የሁለት ዓመቱ ጦርነት ጋዛን ምን ያህል አወደማት?
የሁለት ዓመቱ ጦርነት ጋዛን አውድሟታል።
እስራኤል በጋዛ ላይ ያካሄደችው መጠነ ሰፊ የቦምብ ድብደባ እና የእግረኛ ሠራዊት ጥቃት ከ67 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን መግደሉን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። የግዛቲቱ አጠቃላይ የሚሆነው ሕዝብ ከመኖሪያው እንዲለቅ ተገድዷል፤ የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው በጋዛ ውስጥ ካሉ ቤቶች አብዛኞቹ ወድመዋል ወይም ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ይህ የእስራኤል ጥቃት የተጀመረው ሐማስ ባልታየ ሁኔታ ወደ እስራኤል ዘልቆ በመግባት በፈጸመው ጥቃት 1,200 ሰዎች ከተገደሉ እና 251 ሰዎች ታግተው ወደ ጋዛ ከተወሰዱ በኋላ ነው።
ከአውሮፓውያኑ 2007 አንስቶ ጋዛን የተቆጣጠረው እና እስራኤልን ማጥፋት ዓላማው ያደረገውን የሐማስን ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ አቅምን መደምሰስ በጋዛ ላይ ያካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ ግብ መሆኑን እስራኤል ስትገልጽ ቆይታለች።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዳሉት የመጀመሪያው ዙር የጋዛ የሰላም ዕቅድ እስራኤል እና ሐማስ ጦርነቱን በዘላቂነት ለማስቆም፣ የእስራኤል ታጋቾች እና ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለማስለቀቅ፣ የእስራኤል ኃይሎችን ከጋዛ ለማስወጣት እና ወደ ጋዛ እርዳታ እንዲገባ ያስችላል።
ጋዛ 41 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 10 ኪሎ ሜትር ስፋት ያላት ትንሽዬ ሰርጥ ስትሆን፣ በሦስት በኩል የሚያዋስኗት እስራኤል እና ግብፅ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርጉበት የተዘጋ ድንበር አላት። በስተ ምዕራ�� ደግሞ ከሜዲትራኒያን ባሕር ጋር የምትዋሰን ቢሆንም የባሕር መስመሩ በእስራኤል ቁጥጥር የተዘጋ ነው። ጋዛ በውስጧ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይኖርባታል።
ከ90% በላይ የሚሆኑት የጋዛ ሕንጻዎች ወድመዋል ወይም ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሎ ይገመታል፤ የጤና አገልግሎት፣ የውሃ አቅርቦት፣ የንጽህና እና የጽዳት ሥርዓቶች በጦርነቱ ወድመዋል፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያዎች እንዳሉት ጋዛ ከተማ ውስጥ ረሃብ ተከስቷል። የተባበሩት መንግሥታት አጣሪ ኮሚሽን እስራኤል ጋዛ ውስጥ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ፈጽማለች ያለ ሲሆን፣ እስራኤል ግን የኮሚሽኑን ሪፖርት “የተዛባ እና ሐሰተኛ” በማለት ውድቅ አድርጋዋለች። ይህ ሥዕላዊ መግለጫ እንሚያሳየው አብዛኞቹ የጋዛ ክፍሎች ለሰዎች መኖሪያነት ከመሆን ውጪ ሆነዋል።
ውድመቱ ምን ያህል ሰፊ ነው?
የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሪያ ላይ ትኩረት አድርጎ የነበረው የሐማስ ተዋጊዎች ከሰላማዊ ሰዎች መካከል ተደብቀውበታል በምትለው በሰሜናዊ ጋዛ ላይ ነበረ። ሐማስ ግን ይህንን ያስተባብላል።
በጦርነቱ ወቅት በእስራኤል፣ በዩናይትድ ኪንግደም እና በበርካታ ምዕራባውያን አገራት በሽብር ቡድንነት የተፈረጀው ሐማስ እና ደጋፊዎቹ የሆኑ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ከእስራኤል ኃይሎች ጋር ከባድ የእግረኛ ውጊያ አካሂደዋል። በተለይ በጦርነቱ የመጀመሪያ ወራት በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ተኩሰዋል። በጦርነቱ የጋዛ ሁሉም ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ተቋማት ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል። ሆስፒታል እና መስጂዶች ሲፈርሱ፣ የእርሻ ልማት ቦታዎች በ���ስራኤል ወታደሮች ከባድ ተሽከርካሪዎች እና ታንኮች እንዲወድሙ ተደርገዋል። ሐማስ ሆስፒታልን የመሳሰሉ ሰላማዊ ተቋማትን ለወታደራዊ ዓላማው ይጠቀምባቸዋል በማለት እስራኤል የምትከስስ ሲሆን፣ ሐማስ ግን ይህንን ያስተባብላል።
ከጦርነቱ በፊት ከ2.1 ሚሊዮኑ የጋዛ ሕዝብ አብዛኛው በራፋህ እና ኻን ዩኒስ በደቡብ፣ በዴር አል-ባላህ በማዕከላዊ እና ጋዛ ከተማ በተባሉት በአራት ዋነኛ ከተሞች ውስጥ ይኖሩ ነበረ። ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ በነበሩት 10 ቀናት ውስጥ እስራኤል ባካሄደችው ጥቃት ወደ ግማሽ የሚጠጋው ነዋሪ መኖሪያውን ለቅቆ እንዲሄድ እንዳስገደደው የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ስደተኞች ድርጅት አመልክቷል።
ጦርነቱ ከተጀመረ ከ15 ወራት በኋላ የተኩስ አቁም ይፋ በሆነበት ወቅት ወደ 1.9 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች በጋዛ ውስጥ የተፈናቀሉ ሲሆን፣ አሁንም ድረስ ወደ ቤታቸው መመለስ አልቻሉም።
እስራኤል የወታደራዊ ዘመቻዋን ትኩረት ስትቀይር ነዋሪዎች ብዙ ጊዜ ወደ ተለያዩ ቦታዎች ተዛውረዋል፣ በመጀመሪያ በሰሜን የሚገኙ ሰዎች ከዋዲ ጋዛ ወንዝ በስተደቡብ እንዲሄዱ ስታዝዝ፣ ይህም ጋዛ ሰርጥን በግምት በግማሽ ይከፍላል፣ በኋላ ላይም ነዋሪዎች በደቡብ በተከታታይ “በመውጫ ቀጣናዎች” በኩል ለቅቀው እንዲወጡ ተደርገዋል።
የእስራኤል ጦር ሠራዊት በአካባቢው ዘመቻ ከማካሄዱ በፊት ነዋሪዎች ለቅቀው እንዲወጡ የሚያስጠነቅቁ በራሪ ወረቀቶችን ይበትናል።ነገር ግን ከሁሉም የእስራኤል ጥቃቶች በፊት ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያዎች አይሰጡም።
ክልከላ የተጣለባቸው አካባቢዎች ጨመሩ
እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱ አንዲያበቃ ካደረገች በኋላ ተጨማሪ የጋዛ አካባቢዎችን በመለየት መንቀሳቀስ የማይቻልባቸው ቀጠናዎች - በማድረግ ክልከላ አንዲጣለባቸው አድርጋለች ወይም አካባቢዎቹን በመለየት ነዋሪዎች ሙሉ ለሙሉ ለቅቀው እንዲወጡ የሚያደርግ ትዕዛዝ, ደርሷቸዋል። በመጀመሪያ ላይ አካባቢዎችን ለቅቆ የመውጣት ትዕዛዝ ሁለት ቦታዎችን የሚሸፍን ነበረ፤ እነሱም ሰሜን ጋዛ እና ኻን ዩኒስ አስተዳደሮች ውስጥ በድንበር አካባቢዎች ላይ የተ��ለ "የተከለከሉ" ቦታዎችን የሚጨምር ነው። የእርዳታ ድርጅቶች "በተከለከሉ" ቦታዎች ወስጥ ለመንቀሳቀስ ከእስራኤል ባለሥልጣናት ጋር መቀናጀት ይኖርባቸዋል። ሐማስ የእርዳታ አቀርቦቶችን እየተቆጣጠረ ነው በማለት እስራኤል ወደ ጋዛ የሚገባውን ሰብአዊ እርዳታ ከመጋቢት ወር ጀምራ አግዳለች። የእርዳታ ድርጅቶች በቂ አይደለም ቢሉም ውስን የእርዳታ አቅርቦት ብቻ ነበር የፈቀደችው።
በሚያዝያ መጀመሪያ ላይ በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፉ ሁሉም ዳቦ ቤቶች ሲዘጉ፣ የአትክልት አቅርቦት በጣም ውስን ሆነ እንዲሁም ሆስፒታሎች የሚያቀርቧቸው መድኃኒት በጣም በመቀነሱ በኮታ ማዳረስ ጀመሩ። አክሽን ኤይድ የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በጋዛ ውስጥ “የረሃብ እና የውሃ ጥም” ቀውስ እያንዣበበ ነው ሲል አስጠንቅቆ ነበረ። ጦርነቱ ቢያበቃ እንኳን እስራኤል ዜጎቿን ለመከላከል የሚያስችል ጋዛ ውስጥ የደኅንነት ቀጣና እንዲሚቋቋም የመከላከያ ሚኒስቴሯ በሚያዝያ 16 አስታውቀዋል። ሐማስ ግን ዘላዊ የተኩስ አቁም ከተደረሰ በኋላ የእስራኤል ኃይሎች ከጋዛ ለቅቀው መውጣት አለባቸው ሲል ጠይቋል። በወቅቱ 70 በመቶ የሚደርሰው የጋዛ ክፍል የእስራኤል ዕገዳ - የተጣለባቸው ሲሆን፣ ይህም አብዛኞቹን በሰሜን የሚገኙትን ሰሜን ጋዛ እና ጋዛ ከተማን ጨምሮ በስተደቡብ ደግሞ ሙሉውን የራፋህ አካባቢ እንደሚያካትት የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያመለክታል።
በግንቦት ወር እስራኤል ‘የጌዲዮን ሰረገላ’ የሚል ስያሜ የሰጠችውን የእግረኛ ሠራዊት ዘመቻ ማካሄድ ጀመረች። ይህ ጥቃት ዓላማ ያደረገው ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሟቾች የሚገኙባቸውን ቀሪ 48 ታጋቾችን ማስለቀቅ እና የፍልስጤሙን ታጣቂ ቡድን የሐማስን “ሽንፈት ማጠናቀቅ” መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ተናግረው ነበር።
ከዚያ ጊዜ አንስቶ አካባቢው በእስራኤል ለቅቆ የመውጣት ትዕዛዝ እና ሌሎች ዕገዳዎች ስር ቆይቷል። ይህም ከጋዛ አጠቃላይ ይዞታን 82% የሚሸፍን መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።
የዘመቻው የመጀመሪያ ምዕራፍ ትኩረት ያደረገው በራፋህ፣ በኻን ዩኒስ እና በሰሜናዊ ጋዛ ውስጥ በሚገኙ ዒላማዎች ላይ ሲሆን፣ በነሐሴ ወር ላይ እስራኤል የሐማስ “ጠንካራ ይዞታ” የምትላትን ጋዛን ሙሉ በመውረር ለመቆጣጠር ያላትን ዕቅድ ይፋ አደረገች።
ጋዛ ከተማ ከጦርነቱ በፊት 775 ሺህ ሕዝብ የሚኖርባት ሕዝብ በተጨናነቀ ሁኔታ የሚገኝባት የጋዛ ሰርጥ ክፍል ነበረች።
እዚያ የነበሩ ሰዎች የአየር ጥቃት ወደ ቀጠለበት እና የተባበሩት መንግሥታት አካባቢው የተጨናነቀ እና ለደኅንነት አስተማማኝ አይደለም ወዳለው እንዲሁም እስራኤል 'ሰብአዊ ቀጠና' ብላ ወደ ሰየመችው በሰርጡ ደቡብ ምዕራብ ወደሚገኘው አል-ማዋሲ እንዲሄዱ ታዝዘዋል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ለቀው በወጡባት ጋዛ ከተማ ረሃብ መከሰቱን በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው አካል ነሐሴ 2025 ላይ አረጋግጧል። ቢሆንም ግን የጤና እና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች በፈራረሱበት ሁኔታ ሌሎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች አሁንም በአስከፊ ሰብአዊ ችግር ውስጥ እዚያው ይገኛሉ።
በጥቅምት ወር የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለ 20 ነጥብ የጋዛ የሰላም ዕቅዳቸውን ካስተዋወቁ በኋላ በድርድሩ ውጤት የታየ ሲሆን፣ እስራኤል እና ሐማስ የመጀመሪያ ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ በመድረስ ታጋቾችን በመልቀቅ ጦርነቱ እንዲያበቃ መንገድ ከፍቷል። የእስራኤል ኃይሎች ለቅቀው በመውጣት ወደ ጋዛ ሰርጥ ዳርቻዎች ለመሄድ የተስማሙ ሲሆን፣ ይህም የጋዛ ሰርጥን 53% በቁጥጥራቸው ስር እንዲሆን ያደርጋል።
ጥቅምት 13/2025 በሐማስ ተይዘው የነበሩ 20 ታጋቾች ተለቀቁ። በምላሹ እስራኤል ውስጥ የታሰሩ ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን እስረኞች ተፈትተዋል። በስምምነቱ መሠረት ለሕዝቡ የሚያስፈልገውን አስቸኳይ እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ጋዛ እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል።
የመረጃ እና የምሥል ምንጮች
የውድመት ትንተናው ኮፐርኒከስ ሴንቲኔል-1 መረጃ በኮሪይ ሼር ከከኒ ግራጅዌት ሴንተር እና ጃሞን ቫን ደን ሆክ ከኦሪገን ስቴት ዩኒቨርስቲ። የካርታ መረጃ ከኦፕንስትሪትማፕ። የሕዝብ መፈናቀል መረጃ ከተባበሩት መንግሥታት። ለእንቅስቃሴ የተከለከሉ እና የተፈናቃይ ቀጣናዎች መረጃ ከኦቻ። የሳተላይት ምሥሎች ከፕላኔት ላብ ፒኤልሲ፣ ሌሎች ምሥሎች ከጌቲ እና ከሮይተርስ።