ባይተዋር ከተማ፡ “ፒያሳ፣ ካዛንቺስ... ሰፈሬ አልመስል አሉኝ”

ባለፉት ዓመታት በአዲስ አበባ በቅርስነት ተመዝግበው የነበሩ እንዲሁም ሌሎችም ታሪካዊ ሕንጻዎች፣ ቤቶች እና አካባቢዎች እንደ ዋዛ አፈር ለብሰዋል። በምትካቸው ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ሊቆሙ አፈራቸው እየተማሰ ነው፤ ቀን ከሌት። ጥድፊያው ነጠላ ለመዘቅዘቅ ጊዜ አይሰጥም። በዚህ ዘገባ፣ አንድን ሕንጻ ወይም ቤት ቅርስ አልያም ታሪካዊ ሥፍራ ለማለት መስፈርቱ ምንድን ነው? የታሪካዊ ሕንጻዎች እና ቤቶች መፍረስ በታሪክ፣ በነዋሪዎች ሥነ ልቦና፣ በኪነ ሕንጻ እና በማኅበራዊ መስተጋብር ላይ ምን ጫና ያሳድራል? ቅርሶች እና ታሪካዊ ሥፍራዎችን እንዴት ጠብቆ ማደስ፣ ማዘመን፣ መልሰው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ማድረግ እንዲሁም ከሌሎች ግንባታዎች ጋር ጎን ለጎን እንዲሄዱ ማድረግ ይቻላል? የሚሉት እና ተያያዥ ነጥቦች ይዳሰሳሉ።
“እናቴ ስትሞት መጽሐፍ ቅዱሷ መሀል አንድ ነገር አገኘሁ። የሚያምር ቤት ፎቶ። አባቷ የሰጣት ቤት ነው። . . . ምን ዋጋ አለው፣ ወደ 100 ዓመታት ያስቆጠረውን ቤት አፈረሱት፤ ታሪክና ትውስታ የሞላውን ቤት አወደሙት፤ ሳያመነቱ. . . ።
“. . . እናቴ ስለቤቱ የሰማቻቸውን ታሪኮች ነግራኛለች። አያቴ ፊታውራሪ አጥናፍሰገድ ወልደጊዮርጊስ ነው የገነባው። እናቴ ቤቱን የማደስ ሕልም ነበራት። አንድ ቀን ሰዎች መጥተው በታሪካዊው ቤት ውስጥ ይኖር የነበረውን ጀግና፣ ለአገሩ የነበረውን ሕልም፣ ለባለቤቱ የነበረውን ፍቅርና ሊያቅፋት ያልቻለውን ልጁን ናፍቆት እንዲመለከቱ ቤቱን ለማደስ ትመኝ ነበር። ይህን ቤት አድሰዋለሁ ትል ነበር።
“. . .ደርግ እስከሚያስወጣን ድረስ እዛ ቤት ነው ያደግኩት። አሁንም ድረስ ሳቅ ሲያስተጋባ ይሰማኛል። በጦርነት፣ በሞት፣ በማጣት ውስጥም ቤተሰባችንን ጠብቆ አቆይቷል። ዛሬ ግን ሁሉም ጠፍቷል። ቤቱን አድሼ ሕልሟን እውን ለማድረግ የምችለውን ሁሉ ለመሞከር ለእናቴ ቃል ገብቼ ነበር. . . አዬዬ አላሳካሁትም።
“ይሄን ታሪክ የማጋራው ፍትሕ ለመጠየቅ አይደለም። ፍትሕ እንደማይመጣ አውቀዋለሁ። ይሄን የማጋራው ለትውስታ ነው። አያቴ ፊታውራሪ አጥናፍሰገድ ወልደጊዮርጊስን እና ሌሎች ለኢትዮጵያ የሞቱ ቀደምቶችን እና ታሪኩን ማቆየትን ታልም የነበረችውን እናቴን ለማስታወስ ነው። የቀደመ ታሪካችን ዋጋ አለው። ጀግኖቻችን ዋጋ አላቸው። እኛን እኛ ያደረጉንን ትውስታዎችን ለመጠበቅ መታገል እንዳለብን ለማሳሰብ ነው...”



ይህ ጽሑፍ በሚድየም ድረ ገጽ ላይ Ethiopia’s Forgotten Heroes: The Price of ‘Progress’ በሚል በእንግሊዝኛ የታተመ ሲሆን፣ ለዚህ ዘገባ እንዲስማማ ሆኖ ወደ አማርኛ ተመልሷል።
የፀሐፊዋ አያት ፊታውራሪ አጥናፍሰገድ በፋሺስት ጣልያን ወረራ ወቅት በአርበኝነት ሲዋደቁ ነው የተሰውት። የአያታቸው አያትም በዓድዋ ጦርነት ተሰውተዋል።
ቤቱን “የፍቅር እና መስዋዕትነት ተምሳሌት” ሲሉ በጽሑፋቸው የገለጹትም ለዚሁ ይመስላል።
በፋሺስት ወረራ ዘመን ጣሊያኖች ቤቱን መቀመጫ አድርገው ይጠቀሙበት ነበር። ከድል በኋላ ቤቱ ለቤተሰቡ ተመለሰ።
ደርግ ከወረሰው በኋላ ቤቱን ለማስመለስ ቤተሰቡ ትልቅ ተጋድሎ አድርጓል። የፀሐፊዋ እናት ያደረጉት ጥረት እንዳልተሳካ ፀሐፊዋ ገልጸዋል።
“እናቴ ለ40 ዓመታት ቤቱን ከርቀት አዘውትራ ትመለከተው ነበር” ይላሉ።
“. . . በአዲስ አበባ በዘመናዊነት ስም ብዙ ታሪካዊ ሥፍራዎች እየጠፉ ነው። ከቀድሞው ጋር የሚያስተሳስረን አይተኬ ባህላዊ ሃብት ዋጋ እያጣ ነው። የከተማችን ነፍስ በእድገት ስም እየከሰመ ነው. . .” እያሉ ይቀጥላሉ ፀሐፊዋ።
ይህ ብሶት ግን የአንድ ቤተሰብ አባል ብቻ አይደለም።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ጎምቱ የቅርስ፣ የታሪክ እና የኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች ሐዘናቸው ጥልቅ እንደሆነ ይናገራሉ። አንዳንዶቹ ‘የፈሰሰ ውሃ አይታፈስ’ ሆኖባቸው አስተያየት መስጠት ዋጋ የለውም ይላሉ።
እንደ ፀሐፊዋ ያሉ ደግሞ ቢያንስ እንባቸው ባይታበስም አደባባይ ወጥተው ሐዘናቸውን ለማጋራት ሞክረዋል።
ይህ ካዛንቺዝ የነበረው ቤት፣ የልቤ ፋና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሆኖ ያገለግል ነበር። የዘመናት ታሪክ በሰዓታት ውስጥ በምሽት ጨለማ ላይመለስ ወድሟል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቅርስ ጥበቃ እና የኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች እንዳሉት፣ ሕንጻው አይፈርሱም ተብለው ከነበሩት ቅርሶች መካከል ነበር።
በኢትዮጵያ ኪነ ሕንጻ ላይ የሚያተኩረው የቴሌግራም ገጽ ‘Ethiopian Architecture Construction and Urbanism’ ሕንጻውን የገለጸው እንዲህ ነው።
“. . .የሚያምር ባለ ሁለት ፎቅ ሕንጻ፣ አራት ማዕዘን ቅርፅ ያለው ነበር። በመሬት ወለል ዙሪያውን የሚሄድ ክፍትና ዝግ በረንዳ ያለው ሲሆን፣ በመጀመሪያው ፎቅ ላይ ደግሞ የተዘጋ በረንዳ ነበረው።
“በሮች እና መስኮቶቹ ከፊት ለፊቱ ላይ ወጣ ብሎ የተሠራው ውብ ግንብ ላይ ያሉትን ትናንሽ መስኮቶችን ጨምሮ ቅስቶች (Arched Openings) ነበሩት። ይህ የግማሽ ባለ ስድስት ጎን ግንብ በተለዩ ማዕዘኖች (Quoined Corners) ያጌጠ እና በፒራሚዳዊ ጉልላት የተሸፈነ ነው። ግድግዳዎቹ ከድንጋይ የተሠሩ ሲሆኑ፣ በረንዳዎቹ ግን በእንጨት ተገንብተዋል. . .
“. . .ቤቱ ሕንዳዊ መልክ ሊይዝ የቻለበት ምክንያት በአቅራቢያው የሚገኘውን የገብርኤል ቤተ ክርስቲያንን እና ሌሎችን ጨምሮ የነደፈው ሕንዳዊው ሕንጻ ነዳፊ ወሊ መሐመድ ሕንጻውን የነደፈው በመሆኑ ነው...”
“አፈረሱት አሉ ውቤ በረሃን. . .”
የፊታውራሪ አጥናፍሰገድ ቤት መፍረስ ለዚህ ዘገባ እንደ መነሻ ሆነ እንጂ ባለፉት ዓመታት በአዲስ አበባ በቅርስነት ተመዝግበው የነበሩ እንዲሁም ሌሎችም ታሪካዊ ሕንጻዎች፣ ቤቶች እና ሰፈሮች እንደ ዋዛ አፈር ለብሰዋል።
በምትካቸው ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ሊቆሙ አፈራቸው እየተማሰ ነው፤ ቀን ከሌት። ጥድፊያው ነጠላ ለመዘቅዘቅ ጊዜ አይሰጥም።
ቅርስ ናቸው ወይስ ቅርስ አይደሉም? የሚለውም ውዝግብ ቀጥሏል።
ቅርስ ተብለው ከተመዘገቡ በኋላ፣ ‘ቅርስ አይደሉም’ የተባሉ አሉ። በቅርስ ጥበቃ እና ኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች ትግል ከመፍረስ የዳኑም አሉ። ለጊዜው ድነው ኋላ ላይ የፈረሱም ይጠቀሳሉ።
ለምሳሌ፣ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን በጀርመናዊው ፋርማሲስት ኩርት ሂልደንበርድት የተመሠረተው አንበሳ ፋርማሲ በአዲስ አበባ ከመጀመሪያዎቹ የመድኃኒት መደብሮች አንዱ ሲሆን፣ በከፊል ፈረሳ ተጀምሮ በኢትዮጵያውያን የኪነ ሕንጻና ቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎች እንዲሁም በጀርመን ዲፕሎማቶች ርብርብ በግማሽ ተርፏል።
የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት ሕንጻ በሚል የሚታወቀው ገብረወልድ ሕንጻ በኮሪደር ልማት ከፈረሱ ቅርሶች አንዱ ነው።
ሕንጻው በፀሐፌ ትዕዛዝ ገብረወልድ እንግዳወርቅ በ1940ዎቹ አካባቢ የተገነባ እና ከመጀመሪያዎቹ የአዲስ አበባ ‘ሰማይ ጠቀስ’ ፎቆች መካከል አንዱ ነው። በመስታወት ከተሠሩ የመጀመሪያዎቹ ሕንጻዎች አንዱ እንደነበረም ባለሙያዎች ይናገራሉ።
አዲስ አበባ ውስጥ በዋናነት ከኮሪደር ልማት ጋር በተያያዘ ከፈረሱ ነባር የከተማዋ ማሳያ ከሆኑ ታሪካዊ እና ቅርስ ከሚባሉ መካከል የተወሰኑትን በበይነ መረብ ካርታ እንደሚከተለው ሰንደናል።
መነሻ የሆነን ጀርመናዊው የኪነ ሕንፃ ባለሙያና ተመራማሪ ፒት ኒደር ‘The Addis Ababa House: A Typological Analysis of Urban Heritage in Ethiopia, 1886–1936’ በሚል ላዘጋጀው መጽሐፍ ያሰናዳው በአዲስ አበባ በቅርስነት የተመዘገቡ ቤቶችና ሕንጻዎች ስብስብ የሆነ የበይነ መረብ ካርታ ነው።
የአዛለች ጎበና መኖሪያ ቤት - እአአ በ1900 የተገነባ ነው። አዛለች ጎበና በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ሚኒስቴር ሲሆኑ፣ ቤታቸው በፖላንድና ሩሲያውያን ባለሙያዎች መገንባቱ ይነገራል።
የሼኽ አሕመድ ሳሏህ አልዛሕሪ ሕንፃ - ዋቢ ሸበሌ ሆቴል አጠገብ የሚገኘውና ሎምባርዲያ የሚባለው የየመናዊው ዕውቅ ነጋዴ ቤት ሲሆን፣ ሕንፃው ከ85 ዓመት በላይ የኖረ ነበር።
የሙሴ ናዛሬት እና ባግድራ ኢያና ቤት - መሀል ፒያሳ ይገኝ የነበረ የቀድሞው ዕውቅ ነጋዴዎች መኖሪያ ነበር።
የጳውሎስ ኮርዳስ መኖሪያ ቤት - የግሪክ ኪነ ሕንጻ ስልት ያለውና እአአ በ1934 የተገነባ ነው።
የሙሴ ሚናስ ከርበኪያን መኖሪያ ቤት - በመንገድ እና በሕንጻ ግንባታ ስመ ጥር የነበረው ባለሙያ ራሱ ዲዛይን ያደረገው ቤት ነበር ። አርመናዊው መሀንዲስ እና የኪነ ሕንጻ ባለሙያ በከተማዋ የመጀመሪያ የሆነውን ጣይቱ ሆቴልን ጨምሮ አሁን አዲስ አበባ ሙዝየም የሆነውን የራስ ብሩ መኖሪያ ቤትም ሠርቷል። ሙሴ ሚናስ ‘እንግሊዝም መጣ ሄደ ተመለሰ፣ ጣልያንም መጣ ሄደ ተመለሰ፣ ሙሴ ሚናስ ቀረ ቤት እያፈረሰ’ ተብሎ ተገጥሞለታል።
የግራዝማች ጣሰ አሰግድ መኖሪያ ቤት - በዐፄ ምኒሊክ ዘመን የቴክኒክ ባለሙያ የነበሩ ሲሆን፣ ቤታቸው እአአ በ1900 በሕንዳዊው የኪነ ሕንጻ ባለሙያ ወሊ መሐመድ የተገነባ ነው።
የፊታውራሪ አጥናፍሰገድ መኖሪያ ቤት - እአአ በ1920 የተገነባ ነው።
የሐኪም ወርቅነህ እሸቴ መኖሪያ ቤት - እአአ በ1920ዎቹ የተገነባ ነው። አገር ፍቅር ጀርባ ባንኮ ዲሮማ አካባቢ የነበረው ይህ ሕንጻ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ ዶክተር የሆኑት የሐኪም ወርቅነህ መኖሪያ ነበር።
የግራዝማች ሳሕለማርያም መኖሪያ ቤት - በጣሊያን ወረራ ወቅት በአስተርጓሚነት ይሠሩ የነበሩት የግራዝማች ሳሕለማርያም ቤት እአአ በ1900 የተገነባ ነው።
ኒኮላ ታሪካዊ ሕንጻ - አያሌው ሙዚቃ ቤት በመባል የሚታወቀው ሕንጻ በ1900 ዓ.ም. ገደማ የተገነባ ነው። አሁን ወደ ዓድዋ ሙዝየም የተዛወረው ጥንታዊው መኮንን ቫቅላቫ ቤት መገኛ ነበር።
እነዚህ ሥፍራዎች በአዲስ አበባ የኪነ ሕንጻ ታሪክ ስመ ጥር ከመሆናቸውም ባሻገር የኪነ ሕንጻ፣ የቅርስ ጥበቃ እና የታሪክ ባለሙያዎች የከተማዋ መሠረት ብለው የሚገልጿቸው ናቸው።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች እንደሚሉት ፈረሳ በሚካሄድባቸው ታሪካዊ አካባቢዎች ፎቶ ማንሳት ወይም ተንቀሳቃሽ ምሥል መቅረጽ የተከለከለባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። ይህም ስነዳ እንዳይከናወን እንቅፋት ሆኗል።
ምሥሎች እንዲሰረዙ በፀጥታ ኃይሎች የተገደዱ እና ለቀናት እስራት የተዳረጉ ባለሙያዎች እንዳሉም ቢቢሲ ለማወቅ ችሏል።
በጉዳዩ ላይ በአደባባይ በመናገር እና ቅርሶች እንዲጠበቁ ንቅናቄ በማድረግ የሚታወቁ የኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች እንዲሁም የታሪክ ምሁራን “ጉዳዩ ስሱ ሆኗል” በሚል እና ሊደርስባቸው የሚችለውን ጫና በመፍራት በይፋ አስተያየት ከመስጠት ሲቆጠቡ ይታያል።
ነዋሪዎችም ስለ ጉዳዩ ሲናገሩ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆነው ነው።
ቢቢሲ ያነጋገራት ካዛንቺስ አካባቢ ተወልዳ ያደገች ነዋሪ “ድንገት የማላውቀው ቦታ የተጣልኩ ያህል ነው የሚሰማኝ” ስትል የሰፈሯን 'ለውጥ' ትገልጻለች።
“ብዙ ትዝታዎቼ ያሉባቸው አካባቢዎችን ድንገት ማጣት ልቤን ሰብሮታል። ወደ ፒያሳ፣ አራት ኪሎ እና ስድስት ኪሎ መሄድ በጣም ነው የሚከብደኝ። በወጣትነቴ ቆንጆ ጊዜ ያሳለፍኩባቸውን ቦታዎች ለልጆቼ ማሳየት እፈልግ ነበር። አሁን ግን የማላውቃት ከተማ ውስጥ እንደምኖር ይሰማኛል” ትላለች።









ከፈረሳ በተቃራኒ ደግሞ እድሳት ተደርጎላቸው አገልግሎት የሚሰጡ ወይም ባሉበት ተጠብቀው የሚጎበኙ ውብ ታሪካዊ ሥፍራዎች እና ቅርሶችን እንደ ማሳያ ማንሳት ይቻላል።
ከ119 ዓመት በፊት የተገነባው የመጀመሪያው የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት የነበረው የቢትወደድ ኃይለጊዮርጊስ ኃይለሚካኤል መኖሪያ ቤት በዓለምፀሐይ ወዳጆ ተነሳሽነት ታድሶ ወደ እቴጌ ጣይቱ የባህል እና ትምህርት ማዕከል ተለውጧል።
ወደ ይምጡበዝና ቤተ መዘክር እና የባህል ማዕከልነት የተሻገው 123 ዓመታትን ያስቆጠረው የይምጡበዝናሽ ሃብቴ መኖሪያ ቤት፣ ዓውደ ርዕዮችን ማስተናገድን ጨምሮ የሚጎበኝ መዳረሻ ነው።
የራስ ብሩ መኖሪያ ቤት አዲስ አበባ ሙዝየም ሆኗል።
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በኢዮቤልዮ ቤተ መንግሥት
በፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ እድሳት የተደረገለት ብሔራዊ ቤተ መንግሥት በቅርስ ጥበቃና ጥገና ተጠቃሽ ነው።
በዐፄ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት የሚገኘው እንቁላል ቤት የቀድሞ ይዞታው
አንድነት ፓርክ ውስጥ የሚገኘው እንቁላል ቤት በጥሩ ይዞታ ላይ ከሚገኙ ቅርሶች መካከል አንደኛው ነው።
ፊንፊኔ አዳራሽ፣ የቀኝ አዝማች መኰንን እንዳልካቸው ቤት እና የልጅ ኢያሱ መኖሪያ ቤትም በቅርስ ጥበቃ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው።
በግለሰቦች ተነሳሽነት ጥገና ከተደረገላቸው ቅርሶች መካከል ሞዴል ሊያ ከበደ፣ የአያሌው ብሩን መኖሪያ ቤት ማሳደሷ ይጠቀሳል።
በአዲስ አበባ በቅርስነት የተመዘገቡ ሌሎች ቤቶችን ወይም ሕንጻዎችን ከላይ እንደተጠቀሱት ምሳሌዎች አዘምኖ ጥቅም ላይ ማዋል ለምን አልተቻለም? የሚለው የበርካታ ነዋሪዎች እና ባለሙያዎች ጥያቄ ነው።
‘አዲስ አበባ ስታይል’
አዲስ አበባ ከተቆረቆረች 137 ዓመት ደፍናለች።
የትኞቹን አካባቢዎች ታሪካዊ ወይም የቅርስ መገኛ ልንላቸው እንችላለን? የሚለውን ስንመለከት ከሚጠቀሱ መካከል ፒያሳ፣ አራት ኪሎ እና ካዛንቺስን ማንሳት ይቻላል።
ከተማዋ በመዲናነት የአገሪቱ ማዕከል ስትሆን በዐፄ ምኒሊክ ግቢ (ታላቁ ቤተ መንግሥት) ዙርያ የተሠሩ የክፍለ አገር አስተዳዳሪዎች፣ የራሶች፣ የደጅ አዝማቾች እና ሌሎችም መኳንንት ቤቶች በታሪካዊነት ይጠቀሳሉ።
አራዳ የንግድ ማዕከል የተገነባበት ጥንታዊው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን እና አካባቢው በአዲስ አበባ ኪነ ሕንጻ እንደ አንድ ምዕራፍ ይጠቀሳል።
የአዲስ አበባ ኪነ ሕንጻ ሌላ አካፋይ የታሪክ ክስተት አምስቱ የጣሊያን አገዛዝ ዓመታት (ከ1928-1933 ዓ.ም.) እንዲሁም ከኢትዮጵያ ድል በኋላ ያሉት ዓመታት ናቸው።
የኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት መገንባት፣ ከ1950ዎቹ ወዲህ ደግሞ የአፍሪካ አዳራሽ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ማዘጋጃ ቤትን ጨምሮ ሌሎችም የአዲስ አበባ መለያ የሆኑ ኪነ ሕንጻዎች ግንባታ የከተማዋ ታሪክ አካል ናቸው።
በተለይም የሕንድ፣ የግሪክ እና የአርመን ኪነ ሕንጻ ስልቶች የሚታዩባቸው ሕንጻዎች፣ ከተሠሩበት ግብዐት ስብጥር (በአብዛኛው ድንጋይ፣ እንጨት እና አፈር) ከጣሪያ እና ከኮሪደራቸው ጌጣ ጌጥ አንጻርም ልዩ ናቸው።
የጣልያን፣ የጀርመን፣ የፈረንሳይ፣ የዩናይትድ ኪንግደም እና የሌሎችም ምዕራባውያን አገራት ኪነ ሕንጻ ተጽዕኖ እንዲሁም የኤምባሲዎች መከፈት፣ ውጭ አገር ተምረው ወደ አገር ቤት የሚመለሱ ባለሙያዎች ቁጥር መጨመር እና የኪነ ሕንጻ ትምህርት ቤት መከፈትም እንደ ምዕራፍ በአጥኚዎች ይጠቀሳሉ።
እነዚህን ታሪካዊ ሕንጻዎች እና ቤቶች የኪነ ሕንጻ እና የምህንድስና ባለሙያዎች አዲስ አበባ ‘ስታይል’ (Addis Ababa Style) ይሏቸዋል።
በዚህ ዘገባ፣ አንድን ሕንጻ ወይም ቤት ቅርስ አልያም ታሪካዊ ሥፍራ ለማለት መስፈርቱ ምንድን ነው? የታሪካዊ ሕንጻዎች እና ቤቶች መፍረስ በታሪክ፣ በነዋሪዎች ሥነ ልቦና፣ በኪነ ሕንጻ እና በማኅበራዊ መስተጋብር ላይ ምን ጫና ያሳድራል? ቅርሶች እና ታሪካዊ ሥፍራዎችን እንዴት ጠብቆ ማደስ፣ ማዘመን፣ መልሰው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ማድረግ እንዲሁም ከሌሎች ግንባታዎች ጋር ጎን ለጎን እንዲሄዱ ማድረግ ይቻላል? የሚሉት እና ተያያዥ ነጥቦች ይዳሰሳሉ።.
የጣሊያን ዲፕሎማቲክ ልዑካን ከዐፄ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት ሲወጡ የሚያሳይና እአአ በ1910 በጣልያን ጋዜጣ የወጣ ምሥል
የዐፄ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት
የዐፄ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት
የኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች ዛልማን ኢናቭና ሚካኤል ቴዎድሮስ የነደፉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሕንጻ በአዲስ አበባ ኪነ ሕንጻ ውስጥ ተጠቃሽ ከሆኑ አንዱ ነው።
የኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች ዛልማን ኢናቭና ሚካኤል ቴዎድሮስ የነደፉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሕንጻ በአዲስ አበባ ኪነ ሕንጻ ውስጥ ተጠቃሽ ከሆኑ አንዱ ነው።
የፓርላማ ሕንጻ
የፓርላማ ሕንጻ
የቀድሞው የአዲስ አበባ አውራ ጎዳና
የቀድሞው የአዲስ አበባ አውራ ጎዳና
ማዘጋጃ ቤት የአዲስ አበባ መለያ የሆኑ ኪነ ሕንጻዎች አንዱ ነው።
ማዘጋጃ ቤት የአዲስ አበባ መለያ የሆኑ ኪነ ሕንጻዎች አንዱ ነው።
የኔዘርላንድስ ኤምባሲ በአዲስ አበባ በኪነ ሕንጻ ውበት ተጠቃሽ ከሆኑት መካከል አንዱ ሲሆን፣ የኤምባሲዎች መገንባት በመዲናዋ የኪነ ሕንጻ ታሪክ ውስጥ እንደ አንድ ምዕራፍ ሊወሰድ ይችላል።
የኔዘርላንድስ ኤምባሲ በአዲስ አበባ በኪነ ሕንጻ ውበት ተጠቃሽ ከሆኑት መካከል አንዱ ሲሆን፣ የኤምባሲዎች መገንባት በመዲናዋ የኪነ ሕንጻ ታሪክ ውስጥ እንደ አንድ ምዕራፍ ሊወሰድ ይችላል።
“በከተማ መካከል ያሉ የታሪክ መዛግብት”
ዘላቂነት ያለው ኪነ ሕንጻ ባለሙያ የሆነው ናሆም ተክሉ እንደሚለው፣ ታሪካዊ ሕንጻዎች እና የከተማ ሥፍራዎች “ከዛሬ እና ከነገ የከተማ ገጽታዎች እንዲሁም መልኮች ጋር ተናበው የትላንትን ትውስታ እና ፋይዳ የምንቃኝባቸው የከተማ ታሪክ እና የከተሜነትን ማንበቢያ መነጽሮች” ናቸው።
“በከተማ መካከል ያሉ የታሪክ መዛግብት” የሚላቸው እነዚህ አካባቢዎች ከታሪክ ባሻገር ከከተማው ነዋሪዎች የዕለት ከዕለት ሕይወት ጋርም የጠበቀ ቁርኝት አላቸው።
ይህ የጠበቀ ቁርኝት ከአካላዊ መስተጋብር በጠለቀ መንገድ ከከተማ ነዋሪነት ዕሴት ጋር አብሮ የሚያድግ መሆኑን በመጥቀስም፣ እነዚህን ታሪካዊ ሕንጻዎች እና የከተማ ሥፍራዎችን “ከተገቢው የመከተም ሒደት ውጪ ማፍረስ ታሪክን እንደማፍረስ እንዲሁም የትላንት አሻራዎችን እንደማጥፋት ይቆጠራል” ይላል።
የእነዚህ ቅርሶች እና ታሪካዊ ሥፍራዎች መፍረስ የከተማ ማንነት ቀውስ (Urban Identity Crisis) እንደሚያስከትል ናሆም ይናገራል።
“የሕንጻዎቹን እና የሥፍራዎቹን አሻራ በማጥፋት ከተሞች ሊኖራቸው የሚገባውን የጊዜ ውክልና እና የተማከለ መስተጋብር ያዛባል” ሲልም ያክላል። ይህም በከተማው ነዋሪዎች ዘንድ ያለውን የእኔነት ስሜት ይሸረሽራል።
ከእነዚህ ሥፍራዎች ጋር ማኅበራዊ፣ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ዘርፈ ብዙ ተዛምዶ ያላቸው ነዋሪዎች ላይ ሥነ ልቦናዊ ጫና ያሳድራል።
ከተሞች በሚኖራቸው የለውጥ ሂደት ውስጥ ታሪካዊ ሕንጻዎችን እና የከተማ ሥፍራዎችንም ማልማት “የልማት አንዱ እና ወሳኝ መገለጫ” እንደሆነ ናሆም ይገልጻል።
በሌሎች ከተሞች ታሪካዊ ሕንጻዎች እና ሥፍራዎች በምን መንገድ ጥበቃ ተደርጎላቸው ከልማት ሥራ ጎን ለጎን እንደሄዱ ልምድ በመቅሰም፣ በአዲስ አበባም አካታች በሆነ መልኩ “የከተማ እና የከተሜነት ታሪኮቻችንን ከልማት ጋር አናቦ ለማስኬድ” ዕድል እንዳለ ባለሙያው ይናገራል።
እነዚህ ሥፍራዎች ከታሪካዊ ፋይዳቸው በተጨማሪ ዘላቂ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲኖራቸው ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር መሥራትን ይመክራል።
የአንድ ከተማ ልማት በከተማው ያሉ ወቅታዊ መገ��ጫዎችን ያገናዘበ እና ሥራ አጥነት፣ የትራንስፖርት እጥረት እንዲሁም ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትን ጨምሮ ሌሎችም ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ መሆኑን እንደ መነሻ በመጥቀስ “ልማት፣ ከተማ የመገንቢያ እና የከተማ እድገትን በዘላቂነት ማስቀጠያ ዘዴም ነው” ሲል ናሆም ይገልጻል።
ቅርሶችን ከተጋረጠባቸው ሰው ሠራሽም ሆነ ተፈጥሯዊ አደጋ ታድጎ ቀጣይነት እንዲኖራቸው በማስቻል፤ በነበራቸው አገልግሎት አልያም ለአዲስ አገልግሎት እንዲውሉ በማድረግ የልማት አካል ማድረግ በተለያዩ ከተሞች የተለመደ አሠራር ነው።
“ይህ ሂደት ቅርሶች ከቅርስነታቸው በተጨማሪ ጊዜውን እየዋጁ እና ለጊዜው ፍላጎቶች እንዲስማሙ በማጋፈር ሕልውናቸውን ማቆያ እንዲሁም በከተማ ውስጥ ያሉትን የጊዜ አውታሮች ውክልና (የትናንት፣ የዛሬ እና የነገ) ማስጠበቂያ መንገድ ነው።”
አንድን ሕንጻ ቅርስ ነው ወይስ አይደለም? ብሎ ለመወሰን ዓለም አቀፋዊ እና አገራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት መስፈርቶች እንደሚዋቀሩ፣ በእነዚህ መስፈርቶች መሠረትም ቅርሶች እንደሚለዩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ሕንጻዎች እና የከተማ ሥፍራዎች ቅርስ ከሚባሉባቸው መስፈርቶች መካከል ያለፉባቸው የተለያዩ ጊዜያት እና ታሪካዊ ሁነቶች እንዲሁም የኖረባቸው ግለሰብ ማኅበረሰባዊ እና ሁለንተናዊ አበርክቶን የኪነ ሕንጻ ባለሙያው ይጠቅሳል።
በተጨማሪም ከአካባቢያቸው የከተማ ሥፍራ እና ነዋሪዎች ጋር ያላቸው የጠበቀ ታሪካዊ ቁርኝት፣ የኪነ ሕንጻ እና የከተማ ልህቀት ማሳያነት እና መገለጫነታቸው ከግምት ይገባል።
ከዕድሜያቸው፣ ከተሠሩበት ዘመን፣ ከነደፏቸው እና ከገነቧቸው ባለሙያዎች ማንነት ጋር በተያያዘም የቅርስነትን መስፈርት ያሟላሉ።
[በስተቀኝ በኩል በቅደም ተከተል የሚታዩት የፈረሱት ቅርሶች የሙሴ ሚናስ ከርበኪያን ቤት፣ የሼኽ አሕመድ ሳሏህ አልዛሕሪ ቤት እና የሐኪም ወርቅነህ ቤት ናቸው።]



የቅርሶች ‘የመኖር መብት’
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ኢትዮጵያ እአአ በ1977 የፈረመችው እና 195 አገራት የተስማሙበት ‘World Heritage Convention’ ላይ ቅርሶችን “የትናንት አሻራ፣ ለዛሬ መኖሪያ እና ወደነገ የምናሻግረው አይተኬ የሕይወት ምንጭ” ሲል ይገልጻቸዋል። ቅርሶች “የመኖር መብት አላቸው” ሲልም ከለላ ይሰጣቸዋል።
በኢትዮጵያ ስለ ቅርስ ጥናት እና አጠባበቅ የወጣው አዋጅ ቁጥር 209/1992 ላይ “ተተኪው ትውልድ ስለ ማንነቱ መገለጫ ለሆነው ታሪኩ እና ባህሉ ጥልቅ እና ሰፊ ግንባዜ ይበልጥ እንዲኖረው ቅርስ ከፍተኛ ሚና ስለሚጫወት ቅርስን መንከባከብ እና መጠበቅ የእያንዳንዱ ዜጋ፣ የኅብረተሰቡ እንዲሁም የመንግሥት ግዴታ” መሆኑን በግልጽ ያስቀምጣል።
የኪነ ሕንጻ እና ቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎች ግን ይህ መርኅ መጣሱን ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መቆያ ማሞ ለሪፖርተር ጋዜጣ “መንግሥት ቅርስን በተመለከተ ያወጣው አዋጅ፣ እንዲሁም መመሪያ አለ፡፡ ያንን ተከትሎ ሄዶ ይሄ ቅርስ ነው ብሎ ከመዘገበ በኋላ ቅርሱን ላለማፍረስ እስከመጨረሻው ጥግ መሄድ አለበት” ሲሉ ተናግረዋል።
“ለግንባታ ቅርስ የሆነውን ማፍረስ ነው የሚቀለው ወይስ ሌላ ቦታ መፈለግ? . . . ቅርሶች ዕጣ ፈንታቸው አደጋ ላይ እንዳይወድቅ መንግሥት ዕውቅና ለሰጠው የቅርስ አዋጅ ተገዢ መሆን አለበት” በማለትም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አበባው አያሌው፣ ከኮሪደር ልማት ጋር በተያያዘ የሚፈርሱ ቤቶች በአብዛኛው “የቅርስነት መስፈርትን የማያሟሉ” ናቸው ያሉ ሲሆን፣ “90 ዓመት ከሞላው ሕንጻ ይልቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ለ200 ሺህ ሰዎች የሚሆን የልማት ሥራ ነው” ማለታቸውም በመገናኛ ብዙኃን ተዘግቦ ብዙ አነጋግሯል።
የቀድሞው የአዲስ አበባ ዋና አውራ ጎዳና እአአ በ1927 በጣልያን ጋዜጣ ላይ የወጣ ምሥል

ለገሃር ባቡር ጣቢያ


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኅዳር 2017 ዓ.ም. ላይ ሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በገመገሙበት ወቅት፣ “የአገር ግንባታ” በሂደቱ ወቅት የሚኖሩ ሰዎች “በቀላሉ ተቀብለው፣ ተስማምተው የሚሄዱበት ጉዳይ” እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ አሁን የሚሠራውን ሥራ የሚያደንቁ ሰዎች የሚመጡት “ከተማው የተገነባለት ትውልድ ሲነሳ ነው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የውጭ ኢንቨስትመንት እና ቱሪዝም ለመሳብ ከአዲስ አበባ ድህነትን ማስወገድ አለብን” ብለው ዱባይን እንደ ምሳሌ መጥቀሳቸው ይታወሳል።
በሌላ አጋጣሚ “ማንም ያቦካው ጭቃ ሁሉ ቅርስ አይደለም” ማለታቸው ከቅርስ ጥበቃ እና ከኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን ከነዋሪዎችም ቅሬታ ማስነሳቱ አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ ቅርስ የሚባሉት ላሊበላ፣ አክሱም፣ ሶፍ ዑመር እና የሐረር ግንብን የመሳሰሉት ናቸው በማለት “ዝም ብለን የትውስት ነገሮችንም ቅርስ እያለን በፍርድ ቤት የምናስተጓጉልበትን አካሄድ መቀበል እና ማስተናገድ ተገቢ አይደለም” ሲሉም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በጎንደር እና በጅማ ኮሪደር ልማቶች የታደሱትን የጎንደር ቤተ መንግሥት እና የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥት ጎብኝተዋል።
ስለ እድሳቶቹ ሲነገር የቅርስ ጥበቃ ያለው ዋጋ በጉልህ ተጠቅሷል። በሌላ በኩል ደግሞ ቅርሶች እና ታሪካዊ ሥፍራዎች ሲፈርሱም ይስተዋላል። በሁለቱ መካከል ያለውን ተቃርኖ ነዋሪዎች እና ባለሙያዎች ያነሳሉ።
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ስለ ፒያሳ የኮሪደር ልማት ሲናገሩ፣ ከአካባቢው ወደ 11 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች መነሳታቸውን ገልጸው፣ በአካባቢው በቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን የተመዘገቡ ስድስት ቅርሶች እንደሚገኙ እና እነሱም “ባሉበት እንደሚታደሱ” መናገራቸው ይታወሳል።
ዘ ጋርዲያን ከወራት በፊት ‘Dismay in Addis Ababa as ‘the soul of the city’ is razed for development’ በሚል ባስነበበው ዘገባ፣ “በፒያሳ በቅርስነት ከተመዘገቡ 42 ሕንጻዎች 36 የሚሆኑት ወይ ፈርሰዋል ወይም ለመፍረስ ምልክት ተደርጎባቸዋል” ብሏል።
በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት በአምስት አቅጣጫዎች የሚዘረጋ ሲሆን፣ 40 .7 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን ተገልጿል።
ሰፋፊ የመኪና እና የእግረኛ መንገዶች፣ የሳይክል መስመሮች እና አረንዴ አካባቢዎችን ይዞ የሚገነባው የኮሪደር ልማት ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ መገናኛ፣ ሜክሲኮ፣ ሳር ቤት፣ ወሎ ሰፈር፣ ሲኤምሲ እና ሌሎችም አዋሳኝ ሰፈሮችን ያካትታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስለ ግንባታው ሲናገሩ “አዲስ አበባን በዚህ ደረጃ ደፍሮ መልሶ ለመገንባት የሞከረ አመራር የለም” ብለዋል።

ቅርስ የቱ ነው?
ቅርሶች የትኞቹ ናቸው? አዳዲስ ግንባታዎች ሲካሄዱ ጠብቆ ማቆየት የሚያስፈልገው የትኞቹን ነው? የሚለው ክርክር ከግንባታ እና ከፈረሳ ጋር በተያያዘ ይነሳል።
የቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት፣ አንድን ሕንጻ ወይም ሥፍራ ቅርስ ለማለት ዕድሜው (በአንዳንድ ሁኔታዎች ዓመታት ማስቆጠር ብቻ ሳይሆን በቦታው ምን ተከናወነ? የሚለው ይታያል)፣ በቦታው እና በአካባቢው እነማን ኖሩ? ምን ተፈጸመ? ኪነ ሕንጻውስ ምን ዓይነት ነው? የሚሉት ሊታዩ ይችላሉ።
ልዩ ኪነ ሕንጻ ያለው መሆኑ (ለምሳሌ በአንድ ወቅት ረዥሙ ሕንጻ ሊሆን ይችላል)፣ በታሪክ ውስጥ ያለው ሚና፣ ትልልቅ ታሪካዊ ሁነቶች የተከናወኑበት መሆኑም ይጠቀሳሉ።
ቢቢሲ ያነጋገረው ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የኪነ ሕንጻ እና የከተማ ፕላን ባለሙያ፣ የቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለሥልጣን መስፈርትን ማሟላት ከግምት ውስጥ ከሚገቡ መካከል አንዱ መሆኑን ይገልጻል። ባለሙያዎች አስተያየት ሳይጠየቁ እና ማኅበረሰቡ ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ሳይሰጠው ወደ ማፍረስ መገባቱን ይነቅፋል።
በአዲስ አበባ ቅርስ መሆናቸው በባለሥልጣኑ የተረጋገጡም ጭምር ከመፍረስ አልዳኑም።
በኒኮላ ታሪካዊ ሕንጻ (አያሌው ሙዚቃ ቤት) እና የሼኽ አሕመድ ሳሏህ አልዛሕሪ ቤት (ሎምባርዲያ) ሕንጻዎች ላይ ተቀምጠው የነበሩ የቅርስነት ማረጋገጫዎች
በኒኮላ ታሪካዊ ሕንጻ (አያሌው ሙዚቃ ቤት) እና የሼኽ አሕመድ ሳሏህ አልዛሕሪ ቤት (ሎምባርዲያ) ሕንጻዎች ላይ ተቀምጠው የነበሩ የቅርስነት ማረጋገጫዎች
“ለማኅበረሰብ ውይይት ዕድል ሳይሰጥ ነው ማፍረስ የተጀመረው። ማኅበረሰቡ ቅርስ እንደሆነ ከተስማማበት ማፍረስ ላያስፈልግ ይችላል። መንግሥት የሚፈርስበትን ምክንያት ማሳመን ችሎ በምክንያታዊነት ሳይሆን ማኅበረሰቡን ‘መብት የላችሁም! እናንተ ምን አገባችሁ? ምን ታመጣላችሁ!’ አካሄድ ነው ያለው” ሲል ባለሙያው ይተቻል።

የወራት ዕድሜ የተሰጣቸው አካባቢዎች በቀናት ውስጥ አንዳንዴም በአንድ ጀንበር እንደሚፈርሱ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች እና ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
የከተሞች አዳዲስ ግንባታ ወይም ቀድሞ የነበረን ይዞታ አፍርሶ አዲስ መገንባት በየትኛውም አገር የሚከናወን ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ያለው “ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ማፍረስ፣ የታሪክ ስነዳ ሳይደረግ ማፍረስ፣ ታሪኩ ቢኖርም ባይኖርም ግድ አለመኖር ነው” ሲል የኪነ ሕንጻ እና የከተማ ፕላን ባለሙያው ያስረዳል።
ሕንጻዎቹ ሲፈርሱ የተሠሩበት ግብዐት እንኳን “ለታሪክ መማሪያ እንዳይተርፍ ተደርጎ” ነው ሲልም ያክላል።
መፍረሳቸው ለምን ያሳስበናል?
ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው የኪነ ሕንጻ እና የከተማ ፕላን ባለሙያ አዲስ አበባ ‘ኢንዲጂንየስ የአፍሪካ መዲና’ የምትባለው “በራሷ መንገድ የተሠራች” ስለሆነ ነው ይላል።
ይህንን ‘ልዩ ቀለም’ የሚያሳዩ ቅርሶች እና ታሪካዊ ሥፍራዎች ሲፈርሱ “ባህልን፣ ወግን፣ ስሜትን እና መንፈስን ቆርጦ እንደመጣል ነው” ሲል ይገልጻል።
አንድ ከተማ አድጎ ትልቅ የሚባል ደረጃ ሲደርስ ከየት ተነሳ? የሚለውን ለመረዳት ወደኋላ መመለስ ግድ ይላል። የቀደመው ኪነ ሕንጻ ማሳያ ከሌለ የታሪክ ክፍተት ይፈጠራል።
የኪነ ሕንጻ እና የከተማ ፕላን ባለሙያው “ማኅበረሰብ ታሪክ ከሌለው ምንም ነው” ሲል ይገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ቀደምት ትውስታ ያለባቸው ቦታዎች ሲፈርሱ “የአገር ባለውለታ አዛውንቶችን ድንገት ከኖሩበት መንጭቆ በማውጣት በሐዘን እና በተስፋ መቁረጥ እንዲሞቱ ማድረግ” ነው ይላል።
“ፒያሳ ምድረ በዳ ሲሆን የእኔነት ስሜት ማጣትን እና ባይተዋርነትን ይፈጥራል” ሲል ነው የሚገልጸው።
ዘመናት የተሻገረ የኪነ ሕንጻ ስልትን ከሌሎች አገራት 'በተውሶ' በመጡ ስልቶች መተካትን የቅርስ ጥበቃ እና የኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች ይነቅፋሉ።
ቢቢሲ ያነጋገረው የኪነ ሕንጻ እና የከተማ ፕላን ባለሙያም “በጉልበት ቅኝ ሳንገዛ የራሳችንን ማንነት ትተን የሌላን በመውሰድ በራሳችን ፈቃድ ወደ ግዞት እየወረድን ነው” ሲል ሐሳቡን ይገልጻል።
የኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች ቀደምት ሕንጻዎች ከታሪክ እና ከውበት ባሻገር ከአካባቢ ጥበቃ አንጻርም ያላቸውን ሚና ይጠቅሳሉ።
የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል አንጻር ዘላቂነት ያለው፣ አካባቢ የማይጎዳ እና ኃይል የማይፈጅ ግንባታ ማሳያ ናቸው።
ጥንታዊ ሕንጻዎች የሚሠሩት ለአካባቢ ተስማሚ ከሆኑ ግብዐቶች እንደሆነ እና አካባቢን ለብክለት እንደማይዳርጉ የኪነ ሕንጻ እና የከተማ ፕላን ባለሙያው ይናገራል።
“አሁን ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት እንደ መስታወት ያሉ ግብዐቶች ግን በአዲስ አበባ ትሮፒካል የአየር ሁኔታ ሙቀት ይስባሉ። ዕይታን ይረብሻሉ። ኃይል በብዛት እንዲወጣ ያደርጋሉ።”
የከተሞችን ለውጥ ታኮ የሚመጣን አዳዲስ ግንባታን ማስቆም ባይቻልም፣ ቅርስን ሳያፈርሱ እንዴት አዳዲስ ግንባታን ማስኬድ ይቻላል? ታሪካዊ ሥፍራዎችን አድሶ እንዴት ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል? ለውጥ እና ታሪክን እንዴት ማጣጣም ይቻላል? የሚሉትን ታሳቢ እንዲደረጉ ባለሙያዎች ያሳስባሉ።
“ልማት እና ታሪክን መጠበቅ አይጋጩም። አብረው ይሄዳሉ” ሲል የኪነ ሕንጻ እና የከተማ ፕላን ባለሙያው ያስረዳል።
“መንግሥት እድገትን ማሰብ ኃላፊነቱ ነው። ማንም አይቃወመውም። ግን ከቱሪዝም አንጻርም አያስኬድም። ቱሪስቶች የሚመጡት የሚኖሩበት አካባቢ ሰልችቷቸው እና የተለየ ነገር ለማየት ነው። የሰውን አዋዋል እንዲሁም የአካባቢውን መንፈስ ሊያዩ ነው የሚመጡት። እኛ ደግሞ ዓለም ሊጎበኘው የሚፈልገውን ተወዳጅ ቦታ አፍርሰን ዓለም የሰለቸውን ፎቅ ለመሥራት እየተጣደፍን ነው።”
ጥንታዊ የከተማ ማዕከል (Old Town) ሆነው መቆየት ያለባቸው አካባቢዎች ፈርሰው ከሚገኘው የግንባታ ቦታ ይልቅ ጥበቃ ቢደረግላቸው የሚገኘው የቱሪዝም ገቢ ሊበልጥ እንደሚችል ባለሙያዎች ይስማሙበታል።
“አንድ ልማት ፒያሳ ላይ ስላልሠራ ብቻ አይደ���ም የማይሳካው” የሚለው ባለሙያው፣ ታሪካዊ የከተማ ማዕከልን ጠብቆ በአቅራቢያው መገንባት ወይም ታሪካዊ ሥፍራዎችን በማይጫን መልኩ አዳዲሶቹን መገንባት የሚቻልባቸው መንገዶች እንዳሉም ይጠቅሳል።
‘ቅርስ ጥበቃ እና የከተማ እድገት አይጣሉም’
ከታሪካዊ ሥፍራዎች እና ቅርሶች ጥበቃ ጎን ለጎን የሚነሳው ነጥብ የስነዳ ጉዳይ ነው።
ታሪካዊ ሥፍራዎችን በምሥል እንዲሁም በሦስት አውታር ምሥል (3ዲ) ከሚሰንዱ የኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች ስብስብ መካከል ግምጃ አርክ-ሃይቭ አንዱ ነው።
በግምጃ አርክ-ሃይቭ ውስጥ የሚሠራው እና ለቢቢሲ አስተያየቱን የሰጠው የኪነ ሕንጻ ባለሙያ፣ በስነዳ ካካተቷቸው መካከል የሐኪም ወርቅነህ እና የፊታውራሪ አጥናፍሰገድን ቤቶች ይጠቅሳል።

የሐኪም ወርቅነህ ቤት ሳይፈርስ በፊት

የሐኪም ወርቅነህ ቤት 3ዲ ምሥል

የፊታውራሪ አጥናፍሰገድ ቤት ሳይፈርስ በፊት

የፊታውራሪ አጥናፍሰገድ ቤት 3ዲ ምሥል
የቤቶቹን የቀደመ ይዞታ የሚያሳይ የምሥል ክምችት በድረ ገጻቸው ይገኛል። የአዲስ አበባ ኪነ ሕንጻ ስልት ልዩ ገጽታዎች የሆኑ የቤቶቹን ክፍሎችም አካተዋል።
የኢትዮጵያን ቀደምት የግንባታ ስልት ዘመናዊ ግንባታ ውስጥ ለማዋሀድ እና ለዓለም ለማስተዋወቅ በሚል የስነዳ ሥራውን የጀመሩት ከአንድ ዓመት በፊት ነው።
“እኛን የሚመስል ነገር እንዲሠራ ማድረግ ነው ያነሳሳን” ይላል ባለሙያው።
መስኮቶች፣ በሮች እና የእጅ መደገፊያዎችን ጨምሮ የሕንጻዎችን የሦስት አውታር ምሥል ሰንደው ያስቀምጣሉ።
“ሁሌም ዲዛይን ስናደርግ መጀመሪያ ዐውዱን እንመለከታለን። አዲስ አበባ ውስጥ የምንሠራቸው ዲዛይኖች የአዲስ አበባ ‘ኤለመንት’ ቢኖራቸው ትርጉም ይሰጣሉ” ሲል የኪነ ሕንጻ ባለሙያው ያስረዳል።
ቀደምት ሕንጻዎች እና ቤቶች ሲፈርሱ ይህ የአዲስ አበባ የሚባለው የኪነ ሕንጻ ዘዬም አብሯቸው ይከስማል።
የአዲስ አበባ የሚባሉ የዲዛይን ይዘቶች ሲጠፉ “የእኛ የምንላቸው የዲዛይን ዓይነቶችን እያጣን እንመጣለን” ይላል ባለሙያው።
ቅርስ ላይ የሚገኙ የዲዛይን ዓይነቶችን “ከቴክኖሎጂ ጋር አንድ እርምጃ ወደፊት በመውሰድ ልንጠቀምባቸው ይገባል” ሲልም ያስረዳል።
እነዚህን የአዲስ አበባ የኪነ ሕንጻ ዘዬዎች መውሰድ የሚቻለው ከቅርሶች ላይ መሆኑን በማስረገጥ “እነሱን ማጣት ማጣቀሻ ማጣት ነው” በማለት ጥፋቱ ቀላል እንዳልሆነ አመልክቷል።
አዳዲስ ግንባታዎች ከከተማዋ የኪነ ሕንጻ ታሪክ እየራቁ በሄዱ ቁጥር ‘የእንግዳነት’ ስሜት እንደሚፈጠር ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ይስማሙበታል።
የግምጃ አርክ-ሃይቭ የኪነ ሕንጻ ባለሙያም “ከሕንጻዎቹ ጋር የምናስተሳስራቸው ትዝታዎችን ማጣት ይጎዳናል። ራሳችንን የምናገኘው እንግዳ ቦታ ውስጥ ይሆናል” ይላል።




በአርመናዊው የኪነ ሕንጻ ባለሙያ ሙሴ ሚናስ እአአ በ1990ዎቹ የተገነባው የሕንዳዊው ነጋዴ መሐመድ ወሊ ቤት፣ አሁን ላይ በከፊል ፈርሶ በሞትና ሽረት መሀል እያጣጣረ ይገኛል።
የሕንድ ኪነ ሕንጻ ከሚስተዋልባቸው የአዲስ አባበ ሕንጻዎች አንዱ የሆነው የሼኽ ኦጀሌ ቤተ መንግሥት እንክብካቤና ጥገና በማጣት ከተጎዱ ቅርሶች መካከል እንዱ ነው።
በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የቤተ መንግሥት አዛዥ እና የግቢ ሚኒስትር የነበሩት የደጃዝማች አስፋው ከበደ ቤት ለኮሪደር ልማት ፈረሳ ከመጀመሩ አስቀድሞ ከፈረሱ ቅርሶች አንዱ ነው።
የስዊዝ ተወላጁ የዐፄ ምኒሊክ አማካሪ አልፍሬድ ኢልግ ቤት
‘ቅርሶች ከዘመኑ ዘመናዊነትን ያጎላሉ እንጂ ወደኋላ አይጎትቱም’
የአዲስ አበባን ኪነ ሕንጻ የተለየ ከሚያደርጉት መካከል ጣሪያ የሚያስውቡ ጉልላቶች እና የደረጃ እጅ መደገፊያዎች አሠራር እንዲሁም የድንጋይ ግንባታዎች ይጠቀሳሉ።
አንድነት ፓርክ ውስጥ የሚገኘው እንቁላል ቤት እና ፒያሳ ያለው ፖስታ ቤት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው።
በአካባቢው በተለይም በአርመናውያን የኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች የተገነቡ ሕንጻዎች እንደ አካባቢው ‘መለያ’ ይወሰዱ ነበር።
ከታሪክ አንጻር ሲታይም አዲስ አበባ “ለአርመናውያንም ቤት እንደነበረች” የሚያሳዩ ሕንጻዎች ሲል ባለሙያው ይገልጻቸዋል።
“ቅርሶች ሲጠበቁ የአንድን ዘመን ሥልጣኔ ይገልጻሉ። በተለያዩ አገራት እንዲህ ያሉ አካባቢዎችን ሄደን እንጎበኛለን” ይላል።
የትኛውም ከተማ በሚያልፍበት ለውጥ ውስጥ ግንባታ ሲካሄድ ቅርሶችን ጠብቆ ከማቆየት ሂደት ጋር ማጣጣም እንደሚቻል የኪነ ሕንጻ እና የቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የግምጃ አርክ-ሃይቭ የኪነ ሕንጻ ባለሙያም “ቅርስ ጥበቃ ከከተሜነት ጋር ጎን ለጎን መሄድ ይችላል። ቅርሶች ከዘመኑ ዘመናዊነትን ያጎላሉ እንጂ ወደኋላ አይጎትቱም” ሲል ሐሳቡን ያጠናክራል።
በከተማ መስፋፋት እና ፈጣን እድገት ውስጥ ሕንጻዎች ቀድሞ የነበራቸውን ጥቅም ይዘው መቀጠል ካልቻሉ በአዲስ መንገድ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ማድረግ የሚቻልበት አሠራር አለ።
በእንግሊዝኛው Adaptive Reuse የሚባለው መንገድ ጥንታዊ ሥፍራዎች በዘመነኛ አሠራር አማካይነት በድጋሚ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማድረግ መንገድ ነው።
ከካይሮ እስከ ፊላደልፊያ
ጥንታዊ ሕንጻዎች፣ ታዋቂ ሰዎች የኖሩባቸው ቤቶች ወይም ጉልህ ታሪካዊ ክስተት የተከናወነባቸው ቦታዎችን እንደ ጥንታዊ የከተማ ማዕከል (Old Town) ጠብቆ፣ አዳዲስ ግንባታዎችን በቅርብ ርቀት ማካሄድ በሌሎች አገራት የተለመደ አሠራር ነው።
በቱርክ አንታሊያ ከተማ የሚገኘው የጥንታዊ ከተማ ማዕከል በኦቶማን ኪነ ሕንጻ ስልት የተሠሩ ሕንጻዎችን ይዟል።
ጥንታዊ ቤቶች፣ ሆቴሎች፣ መጻሕፍት መደብሮች፣ የእግረኛ መንገዶች፣ የጌጣ ጌጥ ገበያ. . . በአካባቢው ከሚጎበኙ መካከል ናቸው።
የከተማው ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች ከዚህ ጥንታዊ መንደር በቅርብ ርቀት ይገኛሉ። አካባቢው በርካታ ቱሪስቶችን ከሚያስተናግዱ መዳረሻዎች አንዱም ነው።
በግብፅ መዲና ካይሮ የሚገኘው ‘ኦልድ ካይሮ’ (አሮጌዋ ካይሮ) ሰፈር በከተማዋ እምብርት ዕድሜ ጠገብ መስጊዶች፣ ጎዳናዎች እና የአደባባይ ገበያዎችን ይዟል።
ኻን-አል-አኽሊል እአአ ከ1382 ጀምሮ የኖረ ባዛር (የገበያ ስፍራ) ነው። አንደኛው ሱቅ ከሌላኛው ጋር ያለው ድንበር አይታወቅም። በጠባቡ መንገድ በዝግታ ሲጓዙ መብራት፣ የፓፒረስ ጽሑፍ፣ ቫቅላቫ፣ ፍራፍሬ፣ ቅመማ ቅመም. . . የማያገኙት የለም።
ማሕፉዝ በልብ ወለዱ ‘ሚዳቅ አሊ’ ገናና ያደረገው ጠባብ ጎዳናም ዘመናትን ተሻግሮ ይጎበኛል።
በአሜሪካ፣ ፊላደልፊያ ጥንታዊ የከተማ ማዕከል ውስጥ የሚገኘው ‘ኤልፍሬትስ ጎዳና’ የአደባባይ ሙዝየም ሆኗል። እአአ ከ1703 እስከ 1816 የተገነቡ 32 ቤቶችን ይዟል።
ቤቶቹ ያሉበት ጥንታዊ ይዞታ ሳይለወጥ የአካባቢው ሰዎች አሁንም ድረስ ይኖሩባቸዋል።
እያንዳንዳቸው ከሁለት ሕንጻ በማይበልጡት ታሪካዊ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቅርሶቹን የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው።
[በስተቀኝ በኩል በቅደም ተከተል የሚታዩት ምሥሎች የቱርክ፣ አንታሊያ፤ የግብፅ፣ ካይሮ እና የአሜሪካ፣ ፊላደልፊያ ጥንታዊ ሰፈሮች ናቸው።]
በጀርመን፣ በፈረንሳይ፣ በጣልያን እና በሌሎችም አገራት ጥንታዊ የከተማ ማዕከሎችን ጠብቆ ለማቆየት ብዙ ርቀት ይጓዛሉ የሚለው በጀርመን የኪነ ሕንጻ ባለሙያ የሆነው ክንፈሚካኤል ኃይለሥላሴ ነው።
በቅርስነት ሲመዘገቡ በቦታው የተከናወነው ነገር፣ ዘመኑ፣ የግንባታ ስልቱ፣ የተገነቡበት መሣሪያ እና የቀደመውን ሕዝብ አኗኗር ዘይቤ ማሳየታቸው ከግምት ውስጥ ይገባሉ።
ጀርመን ውስጥ ያለ ሥጋ ቤትን ክንፈሚካኤል እንደ ምሳሌ ይጠቅሳል።
ሥጋ ቤቱ የተሠራበት ሴራሚክ ብቻ በቅርስነት ተመዝግቧል። ቤቱን የገዛው ግለሰብ ጓዳ መሥራት ፈልጎ ፈቃድ ጠየቀ። ሴራሚኩን ማፍረስ እንደማይችል ተነገረው።
“ስለዚህ ሴራሚኩን ሳንነካ ቤቱን 5 ሴንቲ ሜትር አጥብበን በጀሶ ሌላ ግድግዳ ቤቱ ውስጥ ሠራን። ቅርሱን አልነካንም ሰዎቹ ጓዳውን እየተጠቀሙበት ነው” ይላል ባለሙያው።
በቅርስነት የተመዘገበ ቤትን እንኳንስ ማፍረስ ይቅርና ያለ ፈቃድ ማደስም ሆነ ሌላ ግንባታ ማካሄድ የማይታሰብ ነገር ነው።
አንድ ሰው የሚኖርበት ቤት በቅርስነት የተመዘገበ ከሆነና ግለሰቡ ቤቱን ለማደስ ገንዘብ ከሌለው መንግሥት ለግለሰቡ የግብር እፎይታ በመስጠት ይደግፋል።
ግድግዳቸው ብቻ በቅርስነት የተመዘገቡ አሉ። እነዚህን ጣሪያቸውን መቀየር ይቻላል። ጣሪያቸው ብቻ በቅርስነት የተመዘገቡትን ደግሞ ጣሪያውን ትቶ ሌላውን ክፍል ማደስ ይቻላል።
በታሪካዊ ሥፍራዎች አካባቢ መንገድ አይሰፋም። የመንገድ ኮብል ስቶን በቅርስነት ከተያዘም አይነሳም። መንገዱ እና ሕንጻዎች እንዳይጎዱ አካባቢው የእግረኛ መንገድ ብቻ ይሆናል።
“ቅርስ ለመጠበቅ ብዙ ርቀት ነው የሚጓዙት” ሲል የኪነ ሕንጻ ባለሙያው ያስረዳል።


“ቅርስ በገንዘብ አይተመንም”
በጀርመን ኑረምበርግ ከተማ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት 90 በመቶ የሚሆኑ ሕንጻዎች በቦምብ ወድመዋል።
ይህንን ታሪካዊ ሥፍራ መልሶ ለመገንባት 20 ዓመታት ገደማ ወስዷል።
“ውድ ነው። ብዙ ሥራ አለው። ግን መልሰው እንደነበር አድርገው ገነቡት። የፈረሱት ተሰንደው ተቀምጠው ነበር” ይላል ክንፈሚካኤል።
በአዲስ አበባ ቅርሶች እና ታሪካዊ ሥፍራች አይፍረሱ ማለት ‘ፀረ ልማት’፣ ‘የድሮ ሥርዓት ናፋቂ’ የሚያስብል መሆኑን ባለሙያው ይናገራል።
“ቅርስ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ነገር አይደለም። ቅርስ ታሪክ ነው። እኛ አገር ነው የፖለቲካ አጀንዳ የሚሆነው” ይላል።
አዲስ አበባን ከሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ጋር ሲያነጻጽራት “የሆነ የተዘበራረቀ ግንባታ የሚታይባት” በማለት ይገልጻል።
አንዳች ወጥነት አለመኖሩ “በቅኝ ካለመገዛት ጋር ይተሳሰራል። ከተማዋን በራሳችን እንደሠራናት ማሳያ ነው” ይላል።
በአዲስ አበባ በቅርስነት ከተመዘገቡት 90 በመቶው የሚገኙት በአራዳ፣ በጉለሌ እና በየካ ክፍለ ከተሞች ነው።
እነዚህ ወደ 300 ገደማ የሚጠጉት ቤቶች እያንዳንዳቸው ወደ 300 ሜትር ስኩዌር ቦታ የያዙ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ እነዚህን ውስን ቦታዎች ጠብቆ ማቆየት ለአዳዲስ ግንባታዎች እንቅፋት እንደማይሆን ክንፈሚካኤል ያስረዳል።
የተጨናነቁ መንደሮችን ለኑሮ ምቹ አድርጎ መገንባት የሚለውን መከራከሪያ በመጥቀስ “መኖሪያ ቦታ መሥራት እና ቅርስ መጠበቅ የተለያዩ ነገሮች ናቸው” ሲል ይተቻል።
“ለአካባቢው ታሪክ አለመቆርቆር፣ ቦታው ለማኅበረሰቡ ያለውን ዋጋ አለመረዳት፣ ስለ ሥነ ሕንጻ ዕውቀት ማጣት እና የእኔነት ስሜት አለመኖር ነው የሚታየው” ይላል ባለሙያው።
ለምሳሌ እንደ ኢየሩሳሌም ሕንጻ እና አራዳ ሕንጻ ያሉት የመጀመሪያዎቹ ‘ሰማይ ጠቀስ’ ሕንጻዎች ከአዲስ አበባ የቀደመ ታሪክ ጋር ትስስር ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሶ “ሰዎች ፊት፣ እጅ፣ እግር እንዳለን ሁሉ የአዲስ አበባም ቅርስ ሲፈርስ እጅ እንደመቁረጥ ነው። ገጽታውን እና ታሪኩን ማጉደል ነው” በማለት ይገልጸዋል።
“ቅርስ ከጠፋ ጠፋ ነው። የከተማን ነፍስ፣ የከተማን ሕይወት ነው የሚያጠፋው። ቅርስ በገንዘብ አይተመንም” የሚለው ባለሙያው ከዚህ በኋላም የቀሩትን ቅርሶች “ማትረፍ አለብን” ሲል ያሳስባል።
[በስተቀኝ በኩል በቅደም ተከተል የሚታዩት ምሥሎች በአዲስ አበባ ከተማ በቅርስነት ከተመዘገቡ መካከል አንዱ የሆነው በኒ (ሩር) መስጊድ እና አራዳ የንግድ ማዕከል በዙርያው የተገነባበት ጥንታዊው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ናቸው።]
ማኅበረሰቡ ስለእነዚህ ታሪካዊ ሥፍራዎች ምን እንደሚያስብ መጠየቅን እና ያሉበትን ሁኔታ በአግባቡ በምሥል እና በተንቀሳቃሽ ምሥል ሰንዶ ማስቀመጥን ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ምናልባት እንደ ጀርመኗ ኑረንበርግ የአዲስ አበባን ቀደምት የከተማ ማዕከል መልሶ መገንባት ይቻል ይሆን? በሚል ለቀረበለት ጥያቄ “ስነዳ ቢደረግ እንደ አንድ የግንባታ ስልት መልሶ መሥራት ይቻላል” ሲል ክንፈሚካኤል መልሷል።



“ሰፈሬ አልመስል አለኝ. . . አልቅስ አልቅስ አለኝ”
የኪነ ሕንጻ ባለሙያው ክንፈሚካኤል ከጀርመን ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ ቀድሞ የሚያውቃቸውን ታሪካዊ ሥፍራዎች በነበሩበት ሲያጣቸው የተሰማውን እንዲህ ይገልጻል።
“. . . አራዳ አካባቢ ነው ተወልጄ ያደግኩት። ረዥም ጊዜ ቆይቼ ስመለስ የማውቀው ነገር የለም። ሳየው የማስታውሰው ነገር የለም። አልቅስ አልቅስ ነው ያለኝ። በታሪክ የሚታወቁ ቤቶች ሲነሱ፣ ያሳለፍነው ልጅነት፣ በየቀኑ ትምህርት ቤት ስንሄድ የነበረው ስሜት፣ የተዋወቅናቸው ሰዎች ትዝታዎች. . . ይጠፋሉ።
“መጻሕፍት የተጻፈላቸው ሰፈሮች ነበሩ። እነዚህን ማጣት ያማል። ወደእዛ አካባቢ አትሂድ አትሂድ ነው የሚለኝ። ሰፈሬም አልመስል አለኝ። እዛ ተወልጄ ያደግኩኝ አልመስል አለኝ። ትልቅ ውድመት ነው። የማይተካ ታሪክ ማጣት ያማል።”
ቅርሶችን ማጣትን ከኪነ ሕንጻ ባሻገር ከታሪክ ክፍተት አንጻር ያየዋ���። አዲስ አበባ ከቀደምት ማንነቷ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደመስበር ነው። በዚህ ውስጥም ታሪክ፣ ባህል እና ማኅበረሰባዊ ዳራ ይሸረሸራሉ። ቀጣዩ ትውልድ ወደኋላ መለስ ብሎ የሚያየው መነሻ ያጣል።
“ኤልኢዲ መብራት እና የብሎኬት ፎቅ ብዙ ከተማ አለ። ያውም በተሻለ እና በተሟላ ሁኔታ። ይሄ አያስደንቅም። ዱባይን ‘ኮፒ ፔስት’ ማድረግ ምን ዋጋ አለው? የሚመጣው ትውልድ እነዚህን ሕንጻዎች አይቶ ምንድን ነው የሚማረው?“ ሲል ክንፈሚካኤል ይጠይቃል።

‘ባይተዋር ከተማ’
ቢቢሲ ያነጋገራት ካዛንችስ አካባቢ ተወልዳ ያደገችው ነዋሪ እንደምትለው፣ በአዲስ አበባ አረንጓዴ ቦታዎች ወይም ሌሎችም ዓይነት የከተማ ሥፍራዎች መገንባታቸውን “ማንም አይጠላም”።
“የእኔ ጥያቄ መናፈሻዎችን ለመገንባት ለምን የምንወዳቸውን ታሪካዊ ሰፈሮች እናጣለን ነው? መንገዱም ይስፋ፤ የሳይክል መንገድም ይገንባ፤ ዛፎችም ይተከሉ፤ እነዚህን ሁሉ ለማድረግ ለምን ታሪካዊ ቦታ ይፈርሳል? የሚለው ነው የማይገባኝ” ትላለች።
የእሷ እና የ��ድሜ እኩዮቿ ትውስታዎች ያሉባቸውን አካባቢዎች ማጣት ያሳዝናታል። “እኛ እየሆነ ባለው ነገር ካዘንን፣ ታዲያ ግንባታው ለማን ነው?” ስትል ትጠይቃለች።
የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያው ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉም የነዋሪዋን አስተያየት ይጋራል።
“የሰው ልጅ በትዝታ ውስጥ የሚኖር ፍጡር ነው። ከትዝታ መላቀቅ አይችልም። ያደግንበት ከተማ፣ ትዝታችን ያለበት ቦታ ፈርሶ የተተካውን አረንጓዴ መናፈሻና ተወዛዋዥ ውሃ እናደንቃለን፤ ግን ውበቱ የደመና ግላጭ ነው። ዕድሜ አይኖረውም። ምክንያቱም ውስጡ ትዝታ ስለሌለ” ሲል ነው ስሜቱን የሚገልጸው።




‘ባይተዋር ከተማ’
ቢቢሲ ያነጋገራት ካዛንችስ አካባቢ ተወልዳ ያደገችው ነዋሪ እንደምትለው፣ በአዲስ አበባ አረንጓዴ ቦታዎች ወይም ሌሎችም ዓይነት የከተማ ሥፍራዎች መገንባታቸውን “ማንም አይጠላም”።
“የእኔ ጥያቄ መናፈሻዎችን ለመገንባት ለምን የምንወዳቸውን ታሪካዊ ሰፈሮች እናጣለን ነው? መንገዱም ይስፋ፤ የሳይክል መንገድም ይገንባ፤ ዛፎችም ይተከሉ፤ እነዚህን ሁሉ ለማድረግ ለምን ታሪካዊ ቦታ ይፈርሳል? የሚለው ነው የማይገባኝ” ትላለች።
የእሷ እና የዕድሜ እኩዮቿ ትውስታዎች ያሉባቸውን አካባቢዎች ማጣት ያሳዝናታል። “እኛ እየሆነ ባለው ነገር ካዘንን፣ ታዲያ ግንባታው ለማን ነው?” ስትል ትጠይቃለች።
የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያው ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉም የነዋሪዋን አስተያየት ይጋራል።
“የሰው ልጅ በትዝታ ውስጥ የሚኖር ፍጡር ነው። ከትዝታ መላቀቅ አይችልም። ያደግንበት ከተማ፣ ትዝታችን ያለበት ቦታ ፈርሶ የተተካውን አረንጓዴ መናፈሻና ተወዛዋዥ ውሃ እናደንቃለን፤ ግን ውበቱ የደመና ግላጭ ነው። ዕድሜ አይኖረውም። ምክንያቱም ውስጡ ትዝታ ስለሌለ” ሲል ነው ስሜቱን የሚገልጸው።
ዮርዳኖስ የታሪካዊ ሥፍራዎችን መፍረስ የሚመለከተው ከማኅበራዊ ግንኙነት መላላት እና ከኢ-መደበኛ የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ አንጻር ነው።
“የከተማ ማንነት አገራችንን ከምንወድበት ምክንያት አንዱ ነው” የሚለው ባለሙያው፣ በግለሰብ እንዲሁም በማኅበረሰብ ደረጃም የጋራ ትውስታ የያዙ ታሪካዊ ሥፍራዎችን ማጣት “የባይተዋርነት ስሜትን” እንደሚፈጥር ይናገራል።
ምናለሽ ተራ ሄዶ ዕቃ መሸመት፣ ብሔራዊ ቴአትር ጀርባ አሮጌ መጻሕፍት መግዛት፣ ጋዜጣ ማንበብ፣ የጀበና ቡና መጠጣት. . . እነዚህን የመሰሉ ትውስታዎች ከከተማዋ ጋር አንዳች ትስስር ይፈጥራሉ።
ዮርዳኖስ ለሐሳቡ ማጠናከሪያ ምሳሌዎችን ይጠቅሳል። ቦሌ ጎዳና ያለው ጃካራንዳ ተነስቶ በዘንባባ ሲተካ፣ ከአየር ንብረቱም ከከተማው ማንነትም ጋር አብሮ ስለማይሄድ ግር ይላል።
የደንበል ቢጫ እና ጥቁር ቀለም፣ የቦሌ ማተሚያ ቤት አካባቢ ቤቶች ቡናማ የጡብ ቀለም፣ የብሔራዊ ቴአትር ሕብረ ቀለማት. . . በአንዴ ግራጫ ሲሆኑ ግራ ይገባል።
“የመገለል ስሜት ይፈጥራል። የግልም የወልም ታሪክ ማጣት ነው” ሲል ያስረዳል።

ማኅበራዊ መስተጋብር ከኢ-መደበኛ ምጣኔ ሃብት ጋር ይዛመዳል።
ፒያሳ አካባቢ የፈረሱት የአደባባይ ገበያዎች ከንግድ ልውውጥ ባሻገር ማኅበራዊ መስተጋብርን እንደሚፈጥሩ ዮርዳኖስ ጠቅሶ “እነዚህ ተነስተው በግብይት ሕንጻ ሲተኩ ግንኙነቱን ያቀዘቅዙታል” ይላል።
በኢ-መደበኛ የንግድ ልውውጥ ውስጥ ያሉት ሎቶሪ አዟሪዎች፣ ሊስትሮዎች፣ በቆሎ ሻጮች. . .ከገበያው ውጪ ይሆናሉ።
በርካታ ወጣት ሠራተኞችን ያቀፉ እና ሰፊ ቤተሰብ የሚተዳደርባቸው እነዚህ ኢ-መደበኛ የንግድ ልውውጦች ወደ መደበኛ ምጣኔ ሃብት ሳይሻገሩ የሥራ ቦታቸውን መነጠቃቸው የሚፈጥረውን ቀውስ የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያው ዮርዳኖስ ያስረዳል።
እነዚህ ኢ-መደበኛ የንግድ ልውውጦች ምርቶችን በውስን መጠን እና ዋጋ በማቅረብ ማኅበረሰብን ይደግፋሉ። የኑሮ ውድነትን ያረግባሉ። የከተማ ድህነትን ለመቋቋም ያግዛሉ። እርስ በእርስ በሥነ ልቦና ለመደጋገፍም ጉልህ ሚና አላቸው።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢ-መደበኛ ሠራተኞች ከንግድ ቦታቸው ሲነሱ ለመደበኛው ምጣኔ ሃብት የሚያደርጉት አስተዋጽኦ እንደሚቀንስ ባለሙያው ይናገራል።
አዳዲስ ግንባታ ሲካሄድ ምን ያህል የከተማዋን ነዋሪዎች ያማከለ ነው? የሚለውን ጥያቄም ያነሳል።
“የኮሪደር ልማት በተሠራባቸው እና ባልተሠራባቸው አካባቢዎች ስንንቀሳቀስ ስሜቱ አንድ አይደለም። በዓሉ ግርማ ‘መንገዱ ቢሰፋ ቢንጣለል አስፋልቱ፣ ሰው ሰው ካልሸተተ ምንድን ነው ውበቱ‘ እንደሚለው። የሰው እንቅስቃሴ ከሌለ ሙት ከተማ ይሆናል።”

ከተማ እና ሰው
ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች እና ነዋሪዎች ታሪካዊ ሥፍራን ከትውስታ፣ ቅርስን ከማንነት ጋር ያስተሳስራሉ።
ነባር ሰፈሮች እንደ ቅርጫ፣ ዕድር እና ዕቁብ ያሉ ማኅበራዊ መስተጋብሮች መነሻም ናቸው። ነዋሪዎች ሲበተኑ እነዚህ ማኅበራዊ መስተጋብሮች ዕድሜ፣ ሃይማኖት፣ ፆታ፣ ባህል፣ ብሔር እና የኑሮ ደረጃን ተሻግረው የሚፈጥሩት ትስስር ይሸረሸራል።
ዮርዳኖስ ይህ በዘላቂነት የሚፈጥረውን ክፍተት የሚያስረዳው ቦንዲንግ ሶሻል ካፒታል (Bonding Social Capital) እና ብሪጂንግ ሶሻል ካፒታል (Bridging Social Capital) በተባሉ የማኅበራዊ ሳይንስ ኅልዮቶች ነው።
ቦንዲንግ ሶሻል ካፒታል፤ በአንድ ዓይነት ቤተሰብ፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ብሔር ወይም የኑሮ ደረጃ መካከል ያለ ጥብቅ የእርስ በእርስ መስተጋብር ነው።
ብሪጂንግ ሶሻል ካፒታል ግን ድንበር ይሻጋራል። ቤተሰብ፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ብሔር፣ የኑሮ ደረጃ ወይም ሌሎች የማንነት መገለጫዎችን አልፎ ያስተሳስራል።
ሰዎች ለዓመታት ከኖሩበት አካባቢ እና ከገነቡት ማኅበራዊ መስተጋብር ሲነቀሉ የማንነት መገለጫዎችን ተሻግሮ የሚፈጠርን ትስስር ያጣሉ።
ትዝታን የያዙ ታሪካዊ ሥፍራዎች ሲጠፉ እና የእኔነት ስሜት ጠፍቶ ባይተዋርነት ሲነግሥ ድልድዩ ይሰበራል።
ለአብሮነት እና ብዝኃ ዴሞክራሲ የሚበጀው ብሪጂንግ ሶሻል ካፒታል ነው የሚለው የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያው፣ ዓመታትን ወደፊት አሻግሮ በመመልከት በነባር መንደሮች ያለው ነዋሪ ሲበተን “ማኅበራዊ መስተጋብሩም ይበተናል። ግለኛነት ይበረታል። እርስ በእርስ መጠላላት ይመጣል” ይላል።
ምሥል- ጌቲ ኢሜጅስ፣ ግምጃ አርክ-ሃይቭ፣ ዙሪክ ኢትኖግራፊክ ሙዚየም፣ ኢትዮጵያን አርክቴክቸር ኮንስትራክሽን ኤንድ ኧርባኒዝም፣ ይምጡበዝና ቤተ መዘክርና የባህል ማዕክል፣ ኢትዮጵያን ሂስትሪ ኤንድ ቱሪዝም፣ ኢዜአ፣ ሪፖርተር፣ አፍሪካንትሬን፣ ናሆም ተክሉ፣ ኤፍሬም ንጉሤ፣ ቴዎዶራ ብርሃን እና አቤል አሰፋ
አርትኦት- አሻግሬ ኃይሉ
ዲዛይን- ማዮዋ አላቢ እና ጆርጅ ዋፉላ
















