ዓለምን የሚዞረው ኢትዮጵያዊ ከዩቲዩብ ምን ያህል ያገኛል?

የፎቶው ባለመብት, Abel
አቤል ብርሃኑ የወይኗ ልጅ ይባላል። ይህንን ስም ሚሊዮኖች ያውቁታል። አቤል ለአንዳንዶች 'ሁነኛ የመረጃ ምንጭ' ነው።
ለሌሎች ደግሞ ከሀገር ሀገር እየዞረ አስገራሚ ቦታዎችን የሚያስጎበኝ፤ 'ደንቅ ታሪኮችን' የሚያቀርብ ነው።
ዩቲዩብ ላይ ቪዲዮ መጫን ከጀመረ ዘጠኝ ዓመታትን ተቆጥሯል። ያኔ ብዙ ኢትዮጵያዊ በዚህ መድረክ ላይ አልነበረም።
አቤል ግን ይህ ተስፋ አላስቆረጠውም።
ይሠራው ከነበረው የቴሌቪዥን፣ የሬዲዮ፣ የማስታወቂያ እና የፊልም ሥራዎች ጎን ለጎን ዩቲዩብን 'እስኪ ልሞክረው' ብሎ ነበር የጀመረው።
ሕይወቱን እንደሚቀይረው ግን አልገመተም ነበር።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮች እና ተመልካች ይኖረኝል ብሎም አልጠበቀም።
"ለኢንተርኔት ሩቅ አልነርኩም። ወደ ኢንተርኔት ካፌ እየሄድኩ እንዴት በኦንላይን ቢዝነስ እንደሚሠራ እመለከት ነበር" ይላል።
በዩቲዩብ ገንዘብ እንደሚያገኝ ተረዳ። ዩቲዩብ የልጅነት ህልሙን ለማሳካት ትክክለኛው መንገድ እንደሆነ አመነ።
ሥራውን ግን ቀላል አልበረም። ውጤቱን ለማየት ብዙ ደክሟል።
አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ዜሮ በሚባል ደረጃ ቪዲዮዎቹ ዕይታ አልነበራቸውም። በተከታታይ 62 ቪዲዮዎችን ሲጭን የነበረው ተመልካች ሁለት ከፍ ካለ ዘጠኝ ነበር።
"በጣም ትግል ይጠይቅ ነበር። በእያንዳንዷ ቀን ነበር የምሠራው፤ ነገር ግን ተመልካች አልበረኝም" ይላል።
አቤል ይህንን ያህል ያለመሰልቸት እንዴት ቆየህ? ተብሎ ሲጠየቅ መልሱ አጭር ነው።
"በዩቲዩብ እምነት ነበረኝ። አንደ ቀን ስኬት ላይ እንደምደርስ እርግጠኛ ነበርኩ" ይላል።
እውነትም ዩቲዩብ አላሳፈረውም።
ልክ 63ኛውን ቪዲዮ ሲጭን ያላሰበው ሆነ። ተመልካቹ 'ጣራ ነካ'።
አቤል ያንን ቀን አይረሳውም።
የበዓል ፕሮግራም ሬዲዮ ላይ እየሠራ ነበር ያደረው። ከዚያም ወደቤት ሄደ "ከመተኛቴ በፊት አንድ ነገር ልሥራ" አልኩኝ ይላል።
ቪዲዮውን ሠርቶ ዩቲዩብ ላይ ለቀቀው። ከዚያም ወደ መኝታው አመራ።
"ከ5 ሰዓት በኋላ ስነሳ በጣም ደነገጥኩ። ለራሴ ማመን ከበደኝ። በ4 ሰዓት ውስጥ 7 ሺህ ሰው አይቶታል። በቀናት ውስጥ ሦስት አራት ሰው ነበር የሚመለከተኝ። ያንን ቪዲዮ ሳይ ደነገጥኩኝ።ገንዘብ መቁጠርም ጀመርኩ። ምናልባትም በዩቲዩብ ያቀን ይሆናል ለመጨረሻ ጊዜ የደነገጥኩት" ይላል።
ዩቱዩብ ቻናሉ ብዙ አስተያየት መቀበል ጀመረ። 'ሰብስክራይበሮቹ' ከጠበቀው በላይ ጨመሩ።

የፎቶው ባለመብት, Abel
እስከዚህ ቪዲዮ ድረስ በሳንቲሞች ደረጃ ሲያገኝ የነበረው ገቢ ተቀይሮ በአንድ ቪዲዮ 100 ዶላር አገኘ።
ይኼን ሁሉ 'ታሪክ የሠራው' ቪዲዮ ይዘቱ ምንድን ነበር?
"የምሥራች ውጪ ያላችሁ በሀገራችሁ የቤት ባለቤት ልትሆኑ ነው" የሚል ርዕስ ያለው ቪዲዮ ነበር ባልጠበቀው ሁኔታ ተመልካች ያገኘለት።
ይህንን ቪዲዮ የአንድን የሀገር ውስጥ ባንክ መግለጫን ተከታትሎ ነበር የሠራው። 'የምሥራቹ' ለራሱም ሆነ እንጂ።
ይህ ሁሉ ሲሆን አቤል መደበኛ ሥራውን አላቋረጠም ነበር።
"የሆነ ቀን ሊሳካ እንደሚችል እምነቱ ስለነበረኝ። በቀን የሆነ ሰዓት መድቤ እሠራው ነበር" ሲል ይገልጻል።
ከፍተኛ ዕይታ ካስገኘለት ቪዲዮ ሁለት ወራት በኋላ አቤል ሌሎች ሥራዎቹን አቁሞ ወደ ዩቲዩብ ፊቱን አዞረ። 'የጎንዮሽ' ሥራው የነበረው ዩቲዩብ ዋነኛ መተዳደሪያው ሆነ።
የራሱን ድርጅት አቋቋመ። ዕቃዎችን አሟላ። "በወቅቱ ውድ የሆነ ዕቃ አላስፈለገኝም" የሚለው ዩቲዩበሩ በቀላል ቁሳቁሶች መሥራት ጀመረ።
ይህንን ለማድረግ ከዩቲዩብ የሚገኘው ገንዘብ ዋነኛ ምንጩ ነበር።
"ዩቲዩብ በአንድ ወር የሚከፍለው ክፍያ የ50/60 ሰዎች ድምር ደመወዝ ሊሆን ይችላል። በሁለት እና በሦሰት ወር ውስጥ ብዙ ነገርን ለማሳካት የሚያስችል፣ ብዙ ነገሮችን የሚሸፍን ገንዘብ ይገኛል። ፈጣን ለውጥ ነው የሚመጣው" ሲል ያስረዳል።
ከዚህ በኋላ ነገሮች በፍጥነት መቀየር ጀመሩ። ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 'ሰብስክራይበሮቹ' 100 ሺህን ተሻገሩ።
አሁን አቤል 11 ሰዎችን በቋሚ እና በጊዜያዊ የሥራ ውል ቀጥሮ ያሠራል። በአዲስ አበባ ካለው ቢሮ በተጨማሪ በአሜሪካ ለመሥራት የሚያስችል ፍቃድ አለው። አምስት የዩቲዩብ ቻናሎችም አሉት።
ሁለቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተከታይ በማፍራታቸው የዩቲዩብን ወርቃማ ሽልማትን ወይም 'YouTube Creator Awards' ሲያገኙ የተቀሩት ከ100 ሺህ በማለፋቸው ብራማ ሽልማትን አስግኝተውለታል።

የፎቶው ባለመብት, Abel
"ያልሄደኩት አንታርቲካ ብቻ ነው"
ወቅታዊ ዜናዎች ላይ የሚያተኩር ቻናል የነበረው አቤል ተከታዮቹ 500 ሺህ ሲደርሱ ሌላ ቻናል ከፈተ።
ይህ ቻናል አቤል የልጅነት ህልሙን መኖር የጀመረበት ነው። በአዲሱ ቻናል ሀገራትን እየዞረ ለተመልካቾቹ ያሳያል።
የኢትዮጵያዊው ዩቲዩበር የመጀመሪያ መዳረሻ ሀገር ኡጋንዳ ነበረች። የዛሬ 7 ዓመት ወደ ኡጋንዳ ተጉዞ፣ የሀገሪቱን ባህል እና አኗኗር ለተመልካቾቹ ማጋራት ችሏል።
ቀጥሎም ወደ ተባበሩት አረብ አምሬትስ አቀና። በዚያ ሦስት ግዛቶች ላይ ልዩ ልዩ ቪዲዮዎችን ሠርቶ አሠራጨ።
ለመጀመሪያ ጊዜ ኡጋንዳን የረገጡት የአቤል እግሮች አሁን ከአንታርቲካ በስተቀር ሁሉንም የዓለም አህጉራትን ዞረዋል። ነገሮችን ግን አልጋ በአልጋ አልነበሩም።
ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አውሮፓ የሄደው ወደ ፈረንሳይ ነበር።
"ፈረንሳይ ኤምባሲ በጣም ብዙ ጊዜ ቪዛ ከልክሎኛል" የሚለው አቤል ይህንን ለማሳካት ብዙ እንዳንኳኳ ይናገራል።
ፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን "በጣም ብዙ ሀገራት" ቪዛ ለመስጠት አልፈቀዱም ነበር።
"ጃፓን ከልጅነቴ ጀምሮ መሄድ የምፈልገባት ሀገር ነበረች። ብዙ ጊዜ ተከልክያለሁ፤ በቅርቡ ነው ፈቃድ ያገኘሁት" ሲል ያክላል።
አቤል እስካሁን 63 ሀገራትን ዟሯል። የአሜሪካ 50 ግዛቶችን ጎብኝቷል።
ሌላኛው ፈተና ወደ ሀገራቱ ከገባ በኋላ የሚገጥመው ነው። ዝርዝሩን ማስታወስ ባይፈልግም አዘርባጃን እና ጂቡቲ ውስጥ የገጠመው ፈተና 'ምነው እግሬን ባለነሳሁ' ያስባሉት ናቸው።
"የየሀገሩ ባህል ይለያያል፣ ካሜራ የማይወዱ አሉ። ብዙ ቦታ ፋይል ያስጠፉኛል። አንዳንድ ቦታዎች ቋንቋ ፈተና ነው። አንግሊዝኛ እየተናገርክ አስተርጓሚ ኖሮህ እንኳን መግባባት ይከብዳል" ሲል ያስረዳል።
የአየር ሁኔታ ደግሞ ሌላኛው ችግር ነው።
ለመቋቋም የሚያስቸግር ሙቀት ወይም ብርድ በጉዞው ወቅት ያጋጥማሉ።
"በከፍተኛ ብርድ እግሬ የታመመበት ጊዜ አለ" ሲል ያክላል። አንዳንዴም "ጾም ማደር" አለ። እንዲህ ዓይነቱ ገጠመኝ አቤል "ፈጽሞ" ሊመገባቸው የማይችላቸው ነገሮች በሚገኙበት ሀገር የሚያጋጥም ነው።
አቤል ከጉዞ በፊት በቂ ጥናት ያደርጋል። ያነባል። ይዘጋጃል።
ለዚህ ነው "እኔ እንደቱሪሰት ውሃ ዳር ለመዝናናት ወይም ከተማ ላይ ፎቶ ለመነሳት" አይደለም ሀገር የምዞረው የሚለው።
ይልቅ የሀገራቱን ታሪክ፣ ባህል፣ አኗኗር ወይም 'ልዩ ነገራቸውን' ለማሳየት ይጥራል።
ባለትዳር የሆነው አቤል የሁለት ልጆች አባት ነው። ታዲያ ብዙዎች 'ቤተሰብህን ጥለህ ይኼን ሁሉ ሀገር እንዴት ነው የምትሄደው?' ብለው ይጠዩቁታል።
"ሰዎች ዓመቱን ሙሉ የምጓዝ ይመስላቸዋል። ይህ የሚቻል አይደልም። በአንድ ዓመት ውስጥ ሁለት ሦስት ወር ነው የምጓዘው። አንድ ጊዜ ሰጓዝ የ5 ወር ቪዲዮ ይዤ ነው የምመለሰው" ሲል ይጠቅሳል።

የፎቶው ባለመብት, Abel
"ኢትዮጵያ ውስጥ ዩቲዩበር የለም"
"እኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን ሌላም ሀገር ሄጄ በዩቲዩብ ነው የምኖረው ስላቸው አያምኑም። 'እንዴት?' ይሉኛል ትናንሽ ሳንቲም ብቻ የሚገኝ የሚመስላቸው" የሚለው አቤል ዩቲዩብ ላወቀበት ትልቅ የሀብት ምንጭ ነው ሲል ይገልጻል።
ውጤቱ እስኪመጣ ግን ልፋት አለው።
"የሚያደክሙ ነገሮች አሉ። የሚያሰለቹ ብዙ ነገሮች አሉ። ትዕግስት እና ወጥ በሆነ መንገድ መሥራት ያስፈልጋል" ሲል ይገልጻል።
ሌላኛው አቀራረብ ነው።
አቤል "ሰዎች፣ የእኛ ሀገር ሰው ��ምህርታዊ ነገር አይወድም ሲል እሰማለሁ። አኔ በዚህ አልስማማም። ዋናው አቀራረብ ነው፤ ሰው በሚይዝ መልኩ ካቀረብከው ሰው ያየዋል። ድሮ አንዳንድ ትምህርቶችን በአስተማሪዎቹ አቀራረብ ምክንያት እንወድ ነበር። ዩቲዩብም እንደዚያ ነው" ሲል ያስረዳል።
ተጨማሪ ዕውቀት እና ንባብም ለጥሩ ይዘት እና ዝግጅት እንደሚያስፈልግ አንስቷል።
በተለይ በኢትዮጵያ ብዙ ዕድል እንዳለ አቤል ያምናል።
"ኢትዮጵያ ውስጥ ዩቲዩበር የለም። ይህንን አፌን ሞልቼ ነው የምናገረው። ሚሊዮን ስብሰክራይበር ያላቸውን እንቁጠር ብንል በጣም ጥቂት ናችው። በዓለም ራሱ ከ500 ሺህ በላይ ሰብክራይበር ያላቸው በጣም ጥቂት ናቸው" የሚለው አቤል ዩቲዩብ "ገና ያልተነካ" ሰፊ የሥራ ዕድል ያለው መድረክ እንደሆነ ያስረዳል።
ችግሩ ግን "ብዙ ሰው የአንድ ጀምበር ስኬት ይፈልጋል። ሀሉንም ማስደሰት ይፈልጋል" ካለ በኋላ "ማንኛውም ባለሙያ የሚያወቀው ነገር ዩቲዩብ ላይ መሥራት ይችላል። ጥሩ እና ሳቢ እንዲሆን ከጣረ ጊዜ ይፍጅ እንጂ ስኬት ላይ መድረሱ አይቀርም" ሲል አክሏል።
አቤል እሱ የደረሰበትን "ለሌሎች እንዲያውቁት" መጽሐፍም አሳትሟል።

የፎቶው ባለመብት, Abel
"በሚሊዮኖች ይሠራል"
ከዘጠኝ ዓመት በፊት ከዩቲዩብ ጋር የተዋወቀው አቤል በዩቲዩብ ቋሚ የሚባል ክፍያ የለም ይላል።
"ገቢው በየጊዜው ይለያያል። ዛሬ 1 ሚሊዮን ባገኝ በቀጣይ ወር ላላገኝ እችላለሁ። ይህ ነው የሚባል ቋሚ ገቢ የለም። ምንም ጥያቄ የለውም፣ በሚሊዮኖች ይሠራል። የማረጋግጥልህ እሱን ነው። በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ታገኛለህ" ሲል ይገልጻል።
አቤል ከክፍያ በላይ ዩቲዩብ ህልሙ��� እንዲኖር፣ ዓለምን እንዲዞር ረድቶታል። ህልሙ ግን ገና ነው።
"ዓለም ላይ ያሉ ሉዓላዊ የሚባሉ ሀገራትን በሙሉ ማየት እፈልጋለሁ" ይላል።












