ትራምፕ በዲሞክራቲክ ኮንጎ የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ቢያደርጉም አማፂያን ቁልፍ ከተማ መቆጣጠራቸው ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የዲሞክራቲክ ኮንጎ አማፂ ኤም23 ታጣቂዎች በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል በማዕድን የበለፀገችውን ከተማ መቆጣጠራቸው ተገለፀ።
በመንግሥት እና በአማፂያኑ መካከል የተካሄደው ውጊያ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ጎረቤት አገር ብሩንዲ እንዲሰደዱ አድርጓል።
ኡቪራ በምትባለው ከተማ የከባድ መሣሪያ ተኩስ እና ፍንዳታ የሚሰማ ሲሆን በጦርነቱ የተሸበሩ ነዋሪዎች ሁኔታውን ትርምስምስ ያለ ሲሉ ገልጸውታል።
በመንግሥት እና በአማፂያኑ መካከል የሚካሄደው ጦርነት የቀጠለው ትራምፕ ባለፈው ሳምንት በሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ መካከል ለረዥም ዓመታት የዘለቀውን ውጊያ ያስቆማል የተባለ ስምምነት እንዲፈረም ካደረጉ በኋላ ነው።
ኤም23 የተሰኘው የአማፂ ቡድን ከተማዋን "ነጻ ማውጣታቸውን" የገለፁ ሲሆን በመንግሥታቱ ድርጅት የሚደገፈው ራዲዮ ኦካፒ ነዋሪዎችን ጠቅሶ አማፂያኑ በከተማዋ ጎዳና ላይ መታየታቸውን ዘግቧል።
የደቡብ ኪቩ አስተዳዳሪ ዣን ዣኬዌስ ፑሩሲ ግን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን መንግሥት እና አጋር ሚሊሻዎች ከተማዋን እየተቆጣጠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ከተማዋ ከብሩንዲ ዋና ከተማ ቡጁምበራ በታንጋኒካ ሐይቅ በኩል 27 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።
አማፂያኑ ወደ ከተማዋ ሲገቡ የተወሰኑ ሰዎች ደስታቸውን መግለጻቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ከተማዋ ከየትኛውም እንቅስቃሴ ተገድባ ያለች ሲሆን ሱቆች እንዲሁም ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ነዋሪዎች ቤታቸው እንዲቆዩ ተደርጓል።
አንድ ነዋሪ ለኤኤፍፒ "በተራራው ላይ ሦስት ቦምቦች ፈንድተዋል። እያንዳንዱ ሰው ራሱን ለማዳን ነው የሚሯሯጠው" ሲሉ ሌላ ግለሰብ ደግሞ "በኡቪራ የምንገኝ ሰዎች ሁላችንም አልጋ ስር ነው ያለነው፤ ያለው እውነታ ያ ነው" ብለዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የመብት ተሟጋች ቡድን ባለስልጣን ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ቀሪ ወታደሮች አማፂዎቹን ለመገዳደር የሚሞክሩ ከሆነ "ጭፍጨፋ " ይኖራል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
አንድ የብሩንዲ ወታደራዊ መኮንን ለኤኤፍፒ "ውጥንቅጡ የወጣ ነው፤ ማንም ኃላፊነት የሚወስድ የለም። ኡቪራ አክትሞላታል" ሲሉ ተናግረዋል።
ወታደራዊ እና ደኅንነት ምንጮች አማፂያኑ በብሩንዲ ድንበር አቅራቢያ ከሚገኘው ሰሜናዊ ክፍል የተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ብሩንዲ በምሥራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመንግሥት ኃይሎችን ለመደገፍ የተሰማሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች አሏት።
የአገሪቱ ፕሩዚዳንት ኤቫሪስት ንዳዪሺሚዬ ትራምፕ "ተአምር ነው" ሲሉ ያደነቁት የሰላም ስምምነት ሲፈረም ለመመልከት ወደ ዋሺንግተን አምርተው ነበር።
የብሩንዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤዲዋርድ ቢዚማና የኤም23 አማፂ ቡድን ከተማዋን መቆጣጠር ዋሺንግተን የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ላደረገችው ጥረት "ያለን ንቀት የሚገልጽ. . . የመሃል ጣትን እንደማሳየት ነው" ብለዋል።
"ስምምነት ፈርሞ ተግባራዊ አለማድረግ ለሁሉም ውርደት ነው፤ ከምንም በላይ ለፕሬዚዳንት ትራምፕ" ሲሉ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።
አክለውም ድጋፍ ለመስጠት "በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች በመኪና ተጭነው" ከሩዋንዳ ሲመጡ ታይተዋል ብለዋል።
ማክሰኞ ዕለት አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና ስምንት የአውሮፓ አገራት ሩዋንዳ አማፂያኑን እየደገፈች ነው ሲሉ ወንጅለው ውጊያው ወድያውኑ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
ሩዋንዳ በውጊያው ላይ እጇ እንደሌለበት አስተባብላ የኮንጎ እና ብሩንዲ መንግሥታት የተኩስ አቁሙን ጥሰዋል ስትል ወንጅላለች።















