የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ላይ ከሰባት እስከ ስምንት ብር ገደማ የሚደርስ ጭማሪ ተደረገ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የነዳጅ ጭማሪ ይፋ አደረገ። በአዲሱ የዋጋ ጭማሪ መሠረት በቤንዚን ላይ የሰባት ብር ገደማ ጭማሪ የተደረገ ሲሆን ኬሮሲን ደግሞ ዋጋው በስምንት ብር ገደማ ጨምሯል።
ንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ዛሬ ረቡዕ ታሕሳስ 1/2018 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው የዋጋ ማሻሻያ 2018 ዓ.ም. ከገባ ከአውሮፕላን ውጪ ባሉት የነዳጅ ዓይነቶች ላይ የተደረገ የመጀመሪያው ጭማሪ ነው።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መስከረም ወር ላይ የአውሮፕላን ነዳጅ ችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በአዲስ አበባ ከተማ 210.10 ብር እንዲሆን ሲወስን ሌሎች የነዳጅ ዓይነቶች ዋጋቸው ባለበት እንዲቀጥል ወስኖ ነበር።
መንግሥት በቤንዚን፣ ኬሮሲን እና ነጭ ናፍጣ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ጭማሪ ያደረገው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ነበር።
በወቅቱ በተደረገው ማሻሻያ መሠረት ቤንዚን ላለፉት አምስት ወራት ገደማ በ122 ብር ከ53 ሳንቲም ሲሸጥ ቆይቷል። የኬሮሲን እና ነጭ ናፍጣ መሸጫ 120 ብር ከ94 ሳንቲም ዋጋ እንዲሆንም ተደርጎ ነበር።
ዛሬ ይፋ የተደረገው ማሻሻያ ደግሞ የሦስቱም የነዳጅ ምርቶች ዋጋ 129 ብር ከ12 ሳንቲም እንዲሆን አድርጓል።
አዲሱ ተመን የቤንዚን ዋጋ ላይ 6 ብር ከ59 ሳንቲም ጭማሪ ሲያስከትል፣ የኬሮሲን እና ነጭ ናፍጣ ደግሞ የችርችሮ መሸጫ ዋጋቸው በ8 ብር ከ18 ሳንቲም እንዲጨምር ያደርጋል።
የአውሮፕላን፣ የኬሮሲን እንዲሁም የቀላል እና ከባድ ጥቁር ናፍጣ ዋጋ በኅዳር ወር ሲሸጥ በነበረበት እንዲቀጥል እንደተወሰነ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዛሬ ለነዳጅ ኩባንያዎች በላከው ደብዳቤ አስታውቋል።
ንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ይህንን የዋጋ ማሻሻያ ይፋ ያደረገው፤ ከታሕሳስ አንስቶ በሚተገበር የቫት እና የኤክሳይስ ታክስ ምክንያት የነዳጅ ዋጋ "በ30 በመቶ ይጨምራል" የሚሉ መረጃዎች በሠፊው ሲነገሩ ከቆየ በኋላ ነው። ይህንንም ተከትሎ ባለፉት ቀናት በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የነዳጅ እጥረት ተስተውሏል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዛሬ በላከው የዋጋ ጭማሪ ደብዳቤ ላይ የታክስ ጭማሪን በተመለከተ ያለው ነገር የለም።
የመንግሥት ከሐምሌ 2016 ዓ.ም. አንስቶ መተግበር የጀመረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ላይ ተደጋጋሚ ጭማሪዎች ታይተዋል። የቤንዚን ዋጋ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ100 ብር የተሻገረው ባለፈው ዓመት ታሕሳስ ወር ላይ ነበር።
ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ 91 ብር ከ14 ሳንቲም ይሸጥ የነበረው ቤንዚን በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ከመቶ ብር የተሻገረው በዚያው 2017 ዓ.ም. ነበር።
በ2017 ዓ.ም. መጀመሪያ የነበረው የቤንዚን ዋጋ ዛቴ ይፋ ከተደረገው ጋር ሲነጻጸር የ38 ብር ገደማ ጭማሪ ታይቶበታል። ነጭ ናፍጣ ደግሞ በ39 ብር ገደማ ዋጋው አድጓል።















