በስልካችን ጥርት ያሉ የተፈጥሮ ክስተት ፎቶዎችን እንዴት ማንሳት እንችላለን?

በግራ በኩል በጥሩ ሁኔታ የተነሳ የጨረቃ ምስል፣ በስተቀኝ የተበላሸ የጨረቃ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Sheikh Saif/BBC

ዕድለኛ ከሆኑ እና ጥርት ያለ ሰማይ የሚያጋጥምዎ ከሆነ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ ትልቅ፣ ብሩህ ጨረቃ ከሙሉ ውበቷ እና ግዝፈቷ ጋር በምሽቱ ሰማይ ላይ ደምቃ ትታያለች።

ይህንንም በዐይኖችዎ የሚመለከቱት ይሆናል።

ችግር የሚፈጠረው ይህንን ውበት በዐይንዎ እንዳዩት በስልክዎ ለማስቀረት ሲሞክሩ ነው።

ይህ ግን በዋናነት ፎቶ ማንሳት ላይ የሚሳካልዎት ስላልሆነ የመጣ አይደለም። ጨረቃን በስማርት ስልካችን ፎቶ ማንሳት ከባድ የሚሆንባቸው ምክንያቶች አሉ።

ነገር ግን ውጤቱን ለማሻሻል የሚረዱ ጥቂት ነጥቦችን እንካችሁ።

ደብዛዛ፤ ብሎብ ኢፌክት

አብዛኞቻችን በምሽት ከጨረቃ ጋር የሚገጥመን የመጀመሪያው ጉዳይ ከመጠን በላይ መጋለጥ ነው።

በአውስትራሊያ የሞናሽ ዩኒቨርሲቲ የአስትሮኖሚ ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ማይክል ብራውን "ብዙውን ጊዜ ትንሽ ጨረቃን በጣም ጨለማ በሆነ ዳራ ውስጥ እናያለን። ስለዚህ ስልካችን በምሽት ፎቶግራፍ ለማንሳት ይሞክራል።

ነገር ግን ፎቶግራፍ እያነሳን ያለነው የፀሐይ ብርሃን ያገኘውን የጨረቃን ጎን ነው ፣ ስለሆነም እዚያ ልክ ቀን እንደማለት ነው።

ያም ብሩህ፣ ከመጠን በላይ ለብርሃን የተጋለጠ ይሆናል። በዚህ ዙሪያ ቀላሉ እርምጃ ጨረቃን ከመጨለሙ በፊት ማንሳት ነው።

በግራ በጨለማ የተነሳ የጨረቃ ምስል፤ በስተቀኝ በቀን ብርሃን የተነሳ የጨረቃ ምስል

ነገር ግን ጨረቃ ሙሉ በምትሆንበት ወቅት ከፀሐይ በተቃራኒው ከምድር ጎን ትገኛለች። ስለዚህ ሙሉ ጨረቃ ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት አልፎ አልፎ ትታያለች።

ግዙፍ ጨረቃን ፎቶ ለማንሳት ከፈለጉ ልክ ጀምበር ከጠለቀች በኋላ መሞከር የተሻለ ይሆናል።

እንደ ናሳ ሉናር ፎቶግራፊ መመሪያ መሠረት ድንግዝግዝ ሲል ፎቶ ማንሳት በጣም ተመራጭ ነው። ምክንያቱም ስልክዎ በጨረቃ እና በሰማይ መካከል ያለውን ንፅፅር ብዙ ማስተናገድ አይገደደም። ከፊት ለፊት ያሉትም ምሥሎች በጉልህ ይታያሉ።

እንደ አማራጭ፣ ጨረቃን በምሽት ለማንሳት የሚፈልጉ ከሆነ ካሜራው ለብርሃን ያለውን ተጋላጭነት በተለያዩ መንገዶች መቀነስ ይቻላል።

ብራውን በምሽት ፎቶ ግራፍ ለማንሳት የሚረዱ መተግበሪያዎች በመኖራቸው የጨረቃን ምሥል በትክክለኛው የብርሃን ሥርጭት ማንሳት ይችላሉ ሲል ይመክራል።

ወይም ይህንን በተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ 'አውቶ ኤክስፖዠር' የሚለውን በመቆለፍ እና ዝቅ በማድረግ ማንሳት ይቻላል።

ጨረቃ ፎቶ ላይ ትንሽ ሆና የምትታየው ለምንድን ነው?

ጨረቃን በዐይናችን ስንመለከታት ግዙፍ ብትመስልም በምናነሳው ፎቶ ላይ ግን በጣም ትንሽ ትሆናለች።

ይህም በዐይናችን ስናይ በአድማሱ ላይ ግዙፍ መስላ እንድትታየን የሚያደርገው 'ሙን ኢሉዥን' የሚባለው ክስተት ሊሆን ይችላል።

ማንም ይህ ለምን እንደሆነ በትክክል መልስ የለውም። ነገር ግን አእምሯችን በአድማሱ ላይ ጨረቃ ምን ያህል ሩቅ ልትሆን ትችላለች? ሲል የሚያስቀምጠው የርቀት ግምት ስሌት ነው።

ምናልባትም ዛፎች እና ሕንጻዎች ጨረቃን በንጽጽር ግዙፍ አስመስለዋት ሊሆን ይችላል።

ብራውን የስልካችን ካሜራ ስሪትንም ከግምት ማስገባት አለብን ይላል።

ሰልፊዎችን ለማንሳት የተሠራው የስልክ ካሜራ በርቀት የሚገኙ ነገሮችን በጥራት ምሥላቸውን ለማስቀረት አዳጋች ይሆናበታል።

ሰማይ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ 180 ዲግሪ እንደሆነ የምናስብ ከሆነ ጨረቃ በዚህ ውስጥ 0.5 ዲግሪ ብቻ ናት።

"አንዳንድ የስልክ ካሜራዎች በአንድ ፎቶ 90 ዲግሪ ማዳረስ የሚችሉበቸው ስሪቶች አሏቸው" በማለት አስትሮኖመሩ ይገልጻል።

"ጨረቃ የሙሉ ምስሉ ኢምንት ክፍል ብቻ የያዘች ናት. . . ምናልባት በአጠቃላይ 50 ፒክስል ትሆናለች።"

የጨረቃ ምስል ከሕንጻው ጋር በንጽጽር ሲታይ ግዙፍ ይመስላል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አቅርበን ስናነሳ እንጠንቀቅ

አቅርቦ ማንሳት የሚመከር ነው? በጭራሽ።

በርካታ የስማርት ስልኮች በራሳቸው አቅርበው ያነሳሉ። እኛ ለማቅረብ በሞከርን ቁጥር ምሥሉን እየቆረጥን እና እንዲደበዝዝ እያደረግን ነው። ስለዚህ ይህ እምብዛም አይረዳም።

ነገር ግን አንዳንድ ስልኮች የተለየ አቅርቦ ማንሻ አላቸው። ይህም የካሜራውን አጉልቶ የማንሳት አቅም እንደ ኮማፓክት ካሜራ ወይንም ዲኤስኤልአር (DSLR) እንዲሆን ይረዳዋል።

ይህ ካለዎት አቅርበው ለማንሳት ትክክለኛው መሣሪያ ነው።

አለበለዚያ ግን የስልክዎ ካሜራ ላይ የሚገጠሙ ሌንሶች አሉ። ወይንም ቴሌስኮፕ ካለዎት የስልክዎን ካሜራ የቴሌስኮፑ መመልከቻ ላይ ማስጠጋት እና ማንሳት ይችላሉ።

ርካሽ ቴሌስኮፕ ጥሩ የጨረቃ ምሥልን ማስቀረት ያስችልዎታል ይላል ብራውን።

አቅርበው ለማንሳት በሚሞክሩበት ወቅት ትራይፖድ (ማቆሚያ) መጠቀም ወይም ካሜራዎን በማይንቀሳቀስ ነገር ላይ አስቀምጦ ማንሳት ይመከራል።

ምሥሉን ለማንሳት ካሜራዎን በሚጫኑበት ወቅት የሚፈጠር አንቅስቃሴ ለማስወገድ 'ታይመር' መጠቀም ወይም 'ላይቭ ቪው ሞድ' ላይ ማድረግም ተመራጭ ነው።

ከሐውልት ባሻገር የምትታይ ጨረቃ

የፎቶው ባለመብት, Nasa/Bill Ingalls

ፈጠራዎን ይጠቀሙ

ኦፕቲካል ዙም ከሌለዎት እና ትንሽ ጨረቃ ብቻ የምትታይዎት ከሆነ ምሥሎቹ አስቀያሚ እንዳይመስሉ ማድረግ የሚችሉበት ሌላ መንገድ አለ።

ብራውን "በጣም አስደሳች ከሆነ (በፊት ለፊት) ካለው ነገር ጋር ማጣመር ትችላላችሁ" ይላል።

የናሳ ከፍተኛ ፎቶግራፍ አንሺ ቢል ኢንጋልስ ጨረቃን ብቻዋን ማንሳትን አይመክርም።

በናሳ ድረገጽ ላይ በጻፈው መጣጥፍ ላይ "ሁሉም ሰው ያንን ምሥል ያገኛል" ብሏል።

"ይልቁንስ ምሥሉን እንዴት ፈጠራ ማከል እንደሚቻልበት አስቡበት...ለፎቶዎ የቦታ ስሜት ለመስጠት ይሞክሩ።"

እውነታው ግን ሁላችንም ምርጥ የፎቶግራፍ ባለሙያ እንደሚያነሳው ምሥል ማስቀረት አለመቻላችንን አንክድም።

ብራውን አንዳንድ ስልኮች የሰው ሠራሽ አስተውሎት በመጠቀም ምሥሎችን ለማስዋብ መሞከራቸውን ይገልጻል።

ይህ ግን በስልክ አነስተኛ ካሜራ ሊነሳ የሚችለው ነገር ከእውነታው እንዲርቅ ያደርጋል።

እውነተኛ ፎቶ እንዲሆን ግን ደግሞ ውብ ጨረቃን ለማንሳት የሚያስችል የቴክኖሎጂ አቅም ያለው ካሜራ ከሌለዎት የስልከዎ ጥንካሬ ምን እንደሆነ በመለየት እርሱን ይጠቀሙ።

ብራውን "ቀጥ ብለው የቆሙ የማይንቀሳቀሱ ነገሮችን መለየት ጥሩ ነው" አክሎም "ምናልባት ጥርት ያለ የዕይታ መስክ፣ ጥሩ ፎቶ ለማንሳት የሚያስችላችሁን ሌሎች ነገሮች አስቡ።"

ሚልክዌይ፣ አውሮራ ወይም ብሩህ ኮሜቶች ጥሩ ዒላማ ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ይመክራሉ።