የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር የቀድሞ ኮሚሽነ��፣ ባለቤታቸው እና ልጃቸው በሙስና ክስ ተፈረደባቸው

አቶ ምትኩ ካሳ

የፎቶው ባለመብት, Disaster Risk Management Commission/fb

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር የቀድሞ ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር የቀድሞ ኮሚሽነር እና ቤተሰቦቻቸው በተከሰሱባቸው ከባድ የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው እስር ተፈረደባቸው።

አቶ ምትኩ ካሳ፣ ባለቤታቸው ወ/ሮ ሶፊያ ጀማል እና ልጃቸው ወ/ሮ ሚልካ ምትኩ በቀረበባቸው የወንጀል ክስ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ዛሬ ረቡዕ ታኅሣሥ 1/2018 ዓ.ም. የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ችሎት የዐቃቤ ሕግን የቅጣት ማክበጃ እና የተከሳሾችን የቅጣት ማቅለያ ካደመጠ በኋላ አቶ ምትኩ ካሳ በ13 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ50 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል፡፡

በተጨማሪም የአቶ ምትኩ ካሳ ባለቤት ወ/ሮ ሶፊያ ጀማል ላይ የ8 ዓመት ከ4 ወር እስራት እና 3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ሲወስን፣ ልጃቸው ወ/ሮ ሚልካ ምትኩ 5 ዓመት እስራት እና 3 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባታል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ምትኩ ካሳ ከሙስና ጋር በተያያዘ ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ሐምሌ 6/2014 ዓ.ም. ነበር።

በወቅቱ በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አቶ ምትኩ ለእስር የበቁት ኤልሻዳይ ከተባለ አገር በቀል የበጎ አድራጎት ተቋም ጋር ተባብረው ፈጽመውታል በተባለ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መሆኑን ገልጾ ነበር።

አቶ ምትኩ ካሳ ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቬሎፕመንት አሶሴሽን ከተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመመሳጠር በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሌሉ ተፈናቃዮች እንዳሉ በማስመሰል ለሚያቀርበው ጥያቄ የተለያዩ የእርዳታ አቅርቦቶችን እንዲሰጥ አድርገዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ፤ በኮሚሽኑ የተረጂዎችን ቁጥር በማጋነን የተለያዩ የእርዳታ ዓይነቶችን ከመጋዘን ወጪ በማድረግ ለተረጂዎች ሳይደርስ ተሽጦ ለግል ጥቅም መዋሉን በመግለጽ በወቅቱ ክስ መሥርቶ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አቶ ምትኩ ካሳ ከኤልሻዳይ ዳይሬክተር አቶ የማነ ወ/ማሪያም እና ሌሎች ሠራተኞች ጋር ያልተገባ የጥቅም ግንኙነት በመፍጠር በሺዎች በሚቆጠሩ ተረጂዎች ስም እንዲሁም የተረጂዎችን ቁጥር በማጋነን ለበርካታ ጊዜ የምግብ ቁሳቁሶች ከኮሚሽኑ መጋዘን በማውጣት ለዱቄት ፋብሪካዎችና ለሌሎች ግለሰቦች በመሸጥ ሕገወጥ ጥቅም ሲያገኙ እንደነበር የቀረበቸው ክስ ያስረዳል።

በአማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ የቀድሞው ደቡብ ክልል ውስጥ በሚገኙ የግብረሰናይ ድርጅቱ ማዕከላት ለተረጂዎች ሳያደርስ በመሸጥ ለግል ጥቅም ማዋላቸው በክሱ ላይ ተመልክቷል።

እንዲሁም ብድርና ድጋፍ በሚል ሰበብ በሕገ ወጥ መንገድ ከኮሚሽኑ በ100 ሚሊየን የሚገመት ገንዘብ ለእርዳታ ድርጅቱ መሰጠቱ ተገልጿል።

ለዚህም በአቶ ምትኩ ካሳ ቤተሰቦች ስም ከኤልሻዳይ ድርጅት በተለያዩ ጊዜ ክፍያ መፈጸሙ በዐቃቤ ሕግ ክስ ላይ ተጠቅሷል።

በሌላ ክስ ደግሞ ከ472 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ በድጋፍ መልክ በ1ኛ ተከሳሽ አቶ ምትኩ ካሳ ፈቃጅነት በ2ኛ ተከሳሽ አማካኝነት ክፍያ እንደተፈጸመና በ3ኛ ተከሳሽ ወጪ አድራጊነት ለግል ጥቅም በመዋሉ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሷል ተብሏል።

በአቶ ምትኩ ልጆችና ባለቤታቸው ስም ተገዝተው የተገኙ ተሽከርካሪዎችና መኖሪያ ቤቶችም መኖራቸውም በክሱ ላይ ተዘርዝሯል።

ክሱን ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ችሎት የቅጣት ማክበጃ እና ማቅለያ ሃሳቦችን ካዳመጠ በኋላ በአቶ ምትኩ ካሳ ላይ የ13 ዓመት ጽኑ እስራት ፈርዷል።

አቶ ምትኩ ካሳ ለሰባት ዓመታት የአገሪቱ የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው አገልግለዋል።

ኮሚሽኑ በተለያዩ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ለተጎዱ ዜጎች ከአገር ውስጥና ከውጭ የሚገኘውን እርዳታ የሚያስተባብር ነው።

በደቡብ ኢትዮጵያ ይርጋለም የተወለዱት፤ አቶ ምትኩ ካሳ የብሔራዊ የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ከመሆናቸው በፊት በደቡብ ክልል የምግብ ዋስትና ሥራዎች ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ ነበሩ።

አቶ ምትኩ ካሳ እአአ 2019 ላይ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ስር ተቋቁሞ በነበረው የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ውስጥ አባል ሆነው ተመርጠው ነበር።