'ብረት ለበሱ ጭራቅ'፡ በጋዛ ነዋሪዎች ላይ ሽብርን ያነገሠው ያልታወቀው የእስራኤል ጦር መሳሪያ

በፍንዳታ የተጎዳ ሕንጻ እና መኪኖች የሚታዩበት በፍርስራሽ የተሸፈነው የጋዛ ከተማ ሪማል አካባቢ መንገድ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በፍርስራሽ የተሸፈነው የጋዛ ከተማ ሪማል አካባቢ

"ወደ ተንቀሳቃሽ ግዙፍ ቦምብነት የተቀየረ አሮጌ ወታደራዊ መኪናን ከመኖሪያ ሰፈር መካከል ላይ አምጥተው አጥምደው ሁሉንም ቤቶች እንዲያወድም ከርቀት ሆነው አፈነዱት።በአቅራቢያው የነበሩትን በሙሉ በሰከንዶች ውስጥ ዶግ አመድ አደረጋቸው። የፍንዳታው ኃይል የአየር ድብደባዎቸ ከሚያደረሱት ጉዳት በከፋ ሁኔታ አውዳሚ ነው።"

ይህ የጋዛ ነዋሪ የሆነው አላም አል-ጉል ነዋሪዎች "ስውሩ ሮቦት" ማለት ስለሚገልጹት ቦምብ አደገኝነት የገለጸው ነው።

ነዋሪዎቹ ይህንን የጦር መሳሪያ ባለፉባቸው ጦርነቶች ውስጥ ሁሉ አይተውት የማያውቁት እና አሁን በተደጋጋሚ ጥቃት የሚፈጸምበት መሆኑን ይናገራሉ።

"እነዚህ ለጥቃት ጥቅም ላይ የሚውሉት ሮቦቶች አሮጌ አገልግሎት የማይሰጡ ታንኮች ወይም ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ" ይላል ጉል።

"እነዚህን ተሽከርካሪዎች ወስደው በፈንጂዎች ከሞሏቸው በኋላ ከርቀት እየተቆጣጠሩ ወደ ጋዛ ከተማ ጎዳናዎች ያሰማሯቸዋል" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

"ዒላማ ከተደረገው ስፍራ ላይ ከደረሱ ከደቂቃዎች በኋላ ከባድ ፍንዳታ ይከሰታል።በሰከንዶች ውስጥ ሰማዩ እንደ ደም ይቀላል" ብሏል።

"በፍንዳታው አቅራቢያ ሰዎች ከነበሩ ምናቸውም አይገኙም። የአንድም ሰው አስከሬን ባለበት አይገኝም፤ ተበጣጥሶ ነው የሚወድቀው" ይላል አልፎ አልፎ በጋዛ ጦረነት የተገደሉ ሰዎችን አስከሬን ለማግኘት በሚደረገው ፍለጋ ውስጥ የሚሳተፈው ጉል።

ጨምሮም ለእስራኤል ኃይሎች መንገድ "መጥረግ በሚመስል ሁኔታ" በሚፈጸመው በዚህ ከባድ ጥቃት ለፍንዳታው እንዳላቸው ቅርበት ሕንጻዎች ሙሉ ለሙሉ ይወድማሉ ወይም ይቦደሳሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የውድመቱን ውጤት የተመለከተው ጉል ለቢቢሲ እንደተናገረው "ቤተሰቦች ሙሉ ለሙሉ አልቀዋል።"

ቢቢሲ እንዲህ ያለው ጥቃት በ300 እና በ500 ስኩዌር ሜትር ዙሪያ የሚያደርሰው ውድመት ምን ያህል እንደሆነ ለመረዳት ሦስት ነዋሪዎችን አነጋግሯል።

"ሮቦቶቹ ሲፈነዱ ቤተሰቦች ቤታቸው ውስጥ ነበሩ።ቤቶቻቸውም በላይቸው ላይ ፈርሰዋል።አል-ዛይቱን፣ ሼክ ራድዋን እና ጃባሊያን በመሳሰሉት የጋዛ ከተማ አካባቢዎች እስካሁን ድረስ አንዳንዶች በርስራሽ ውስጥ እንደተቀበሩ ናቸው።"

በሐማስ የሚመራው የጋዛ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ጽህፈት ቤት እንዳለው ከነሐሴ መጀመሪያ አንስቶ የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ ውስጥ እያካሄደ ባለው የእግረኛ ሠራዊት ዘመቻ 1,100 ሰዎችን ገድሎ 6,008 ሰዎች አቁስሏል።

የጋዛ ባለሥልጣናት ባወጡት መግለጫ እየተካሄደ ባለው ወታደራዊ ዘመቻ ከ70 በላይ በጦር ጄቶች የተፈጸሙ ቀጥተኛ ከባድ የአየር ድብደባዎችን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን እንዲፈናቀሉ ያደረጉ በሮቦቶች የሚመሩ ከ100 በላይ ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ላይ የደረሱ ከባድ ፍንዳታዎች ተፈጽመዋል።

የእስራኤል ሠራዊት በጋዛ ከተማ ላይ የተጠናከረ ጥቃት እያካሄደ ሲሆን፣ የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በጋዛ ውስጥ የሚፈጸሙት ፍንዳታዎች ከከባድነታቸው የተነሳ 70 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ቴል አቪቭ ድረስ ይሰማል።

ቢቢሲ አረብኛ የእስራኤል ሠራዊት በጋዛ ውስጥ እንደዚህ ከባድ ፍንዳታ የሚያስከትሉትን መሳሪያዎች በሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ አካባቢዎች እየተጠቀመ ነው ለሚለው ክስ የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ የሆኑት ኮሎኔል አቪቻይ አድሬ ምላሽን ጠይቋል።

ቃል አቀባዩ በሰጡት ምላሽ "ዘመቻዎች የሚካሄዱበትን መንገዶች አንገልጽም፤ ነገር ግን ዓላማችንን ለማሳካት፣ የሐማስ አሸባሪዎችን ለመደምሰስ እና የእስራኤል ወታደሮችን እና ሲቪሎችን ለመጠበቅ የተለያዩ አንዳንዶቹም አዲስ ፈጠራዎች እና ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋሉ አማራጮችን እንጠቀማለን" ብለዋል።

አውዳሚው ፍንዳታ

ሌላኛው የጋዛ ከተማ ነዋሪ ኒዳን ፋውዚ ሮቦቶች የሚባሉት "በተለይ በሴቶች እና በሕጻናት ላይ ሽብር የፈጠሩ እና ሰዎች ከመኖሪያቸው እንዲሸሹ እያስገደዱ ነው" በማለት ጋዛ ለእስራኤል ጦር መሳሪያዎች የመሞከሪያ ቦታ ስለመሆኗ ጥያቄ ሰንዝሯል።

ለቢቢሲ እንደተናገረው ቀደም ባለ ወታደራዊ ዘመቻ ወቅት የእስራኤል ሠራዊት እነዚህ የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ሲያውል ተመልክቷል።

"ዕኩለ ሌሊት በወታደራዊ ተሽከርካሪ የሚጎተት ግዙፍ የአራት ማዕዘን ቅርጽ ያለውን 'ሮቦት' አየሁ። ከግድግዳ ጋር አስጠግተው አቁመውት በመኪናቸው ሄዱ። እኔም ቤተሰቦቼ ቶሎ ቤቱን ለቅቀው እንዲወጡ ጮህኩ። ቤቱን ለቅቀን ከወጣን ከደቂቃዎች በኋላ በሕይወቴ ሰምቼው የማላውቀው ዓይነት ፍንዳታ ከተከሰተ።"

ፋውዚ እንዳለው ፍንዳታው እጅግ በጣም አውዳሚ ነበር።

"አል-ዛይቱን ውስጥ ብጥስጥስ ያሉ የሰው አካላትን አይቻለሁ።ከፍንዳታው ቦታ 100 ሜትር ርቀት ላይ የነበሩ ሰዎች ሳይቀሩ በተፈጠረው ግፊት እና በመታፈን ሞተዋል። ይህ መሳሪያ በዚህ ጦርነት ውስጥ ካየነው ሁሉ በጣሙን የሚያስፈራ ነው።"

ከመፈንዳቱ በፊት የሚሸሹት ነዋሪዎች "ከሚፈነዳው ብረት ለበስ ጭራቅ" ለማምለጥ "ብቸኛው የሚያስቡት ነገር ለቅቆ መውጣትን ነው" ብሏል ፋውዚ።

በከባድ ሁኔታ የወደመ ሕንጻ ውስጥ አንድ አዋቂ እና ሕጻናት ከታች እና ከላይ ባሉ የፎቁ ክፍል ውስጥ ሆነው በዙሪያቸው ፍርስራሽ ይታያል

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የወታደራዊ ፍልሚያ ጉዳትን መቀነስ

በኳታር የመከላከያ ጥናቶች አካዳሚ የደኅንነት ባለሙያ የሆኑት እና ቀደም ሲል በጋዛ ሰርጥ ውስጥ የሠሩት ፕሮፌሰር ሃኒ አል-ባሱስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የእስራኤል ሠራዊት እነዚህን በርቀት መቆጣጠሪያ የሚመሩ የተሽከርካሪ ፈንጂዎችን የመኖሪያ አካባቢዎችን፣ ዋሻዎችን እና ትላልቅ ሕንጻዎችን ካለቀጥተኛ ፍልሚያ ለማውደም የሚጠቀመው "ወታደራዊ ውጊያን የሚያስከፍለውን ዋጋ እና በእስራኤላውያን ላይ የሚደርስን ጉዳት ለመቀነስ ነው።"

ጨምረውም ተሽከርካሪዎቹ ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ፈንጂዎች መሸከም የሚችሉ እና በዋሻዎች ውስጥ እና በመኖሪያ ሕንጻዎች ላይ ጥቅም ላይ ውለው ሰፊ ፍንዳታዎችን ፈጥረዋል።

ካሬም አል-ጋራበሊ የተባሉት ሌላ የጋዛ ነዋሪ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ እስራኤል በጋዛ ከተማ ምሥራቃዊ ክፍል ውስጥ በሚገኝ ባለብዙ ፎቅ የመኖሪያ ሕንጻ ላይ ጥቃት ስትፈጽም መሳሪያው ጥቅም ላይ ሲውል መመልከ��ቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"የነበርኩት ከፍንዳታው 400 ሜትር ያህል ርቀት ላይ ነበረ፤ ነገር ግን ሁሉም ፍንጣሪዎች እና አለቶች ቤታችን ደርሷል" ሲሉ ክስተቱን ያስታውሳሉ።

በፍንዳታው ወቅት "የተፈጠረው ብርሃን ዓይንን የሚያጠፋ ያህል የነበረ ሲሆን፣ ሰማዩ ቀይ ሆኖ የሚያስፈራ ነበር።"

የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙኒራ አል-ቡርሽ እንደሚሉት አሁን የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ ውስጥ እነዚህን ፈንጂ 'ሮቦቶች' ስልት በየዕለቱ በመጠቀም "በሲቪሎች ላይ ቀጥተኛ ስጋትን በመደቀን እና ሰብዓዊ ሁኔታውን አስከፊ አድርጎታል።"

እያንዳንዱ 'ሮቦት' እስከ ሰባት ቶን ወይም ሰባት ሺህ ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ፈንጂዎችን ይሸከማል የሚሉት ዶክተሩ፣ በየዕለቱም ከሰባት እስከ 10 የሚደርሱ ፍዳታዎች ይፈጸማሉ። በዚህም ሳቢያ የብዙኃን መፈናቀል ተፈጥሮ በምዕራባዊ ጋዛ ከፍተኛ ሕዝብ እንዲከማች ምክንያት ሆኗል።

እነዚህን ሮቦቶች መጠቀሙ ከቀጠለ በተለይ ወደ ጋዛ መግባት በተከለከለበት ሁኔታ ውስጥ የነፍስ ማዳን እና የእርዳታ አቅርቦት ባለመኖሩ "እልቂት እና በቤቶች መሠረተ ልማት ላይ አጠቃላይ ውድመትን" ሊያስከትል ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

*በአሁኑ ወቅት በጋዛ ውስጥ ባለው ሁኔታ ምክንያት በዚህ ዘገባ የተጠቀሱትን የሚፈነዱ ተሽከርካሪዎችን ወይም ከፍንዳታ በኋላ የደረሰውን ጉዳት የሚያሳዩ ምሥሎች ማግኘት አስቸጋሪ ነው። በዚህ ዘገባ ውስጥ የተካተቱት ፎቶግራፎች እስራኤል በጋዛ ከተማ በቅርቡ ከፈጸመችው ጥቃት በኋላ የተነሱ ናቸው።