እነ ሞገስ አስገዶም፣ አብረሃ ደቦጭ፣ ፕ/ር አስራት ወልደየስ፣ ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም፣ ስብሐት ገ/እግዚአብሔር የተማሩበት ተፈሪ መኰንን

የዛሬ 100 ዓመት የኢትዮጵያ ሕዝብ 12 ሚሊዮን ግድም ነበር።
አስኳላ አልነበረውም፣ ጠመኔ አልነበረውም፣ ጥቁር ሰሌዳ አልነበረውም። አንድ አርቆ አሳቢ 'ንጉሥ' ግን ነበረው።
በእርግጥ ንጉሡ ያኔ ገና ንጉሥ አልነበሩም። አልጋ ወራሽ ነበሩ።
አልጋ ወራሽ ኾነው በአውሮጳ ጉብኝት አደረጉ። ይሄ ጉብኝት ኢትዮጵያ ''የምትነዳበትን ማርሽ" ቀየረ።
'ጃንሆይ' በዚያ ጉብኝት ደንግጠዋል። በእርግጥ ከዚያ በፊት በምኒልክ ጊዜ አባታቸውም እንዲሁ አውሮጳን ጎብኝተው ደንግጠዋል።
አባት እና ልጅ ለምን ደነገጡ?
አውሮጳ መጥቋል፤ ዘምኗል፣ ተመንድጓል። ሕዝባችን ግን ኋላ ቀርቷል።
እኛ ከተቀረው ዓለም በመንፈስም በግብርም ሩቅ ነን። ተዘግተናል። ትንሽ ጠቅሞን ይኾናል፤ ብዙ ግን ጎድቶናል።
ዓለም በዝማኔ ጥሎን ገስግሷል። ለካንስ ምን ያህል ድሆች እንደነበርን ለማወቅ ራሱ ወጣ ማለት ያስፈልግ ነበር።
"እንዴት ነው ከዚህ በኋላ አውሮጳ የደረሰበት የምንደርስ?" እያሉ አልጋ ወራሽ በሐሳብ ነጎዱ።
አቋራጩን መንገድ ማግኘትን ፈቀዱ።
ትምህርት!
ሚያዝያ 19/1917 ዓ.ም. ተፈሪ መኰንን ትምርት ቤት ተመረቀ።
ይሄ ትምህርት ቤት ከሰሞኑ 100 ዓመት ደፈነ።
የዚህ ትምህርት ቤት 'ግለ ታሪክ' የዘመናዊት ኢትዮጵያ 'አስኳል እና ቅርፊት' ነው። በሰፊው ቢዘከር፤ ቢሰነድ፣ ምናልባት ደግሞ ቢነበብ ብለን ይህን ዥረት ዘጋቢ ሐተታ ጻፍን።
'ራት 'ከቤተ መንግሥት' እየመጣላቸው የተማሩ ልጆች
ከመጀመሪያ ተማሪዎች ዛሬ በሕይወት ያለ አለ? ያ ሰው ዕድሜው 110 አልፏል ማለት ነው። ከኋለኞቹ ተማሪዎች ግን ብዙ አሉ።
በአንድ ዘመን በተፈሪ ቤት አብረው የተማሩ ድንገት ከተገናኙ ፍቅራቸው ለጉድ ነው፤ ''ትዝ ይልኻል? ትዝ ይልሻል?'' መባባል ከጀመሩ መሽቶ ይነጋል።
ድሮ የራሳቸው 'ብሔራዊ' መዝሙር ሁሉ ነበራቸው። ዛሬም በስተርጅና ያልረሱት መዝሙር። ሲገናኙ ይዘምሩታል። ''We are the Voice of Teferi Mokonnen'' ይሰኛል።
"Tri-Tru-Tri La-La!
Tri-Tru-Tri Tra-La-la" እያለ የሚቀጥል ነው። የራሱ ብሔራዊ መዝሙር ያለው ሌላ ትምህርት ቤት አለ? እንጃ።
የመጀመሪያዎቹ አዳሪ ተማሪዎች 30 ብቻ ነበሩ። ተቀማጥለው ነው የተማሩት። በእርግጥ ጫማ አልነበራቸው ይሆናል። ግን በጊዜው መለኪያ 'እንደ ዕንቁላል' ነበር የተያዙት።
የደምብ ልብስ ነበራቸው። እራት ከአልጋ ወራሽ ግቢ ይመጣላቸው ነበር። ዘወትር ሐሙስ የአልጋ ወራሽ ሚስት ወ/ሮ መነን [የወደፊቷ እቴጌ] የማር ብርዝ እና እንጀራ ወጥ ያበሏቸዋል።
ከዚህ በላይ ምን መቀማጠል አለ?
የሚገርመው የተማሪዎቹ ዕድሜ እና መደብ ለየቅል ነው መኾኑ ነው።
ከመካከላቸው የ9 ዓመት ልጆች ነበሩበት። ግን ደግሞ የ19 ዓመት ጎረምሳም አይጠፋም።
ካጣ ከነጣ የገበሬ ልጅ ተወልደው፣ ከዳር አገር የመጡ ገራገር ባላገር ልጆች ነበሩበት።
አሽከር አጅቧቸው፣ ፈረሳቸውን እንደ 'ላምቦርጊኒ' ደጅ አቁመው ወደ ክፍል የሚገቡ የመሳፍንት ልጆችም ነበሩ።
በሕይወታቸው እስክሪብቶ አይተው የማያውቁ ልጆች ነበሩበት። ሽጉጥ ታጥቀው የሚመጡ የመሳፍንት ልጆችም እንዲሁ። ይሄ ታዲያ መናኛ የፈረንጅ ልቦለድ እንጂ እውን ይመስላል?
የንጉሥ ዐፄ ዮሐንስ የልጅ ልጅ ደጃዝማች ዘውዴ ገብረሥላሴ በዚህ ረገድ የዋህነታቸውን ሲያሰረዱ፣ ''ያኔ ከኔ ጋር የሚኖሩ መስሎኝ ሁለት አሽከር አስከትዬ ነበር እኮ የመጣሁት'' ሲሉ ለዶ/ር ሞገስ ገብረማሪያም ነግረዋቸዋል። ምባልባት ደጃዝማች ይህን ያደረጉት ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት በመጡ ጊዜ ይኾን?
ኋላማ ደጃዝማች ዘውዴ፣ ኦክስፎርድ ገብተው፣ ዶክተር ተብለው፣ አገራቸውን በአምባሳደርነትም በሚኒስትርነት አገልግለው 'ቤት አልባው ከንቲባ' እንደተባሉ አረፉ።
ከንቲባ ዘውዴ ጣሊያንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝኛ፣ አረብኛን አቀላጥፈው ይናገሩም ነበር። ብዙዎቹ የተፈሪ ዘመን ልጆች እንዲያ ነበሩ። 'ሳት የላሱ።

ያኔ ተማሪዎች በሁለት ይከፈሉ ነበር፤ አዳሪ እና ተመላላሽ። ከአልጋ ወራሽ ግቢ እራት የሚመጣላቸው ታዲያ ለአዳሪ ተማሪዎች ብቻ ነው።
ጃንሆይ ድንገት መጥተው ይጎበኟቸዋል። ጃ ቢቀሩ ቢቀሩ በሳምንት ዐርብ አይቀሩም።
"በርቱልኝ ልጆቼ" ብለው፤ ግንባራቸውን አሻሽተው "አንተ ደግሞ የማንኛው ልጅ ነህ?'' ብለው፣ ስጦታ ሰጥተዋቸው ይሄዳሉ።
ድንገት ኩስስ- ክስት- ሙዝዝ-ፍዝዝ ያለ ተማሪ ካዩ ''ምን ኾኖ ነው ይህ ልጅ?" ብለው ይጠይቃሉ። የታመመ ከመሰላቸው አጥሚት ያዙለታል።
ነፍስ ኄር ደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ድሮ እዚያ ተምሯል። ስለ ንጉሡ ፍቅር አውርቶ አይጠግብም ነበር። ስለተንከባከቡት ይሆናል። አንድ ጆግ አጥሚት አዘውለትም ይሆናል፤ ማን ያውቃል?
ስብሐት ፈረንሳይኛ እና አማርኛ ልቅም አድርጎ ይናገራል፤ ይጽፋልም። ቀድሞ ጊዜ በአማርኛ ሐሳብ መግለጽ የሚቻልም አይመስለውም ነበር አሉ። በኋላ ነው ነገሩ የተገላቢጦሽ መኾኑ የተገለጠለት።
ይህቺ የቋንቋ ንጽጽሩ በተደጋጋሚ ትዘከርለታለቸ፦
"እንግሊዝኛ እንደ አማርኛ የልብ ያደርሳል? እስቲ አሁን 'አይዞህ' በእንግሊዝኛ እንዴት ይገለጻል ?
እንግሊዝኛ እንደ ቋንቋ መተሳሰብን መች ይደግፋል? እስቲ አሁን፣ 'እኔን' ብሎ ነገር የት አባቱ ያውቃል? እሱን ተውት ፣ 'የት አባቱ !' ማለትንስ የት አባቱ አውቆት?
ሰው እንቅፋት ሲመታው 'እኔን ' በሚለው መተሳሰብ ፋንታ፣ 'ዋች አውት ! አር ዩ ኦ ኬ?' የት ያደርሳል?
'ዋች አውት ' አጠጋግተን ስንተረጉመው እንግዲህ ፣ 'ምን አባሽ ያደናብርሻል?' አይደለም ?"
ስብሐት ብቻ ሳይሆን ተፈሪ መኰንን የተማሩ ብዙዎቹ ፈረንሳይኛ እና እንግሊዝኛ ነበር የሚቀናቸው። ያለ ምክንያት አይደለም። ትምህርት የሚሰጠው በፈረንሳይና በእንግሊዝ አፍ ስለነበረ ነው።
በተፈሪ ተማሪ ቤት፣ ትምህርት በየትኛው ቋንቋ ይሰጥ የሚለው፣ ራሱን የቻለ 'ቀዝቃዛ ጦርነት' ያስነሳ ጉዳይ ነበር። ኋላ በጨረፍታ እናነሳዋለን።

አንቀጽ-43
“እየተመላለሱ የሚማሩ ልጆች ምሳቸውን በትምህርት ቤቱ መብላት የፈለጉ እንደሆነ በየወሩ ሦስት- ሦስት ብር ይከፍላሉ፤ አከፋፈሉም ባመት ሦስት ጊዜ ነው።"
"እኔ የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ ተፈሪ ለቤተ መንግሥትም ሥራ ቢኾን፣ ለቤተ ክህነትም ሥራ ቢኾን ወይም ለራሱ ሥራ ቢኾን ለሰው ሁሉ መጀመሪያ የሚያስፈልገው ትምህረት መኾኑን ስለተረዳሁ ይህን ትምህርት ቤት አቁሜያለሁ። ስሙም ተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ተብሏል።"
የሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ውለታ
ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ በፈረንጅኛ ስማቸው ዶ/ር ቻርለስ ማርቲን ይባላሉ። እንግሊዛዊ ኾነው ያደጉ፣ ግን ደግሞ የቋራ ሰው ናቸው።
የልደት ስማቸው ወርቅነህ መሆኑን ያወቁት ራሱ ከጎለመሱ በኋላ ነው።
በመቅደላ ጦርነት ሕጻን ሳሉ የናፒየር ጦር ይዟቸው ሄደ፤ ወደ ሕንድ፣ ወደ በርማ። ታሪካቸው የዐጤ ቴዎድሮስን ልጅ፣ የልዑል ዓለማየሁን ይመስላል።
ልዩነቱ እሳቸው በአጭር አልተቀጩም። ልዩነቱ እርሳቸው የንጉሥ ልጅ አልነበሩም። ልዩነቱ እሳቸው ወደ አገራቸው መጥተው ድንቁርናን ለመበቀል ዕድል ማግኘታቸው ነው።
ከዚህ 100 ዓመት ከደፈነው ትምህርት ቤት ጋር ታዲያ ምን ያያይዛቸዋል?
በጣም ነው እንጂ የሚተሳሰሩት።
የተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት አባት ጃንሆይ ናቸው ካልን፣ የትምህርት ቤቱ 'እናት' ያለ ጥርጥር ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ናቸው። አዋልደውታላ።
እንዲህ ነው ታሪኩ።
ጃንሆይ ከንግሥና በፊት ባደረጉት ጉብኝት ''በአውሮፓ ሥልጣኔ በቅናት 'ት-ክ-ን' ብለው መጡ'' አላልንም ቅድም? አልጋ ወራሽ ሳሉ።
ይሄን በመጠኑ ከፍ ያለ መንገብገብ እና ቁጭት የሚጋራቸው ሰው ግን አላገኙም ነበር። መኳንንቱ አልተረዷቸውም። ከሐኪም ወርቅነህ ጋር ግን ልብ ለልብ ተናበቡ።

ሐኪም ወርቅነህ በዕድሜ የጃንሆይ ታላቅ ናቸው። የትና የት። የተማሩትም እንግሊዝ ነው። ያጠኑትም ሕክምና ነው።
በዚያ ዘመን ውጭ አገር የተማረ ኢትዮጵያዊ ማግኘት፣ ጣሊያን የቀበረውን ወርቅ እንደማግኘት ያለ ብርቅ ነገር ነበር።
ከዕለታት አንድ ቀን፣ ከአውሮፓ ጉዟቸው በፊት፣ ሐኪም ወርቅነህ ተፈሪ ዘንድ ይሄዱና "ለምን በስምዎ ትምህርት ቤት አይከፍቱም?" ይሏቸዋል።
ጃንሆይ ደስታ ተናነቃቸው። የጃንሆይ ፊት እኮ ሲከፋውም ሲደሰትም አያስታውቅም። ያን ቀን ግን ፈካ።
"ይሄማ በአእምሮዬ ሲመላለስ የነበረ ጉዳይ ነው፤ ችግሩ ማን ያስተዳድርልኛል? አንተ ካልያዝከው" አሉ።
ሐኪም ወርቅነህ ወዲያው ፈቃደኝነታቸውን ገለጹ።
ከዚህ ወዲያ ያለው ታሪክ በጣም ረዥም ስለሆነ እንዘለዋለን።
ብቻ በዚያን ጊዜ የ60 ዓመቱ ሐኪም ወርቅነህ ወገባቸው እስኪጎብጥ ሌት ተቀን ቆመው ትምህርት ቤቱን አስገነቡ። በዚያ ላይ ማስገንባት ይወዳሉ። አዲስ አበባ በዚያ ዘመን አይታው የማታውቀው፣ ምናልባትም የመጀመርያው ዘመናዊ መኖርያ ቤት ጃንሜዳ ጋ አስገንብተው ነበር፤ ለዚያውም አርመኖችን፣ ሕንዶችንና ሌሎች የውጭ ዜጎችን ቀጥረው።
ሐኪም ግንባታ ይዋጣላቸዋል፤ ይህን ተማሪ ቤትም በ1915 አስጀምረው፣ በሚያዝያ 19/1917 ዓ. ም. ተመረቀ።
ሐኪም ወርቅነህ በዚያች ዕለት ይህን ታሪካዊ ንግግር አሰሙ፦
“…ጸንቶ የቆመ የፍጥረት ሕግ ነውና፣ ማናቸውም ሕዝብ ባለው አኳኋን ብዙ ጊዜ ሊቆይ አይችልም። ወይ ወደፊት ይገፋል፣ ወይ ወደ ኋላ ይቀራል። ወደ ኋላ የቀረ እንደሆነ ከርሱ በበለጡ ሕዝቦች ይሰጥማል። ይህ ሕግ በዓለም ሙሉ የጸና ነው።
...የጃፓን ሰዎች ሕይወትና ነጻነት ከጥፋት ያዳኑ ይህን ዋና የሚያሻቸውን ነገር [ትምህርት] በጊዜ ስላወቁ እኮ ነው።”"
ይህን ታላቅ ንግግር ያደረጉት ሐኪም ወርቅነህ ትምህርት ቤቱን ለአምስት ዓመታት አስተዳደሩት።
ይህን ተማሪ ቤት ማስተዳደር ግን ቀላል አልነበረም። አ!ቤ!ት! አስተማሪ ለማግኘት ያዩት ፍዳ። አ!ቤ!ት! ገንዘብ ለማግኘት የገረፋቸው ፊት ብዛት።
". . . ዕውቀት ዘላቂ ሃብት ነው። ማንም ሊቀማችሁ አይችልም። …ትምህርት ያልዘለቀበት አገር ነጻነቱን ይዞ ብዙ አይዘልቅም። በክንደ ብርቱ አገር ይወሰዳል። ጃፓኖች ነጻነታቸውን መጠበቅ የቻሉት እኮ ስለተማሩ ነው…"
አንቀጽ-25
“ተማሪዎች ጥፋት ባጠፉ ጊዜ አስተማሪዎቻቸው ቁም፣ ተቀመጥ፣ እጅህን ዘርጋ፣ እጅህን ሰብስብ እያሉ በቀላል ቅጣት ይቀጧቸዋል እንጂ፤ በአለንጋ፣ በጥፊ፣ በበትር፣ በክርን፣ ይህን በመሰለ በልጆች ላይ በሽታ የሚያመጣ በብርቱ ቅጣት እንዳይቀጡ ተከልክሏል። ነገር ግን በትምህርት ቤቱ አጥር ግቢ የአትክልትና የአበባ ሥራ በማሠራት ቢቀጧቸው አይከለከሉም። ”
አልጋ ወራሽ ተፈሪ አንድ መካነ እንሰሳት ሲጎበኙ ይታያል (ሎንዶን)። ለአራት ወራት በዘለቀው ጉብኝት ግሪክ፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና ጣሊያንን አዳርሰዋል። በቫቲካን የያኔውን የካቶሊክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒየስ 11ኛን አግኝተዋል። ለአጭር ደቂቃ ሙሶሎኒን ሳያገኙት አልቀሩም። የወደፊት አሳዳጃቸው መኾኑን ሳያውቁ።
አልጋ ወራሽ ተፈሪ አንድ መካነ እንሰሳት ሲጎበኙ ይታያል (ሎንዶን)። ለአራት ወራት በዘለቀው ጉብኝት ግሪክ፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና ጣሊያንን አዳርሰዋል። በቫቲካን የያኔውን የካቶሊክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒየስ 11ኛን አግኝተዋል። ለአጭር ደቂቃ ሙሶሎኒን ሳያገኙት አልቀሩም። የወደፊት አሳዳጃቸው መኾኑን ሳያውቁ።
በንግሥት ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት፣ አልጋ ወራሽ ተፈሪ ወደ አውሮጳ ያደረጉት ጉብኝት በትምህርት ላይ ጽኑ እምነት እንዲያሳድሩ ምክንያት ሳይኾን አልቀረም።
በንግሥት ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት፣ አልጋ ወራሽ ተፈሪ ወደ አውሮጳ ያደረጉት ጉብኝት በትምህርት ላይ ጽኑ እምነት እንዲያሳድሩ ምክንያት ሳይኾን አልቀረም።
ቀዝቃዛው የቋንቋ ጦርነት፣ በተፈሪ ቤት
ፈረንሳዮች የዚህ ትምህርት ቤት ማስተማሪያ ቋንቋ ፈረንሳይኛ ካልሆነ ሞተን እንገኛለን አሉ።
ጃንሆይ ፈረንሳይኛ ስለሚችሉ ለፈረንሳይ ስስ ልብ አላቸውና "ይሁን" አሉ።ሐኪም ወርቅነህ ደግሞ ግማሽ አካላቸው እንግሊዛዊ ስለሆነ "ሞቼ ነው ቆሜ!" ሳይሉ አልቀሩም።
ጃንሆይ ገና ሐረር ልጅ እያሉ በካቶሊክ ሚሽነሪዎች ነው የፈረንሳይ ፊደል የቆጠሩ።
አባ ዣሩሶ እና አባ ሳሙኤል ወልደ ካህን ከፈረንሳይኛ ሌላ ጂኦግራፊን አስተምረዋቸዋል። ትንሽ ታሪክ፣ ትንሽ ፍልስፍናም አቅምሰዋቸዋል። ስለዚህ ጃንሆይ ለፈረንሳይኛ ቅርብ ቢኾኑ አይገርምም።
ሐረር ሳሉ፣ ከጓደሉፕ የካሪቢያን ደሴት ተወላጅ የነበሩት ፈረንሳዊው ዶ/ር ጆሴፍ ቪታሊየንንም አግኝተዋል። የአባታቸው የራስ መኰንን የግል ሐኪም ነበሩ። ተፈሪ በልጅነታቸው እኚህን ቀዶ ጠጋኝ ሐኪም ማየታቸው አስተሳሰባቸውን ጠግኖታል፤ ዐይናቸውን ገልጦታል። ገና ድሮ።
አባ ሳሙኤል ኋላ በክፉ አጋጣሚ ዓለማያ ሐይቅ ሰምጠው ሲሞቱ ተፈሪ በተአምር ተረፉ። እንኳንም ተረፉ። ኢትዮጵያን ማን የዕውቀት ጠበል ይረጭ ነበር?
እንደው ነገሩን አበክረን ካሰብነው'ኮ ባለፉት መቶ ዓመታት ዘመናዊ ትምህርት የቀመሰ ዜጋ የተፈሪ ውለታ የለበትምን? አለበት እንጂ። እንዴት ማለት ጥሩ ነው።
ወይ እርሳቸው በገነቡት ተማሪ ቤት ነው የተማረ፤ ወይ እርሳቸው ባስተማሩት ዜጋ ነው የተማረ። በቀጥታም ባይኾን በተዘዋዋሪ፤ በአንድም ኾነ በሌላ።

ወደ 'ቋንቋ ክርክሩ' እንመለስ።
ሐኪም ወርቅነህ ገና የሦስት ዓመት ሕጻን ሳሉ ከመቅደላ በእንግሊዞች ስለተወሰዱ ልሳናቸው እንግሊዛዊ ነው። ልባቸው ነው ኢትዮጵያዊ። አማርኛ መናገርም መጻፍም የቻሉት በጎልማሳ ዕድሜያቸው ነው።
ለዚህ ነው የትምህርት ቤቱ ይፋዊ ማስተማሪያ ቋንቋ ምን ይሁን በሚለው አለመግባባቱ ያየለው።
ያንን ዘመን ያጠናው የታሪክ ፀሐፊ ፒተር ጋሬትሰን ይህን ቀዝቃዛ ጦርነት 'የሥነ ልሳን ጦርነት' ወይም 'The linguistic war' እያለ ይጠራዋል።
በመጨረሻ ጦርነቱ ተፋፋመና አስታራቂ ሐሳብ መጣ። ትምህርት በሁለቱም ቋንቋ ይሰጥ ተባለ። ሐኪም ወርቅነህ የትምህርት ቤቱ ሹም ኾኑ። ፈረንሳያዊው ሙሴ ዣን ጊየን ዳይሬክተር ኾነ።
ከፈረንሳይ አገር የፈረንሳይኛ መጻሕፍት መጡ። ከእንግሊዝ አገር የእንግሊዝኛ መጻሕፍት ገቡ። የአማርኛ መጽሐፍ ግን ከየት ይምጣ? በብዙ አማርኛ በሚናገር ሕዝብ መሀል አማርኛ መጽሐፍ ጠፋ።
ከንቲባ ገብሩ ከጻፏት አንዲት መጽሐፍ ውጪ ወላ ሃንቲ። አፈወርቅ ገብረየሱስ ከጻፏት አንዲት ልቦለድ ውጪ ወላ ሃንቲ። ይሄኔ ነበር ብላታ መርስዔሐዘን ወልደቂርቆስ የደረሱት።
ዝነኛው መርስዔሐዘን በዚያው አማርኛ መምህር ኾኑ። ግዕዝም ያስተምሩ ነበር።
እሳቸው ያኔ በጭንቅ ያዘጋጇት የሰዋሰው መጽሐፍ ለቀጣይ ግማሽ ምዕተ ዓመት የአገሪቱ ብቸኛ ማስተማሪያ ኾና ዘለቀች።
የቀለም ትምህርት ብቻውን ምን ይፈይዳል?
ሐኪም ወርቅነህ አካዳሚክስ 'ልሙጥ' መሆን የለበትም በሚለው ጽኑ አቋማቸው ይታወቃሉ።
"የሰው ልጅ ሙያ መማር አለበት፤ ሙያ የሌለው ሰው ምን ይፈይዳል?" ይሉ ነበር። አገር የምትለወጠው በሙያ ጭምር ነው የሚል አቋም ነበራቸው።
ሐኪም ወርቅነህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከእንግሊዝ አገር ሲመጡ ያስተዋሉት ነገር - ያበሳጫቸውም ነገር- ይኸው ነው። ሕዝቡ ሙያ የለውም። ለመማርም ግድ የለውም። አለማወቁም ብዙ አያውከውም።
ለመጀመርያ ጊዜ እናት አገራቸው ገብተው ዞር ዞር ሲሉ፣ የአዲሳ ሕዝብ ቆሞ ወሬ ያያል፤ ሐኪም ወርቅነህ በገኑ። ተንጨረጨሩ። ኋላ የጨርጨር ገዥ ሳሉም ሕዝቡን ሙያ ተማር እያሉ ጨቅጭቀው ገደሉት።
እዚያ ጨርጨርም ተማሪ ቤት፣ ሙያ መማሪያ ቤት ከፍተው ነበር። ይሄ በኋለኛው ዘመን ነው የኾነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ባሪያ ነጻ ይሁን ሲባል የመጀመሪያውን አገር በቀል 'ኤንጂኦ' የከፈቱ እና የባሪያ ልጆችን ሙያ ያስተማሩ እሳቸው ናቸው።
እና ተፈሪ መኰንን ተማሪ ቤት ልሙጥ የቀለም ትምህርት ብቻ እንዳይሰጥ የፈለጉትም ለዚሁ ይመስላል። ከዚያ በፊት ሽመና፣ ብየዳ፣ አናጢነት ለአገሬው ዝቅ ያሉ ሙያዎች ነበሩ። ሐኪም ወርቅነህ አስከበሩት።
በእርሳቸው ጉትቶታ የእጅ ሙያ ተካተተ። ሙዚቃ እና ሥዕል ሁሉ አልቀረም። እነ ሙሴ ፓፓዚያን ሥዕል፣ ሙሴ ናልባንዲያን ደግሞ ሙዚቃ ማስተማር ጀመሩ።
ቆይቶ ሙሴ ዲትሪሽ የሚባል የጂምናስቲክ አስተማሪም ተቀጠረ። ሩሲያው ሳይሆን አይቀርም።
እንዲህ ያለ ነገር በጊዜው ለአገሪቱ ፍጹም እንግዳ ነበር።
'ቢሊየነሩ' ራስ ኃይሉ 300 ብር ለገሱ
ተፈሪ መኰንን በዘመኑ 'የአፍሪካ ሃርቫርድ' እየተባለ ይጠራ ነበር። እንዲያ ያስባለው ጥራቱ ብቻ ሳይሆን ወጪው ከባድ ስለነበረ ነው።
የአንድ ተመላላሽ ተማሪ የምሳ ወጪ ብቻ በወር 3 ብር ደረሰ። ኑሮ እሳት ሆነ።
የአንድ ተማሪ የእርሳስ፣ የእስክሪብቶ የደብተር ጠቅላላ የትምህርት መሣሪያ ወጪ በወር 1 ብር ደረሰ። ጉድ ተባለ።
የትምህርት ቤቱ ጠቅላላ ዓመታዊ በጀት ወደ 80 ሺህ ተጠጋ። የቸሩ 'ንጉሥ' ኪስ ተሟጠጠ።
አልጋ ወራሽ ለትምህርት እና ለተማሪ አይሰስቱም። ትምህርት ቤቱ ራሱ የተገነባው በገዛ ርስታቸው ላይ አይደለምን?
ምን ተሻለ? ሐኪም ወርቅነህ ጨነቃቸው።
ልዑላኑን፣ መሳፍቱን እና መኳንንቱን ማስቸገር ጀመሩ። ለግንባታ ያዋጡት ሰዎች ዝም ዝረዝር ሐኪም ወርቅነህ መዝግበው ይዘዋል።
የዘመኑ ቢሊየነር የነበሩት ('ሺሊየነር' የሚል ቃል የተሻለ ይስማማል)የጎጃሙ ራስ ኃይሉ 5 ሺህ ብር ለገሱ። አገር ጉድ አለ።
ራስ ጉግሳ አርአያ 300 ብር ሰጡ። አገር ጉድ አለ። ''እንዲያው የመሳፍንቱ አዱኛ ማለቂያም የለው'' እያለ ባላገር ተንሾኳሾከ። የጣፈው የለም እንጂ አዝማሪ ብዙ ብሎ ሊኾን ይችላል።
በነገራችን ላይ ጃንሆይ በዚህ ትምህርት ቤት በጣም ነበር የሚኮሩት።
የውጭ እንግዳ ሲመጣ ቶሎ ብለው ወደዚህ ትምህርት ቤት ወስደው ያስጎበኛሉ። የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር እንግዳ ሲመጣባቸው ወደ ፓርኮች እንደሚወስዱት ዓይነት መኾኑ ነው።
ጃንሆይ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ርዕይ የሚያሳይላቸው ይኸው ትምህርት ቤት ስለነበረ ነው ያን ያደርጉ የነበረው።
በዚህ የተነሳ የሮዝቻይልድ ቤተሰብ አልቀረም፤ የጃፓን፣ የሆላንድ፣ የጣሊያን መሳፍንት አልቀሩም፤ ማንኛውም መሪ አዲሳ'ባን ከረገጠ ተፈሪ መኰንን ተማሪ ቤት ይወሰድ ነበር።



ምኒልክ እና ተፈሪ መኰንን
እዚህ ጋ የተፈሪ መኰንን ታላቅ ወንድም የኾነውን ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤትን እናንሳ።
ምኒልክ ፈር ቀዳጅ ነው፤ ይሄ አንድና ሁለት የለውም። ግን እንደ ተፈሪ መኰንን ገናና አልነበረም። ዝ'ም'ን አላላም። እንዲያውም ሐኪም ወርቅነህ በምኒልክ ትምህርት ቤት ጭራሽ ደስተኛ አልነበሩም።
እርግጥ ነው ሐኪም ወርቅነህ መጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ ንጉሥ ምኒልክ ይህን የመጀመሪያ ትምህርት ቤት እንዲመሠርቱ አበረታተዋል። እጃቸው አለበት።
ሐኪም ወርቅነህ የንጉሥ ምኒልክ የግል ሐኪም መኾናቸው ሳይዘነጋ።
ንጉሡን ብቻ ሳይሆን እቴጌ ጣይቱን፣ፓትሪያርኩን አቡነ ማቴዎስን ጭምር "ዘመናዊ ትምህርት እንደምታስቡት የሰይጣን አይደለም" እያሉ በማሳመን ብዙ ጉልበት ጨርሰዋል። ከእቴጌይቱ ጋር ብዙም ኮከባቸው ባይገጥምም እንደነገሩ አብረው ሠርተዋል።
ምኒልክ ተከፈተ። ሐኪም ግን በውጤቱ ደስተኛ አልነበሩም። ለምን?
ምክንያቱም ሐኪም ወርቅነህ ከግብፅ የመጡትን 'አስተማሪዎች' አልወደዷቸውም። ካህናት ነበሩ።
ከግብፅ እንዲመጡ የኾነው ደግሞ የኢትዮጵያ አንዳንድ ካህናት በዘመናዊ ትምህርት ላይ ጥርጣሬ ስለነበራቸው ነበር። በአጋጣሚ የኾ ነገር አይደለም። ነገሩ ከባድ የሕዝብ ዲፕሎማሲ ነው።
ንጉሡ ጥበበኛ ስለነበሩ መምህራኑን ሆን ብለው ከግብፅ ኮፕቲክ አስመጡ። እነዚህ መነኮሳት ናቸው በምኒልክ ተማሪ ቤት አስተማሪ የኾኑት።
እነዚህን መምህራን ሐኪም ወርቅነህ ባገኙት አጋጣሚ ይወርፏቸዋል። "ብዙም የዘመናዊ ትምህርት ዕውቀት አልነበራቸው" ሲሉ ይወቅሷቸዋል።
ባልታተመው የግል ማኅደራቸው እንዲህ ጽፈዋል፤ ". . .18 ዓመት ሙሉ አንድ እንኳ የረባ ሰው አላፈሩም!"
ሐኪም እንዲያ ይበሉ እንጂ ኋላ የኢትየጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መኾን የቻሉትን እነ አክሉሉ ሃብተወልድን እነ ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸውን ያፈራ' ኮ ምኒልክ ትምህርት ቤት ነው። ንጉሡስ ቢኾኑ የት ተማሩና።
ምናልባት የቁጭታቸው ምንጭ እርሳቸው በተማሩበት የምዕራቡ የጥራት ከፍታ ልክ አለመኾኑ ይኾን? ለነገሩ እንኳንም ተቆጩ። ይሄ ቁጭት እኮ ነው ተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤትን ከምኒልክ የላቀ ለማድረግ ያነሳሳቸው።
ደግነቱ ሐኪም ወርቅነህ እና አልጋ ወራሹ ሽርክ ነበሩ፤ በትምህርት ፍልስፍናቸው ስምም ናቸው።
የሁለቱ መቀናጀት ተፈሪ መኰንን ከፈር ቀዳጁ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ይልቅ ብዙ የተማረ እንዲያፈራ፤ ብዙ ርቀት እንዲሄድ አስችሎታል።
ለዘመናዊት ኢትዮጵያ እንደዚህ ትምህርት ቤት አስተዋጽኦ አለው የሚባል አንዳችም ተቋም የለም፤ ኋላ ከመጣው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በስተቀር። እሱንም ቢኾን ያዋለዱት የተፈሪ ትምህርት ቤት ካናዳዊ መምህራን መኾናቸውን ልብ ይሏል።
ካናዳዊያኑ መምህራን ለኢትዮጵያ ካስተዋወቁት ‘ባዕድ' ስፖርት አንዱ ቤዝቦል ነበር። እንደ እግር ኳስ ከግቢው ወጥቶ ሊወደድ አልቻለም እንጂ።
ካናዳዊያኑ መምህራን ለኢትዮጵያ ��ስተዋወቁት ‘ባዕድ' ስፖርት አንዱ ቤዝቦል ነበር። እንደ እግር ኳስ ከግቢው ወጥቶ ሊወደድ አልቻለም እንጂ።
አሜሪካዊው ዳግላስ ኤዲ በተፈሪ ትምህርት ቤት ከተማሪዎቹ ጋር በ1950ዎቹ መጨረሻ
አሜሪካዊው ዳግላስ ኤዲ በተፈሪ ትምህርት ቤት ከተማሪዎቹ ጋር በ1950ዎቹ መጨረሻ







አንቀጽ- 49
"ለእያንዳንዱ ተማሪ የሚያስፈልግ የበዓል ወይም ከሰው መገናኛ ልብስ የሚከተለው ይሁን፦ “አንድ ኮት፣ አንድ ሱሪ፣ ሁለት የገላ የውስጥ ሹራብ ጥጥ፣ ሁለት መሐረም፣ አንድ የአውሮጳ ጫማ”
"ጃንሆይ ድንገት ክስት-ሙዝዝ-ፍዝዝ ያለ ተማሪ ካዩ ''ምን ኾኖ ነው ይህ ልጅ?" ብለው ይጠይቃሉ። የታመመ ከመሰላቸው አጥሚት ያዙለታል። "
በዚያ ዘመን ተፈሪ መኰንን ተማሪ ቤት የኬሚስትሪ ቤተ ሙከራ ክፍል ነበረው። ከመቶ ዓመት በኋላ ይህ ያልተሟላላቸው ዩኒቨርስቲዎች መኖራቸው ሲታሰብ የታሪክ ምጸት ይመስላል።
የተፈሪ የቀድሞ ተማሪዎች በ1973 ዓ/ም የተነሳ ፎቶ
ተፈሪ መኰንን እነማንን አፈራ?
ይህ ንዑስ ርዕስ እንዳይረዝም ስንል በዝነኞች ላይ ብቻ እናተኩራለን።
ተማሪ ቤቱ ክፍለ ዘመን በደፈነ ዕድሜው ፣ በውትድርና፣ በፖለ���ካ፣ በሳይንስ፣ በፍልስፍና፣ በሕክምና ታላላቅ ሰዎችን አፍርቷል። ሚኒስትሮች እና ርዕሳነ ብሔራት አልቀሩትም። የኪነ ጥበብ ሰዎችም አያንሱትም።
በታሪክ ከመፈንቅለ መንግሥት ጋር ስማቸው የሚነሱ ብዙዎቹ ከዚህ ትምህርት ቤት የወጡ መኾናቸው የሚነግረን ነገር ይኖር ይኾን? ወይስ አጋጣሚ ነው?
ለምሳሌ ከድሮዎቹ እነ ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ ሌ/ጄኔራል ዐቢይ አበበ፣ መንግሥቱ ነዋይ . . . ወዘተረፈ።
ለነገሩ በጣም ብዙ የጦር መሪዎች እና ሚኒስትሮች ከዚህ ተማሪ ቤት መውጣታቸውን ልብ ይሏል። ጀጋማ ኬሎም ተፈሪ ተምረዋል። ጠላት በመጣ ጊዜ ሆለታ ገነት የጦር አካዳሚ ገብተው፣ የውጊያ ትበብ ተምረው፤ ጣሊያንን የተፋሉ የተማሩ ወታደሮች ከዚህ ነው የወጡት።
በጦር ሳይንስ ገናና ከነበሩትና ከወለጋ ወደ ተፈሪ ቤት ከመጡ የመጀመሪያ አዳሪ ተማሪዎች መካከል ሜ/ጄኔራል ዋቅጅራ ሰርዳ ይጠቀሳሉ።
ተፈሪ ከተማሩ በኋላ የፈረንሳዩን ፕሬዝዳንት እና ጦር አዋቂ ቻርለስ ደጎልን ያፈራው የዓለም ስመ ጥሩ ሳን ሲር (Saint-Cyr) የጦር አካዳሚ ተልከው የተማሩ ናቸው። ምባልባት ከደጎል ጋር የፈረንሳይ ጢቢኛ ዳቦ (ባጌት) ቆርሰው ይኾናል። ማን ያውቃል?
አብረዋቸው ከወለጋ ወደ ተፈሪ ከመጡት ቀደምት ተማሪዎች መካከል ታላቁ አምባሳደር፣ ሚኒስትር እና ዲፕሎማት አማኑኤል አብረሃም ይጠቀሳሉ። ኹሉም ተፈሪ ነው የተማሩት።
ዶ/ር ሞገስ ገብረማሪያም በ8 ዓመታቸው በ1948 ተፈሪ መኰንን ተመዘገቡ። እርግጥ የአባታቸው ሕልም ዲያቆን እንዲሆኑላቸው ነበር። በድምጻቸው አለማማር ምክንያት አባታቸው ተስፋ ቆርጠው ‘በቃ እንግዲህ የፈረንጅ ትምህርት ይሞከር’ ብለው አስመዘገቧቸው። ዶ/ር ሞገስ በሕክምና ተመርቀው ከንጉሡ ዲግሪያቸውን ሲቀበሉ ይታያሉ። ፊት ለፊት ቆመው የሚታዩት ዶ/ር አክሊሉ ሃብቴ ናቸው። 1965 ዓ/ም ነው።
ዶ/ር ሞገስ ገብረማሪያም በ8 ዓመታቸው በ1948 ተፈሪ መኰንን ተመዘገቡ። እርግጥ የአባታቸው ሕልም ዲያቆን እንዲሆኑላቸው ነበር። በድምጻቸው አለማማር ምክንያት አባታቸው ተስፋ ቆርጠው ‘በቃ እንግዲህ የፈረንጅ ትምህርት ይሞከር’ ብለው አስመዘገቧቸው። ዶ/ር ሞገስ በሕክምና ተመርቀው ከንጉሡ ዲግሪያቸውን ሲቀበሉ ይታያሉ። ፊት ለፊት ቆመው የሚታዩት ዶ/ር አክሊሉ ሃብቴ ናቸው። 1965 ዓ/ም ነው።

ወደ ኋለኛው ዘመን ከመጣን ተፈሪ መኰንን ያፈራው ቁጥር ስፍር የለውም። ሕዝብ የሚያውቀው ግን ሚዲያ የዘመረላቸውን ብቻ ነው።
በፖለቲካ ንቁ ከነበሩት ውስጥ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም እና ታላቁ ሐኪም ፕ/ር አስራት ወልደየስ ይነሳሉ።
ርዕሰ ብሔር ከኾኑት ደግሞ መቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ይጠቀሳሉ። በነገራችሁ ላይ የቀድሞዋ ርዕሰ ብሔር የሳሕለ ወርቅ ዘውዴ አባት፣ ኮ/ል ዘውዴ ዘረፋ እዚሁ ነበር የተማሩት።
ከጥበብ ሰዎች ደበበ እሸቱ፣ ወጋየሁ ንጋቱ ፣ሃይማኖት ዓለሙ (ቴአትር)፣ ደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ፣ ስብሐት ገ/እግዚአብሔር፣ ተስፋዬ ገሰሰ፣ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ ሰለሞን ደሬሳ፣ ልዑልሰገድ ረታ ይጠቀሳሉ።
ከቅርቦቹ የኪነ ሕንጻ ነዳፊው ፋሲል ጊዮርጊስ እና ታላቁ የሕግ ሰው አቶ ተሾመ ገብረማሪያምን ማንሳት ይቻላል።
የአፍሪካ የእግር ኳስ አባት ይድነቃቸው ተሰማም የተፈሪ ልጅ ናቸው። ልጃቸው ታደለ ይድነቃቸውም እንዲሁ።
የጅማው አባጅፋር የልጅ ልጅ አምባሳደር አባቢያ አባጆቢር አባጂፋርም የተፈሪ ፍሬ ናቸው። ዛሬም በሕይወት አሉ።

በነገራችሁ ላይ ብዙ ሰዎች ይህ ትምህርት ቤት የመሳፍንቱና መኳንንቱ ልጆች ብቻ የተርመሰመሱበት ይመስለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቀድሞ ተማሪዎች ግን ይህ እውነት እንዳልሆነ መስክረዋል።
ከየጠቅላይ ግዛቱ፣ ከጠረፍ ሳይቀር ተማሪ ላኩ እየተባሉ ብዙ የገበሬ ልጆች በዕድሉ ተጠቅመዋል።
እንዲያውም ችግሩ የነበረው ሕዝቡ ልጁን እንዲልክ ማሳመኑ ላይ ነበር።
ብዙ ወላጅ ዘመናዊ ትምህርትን ከሰይጣን በላይ ይፈራ ነበር - ከእምነት ጋር በተያያዘ ነው ነገሩ።
ትምህርት እየተስፋፋ ሲመጣም ይህ ችግር በብዙ ተንጸባርቋል።

ዶ/ር አክሊሉ ሃብቴ (ከግራ 2ኛ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 2ኛው ኢትዮጵያዊ ፕሬዝዳንት ነበሩ። በቀኝ በኩል ያየህይራድ ፍቅሬና ዶ/ር ሙሉጌታ ወዳጆ ይታያሉ።
ዶ/ር አክሊሉ ሃብቴ (ከግራ 2ኛ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 2ኛው ኢትዮጵያዊ ፕሬዝዳንት ነበሩ። በቀኝ በኩል ያየህይራድ ፍቅሬና ዶ/ር ሙሉጌታ ወዳጆ ይታያሉ።
ዶ/ር ጴጥሮስ አክሊሉ ወደ ማሳቹሴትስ ከማምራታቸው በፊት ተፈሪ መኰንን ነው የተማሩት። ወንድማቸው ኮ/ል ጳውሎስም ተፈሪ መኰንን ነው የተማሩት። አባታቸው በ1917 ከተመዘገቡ የመጀመርያዎቹ ተማሪዎች አንዱ ነበሩ።
ዶ/ር ጴጥሮስ አክሊሉ ወደ ማሳቹሴትስ ከማምራታቸው በፊት ተፈሪ መኰንን ነው የተማሩት። ወንድማቸው ኮ/ል ጳውሎስም ተፈሪ መኰንን ነው የተማሩት። አባታቸው በ1917 ከተመዘገቡ የመጀመርያዎቹ ተማሪዎች አንዱ ነበሩ።
ሐርቫርድ የገቡት የተፈሪ መኰንን ልጆች
ሐኪም ወርቅነህ በጃንሆይ እርዳታ ምርጥ ተማሪዎችን ስኮላርሺፕ እንዲያገኙ ይጥሩ ነበር። ያኔ ገና ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በአገሪቱ የለማ።
ተማሪዎቹ 2ኛ ደረጃ ጨርሰው ቁጭ ይበሉ? ጭንቅ ሆነ።
ሐኪም ወርቅነህ ይህን ለማሳካት ያልረገጡት ምድር አልነበረም። መጀመሪያ ከተፈሪ የተመረቁ 12 ተማሪዎች ውጭ አገር ተላኩ።
6 ፈረንሳይ፣ 6 ሊባኖስ። በሊባኖስ የአሜሪካን ዩኒቨርስቲ የሚባል ድንቅ ኮሌጅ አለ።
የሚገርመው እነዚህ ተማሪዎች የኪስ ገንዘባቸውን የሚያገኙት ከጃንሆይ ኪስ ነበር። በኋላ ነው ወጪው ከትምህርት ሚኒስቴር የሆነው።
በእንሰሳት ሕክምና ምናልባትም የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ዶ/ር ዮሐንስ እንግዳ ኒውዮርክ ነው የተማሩት።
ጃንሆይ ከኪሳቸው ከፍለው አሜሪካ ልከው ካስተማሯቸው መካከል ታላቁ የጥቁር መብት አቀንቃኝ መላኩ በያን ይገኝበታል።
መላኩ በያን ማለት እኮ የማርከስ ጋርቬይ ወዳጅና የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሐኪም ነበር። (ሐኪም ወርቅነህን እንግሊዛዊ አድርገን ከቆጠርን ማለት ነው።) እሱ ግን ተፈሪ አልተማረም። መጀመርያ ሐረር፣ ከዚያ ሕንድ፣ ከዚያ አሜሪካ ሐዋርድ ነው የተማረው።
ይልቅ መኮንን ደስታ፣ ተፈሪ መኰንን ነው የተማሩት። መኮንን ደስታ ምናልባትም ሃርቫርድ ገብቶ ለመማር የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሳይኾኑ አይቀሩም።
ሕክምና ጀምረው በኋላ ወደ ሰው ዘር ጥናት ክፍል ዞሩ። ጃንሆይ ከስደት ከተመለሱ በኋላ ካቤኒያቸውን ሲያዋቅሩ መኮንን ደስታ የመጀመሪያው የትምህርት ሚኒስትር ነበሩ።
ከእርሳቸው በኋላ ለ20 ዓመት አካባቢ የትምህርት ሚኒስትር ራሳቸው ንጉሡ ነበሩ። ንጉሡ የትምህርት ጉዳይ የግል ጉዳያቸው አድርገው ነበር የሚወስዱት። ለዚያ ነው ለትምህርት ገንዘብ የማይሰስቱት። ለዚያ ነው ሚኒስትር እንኳ ለመሾም የሚሳሱት።
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ንጉሡ እንዲያ እንዳያደርጉ የመከሩ ነበሩ። ያስተማሯቸው ተማሪዎች ኋላ ለዙፋናቸው አደጋ እንደሚኾኑ ያስጠነቀቁ ባለሟሎችም ነበሩ።
የነዚህ ሰዎች ትንቢት መድረሱ ባይቀርም የንጉሡ የትምህርት ፍቅር ግን ጥልቅ ስለነበር በጄ አላሉም።
በርሳቸውና በሐኪም ወርቅነህ እርዳታ በአውሮፓ እና በአሜሪካ ስመ ጥር ዩኒቨርስቲዎች ገብተው የተማሩ የተፈሪ መኰንን ተማሪ ቤት 'ፍሬዎች' ቁጥር ሥፍር የለውም።
ክፍሌ ወዳጆ እና ሙሉጌታ ወዳጆ
ሐርቫርድ ከገቡት የተፈሪ ልጆች አንዱ ዶ/ር ሙሉጌታ ወዳጆ ናቸው።
ከሐርቫርድ በኋላ በዝነኛው ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ተምረዋል። እሳቸው ከሐርቫርድ የተመረቁት በአውሮፓውያኑ 1957 ነበር።
"የኔም ሆነ የእኩዮቼ የከፍተኛ ትምህርት ወጪ የተሸፈነልን በጃንሆይ ነበር" ሲሉ ለልጃቸው ለዶ/ር ፈላስፋ ወዳጆ ነግረውታል።
በሜሪላንድ ሥመ ጥር የአጥንት ካንሰር ልዩ ሐኪም የኾነው ዶ/ር ፈላስፋ ሙሉጌታ የአባቱን የዶ/ር ሙሉጌታ ወዳጆን የተፈሪ ትምህርት ቤት ትዝታ ዘለግ ላለ ጊዜ ቃለ መጠይቅ በማድረግ በድምጽ ቀርጾ አስቀምጦታል።
በዚያ ቃለ ምልልስ አባቱ ዶ/ር ሙሉጌታ ወዳጆ አስገራሚ ትዝታቸውን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተርከውለታል።
ለምሳሌ ጃንሆይ ትምህርት ቤት ሲመጡ ብርቱካን፣ እንጆሬ እና ዓሣ ያመጡላቸው እንደነበር ተናግረዋል። ስለጃንሆይ የሚገርም የማስታወስ ችሎታም ለለጃቸው ተርከውለታል።
"...ጃንሆይ ነገር አይዘነጉም። ከወር በፊት እንደቀልድ የነገርናቸውን ነገር እኛ ተማሪዎች ጭራሽ ረስተነው ሳለ፣ እሳቸው ግን በወሩ አስታውሰው ይጠይቁን ነበር።"
ስፔሻሊስት ዶክተር ፈላስፋ ሙሉጌታ ከአባታቸው ዶ/ር ሙሉጌታ ወዳጆ ጋር
ስፔሻሊስት ዶክተር ፈላስፋ ሙሉጌታ ከአባታቸው ዶ/ር ሙሉጌታ ወዳጆ ጋር
ወንድማማቾቹ ሙሉጌታ ወዳጆ (ቀኝ) እና ክፍሌ ወዳጆ ተፈሪ መኰንን ያፈራቸው ናቸው።
ወንድማማቾቹ ሙሉጌታ ወዳጆ (ቀኝ) እና ክፍሌ ወዳጆ ተፈሪ መኰንን ያፈራቸው ናቸው።
ዶ/ር ሙሉጌታ ወዳጆ የሐርቫርድ ምሩቅ ሲሆኑ በድኅረ ጣሊያን ዘመን ተፈሪ ካፈራቸው ታላላቅ ተማሪዎች አንዱ ነበሩ። በበተወለዱ በ89 ዓመታቸው በቅርቡ በቤቴስዳ፣ ሜሪላንድ አርፈዋል።
ዶ/ር ሙሉጌታ ወዳጆ የሐርቫርድ ምሩቅ ሲሆኑ በድኅረ ጣሊያን ዘመን ተፈሪ ካፈራቸው ታላላቅ ተማሪዎች አንዱ ነበሩ። በበተወለዱ በ89 ዓመታቸው በቅርቡ በቤቴስዳ፣ ሜሪላንድ አርፈዋል።
ከዶ/ር ሙሉጌታ ውብ ትዝታዎች አንዱ የድሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ይመለከታል።
ያኔ በ50ዎቹ የ12ኛ ክፍል ማትሪኩሌሽን ፈተና የሚዘጋጀው በኢትዮጵያ አልነበረም። ከዩናይትድ ኪንግደም ነበር በቀጥታ የሚመጣው።
ዶ/ር ሙሉጌታ ወዳጆ ከ70 ዓመት በኋላም ያልረሱት ፈተና ላይ የተጠ��ቁት ጥያቄ እንዲህ ይል ነበር፦
Write an Essay on the following:
A: Summer day at the beach
B: Busy day at the London post office
"እኛ የባሕር ዳርቸውንም ፖስታ ቤቱንም የት አይተነው እናውቅና..." ብለው ይስቃሉ።
የሐርቫርዱ ዶ/ር ሙሉጌታ ወዳጆ ይህን ትዝታቸውን ለልጃቸው አውርሰው፣ የተማሩበት ተፈሪ መኰንን 100ኛ ዓመቱን ሊያከብር መሰናዶ በጀመረበት ዓመት በተወለዱ በ89 ዓመታቸው በሜሪላንድ ቤተሰዳ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
የእርሳቸው ወንድም ታዋቂው ክፍሌ ወዳጆም የተፈሪ መኰንን ተማሪ ቤት ካፈራቸው ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነበሩ።
ክፍሌ ወዳጆ ከፍተኛ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በዊስኮንሰን ዩኒቨርሰቲ ነው። ታሪካቸው ደማቅ ነው።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በተጠባባቂ ዋና ፀሐፊነት መርተዋል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ በተባበሩት መንግሥትታ ቋሚ መልዕክተኛ እንዲሁም ለአጭር ጊዜ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ።
ይበልጥ የሚታወቁት ግን አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው ሕገ መንግሥት ሲጻፍ በአርቃቂ ኮሚሽን መሪነታቸው ነበር።
የ1950 ተመራቂ ከኾኑት ውስጥ አክሊሉ ሃብቴ፣ተሾመ ገ/ማሪያም፣እና አስመሮም ለገሰ ይታያሉ። ሦስቱም ስኬታማ ኾነዋል። ዶ/ር አክሊሉ በኋላ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 2ኛው ኢትዮጵያዊ ፕሬዝዳንት፣የባሕል ሚኒስትር፣ የዓለም ባንክ የትምህርት ክፍል ዋና ኃላፊ ኾነዋል። ፕ/ር አስመሮም ደግሞ በይበልጥ በገዳ ጥናት ሥራቸው ይታወቃሉ። ተሾመ ገብረማሪያም ታላቅ የሕግ አዋቂ ነበሩ።
የ1950 ተመራቂ ከኾኑት ውስጥ አክሊሉ ሃብቴ፣ተሾመ ገ/ማሪያም፣እና አስመሮም ለገሰ ይታያሉ። ሦስቱም ስኬታማ ኾነዋል። ዶ/ር አክሊሉ በኋላ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 2ኛው ኢትዮጵያዊ ፕሬዝዳንት፣የባሕል ሚኒስትር፣ የዓለም ባንክ የትምህርት ክፍል ዋና ኃላፊ ኾነዋል። ፕ/ር አስመሮም ደግሞ በይበልጥ በገዳ ጥናት ሥራቸው ይታወቃሉ። ተሾመ ገብረማሪያም ታላቅ የሕግ አዋቂ ነበሩ።
ምናልባት የተማሪ ቤት መዝሙር የተጀመረው በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ሳይኾን አይቀርም። መዝሙሩን የጻፉት እንግሊዝኛ አዋቂው ኤፍሬም ተወልደ መድኅን ነበሩ። መዝሙሩ ውስጥ እነዚህ ስንኞች ይገኙበታል፦
“የተፈሪ መ. ተማሪዎች፣
ለነጻነት ብሎ መሞት፣
ይህ ነው የኛ ዋናው ምኞት”

ፕ/ር አስራት ወልደየስ እና ተፈሪ መኰንን
ታላቁ የቀዶ ጥገና ሐኪም እንዲሁም ፖለቲካኛ፣ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ከተፈሪ ተማሪ ቤት ጋር ያላቸው ግንኙነት መልከ ብዙ ይመስላል።
አንደኛ የተማሩት እዚያ ነው። ያስተማሯቸው ደግሞ ጃንሆይ ናቸው።
ከተፈሪ መኰንን በከፍተኛ ውጤት ጨርሰው፣ ግብፅ፣ ቪክቶሪያ ኮሌጅ ተልከው፣ ከዚያም ዩናይትድ ኪንግደም፣ ስኮትላንድ፣ ኤደንብራ ዩኒቨርስቲ ለሕክምና ትምህርት ሄደው-በማዕረግ ተመርቀው፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕክምና ፋከልቲን መሥርተው፤ የመጀመርያው ዲን ኾነው...፤
ዞረው ዞረው ዞረው፣ ደርግ ጃንሆይን ሊገድላቸው ዋዜማ የንጉሡ የግል ሐኪም ኾኑ።
አሳድገው፣ ላስተማሯቸውን ንጉሥ ተምረው ደረሱላቸው። የሕይወት ክብነት።
ፕሮፌሰር አስራት በኤደንብራ በሕክምና ዘርፍ ለመመረቅ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ናቸው።
በ1920 አዲስ አበባ ተወልደው፣ ድሬዳዋ አድገው፣ ተፈሪ ፊደል ቆጥረው፣ ስኮትላንድ ተመርቀው፣ ሕዝባቸውን አገልግለው፣ ለ2 ዓመት ታስረው ከቆዩ በኋላ ታመሙ።
መንግሥት ላይ በደረሰ ዓለም አቀፍ ጫና ከእስር ተፈቱ። ለሕክምና ወደ ሎንዶን፣ ከዚያም ሂውስተን፣ ቴክሳስ ተላኩ።
በመጨረሻ ፔንሴልቬኒያ ግዛት፣ ፊላደልፊያ ከተማ፣ በፔን ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ቆይተው አለፉ።
ንጉሡ ከግል ርስታቸው ቆርሰው የሰጡት የተማሪ ቤቱ ካርታ
ንጉሡ ከግል ርስታቸው ቆርሰው የሰጡት የተማሪ ቤቱ ካርታ
የጃንሆይ ልጆች የት ተማሩ?
የሐረሩ መስፍን ልዑል መኰንን ኃይለሥላሴ እና ልዕልት ሰብለ ደስታ። ሥፍራው አልተገለፀም። ዘመኑ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ጥቅምት 13፣ 1947 ነው።
የሐረሩ መስፍን ልዑል መኰንን ኃይለሥላሴ እና ልዕልት ሰብለ ደስታ። ሥፍራው አልተገለፀም። ዘመኑ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ጥቅምት 13፣ 1947 ነው።
ፕሮፌሰር ጊልበርት ሙራይ ከአልጋ ወራሽ አስፋ ወሰን ኃይለሥላሴ ጋር በዓለም መንግሥት ማኅበር ዩንየን በተዘጋጀ ግብዣ ላይ፤ ግንቦት 3፣ 1936
ፕሮፌሰር ጊልበርት ሙራይ ከአልጋ ወራሽ አስፋ ወሰን ኃይለሥላሴ ጋር በዓለም መንግሥት ማኅበር ዩንየን በተዘጋጀ ግብዣ ላይ፤ ግንቦት 3፣ 1936
አልጋ ወራሽ ተፈሪ በፈረንሳይ ይፋዊ ጉብኝት ላይ ሳሉ። ዘመኑ 1916 ዓ/ም ነው። በትምህርት ረገድ ከፈረንሳይ ብዙ እገዛን ጠብቀው ነበር።
አልጋ ወራሽ ተፈሪ በፈረንሳይ ይፋዊ ጉብኝት ላይ ሳሉ። ዘመኑ 1916 ዓ/ም ነው። በትምህርት ረገድ ከፈረንሳይ ብዙ እገዛን ጠብቀው ነበር።
አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰን ኃይለሥላሴ፣ ከባለቤታቸው ልዕልት መድፈሪያሽወርቅ አበበ ጋር በሎንደን አውሮፕላን ጣቢያ። ዘመኑ 1952 ዓ/ም ነው።
አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰን ኃይለሥላሴ፣ ከባለቤታቸው ልዕልት መድፈሪያሽወርቅ አበበ ጋር በሎንደን አውሮፕላን ጣቢያ። ዘመኑ 1952 ዓ/ም ነው።
የሐረሩ መስፍን ልዑል መኰንን ኃይለሥላሴና እህቱ ልዕልት ፀሐይ ኃይለሥላሴ በምዕራብ ሎንደን ኬንሲንግተን የሚኖሩበት ግቢ ከመጡ እንግዳ ጋር ሲያወጉ ይታያሉ። ዘመኑ ግንቦት፣ 1928 ነው።
የሐረሩ መስፍን ልዑል መኰንን ኃይለሥላሴና እህቱ ልዕልት ፀሐይ ኃይለሥላሴ በምዕራብ ሎንደን ኬንሲንግተን የሚኖሩበት ግቢ ከመጡ እንግዳ ጋር ሲያወጉ ይታያሉ። ዘመኑ ግንቦት፣ 1928 ነው።
የጃንሆይ የመጨረሻ ልጅ ልዑል ሣህለ ሥላሴ ኃይለ ሥላሴ፣ ወደ ኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ከማምራታቸው በፊት እንደ ታላቅ ወንድማቸው ሁሉ በተፈሪ መኰንን ተማሪ ቤት ገብተው ተምረዋል።
የጃንሆይ የመጨረሻ ልጅ ልዑል ሣህለ ሥላሴ ኃይለ ሥላሴ፣ ወደ ኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ከማምራታቸው በፊት እንደ ታላቅ ወንድማቸው ሁሉ በተፈሪ መኰንን ተማሪ ቤት ገብተው ተምረዋል።
ሐረር ተወልደው፣ መርእድ አዝማች ተብለው፣ የወሎ ገዥ ኾነው፣ ሎንዶን ኖረው፣ ፌየርፋክስ፣ ቨርጂኒያ ያለፉት የጃንሆይ ልጅ አልጋ ወራሽ አስፋወሰን ኃይለ ሥላሴ ለአጭር ጊዜ ተፈሪ ተማሪ ቤት ገብተዋል። ከዚያ በኋላ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከሊቨርፑል ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል።
ሐረር ተወልደው፣ መርእድ አዝማች ተብለው፣ የወሎ ገዥ ኾነው፣ ሎንዶን ኖረው፣ ፌየርፋክስ፣ ቨርጂኒያ ያለፉት የጃንሆይ ልጅ አልጋ ወራሽ አስፋወሰን ኃይለ ሥላሴ ለአጭር ጊዜ ተፈሪ ተማሪ ቤት ገብተዋል። ከዚያ በኋላ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከሊቨርፑል ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል።
ልዑል መኰንን ኃይለ ሥላሴ፣ እጅግ ተወዳጁና ተመራጩ የጃንሆይ ልጅ ነበሩ። አዲስ አበባ ተወልደው ሳራ ግዛውን አግብተው፣ በዚች ምድር 32 ዓመት ብቻ ኖረው፣ በመኪና አደጋ ነበር ያረፉት። ተፈሪ መኰንን ተማሪ ቤት ለአጭር ጊዜ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
ልዑል መኰንን ኃይለ ሥላሴ፣ እጅግ ተወዳጁና ተመራጩ የጃንሆይ ልጅ ነበሩ። አዲስ አበባ ተወልደው ሳራ ግዛውን አግብተው፣ በዚች ምድር 32 ዓመት ብቻ ኖረው፣ በመኪና አደጋ ነበር ያረፉት። ተፈሪ መኰንን ተማሪ ቤት ለአጭር ጊዜ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰን ኃይለሥላሴ ፣ ኅዳር 12/ 1928 ዓ/ም የተነሳ ፎቶ፤ ቦታው አልተገለፀም።
አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰን ኃይለሥላሴ ፣ ኅዳር 12/ 1928 ዓ/ም የተነሳ ፎቶ፤ ቦታው አልተገለፀም።
ልዑላኑ አስፋ ወሰን እና መኰንን ከእህታቸው ልዕልት ፀሐይ ጋር ቆመው ይታያሉ። ቦታው ዊምብልደን ነው። ሰኔ 1/1928 ዓ/ም የተነሱት ፎቶ።
ልዑላኑ አስፋ ወሰን እና መኰንን ከእህታቸው ልዕልት ፀሐይ ጋር ቆመው ይታያሉ። ቦታው ዊምብልደን ነው። ሰኔ 1/1928 ዓ/ም የተነሱት ፎቶ።
የጣሊያኑ ንጉሥ ቪክቶር ኢማኑኤል ሣልሳዊ ከአልጋ ወረሽ አስፋ ወሰን ኃይለሥላሴ ጋር፣ ሮም፤በዕለት እሑድ ፣ጥር 22፣ 1924 ዓ/ም።
የጣሊያ�� ንጉሥ ቪክቶር ኢማኑኤል ሣልሳዊ ከአልጋ ወረሽ አስፋ ወሰን ኃይለሥላሴ ጋር፣ ሮም፤በዕለት እሑድ ፣ጥር 22፣ 1924 ዓ/ም።
ሊዮ ዚፌል (ከተቀመጡት 3ኛው) በጣም የሚፈሩና የሚከበሩ የትምህርት ቤቱ የዲሲፕሊን አለቃ ነበሩ።
ሊዮ ዚፌል (ከተቀመጡት 3ኛው) በጣም የሚፈሩና የሚከበሩ የትምህርት ቤቱ የዲሲፕሊን አለቃ ነበሩ።
ከካናዳዊያን ጄስዊት መምህራን አንዱ የነበሩት ክላውድ ሰምነር ተፈሪ መኮንን ካስተማሩ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከመጀመርያዎቹ መምህራን አንዱ ነበሩ።
ከካናዳዊያን ጄስዊት መምህራን አንዱ የነበሩት ክላውድ ሰምነር ተፈሪ መኮንን ካስተማሩ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከመጀመርያዎቹ መምህራን አንዱ ነበሩ።
ሉሲየን ማት እና ዜፌል ከተማሪዎቻቸው ጋር ይታያሉ። ዘመኑ አልተገለጸም።
ሉሲየን ማት እና ዜፌል ከተማሪዎቻቸው ጋር ይታያሉ። ዘመኑ አልተገለጸም።
የሥነ ሕይወት መምህር የነበሩት አራጃንድራት ራጃ ከተማሪዎቻቸው ጋር 1973 ዓ/ም
የሥነ ሕይወት መምህር የነበሩት አራጃንድራት ራጃ ከተማሪዎቻቸው ጋር 1973 ዓ/ም
ሞገስ አስገዶም እና አብረሃ ደቦጭ
በ1928 ጣሊያን ሲገባ ትምህርት ቆመ።
በስኮላርሺፕ ውጭ የሄዱ የተፈሪ መኰንን ተማሪዎች "ኧረ ጥራኝ ዱሩ" ብለው ከፓሪስ ወደ ቡልጋ እንዲሁም ወደ ወለጋ ጫካ ገቡ። ጥቁር አንበሳን መሠረቱ።
አንዳንዶቹ ነጭ ለባሽ፤ የውስጥ አርበኛ ኾኑ። ብዙዎቹ የተፈሪ ተማሪዎች ግን አለቁ። ያ ሁሉ የተደከመባቸው፣ አገሪቱን ከድንቁርና ያወጣሉ የተባሉ ወጣቶች ጣሊያን ቀረጣጥፎ በላቸው።
ሞገስ አስገዶም እና አብረሃ ደቦጭ ተፈሪ መኰንን ነው የተማሩት። እዚያ የተማሩ ደግሞ፣ ምን እንደሚያስነኳቸው እንጃ፣ በአገር ፍቅድ የነደዱ ኾነው ነው የሚወጡት።
እነ ሞገስ አውቀው ለጣሊያን አደሩ። ዋናውን 'ሸይጣን' ለመግደል እያሴሩ ነበር፤ ግራዚያኒን።
አብረሃ ደቦጭ ጣሊያንኛ መቻሉ ከነ ግራዚያኒ ጋር አቀራረበው። እሱን ለመግደል አመቺ ጊዜ ጠበቀ። ከወዳጁ ሞገስ ጋር ተማከረ።
አብረሃና ሞገስ በእረፍት ቀን ከጣሊያን አለቆቻቸው እየተሰወሩ፣ ከአዲስ አበባ ወጣ እያሉ፣ ገለጣ ሜዳ ላይ ቦምብ አጣጣል ሁሉ ተለማመዱ።
ለወራት ያቀዱትን የካቲት 12 ተገበሩት። እነሱ የሠሩት ጀብዱ ግራዚያኒን ቢያቆስልም፣ ብዙ ጣጣ አስከተለ።
ባዲሳባ በሦስት ሌሊት 30 ሺህ ሰው ጭጭ።
ጣሊያን ጨከነ። ቤተሰብ ከልጆቹ ጋር ቤት ውስጥ እሳት እየሞቀ ከውጭ እሳት ተለቀቀበት።
የአዲስ አበባ ወጣት በትሬንታኳትሮ አስፋልት ላይ ተጨፈለቀ። በከተማዋ ደም እንደ ቀበና ወንዝ ፈሰሰ።አንዳንድ የጣሊያን ወታደሮች ሕዝብ መግደል ደክሟቸው የፋሺስት መንግሥትን የሥራ እረፍት ጠየቁ።
ደም አስክሯቸው፣ ክንዳቸው ቃታ በመሳብ ዝሎ ነበር። 30ሺህ ሰው መጨረስ ቀላል አልነበረም።
የሚገርመው የተፈሪ ተማሪ የነበሩት ፕ/ር አስራት አባታቸው አቶ ወልደየስ አልታዬ የተገደሉት በዚሁ ቀን ነበር፤ ከዚሁ ከተፈሪ መኰንን ተማሪ ቤት በወጡት በነ አብረሃ ደቦጭ በተቆሰቆሰ እሳት።
የደብረ ሊባኖስ ገዳም መነኮሳት አርበኛ ታስጠልላላችሁ ተብለው ተረሸኑ። ሁለቱ ጓደኛሞች፣ አብረሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም፣ ተሳደው ሱዳን ድንበር ሲደርሱ ባልታወቁ ሰዎች ተገደሉ።
በዚህ ክፉ ዕለት ጃንሆይ አሜሪካ፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ ልከው ካስተማሯቸው የመጀመርያዎቹ ውድ ተማሪዎች መሀል አያና ብሩ፣ ዮሐንስ ቦሩ፣ በሻ ወርድ ሀብተወልድ፣ ክፍሌ ነሲቡ ተገድለዋል። የሐኪም ወርቅነህ ውድ ልጆች ዮሴፍና ቤንጃሚንም አልቀሩም። ጆሴፍ አውሮፕላን አብራሪ ነበር። ጣሊያንን ለመዋጋት ነበር ከለንደን ወደ ኢትዮጵያ የገባው።
ብቻ ታሪኩ እንደ የ5 ዓመቱ የስቃይ ዘመን ረዥም ነው።
ጣሊያን ሲገባ እነሱን ያፈራው ተፈሪ መኰንን ተዘጋና ብዙም ሳይቆይ ተከፈተ።
ሲከፈት ግን የቅኝ ገዢ ልጆች ብቻ መማሪያ ኾነ። ጥቁር ወደዚያ ዝር እንዳይል ተባለ። ስሙም ‘ቪክተር ኢማኑኤል' ይሉት ኾነ።
ከአምስት ዓመት በኋላ ጣሊያን ሲወጣ እንግሊዝ ገባ። እንግሊዞች ተማሪ ቤቱን ማስተዳደር ጀመሩ።
እንግሊዞች ሲወጡ ጃንሆይ ደስ አላቸው። ልዝብ ቅኝ ገዥ ኾነው አስቸግረዋቸው ነበር። ግን ወዲያው ሐሳብ ገባቸው። ተማሪ ቤቱን ማን ያስተዳድረው?
ጃንሆይ በዚያ ወቅት ቅኝ ገዢ የሚባል ጥልት አድርገው ጠልተዋል።
ገለልተኛ አገር ፈለጉ። ካናዳን ወደዱ። በቫቲካንን ሊቃነ ጳጳሳትን አነጋግረው ከካናዳ ኢየሱሳውያን መነኮሳትን (Jesuits) በአስተማሪነት አስመጡ።
ከማስጠንቀቂያ ጋር ነው ታዲያ።
''አደራችሁን፣ ሃይማኖት መስበክ ብሎ ነገር የለም። 'አባ' ተብሎ መጠራት የለም። የሃይማኖት ካባ መልበስም የለም። ልጆቼን ቀለም ብቻ አጠጡልኝ'' አሉ።
ካናዳውያኑ ጨዋ ነበሩ፤ እንደተባሉት አደረጉ። ለረዥም ዘመን ካስተማሩ በኋላ በኢትዮጵያ ፍቅር ወደቁ። አንዳንዶቹ ኢትዮጵያ ኖረው ሞቱ።
ተወዳጁ መምህር ግን በኢትዮጵያ መቀበር እንደተመኘ ሳይሳካለት ቀረ። ማነው ይህ መምህር?








ሉሲያ ማት ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ኦፍ አዲስ አበባን (የአሁኑን አአዩ) በፕሬዝዳንትነት ለመምራት የመጀመርያው ነው። በፕሬዝዳንትነት 12 ዓመታት ከዘለቀ በኋላ ወደ ካናዳ ተመለሰ። በኦንታሪዮ ካናዳ ሰድቤሪ ዩኒቨርስቲ ሥራ ጀመረ። ጃንሆይ በሉሲያ ማት የኢትዮጵያ ቆይታ ደስተኛ ስለነበሩ ለዚህ የካናዳ ዩኒቨርስቲ እርዳታ እንደሰጡ ይነገራል። ሉሲያ ማት ኢትዮጵያ ሲመጣ 35 ዓመቱ ነበር።
ማርሴል ሻኽፖንቺዬ ከካናዳ ኪዩቤክ ግዛት ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በ1939 ዓ/ም ነበር። ወደ አገሩ የተመለሰው በ1967 ዓ/ም ነበር። ለ30 ዓመታት ኢትዮጵያን አገልግሏል። በተፈሪ ተማሪ ቤት የዕደ ጥበብ ዎርክሾፕ የጀመረው እርሱ ነው።
ከካናዳ ኩቤክ ግዛት የመጣው ሉሲያ ማት በአስተዳደር ችሎታው ከተፈሪ መኰንን አልፎ የመጀመርያውን ዩኒቨርቲ ኮሌጅ በመመሥረቱ የኢትዮጵያ ባለውለታ ኾኖ ይዘከራል።
ክላውድ ሰምነር የሞንትሪያል ሰው ነበር። ፍልስፍናና ሥነ ጽሑፍ ነው ያጠናው። በዩኒቨርስቲ ኮሌጅ አዲስ አበባ (የአሁን አአዩ) ፍልስፍናን ለማስተማር ምናልባትም ቀዳሚው ሰው ነበር። በግዕዝና በአማርኛ የተጻፉ የፍልስፍና ጽሑፎችን ለዓለም አስተዋውቋል።
ማርሴል ሻኽፖንቺዬ
ማርሴል ሻኽፖንቺዬ
ሉሲየን ማት ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ኦፍ አዲስ አበባ (በኋላ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ የኾነውን) ያደራጀ ካናዳዊ ባለውለታ ነው። እውቅ የተፈሪ መኰንን ዳይሬክተር ነበር።
ሉሲየን ማት ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ኦፍ አዲስ አበባ (በኋላ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ የኾነውን) ያደራጀ ካናዳዊ ባለውለታ ነው። እውቅ የተፈሪ መኰንን ዳይሬክተር ነበር።
በግራ በኩል ብዙ የቀድሞ ተማሪዎች የሚያስታውሱት ረዳት ዳይሬክተሩ ጌራርድ ጋኞን ከማርሴል ጋሪዮ ጋር ይታያል። ዓ/ም አልተጠቀሰም።
በግራ በኩል ብዙ የቀድሞ ተማሪዎች የሚያስታውሱት ረዳት ዳይሬክተሩ ጌራርድ ጋኞን ከማርሴል ጋሪዮ ጋር ይታያል። ዓ/ም አልተጠቀሰም።
"ጃንሆይ እኛን ከጎበኙ በኋላ ከሉሲዬ ማት ጋር 'ፍስስ' በሚል ፈረንሳይኛ ሲያወሩ ትዝ ይለኛል። "ሲሉ የሐርቫርዱ ምሩቅ ዶ/ር ሙሉጌታ ወዳጆ ለልጃቸው ዶ/ር ፈላስፋ ሙሉጌታ ተርከውለታል።
"ጃንሆይ እኛን ከጎበኙ በኋላ ከሉሲዬ ማት ጋር 'ፍስስ' በሚል ፈረንሳይኛ ሲያወሩ ትዝ ይለኛል። "ሲሉ የሐርቫርዱ ምሩቅ ዶ/ር ሙሉጌታ ወዳጆ ለልጃቸው ዶ/ር ፈላስፋ ሙሉጌታ ተርከውለታል።
ሾርባ ውስጥ 'ምናምን' ተገኘ
ከዚህ ተማሪ ቤት የወጡ ብዙዎቹ በተለያየ ጊዜ በሰጡት ቃለ መጠይቅ በሕይወታቸው እጅግ ሥነ ሥርዓት አክባሪ እና ሥራ ወዳድ ያደረጋቸው በተፈሪ የነበረው ጥብቅ ግብረ ገብነት እንደሆነ ሲናገሩ ይሰማል።
እውነተቸውን ነው። ይህ ትምህርት ቤት ጥብቅ ደንቦች ነበሩት። ሰዓት አለማክበር 'የጦር ወንጀል' ነበር። መኝታ ክፍል አያያዝ፣ የግል ንጽህና አጠባበቅ ላይ ቀልድ አልነበረም።
አበራ የማነ አብ የተባሉ የቀድሞ ተማሪ ይህን ምስክርነታቸውን በጻፉት መጽሐፍ ገልጠዋል።
ለምሳሌ በየሳምንቱ የቆሸሸ ልብስ ተወስዶ ታጥቦ እና ተተኩሶ በተማሪዎች አልጋ ላይ ይቀመጣል።
ዐርብ በ5 ሰዓት ሙስሊሞች ትምህርት አቁመው መስጊድ ይሄዳሉ።
ምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን እሑድ ጠዋት የቅዳሴ እና የፀሎት ሥርዓት እስኪጠናቀቅ ለክርስቲያኖች ቁርስ አይቀርብም።
አበራ የማነ አብ "ለውጥ ናፋቂው ሕይወቴ" በተሰኘ መጽሐፋቸው፣ ገጽ-14 ላይ ደግሞ፣ አንድ አስገራሚ ትዝታ ስለ ተፈሪ ተማሪ ቤት አጋርተዋል።
ንጉሡ ለዚህ ትምህርት ቤት የነበራቸውን ቦታ የሚያሳይ ነው።
" ...በዐቢይ ጾም ወቅት ንጉሠ ነገሥቱ ትምህርት ቤቱን ይጎበኛሉ። በራት ሰዓት ምግብ ቤት ገብተው የምንመገበውን እየቀመሱ ያያሉ። ብዙ ጊዜ ምሳና ራት ላይ የሚቀርበው ፋጆሊ ሾርባ፣ ሚኒስትሮኒ ምናምን ነው። አንድ ቀን ሾርባው ውስጥ ትል ተገኘና ትምህርት አቆምን። ከሁለት ነው ከሦስት ቀን በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድንገት መጥተው አዳራሽ ውስጥ ሰበሰቡንና ባደረጉት ንግግር 'የሠራችሁት ሥራ በነጭ ሸማ ላይ ጥቁር ቀለም እንደማፍሰስ ነው፤ አሁኑኑ ትምህርታችሁን ጀምሩ' ብለው ገሰጹን። እኛም ጉዳዩ ንጉሠ ነገሥቱ ጋር በመድረሱ ተደናግጠን በማግሥቱ ትምህርት ቀጠልን። ''
''...ወደ ኋላ መለስ ብዬ ያኔ የሆነውን ባሰብኩ ቁጥር፣ ንጉሠ ነገሥቱ ሥራዬ ብለው አድመን ትምህርት ያቆምነውን የአንድ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ለመምከርና ለመገሰጽ መምጣታቸው ሁሌም ይደንቀኛል። "
የመጀመሪያው ''ዴይ ፓርቲ''?
በ60ዎቹ ከተመረቁት መሀል አቶ ኤርሚያስ አማረ ይገኙበታል። ''የተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ት���ታ'' የሚል መጽሐፍ ጽፈዋል።
በዚህ መጽሐፍ ዙርያ ከቀድሞው አሜሪካዊ መምህራቸው ዳግ ኤዲ ጋር በአንድ ቆየት ያለ የሚስተር ዳግ ፖድካስት ላይ ሲጨዋወቱ አስቂኝ ትዝታ አጋርተዋል። አጠር ተደርጎ ሲተረክ ይህን ይመስላል።
"በዘመኑ ከተፈሪ መመረቅ ኮሌጅ የመበጠስ ያህል ከባድ ነበር። 42 ብቻ ነበርን። ሁላችንም አለፍን። ደስታችንን በተለየ ማክበር ፈለግን። ለምን የተማሪ ፓርቲ አናሰናዳም ተባለ። እንዲህ ዓይነት ጉድ ተሰምቶ አይታወቅም፥ ከዚያ በፊት። አንዳንዶቻችን ሴቶች በፓርቲው እንዲገኙልን በጥብቅ ፈለግን።
ዳይሬክተራችንን ሚስተር ጋኞን 'እባክህን ፍቀድልን' አልነው። 'ይኼ ምን ችግር አለው? አሪፍ ሐሳብ ነው!' አለን።
'ግን እኮ እንግሊዝኛ ሙዚቃ እና ሴቶች በፓርቲው እንዲገኙ እንፈልጋለን' አልነው። 'ምን!' ብሎ ተቆጣ።
በቃ ከትምህርት ቤቱ ውጭ አንድ ክለብ ተከራይተን ፓርቲውን በምሥጢር እናዘጋጅ ተባለ።
ከእቴጌ መነን ሴት ተማሪዎችን ጋበዝን። ደግነቱ የመነን ሴቶች ስለተፈሪ መኰንን ተማሪዎች ጥሩ አመለካከት ስለነበራቸው በርከት ብለው፣ ዝንጥ ብለው መጡ።
ምን ዋጋ አለው! ብዙዎቻችን ከሴቶች ጋር ቅርርብ አናውቅም። በአንድ ክለብ ለመቀመጥ ነፍሳችን ተጨነቀች። ማን ተነስቶ ይደነስ?
ፓርቲው እንደጠበቅነው አልሆን አለን። [ለቅሶ ቤት መሰለ]። እጆቻችንን አጣምረን መፋጠጥ ሆነ።
ድንገት ሦስት ወይም አራት ደፋር ተማሪዎች ከመሀላችን እምር ብለው ተነሱ። ሴት ሊያስደንሱ። ክው አልን። እንደተፈራው ከሴት ጋር ደነሱ።
እየቀናንባቸውም፤ እያሳፈረንም ፓርቲው አለቀ። ይህን አልረሳውም።
ምናልባት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው 'ዴይ ፓርቲ' ይህ ሳይሆን አይቀርም።"



''ኢትዮጵያ ቅበሩኝ'' ካናዳውያን መነኮሳት
''አደራ ኢትዮጵያ ቅበሩኝ" ይሉ ከነበሩት የድሮ ካናዳዊ መምህራን መካከል ሚስተር ጋኞ ይገኝበታል።
የቀድሞ ተማሪዎች ሁሉ መቼም የማይረሱት ዝነኛው ሚስተር ጋኞ ለረዥም ጊዜ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ነበር። ድንገት ታመመና ለሕክምና ኬንያ ተወሰደ። በሳምንቱ ሞተ።
አስክሬኑ ኢትዮጵያ ሊመሰለስ አይችልም። ለምን?
በጄስዊቶች ሕግ አንድ 'አባት' አስክሬኑ ወደተናዘዘበት አገር የሚመለሰው በሞተበት አገር ጄስዊቶች ከሌሉ ብቻ ነው።
ለክፋቱ ኬንያ ጄስዊቶች አሉ። ጋኞ ኑዛዜው አልተፈጸመም። እዚህ ኬንያ ተቀበረ።
የሚስተር ጋኞ ወዳጅ በዚህ ባልደረባቸው ወጥቶ መቅረትና ኬንያ መቀበር ተንገበገበ። ''ጋⶉ ሕይወቱን ሙሉ ኢትዮጵያ ኖሮ እንዴት በኬንያ ይቀረበራል?'' ሲል አዘነ።
ይህ ሰው ሮናልድ ጄ ቱሬን (R. J Turenne) ይባላል። አደገኛ የጂኦግራፊ አስተማሪ ነበር።
ታላቁን የጂኦግራፊ ምሁር ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያምን እጃቸውን ይዞ፣ ማስመሪያ ሰጥቶ ያስተማረ እሱ ነው።
ይህ ሰው 60 ዓመት በኢትዮጵያ ኖረ። ከዕለታት አንድ ቀን ዕድሜውን ሲቆጥር 99 ዓመት ሞልቶታል።
ከዚያ በፊት ግን ከአገሬ ኢትዯጵያ ወዴትም ንቅንቅ አልልም ብሎ አምርሯል።
የኾነ ቀን ግን በጣም ታመመ። ለተሻለ ሕክምና ኬንያ ሂድ ሲባል የጓደኛው የሚስተር ጋኞ ዕጣ ፈንታ ትዝ ብሎት አሻፈረኝ አለ።
በስንትና ስንት ጉትጎታ ለሕክምና ወደ እናት አገሩ ካናዳ ተወሰደ። እሱ እንኳ እናት አገሬ የሚላት ኢትዮጵያን ነበር።
ብቻ ታሪኩ ረዥም ነው። በመጨረሻ በካናዳ 'መቄዶንያ' ገባ። የአረጋዊያን እንክብካቤ ማዕከል እንደማለት። የድሮ ተማሪዎቹ በየዓመቱ እየሄዱ ይጠይቁት ነበር። ምክንያቱም ይወዱታላ።
ከ2 ዓመት በፊት ሊጠይቁት ሲሄዱ 99 ዓመት አልፎታል። መቶ ሊደፍን 4 ወር ገደማ ብቻ ነበር የቀረው።
''ጋሽ ቱሬን፤ ልደትህን ከተፈሪ መኰንን 100 ዓመት ጋር እናከብርልሃለን" አሉት፣ የቀድሞ የተፈሪ ተማሪዎች ኅብረት የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ብሥራትና ጓደኞቹ።
ቱሬ ግን በሚንቀጠቀጥ ድምጽ "አይመስለኝም፤ እኔ ቀድሜ እሞታለሁ" አላቸው።
''ተው አትሞትም እንደሱ አትበል!'' አሉት።
እንደፈራው ሞተ።
ነፍስ ኄር!!




የፕ/ር መስፍን የቀለም አባት የነበሩት የሚስተር ቱሬ የመጨረሻ ቃል
የፕ/ር መስፍን የቀለም አባት የነበሩት የሚስተር ቱሬ የመጨረሻ ቃል



''ለትምህርት ቤቱ የመጀመሪያው ጥቁር ነበርኩ''
ድሮ የተፈሪ ተማሪዎች 11ኛ ክፍል ሲጨርሱ አሜሪካ ይላኩ ነበር - ተወዳድረው።
12ኛ ክፍልን ብቻ እዚያ ተምረው እንዲመለሱ ነው - ሐሳቡ። ልምድ አንዲኾናቸው።
ያኔ ከአገር ወጥቶ መጥፋት ጽዩፍ ነበር።
በፎተው ላይ በውብ ፈገግታ ዋንጫ ይዞ የሚታየው የያኔው ወጣት - የነብር ጣት፣ ብሥራት አክሊሉ፣ ሜኔሶታ ግዛት ተላከ። አንድ ከከተማ ወጣ ያለ ቦታ የሚገኝ የሃብታሞች ትምህርት ቤት ተመደበ።
የተቀበሉት አሜሪካውያን ቤተሰቦች ግን ፈሩ። በተለይ የቤቱ አባወራ ፈረንጅ ሐኪም ናቸው።
"This kid from Africa . . . I don't know what to do with him'' ብለው ተጨነቁ።
''አሁን እንዴት ኾኖ ነው እሳት ከላሱ አሜሪካውያን ልጆች ጋር እኩል የሚማረው?'' ብለው ሐሳብ ገብቷቸዋል።
ልጅ ብሥራትን ፈራ ተባ እያሉ አማከሩት።
"አንተ ልጅ፣ ፈራሁ እኮ። 12ኛ ክፍል ይከብድህ ይኾን? ትምህርቱን ትችለዋለህ? አሜሪካ እኮ እንደ አፍሪካ አይደለም። እንዲያው ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ሄደን ከአስተማሪዎቹ ጋር ብንማከር?'' ብለው ወሰዱት።
ፈረንጅ መምህራን ጥቁሩን ብሥራትን በጥያቄ አጣደፉት።
''ለመሆኑ ሒሳብ ታውቃለህ? የፊዚክስ ሕግስ ተምረሃል? ለመሆኑ ጂኦግራፊ ታውቃለህ? ታሪክስ? ያንን ታውቃለህ? ይህንንስ?'' እያሉ አስጨነቁት።
የያኔው ብሥራት ገርሞት ያያቸዋል። እየቀለዱ ነው ወይስ የምራቸውን?
ብሥራት በሚጠይቁት ጥያቄ ቅለት ነው የተገረመው።
"ውይ ይሄንን እኮ እኛ 9ኛ ክፍል ተምረነዋል፤ ያንን እኮ እኛ ድሮ ነው የተማርነው" ሲል መለሰ።
ፈረንጅ አስተማሪዎች ባያምኑትም ትምህርቱ ተጀመረ። በዚህ ሜኔታንንታ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመግባት ብሥራት የመጀመሪያው ጥቁር ነበር።
የሁሉም ጭንቀት 'ይሄ አፍሪካዊ ትምህርቱን እንዴት ሊወጣው ነው?' የሚል ነበር።
የክፍሉ 1ኛ ሆኖ ጨረሰ። ለዚያውም በማዕረግ። ፈረንጆቹ አሁንም አልተዋጠላቸውም።
"የንጉሣውያን ቤተሰብ ነህ?"
''ኧረ በጭራሽ!''
"የሃብታም ትምህርት ቤት ነው የተማርከው?"
"እንዲያውም!"
"Did you go to a private school?"
"ኧረ የሕዝብ ነው! ተፈሪ ይባላል።"
ብቻ ታሪኩ ረዥም ነው። ለማሳጠር ወደፊት እንስፈንጠር።
ብሥራት፣ ከዚያ በኋላ ተምሮ ተምሮ፣ በኢኮኖሚክስ ዶክትሬቱን ሠርቶ፣ ቦስተን ዩኒቨርስቲ በፕሮፌሰርነት ተቀጥሮ፣ ለዓመታት ፈረንጅ ፊደል አስቆጥሮ፣ 32 ዓመታት በተባበሩት መንግሥታት በከፍተኛ ኃላፊነት ሠርቶ፣ አሁን ደግሞ ለዚህ ወግ ማዕረግ ያበቃውን ተማሪ ቤት ውለታ እየመለሰ ነው።
ከዚህ ወዲህ አንቱ እንለዋለን።
አሁን ዶ/ር ብሥራት የቀድሞ የተፈሪ መኰንን ተማሪዎች ኅብረት ሊቀመንበር ናቸው።
"ያኔ አሜሪካ ከላኩኝ በኋላ የገባኝ ነገር፣ በተፈሪ መኰንን በጣም የላቀ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ይሰጥ እንደነበረ ነው።"
መለስ ዜናዊና አዳነች አበቤ
ተፈሪ የሚለውን የትምህርት ቤቱን ስም ደርግ መጣና "እንጦጦ" ብሎ ቀየረው።
በዓለም የተዘሩት የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ከፋቸው። በስሙ መቀየር ትዝታቸው ደበዘዘባቸው።
ግንባር ፈጠሩ፣ ትግል ጀመሩ። ሰላማዊ ትግል፤ ስም የማስመለስ ትግል።
ይህን መራራ ትግል በፊታውራሪነት ከመሩት ውስጥ ዶ/ር ብሥራት አንዱ ናቸው። ለቢቢሲ ያጋሩትን ታሪክ ጨምቀን ስናቀርበው ይህን ይመስላል።
ኢህአዴግ ሲገባ ተፈሪ የሚለው ስም ሊመለስ የሚችልበት ዕድል ተፈጠረ።
ነገር ግን ዋናውን ሰው መለስ ዜናዊን ማን ያግኝ?
ብዙውን ጊዜ ለተፈሪ ተማሪዎች ባለሥልጣን ማግኘት ከባድ አይደለም። ለምን? በየሄዱበት ቢሮ የቀድሞ ተማሪዎች አይጠፉማ። መለስ ደግሞ ተፈሪ አልተማረም። ዊንጌት ነው የተማረው።
በስንት መከራ አፈ ጉባኤ ዳዊት ዮሐንስ ተገኙ። ለካንስ እሳቸውም የተፈሪ ተማሪ ነበሩ።
አፈ ጉባኤ ዳዊት እና መለስ ዜናዊ ደግሞ ከባድ ወዳጅ ነበሩ። ዳዊት ለመለስ ነገሩን ነገሩት። ''እንጦጦ የሚለው ስም ወደ ተፈሪ ይመለስ፤ ፍቀድልን?'' አሉት።
መለስ ፈጣን መልስ ሰጠ።
"ይሄ ምን ችግር አለው ታዲያ? መቀለ ያለው ትምህርት ቤት ዐፄ ዮሐንስ እኮ ነው የሚባለው፤ ሕጉን ተከትሎ ስሙ መቀየር ይችላል" አለ።
ሂደቱ ግን መለስ ዜናዊ እንዳቀለለው ቀላል አልሆነም።
"ብቻ ምን አለፋህ ስሙን ለማስመለስ፣ 6 ከንቲባዎችና 25 ዓመታት ፈጅቶብናል" ይላሉ ዶክተር ብሥራት።
"ስድስቱም ከንቲባዎች ታዲያ አንዳቸውም 'አይኾንም!' ብለውን አያውቁም።"
ዶ/ር ብሥራት የሚመሩት ማኅበር ጠንካራ ነው። በካሊፎርኒያ፣ በዋሺንግተን፣ በኒውዮርክ፣ በቴክሳስ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአውሮፓ በድምሩ 12 ቻፕተሮች አሉት።
የቀድሞ ተማሪዎች እኮ አሁን 250 ሺህ አልፈዋል። እንጦጦ የሚለውን የሚወድ ግን የለም። የተራራ እንጂ የትምህርት ቤት ስም አይደለም። ትዝታ ያደበዝዛል።
ብቻ ስም የማስመለሱ ትግል ለዓመታት ቀጠለ። በመጨረሻ ትግሉ ፍሬ አፈራ። ከወራት በፊት እንጦጦ ቴክኒክና ሞያ ወደ 'ተፈሪ መኰንን' ተመለሰ።
አሁን ሁሉም የቀድሞ ተማሪ ተደስቷል።
"ይህ እንዲሳካ ደበበ እሸቱን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ረድተውናል። የአዲስ አበባ የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ጥራቱ በየነ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ከንቲባ አዳነች አበቤ ሊመሰገኑ ይገባል" ይላሉ፣ ዶ/ር ብሥራት።





የሼኽ አላሙዲን ስጦታ
የቀድሞ ተማሪዎች ማኅበር 100 ዓመት ለደፈነው የቀድሞ ትምህርት ቤታቸው ሕንጻ ሠርተው ሊያስረክቡ ተፍ ተፍ ማለት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
ደግነቱ የሚደግፋቸው ብዙ ነው። በየሄዱበት ተፈሪ የተማረ አያጡም።
ለምሳሌ የሚያስገነቡትን ሁለገብ ሕንጻ ዲዛይን ማሠራት ሲፈልጉ የደረሰላቸው ጎምቱው ነዳፊ ፋሲል ጊዮርጊስ ነው። እሱ ራሱ የተፈሪ ፍሬ ነው።
ገነዘብ ሲፈልጉም እንዲሁ የድሮ የተፈሪ ተማሪ ፈለጉ። አለመታደል ሆኖ ተፈሪ ብዙ ነጋዴ አላፈራም። ቢሊየነሩ ብዙአየሁ ተገኙ። እሳቸው ብዙ ረዷቸው።
ነገር ግን 60 ሚሊዮን ነው የሚፈልጉት። ተጨማሪ ገንዘብ ከየት ይምጣ?
መቼስ ቴሌቶን ያለ ሼክ አ��ሙዲ ተሳትፎ ግቡን አይመታምና ይጠየቁ ተባለ። ችግሩ እሳቸው ተፈሪ አልተማሩም።
ከሚወዷቸው ሥራ አስፈጻሚዎች አንዱ ግን ተፈሪ ተምረዋል። የደርባ ሥራ አስፈጻሚ ኃይሌ አሰግዴ።
እነ ዶ/ር ብሥራት ደብዳቤ አረቀቁ፤ ደብዳቤው ወደ ሳዑዲ ተላከ። ቢጠበቅ ቢጠበቅ ምላሽ የለም።
ኮሚቴው ኃይሌ አሰግዴ ጋር ደወለ። "ሼኹ ዝም አሉን እኮ ምን ይሻላል?"
"ሼኽ አላሙዲ ዝም አይሉም፤ ታገሱ" ተባሉ።
ከዕለታት አንድ ቀን ሼኽ መሐመድ ወደ ኃይሌ ደወሉና "እንዴት ያሉ አገር ወዳድ ናቸው ባክህ! ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ ድሮ የተማሩበትን ትምህርት ቤት አስታውሰው…ማሻላህ!'' አሉ።
ኃይሌ አሰግዴ እየሰሙ ነው።
"በል አንድ 5 ሚሊዮን ስጣቸው- ባክህ! ኢትዮጵያን የሚወድ 'ወዳለሁ። "
"እሺ እሺ፤ በነገርዎ ላይ እኔም እዚያ ነው እኮ የተማርኩት?"
"እውነትህ ነው? ለምን አልነገርከኝም ታዲያ? በል ሌላ 5 ሚሊዮን ጨምርበት።" ምናባዊው የስልክ ንግግራቸው ይህን ይመስላል።
እነ ዶክተር ብሥራት አንድ ሁለገብ ሕንጻና የግቢውን ዋና በር ውብ አድርገው ለማሠራት ወጥነዋል። በሩ ላይ የሚጻፈው ነገር በጭራሽ አላከራከረም።
ድሮ ጃንሆይ ትምህርት ቤት መጥተው የመከሯቸው ምክር ለሁሉም ተማሪዎች የኑዛዜ ቃል ማለት ነው። እስከዛሬ ከልባቸው አልወጣም።
እሱ ራሱ ጥቅስ ነው በሩ ላይ የሚጻፈው። መልእክቱ ጥልቅ ነው።
እንዲህ ይላል፦
"ይህችንም የዕውቀት ምግብ ሰጥታ የምታሳድጋችሁን ተማሪ ቤት፣ (ወደፊት) በጥበብ አድጋችሁ፣ በአእምሮ በምትጐለምሱበት ጊዜ እግዚአብሔር እንደየዕድላችሁ በሚሰጣችሁ ዕውቀት፣ (ትምህርት ቤቷ) የሀገራችን መሣሪያ ናትና እንዳትጠብ እንድትሰፋ፣ እንዳትወድቅ እንድትበረታ እንድትረዷት እለምናችኋለሁ።"
የቀድሞ ተማሪዎች ማኅበር አባላት 100ኛ ዓመት ባከበሩበት ወቅት፤ የቀድሞ ተማሪ ደጃዝማች ወልደሰማያት ገብረወልድ በ101 ዓመታቸው መሀል ላይ ይታያሉ።
የቀድሞ ተማሪዎች ማኅበር አባላት 100ኛ ዓመት ባከበሩበት ወቅት፤ የቀድሞ ተማሪ ደጃዝማች ወልደሰማያት ገብረወልድ በ101 ዓመታቸው መሀል ላይ ይታያሉ።
የ100 ዓመት ሐዲድ
1915 ዓ/ም ግንባታ ተጀመረ። 1917 ዓ/ም በአልጋ ወራሽ ተፈሪ ተመረቀ።
"ቪክተር ኢማኑኤል" በሚል ስም የጣሊያን ልጆች ት/ቤት ኾነ
በአሜሪካዊ ሔነሪ አስተዳዳሪነት በድጋሚ ተከፈተ
አራት ካናዳዊያን ኢየሱሳዊያን በመምህርነት ተቀጠሩ
ሴት ተማሪዎችን መቀበል ጀመረ
ተፈሪ መኰንን ወደ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትነት አደገ
ስሙ ወደ 'እንጦጦ ሙያና ቴክኒክ ትምህርት ቤት' ተቀየረ
የቀድሞ ስሙ ተመለሰ
አርትኦት፡ አሻግሬ ኃይሉ
ቅንብር ገጽ ወምሥል፡ ምሕረተሥላሴ መኰንን
የካርታ ሥራ፡ ማዮዋ አላቢ
ተጨማሪ ምሥሎችና ግብዓቶች፡ ጌቲ ኢሜጅስ፣ ኤዲ ዳግ (አሜሪካዊ የቀድሞ የተፈሪ መኰንን መምህር ፖድካስት)፣ ተፈሪ መኰንን አሉሙናይ፣ ዶ/ር ፈላስፋ ሙሉጌታ ድረ-ገጽ፣ የካናዳ ጄስዊቶች ማኅበር ድረ ገጽ፣ ፕሮፌሰር ፒተር ጋሬትሰን
ምስጋና፡ ወ/ሮ ቆንጂት ተድላ፣ ስለሺ ይልማ ረታ፣ ሚስተር ቻ፣ ዮሐንስ ገብረተክሌ



















































