበር" ትላለች።

"የተሻልኩ ሰው መሆን ነው የምፈልገው። አሁን የተሻልኩ ሰው እንደሆንኩ ይሰማኛል" ስትልም አክላለች።

ከዩናይትድ ኪንግደም የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ባለፉት 12 ወራት የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና 8 በመቶ ጨምሯል።

የአሜሪካ የፕላስቲክ ቀዶ ሐኪሞች ማኅበር እንደሚለው ከ45 እስከ 60 ዓመት ያሉ ሰዎች ፊታቸውን በቀዶ ሕክምና የማሠራት ፍላጎታቸው ጨምሯል።

የእንግሊዝ የፕላስቲክ ቀዶ ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኖራ ነርጀንት እንደሚሉት፣ ቀዶ ሕክምና የሚፈልጉ ሰዎች ዕድሜ እያነሰ የመጣው ያለ ምክንያት አይደለም።

"በመድኃኒት ሰውነትን ሲቀንሱ ቆዳቸው ተሸብሽቦ ይቀራል። በቀዶ ሕክምና የፊት ቆዳን መሰብሰብ ይቻላል" ሲሉ ያስረዳሉ።

የፊት የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ከዚህ ቀደም ከነበረው ተለውጧል። የፊት ቆዳ በቀዶ ሕክምና ምክንያት ከሚገባው በላይ እንዳይለጠጥ ማድረግ ተችሏል።

ቀዶ ሕክምናው መከናወን ያለበት በባለሙያዎችና በተገቢው ሕክምና መስጫ ተቋም ውስጥ ነው።

ሳይመን ሊ በብሪስቶል የቀዶ ሕክምና መስጫ አላቸው። በመቶዎች የሚቆጠሩ የፊት ቀዶ ሕክምናዎች አከናውነዋል።

ጁልያ

የፎቶው ባለመብት, Julia Gilando

የምስሉ መግለጫ, ጁልያ

ቀዶ ሕክምናውን ሲያከናውኑ ታካሚዎች በፊታቸው ላይ ብቻ ማደንዘዣ ይወጋሉ።

ቀዶ ሕክምናው የሚደረግለት ሰው ፊት ላይ ምልክት ካደረጉ በኋላ ከቆዳ በታች ወዳለው የፊት ክፍል ይገባሉ። ቆዳ ላይ ያለውን ስብ እና የፊት እንቅስቃሴን የሚቆጣጠረውን ሕዋስ አልፈው ወደ ሥር ይዘልቃሉ።

ከቆዳ ሥር ያለውን ስብና ጡንቻ ከቦታ ቦታ በማዘዋወር ፊት የሚፈለገውን ቅርጽ እንዲይዝ ያደርጋሉ። ሒደቱ ሰዓታት ይወስዳል።

የፊትና የአንገት ቆዳን ለመሰብሰብ ቀላል እየሆነ መምጣቱ የቀዶ ሕክምናው ተፈላጊነት እንዲጨምር ምክንያት መሆኑን ባለሙያው ያስረዳሉ።

"በዚህ ዘርፍ አነቃቂ የሆነ ወቅት ላይ ነው ያለነው። በፍጥነት ለውጦች እየታዩ ነው" ሲሉም ለውጡን ይገልጹታል።

አገጭ እና አንገት ላይ ያተኮረ ቀዶ ሕክምና አሁንም ተፈላጊ ነው። ዕድሜ እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳዩ የፊት ክፍሎች ላይ ቀዶ ሕክምና ማካሄድ በወጣቶች ዘንድ እየተለመደ መጥቷል።

የፊት ቆዳን መሰብሰብ ከ40 ዓመት በላይ ላሉ ሰዎች የሚመከር ነው። በ20ዎቹ እና በ30ዎቹ ዕድሜ ላሉ እምብዛም አይመከርም።

ቀዶ ሕክምናው ውስብስብ ስለሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድርበት ዕድል ሰፊ ነው።

ከቆዳ ሥር ደም ሊቋጥር ይችላል። ይህም በአካባቢው ያሉ ሕዋሶችን ይገድላል። ኢንፌክሽን፣ የነርቭ ጉዳት እና የፀጉር መመለጥም ሊከሰት ይችላል።

ካሮላይን

የፎቶው ባለመብት, Caroline Stanbury

የምስሉ መግለጫ, ካሮላይን
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እንደ ዩናየትድ ኪንግደም ባሉ አገራት ቀዶ ሕክምናው ከ15 ሺህ እስከ 45 ሺህ ፓውንድ ያስወጣል። ሆኖም ግን እስከ 5,000 ፓውንድ ቀዶ ሕክምናው የሚሰጥባቸው አገራትም አሉ።

የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ከማድረግ በፊት ስለ ሕክምና መስጫው፣ ባለሙያዎቹ እና መሣሪያው በቂ ጥናት ማድረግ ያሻል።

ጁልያ ጊላንዶ 34 ዓመቷ ነው። ፊቷ ላይ የተዛባ አቀማመጥን ለማስተካከል ነው ቀዶ ሕክምና ለማድረግ የወሰነችው።

ጓደኞቿ ፊቷ የተስተካከለ እንደሆነ ቢነግሯትም 8,000 ዶላር አውጥታ ለቀዶ ሕክምናው ወደ ቱርክ አቀናች።

በቱርክ በአነስተኛ ዋጋ ቀዶ ሕክምናው ስለሚደረግ ብዙዎች ይመርጡታል።

"መጀመሪያ ላይ ሐሳቡ የእብደት ነበር የመሰለኝ። ጉዳዩን በጥልቀት ከመረመርኩ በኋላ ግን ቀዶ ሕክምናውን ለማድረግ ወሰንኩ። መጀመሪያ ፈርቼ ነበር። በማላውቀው አገር ብቻዬን ነበርኩ" ትላለች።

የጤና ባለሙያ የሆነችው ጁልያ ቀዶ ሕክምናው ከተደረገላት በኋላ ለሁለት ቀናት በሆስፒታል ቆይታለች።

"ከዚያ ፊቴ ስላበጠ ማየት አልቻልኩም። አንዳንዴ ፈሳሽ ይወጣም ነበር። ጭልምልም ያለብኝ ጊዜ ነበር። የስሜት መዋዠቅ ውስጥ ከቶኝ ነበር" ስትል ታስታውሳለች።

የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ምን ያህል በራስ መተማመን ይጨምራል? የሚለው አጠያያቂ ነው።

"በተለይ ፊት ምን መምሰል አለበት የሚለው ላይ ማኅበረሰባዊ ጫና አለ። ራሳችንን ሁሌም ስለምናየው ከሌሎች ጋር ራሳችንን እናነጻጽራለን" ሲሉ ዶ/ር ክርስቲ ጋርበርት ይገልጻሉ።

ብዙዎች በሰው ሠራሽ አገልግሎት በመታገዝ ምሥላቸው ላይ ማስተካከያ ያደርጋሉ። ይህ ገጽታ እውነተኛ ገጽታ ባይሆንም የመልክ ልኬት ተደርጎ ይወሰዳል። በተለይ ወጣቶች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።

ታዋቂ ሰዎች ስለ ቀዶ ሕክምና ማውራታቸው በጎ ነገር ቢሆንም "በጣም የተለመደ የሕይወት ክፍል" ተደርጎ እንዲወሰድ ማድረጉ እንደማይቀርም ዶ/ር ክርስቲ ይናገራሉ።

የቴሌቭዥን መሰናዶ አቅራቢዋ ካሮላይን ስታንበሪ 47 ዓመቷ ሲሆን፣ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ያደረገችው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።

"በሕይወቴ ካደረግኳቸው ነገሮች ሁሉ ትልቁ ነው። ለምን 60 ዓመት እስኪሞላኝ ድረስ እጠብቃለሁ? አሁን ቢያምርብኝ ይሻለኛል" ትላለች።

ለ20 ዓመታት በቦቶክስ ነበር ቆዳዋን የምታስተካክለው።

አሜሪካ ሄዳ 45 ሺህ ዶላር ከፍላ የፊት ቆዳዋ ከፍ እንዲል አደረገች።

"መልኬ አሁንም እንዳለ ነው። ቀዶ ሕክምናው ለቀጣይ 20 ዓመታት ጥሩ ስሜት ተሰምቶኝ እንድቆይ ያደርጋል" ስትልም ትናገራለች።

በቤልጄም የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ባለሙያ የሆኑት አሌክሲስ ቫርፔል ግን ወጣቶች ቀዶ ሕክምናውን ማድረጋቸው ያሰጋቸዋል።

ያለ ቀዶ ሕክምና እንዴት ገጽታን መለወጥ እንደሚቻል ለታካሚዎቻቸው ይመክራሉ።

"በ20ዎቹ ዕድሜ ክልል የፊት ቆዳቸው ቢሠራ እስከ 15 ዓመት ይቆያል። የሚያደርስባቸው ጣበሳ ግን ዘላቂ ነው" ይላሉ።