የ200 ሕጻናትን ሕይወት አደጋ ላይ የጣለው በልገሳ የተገኘው የአንድ ወንድ ዘር

የፎቶው ባለመብት, Shutterstock
በልገሳ የተገኘ የወንዴ ዘር ለካንሰር አጋላጭ የሆነ ጂን መያዙ ሳይታወቅ በአውሮፓ የተለያዩ አገራት 197 ሕጻናት መወለዳቸውን የተደረገ ምርመራ አረጋገጠ።
በዚህ የተነሳ አንዳንድ ልጆች መሞታቸው ሲታወቅ ከወንዴው ዘር ካንሰር አምጪውን ሕዋስ የወረሱ ጥቂት ሕጻናት ብቻ በሕይወት ዘመናቸው ከካንሰር ሊድኑ እንደሚችሉ ተገልጿል።
የወንዱ የዘር ፈሳሽ በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኙ ክሊኒኮች ለሽያጭ ባይቀርብም በዴንማርክ የወሊድ ሕክምና የተደረገላቸው የብሪታንያ ቤተሰቦች ይህንን በልገሳ የተገኘ የወንዴ ዘር መጠቀማቸውን ቢቢሲ ማረጋገጥ ችሏል።
በልገሳ የተገኘውን የወንዴ ዘር የሸጠው በዴንማርክ የሚገኘው የአውሮፓ የወንዴ ዘር ባንክ በዚህ ስህተት ምክንያት ለተጎዱ ቤተሰቦች የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጾ፣ ዘሩ በአንዳንድ አገራት ብዙ ሕጻናትን ለመውለድ ጥቅም ላይ መዋሉን አምኗል።
ምርመራው የተካሄደው ቢቢሲን ጨምሮ በአውሮፓ በሚገኙ በ14 የሕዝብ መገናኛ በብዙኃን ነው።
የወንዴው ዘር የተገኘው ማንነቱ ካልተገለጸ ተማሪ ሲሆን፣ ከአውሮፓውያኑ 2005 ጀምሮ እየተከፈለው ሲለግስ መቆየቱ ተገልጿል።
የእርሱ የዘር ፈሳሽ መውለድ ለሚፈልጉ ሴቶች ለ17 ዓመታት ያህል ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል።
ለጋሹ ጤናማ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የተደረገለትንም ምርመራ በሚገባ አልፏል። ይሁን እንጂ በአንዳንድ ህዋሶቹ ውስጥ ያለው ዘረ መል ከመወለዱ በፊት ተለውጠዋል።
ይህም የሰውነት ህዋሶች ወደ ካንሰርነት እንዳይቀየሩ ለመከላከል ወሳኝ ሚና ያለውን ቲፒ53 (TP53) ጂንን ጎድቶታል።
አብዛኛው የለጋሽ ሰውነት አደገኛውን የቲፒ53 (TP53) ዓይነትን አልያዘም፤ ነገር ግን እስከ 20 በመቶ የሚሆነው የዘር ፈሳሹ ይህንን ይዞ ተገኝቷል።
ይሁን እንጂ ከተጠቃው የወንድ ዘር (sperm) የተወለዱ ሕጻናት በእያንዳንዱ የሰውነታቸው ህዋስ ውስጥ ይህ ካንሰር አምጭ (ሚውቴሽን) ይኖራቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ይህም ሊ ፍራውሜኒ ሲንድሮም (Li Fraumeni syndrome) በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ በተለይም በሕጻንነት ጊዜ እስከ 90 በመቶ እንዲሁም በኋለኛው የሕይወት ዘመን በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድልን ይጨምራል።
በለንደን የካንሰር ምርምር ኢንስቲትዩት የካንሰር ጄኔቲክስ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ክላሬ ተርንቡል ለቢቢሲ "ይህ አስከፊ ምርመራ ነው" ብለዋል።
"በአን ቤተሰብ ላይ የደረሰው ፈተና የሞላው ምርመራ ነው። ከዚህ አደጋ ጋር አብሮ የመኖር የሕይወት ዘመን ሸክም አለ። በግልጽ የሚረብሽ ነው።"
ዕጢዎችን ለመለየት በየዓመቱ የሰውነት ክፍሎችን እና ጭንቅላትን በኤምአርአይ እንዲሁም የሆድ እቃን በአልትራሳውንድ መታየት ያስፈልጋል። ብዙውን ጊዜ ሴቶች በካንሰር የመያዝ ዕድላቸውን ለመቀነስ ጡቶቻቸውን በቀዶ ሕክምና ማስወገድን ይመርጣሉ።
የአውሮፓ የወንዴ ዘር ባንክ "ለጋሹ እና ቤተሰቡ አልታሙም" ያለ ሲሆን፣ እንዲህ ዓይነቱን ልውጥ ጂን (ሚውቴሽን) "በጄኔቲክ ምርመራ ወቅት ለመከላከል በሚያስችል መልኩ አልተገኘም" ብሏል።
የወንዱ ዘር ችግር እንዳለበት ከታወቀ በኋላ "ወዲያውኑ እንዳይሰጥ መታገዱን" ጨምሮ ገልጿል።
ሕጻናት ሞተዋል
በዚህ ዓመት በልገሳ ከተገኘ የወንዴ ዘር የተወለዱ ሕጻናት ካንሰር እንዳለባቸው ያወቁ ዶክተሮች በአውሮፓ ሂውማን ጄኔቲክስ ማኅበር ስጋታቸውን ተናግረዋል።
በወቅቱ ከ67 ሕጻናት መካከል 23ቱ ተመሳሳይ የካንሰር ዓይነት እንደተገኘባቸው አስታውቀዋል። ከዚያ አስቀድሞ አሥር ሕጻናት በካንሰር መያዛቸው ታውቆ ነበር።
ከሕክምና ባለሙያዎች እና ከታካሚዎች ጋር በተደረገ ቃለ መጠይቅ ከለጋሹ ከተገኘ የወንዴ ዘር ብዙ ልጆች መወለዳቸው ታውቋል።
ከዚህ የወንዴ ዘር ብቻ ቢያንስ 197 ሕፃናት የተወለዱ ሲሆን፣ ነገር ግን ከሁሉም አገራት መረጃዎች ስላልተገኙ ይህ የመጨረሻው ቁጥር ላይሆን ይችላል።
ከእነዚህ ልጆች መካከል ምን ያህሉ አደገኛውን የካንሰር ዓይነት እንደወረሱ አይታወቅም።

የመጀመሪያውን መረጃ ይፋ ያደረጉት በፈረንሳይ የሩየን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የካንሰር ጄኔቲክስ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ኤድዊጅ ካስፐር ናቸው።
ዶ/ር ካስፐር ስለምርመራው ሲናገሩ "በአሁኑ ጊዜ ካንሰር ያለባቸው ብዙ ልጆች አሉን" ብለዋል።
አክለውም "ቀደም ሲል ሁለት የተለያየ ዓይነት ካንሰር የተያዙ ልጆች ነበሩን፤ አንዳንዶቹ ገና በለጋ ዕድሜያቸው ሞተዋል" ሲሉ አስረድተዋል።
በፈረንሳይ የምትኖረው ሴሊን (ስሟ የተቀየረ) በልግስና ከተገኘ የወንዴ ዘር የፀነሰችው ከ14 ዓመት በፊት ሲሆን ልጇ ልውጥ ጂን እንዳለበት ተረጋግጧል።
ሕክምናውን ካገኘችበት በቤልጂየም ከሚገኘው ክሊኒክ ተደውሎ ልጇን እንድታስመረመር ተነግሯታል።
ለጋሹ ላይ ምንም ዓይነት የጥላቻ ስሜት እንደሌላት ትናገራለች፤ ነገር ግን "ንፁህ ያልሆነ፣ ደኅንነቱ ያልተጠበቀ፣ አደጋ የሚያስከትል" የወንድ ዘር መሰጠቷ ግን ተቀባይነት እንደሌለው ተናግራለች።
እና በቀሪው ሕይወታቸው ሁሉ የካንሰር ስጋት በላያቸው ላይ እንደሚያንዣብብ ታውቃለች።
"መቼ እንደሆነ አናውቅም፤ የትኛው እንደሆነ አናውቅም፤ ምን ያህል እንደሆነም አናውቅም" ትላለች።
"ይህ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ተረድቻለሁ፤ እናም ሲከሰት እንዋጋዋለን እና ብዙ ጊዜ የሚደጋገም ከሆነ ብዙ ጊዜ እንታገለዋለን።"

የለጋሹን ዘር በ14 አገራት በሚገኙ 67 የወሊድ ክሊኒኮች ጥቅም ላይ ውለዋል።
የዚህ ለጋሽ የዘር ፈሳሽ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ለሚገኙ ክሊኒኮች አልተሸጠም።
ሆኖም በዚህ ምርመራ ምክንያት በዴንማርክ የሚገኙ ባለሥልጣናት ብሪታኒያውያን ሴቶች ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገራት በመሄድ የግለሰቡን ዘር ተጠቅመው መውለዳቸውን ለዩኬ የጽንስ እና ወሊድ ጥናት ባለሥልጣን ሰኞ ዕለት አሳውቀዋል።
የለጋሹን ዘር ተጠቅመው የወለዱ ሴቶች ስለሁኔታው እንዲያውቁ ተደርጓል።
የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፒተር ቶምፕሰን "በጣም ጥቂት ቁጥር ያላቸው" ሴቶች ተጎድተዋል፤ "ስለለጋሹ አገልግሎቱን ባገኙበት የዴንማርክ ክሊኒክ ተነግሯቸዋል" ብለዋል።
የለጋሹ ዘር ከተከፋፈለባቸው ሌሎች አገራት ተጨማሪ ብሪታንያውያን ሴቶች ሕክምና ስለማግኘታቸው ምንም አናውቅም።
በዚህ መረጃ የተነሳ ስጋት የገባቸው ወላጆች አገልግሎት ያገኙበትን ክሊኒክ እና የአገሪቱን የጤና ባለሥልጣናት እንዲያነጋግሩ መክረዋል።
ቢቢሲ ለጋሹ የዘር ፈሳሹን የሰተው በቅን ልቦና ተነሳስቶ ነው በሚል ምክንያት እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም ያሉ ቤተሰቦች ስለጉዳዩ እንዲያውቁ በመደረጉ የለጋሹን ማንነት ማወቅ የሚያስችለውን የመለያ ቁጥር ይፋ ላለማድረግ ወስኗል።
በዓለም ላይ ከአንድ ለጋሽ የሚገኝ ዘር ምን ያህል ጊዜ ጥቅም ላይ መዋል አንዳለበት የሚደነግግ ሕግ የለም። ሆኖም አገራት የራሳቸውን ገደብ ያስቀምጣሉ።
የአውሮፓ የወንዴ ዘር ባንክ እነዚህን ገደቦች ቢቀበልም "በሚያሳዝን ሁኔታ" በአንዳንድ አገራት ተጥሷል።
በዚህም የተነሳ "በዴንማርክ እና ቤልጂየም ከሚገኙ ባለሥልጣናት ጋር በመነጋገር ላይ" ነበር።
በቤልጂየም አንድ ከለጋሽ የተገኘ ዘር በስድስት ቤተሰቦች ብቻ ጥቅም ላይ መዋል አለበት።
ከዚያ በተለየ ግን 38 የተለያዩ ሴቶች የለጋሹን ዘር ተጠቅመው 53 ልጆችን ወልደዋል።
በዩኬ ከአንድ ለጋሽ የሚገኝ ዘር ጥቅም ላይ መዋል የሚችለው በ10 ቤተሰቦች ብቻ ነው።
'ሁሉንም ነገር መመርመር አይቻልም'
በሼፊልድ የሚገኝ የወንዴ ዘር ባንክን ያስተዳድሩ የነበሩት እና አሁን በማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ የጤና ፋክልቲ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ፕሮፌሰር አለን ፓሲ እንዳሉት አገራት በትልልቅ ዓለም አቀፍ የወንዴ ዘር ባንኮች ላይ ጥገኛ ሆነዋል። ግማሹ ዩናይትድ ኪንግደም የምትጠቀምበት ዘር ከሌላ አገራት የሚገባ ነው።
ፕሮፌሰሩ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ከትላልቅ ዓለም አቀፍ የወንዴ ዘር ባንኮች ለማምጣት ተገድደናል። እነዚህ ባንኮች ደግሞ ወደ ሌላ አገርም እየሸጡ ገንዘብ የሚያገኙት መንገድ ነው። ችግሩ የሚጀምረውም እዚያ ላይ ነው። ምክንያቱም ዘሩን ምን ያህል ጊዜ መጠቀም እንደሚችሉ የሚገልጽ ዓለም አቀፍ ሕግ የለም።"
ፕሮፌሰሩ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሁሉ "አሰቃቂ" መሆኑን ገልጸው፣ የወንድ የዘር ፍሬን ሙሉ በሙሉ ደኅንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ የማይቻል መሆኑን ተናግረዋል።
"ሁሉንም ነገር ማጣራት አይቻልም፤ አሁን ባለው የምርመራ ዝግጅት የወንድ የዘር ፈሳሽ ለጋሽ ለመሆን ከሚያመለክቱ ወንዶች 1 በመቶ ወይም 2 በመቶዎቹን ብቻ እንቀበላለን። ስለዚህ ከዚያ በላይ መስፈርቱን ካጠበቅነው ምንም ዓይነት ለጋሽ አይኖረንም፤ እዚያ ላይ ነው ሚዛኑ ያለው።"

በለገሰው ዘር 550 ልጆችን የወለደውን ግለሰብ ታሪክ እንዲሁም ይህንን ዜና የሰሙ አካላት ጠንከር ያለ ገደብ ሊኖር ይገባል ወይ የሚል ጥያቄ አንስተዋል።
የአውሮፓ የወሊድ እና ጽንስ ጥናት ማኅበር ከአንድ ለጋሽ የሚገኝ ዘር ከ50 ቤተሰቦች በላይ እንዳይጠቀሙ የሚል ገደብ እንዲኖር ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።
ይሁን እንጂ ይህ በዘር የሚተላለፉ ያልተለመዱ በሽታዎችን የመውረስ ዕድልን አይቀንስም ብሏል።
ይልቁንም በመቶዎች ከሚቆጠሩት ግማሽ ወንድም እና እህትማማቾች መካከል አንዱ መሆናቸውን ለሚያወቁ ���ፃናት ደኅንነት የተሻለ ነው ብለዋል።
በመሃንነት እና በዘረ መል ችግሮች ለተጎዱ ቤተሰቦች የሚሟገተው የፕሮግረስ ኢጁኬሽናል ትረስት ዳይሬክተር የሆኑት ሳራ ኖርክሮስ "በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተመሳሳይ ለጋሾች የሚወለዱትን ልጆች ቁጥር ለመቀነስ የበለጠ መደረግ አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።
"እነዚህ በመቶዎች የሚቆጠሩ ግማሽ ወንድማማቾች እና እህትማማቾች የሚገጥማቸው ማኅበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ አንድምታ ምን እንደሚሆን ሙሉ በሙሉ ገና ግልጽ አይደለም። ይህ የሚረብሽ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአውሮፓ የወንዴ ዘር ባንክ "ከዚ ህክስተት ጋር በተያያዘ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች እና ጥንዶች ከለጋሽ ከሚገኝ ዘር ውጪ ልጅ የመውለድ ዕድል እንደሌላቸው ማስታወስ አስፈላጊ ነው" ብሏል።
"ለጋሾች በሕክምና መመሪያ መሠረት ከተመረመሩ በኋላ በሚገኝ የወንድ ዘር ልገሳ አማካኝነት ልጅ መውለድ በአጠቃላይ ደኅንነቱ አስተማማኝ ነው።"
ከለጋሽ የሚገኝ የወንድ ዘርን ለመጠቀም የሚያስቡ ቢሆንስ?
ሣራ ኖርክሮስ በልገሳ ከተገኘ ዘር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ሲታሰብ እንዲህ ዓይነት የጤና ስጋቶች "በጣም ትንሽ ናቸው" ይላሉ።
ቢቢሲ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች በሙሉ ፈቃድ ያለው ክሊኒክ ተጠቅመው በዚህ ሕክምና መሠረት የሚወልዱ እናቶች ከበርካታ አባቶች በበለጠ በልገሳ የተገኘው የወንዱ ዘር ምርመራ ስለሚደረግለት ስጋት ሊገባቸው እንደማይገባ ተናግረዋል።
ፕሮፌሰር ፓሲ በበኩላቸው "ይህ በዩናይትድ ኪንግደም ከሚኖር ለጋሽ የተገኘ ነው ወይስ ከሌላ ቦታ የተገኘ?" ብለው እንደሚጠይቁ ይናገራሉ።
"በሌላ አገር ከሚኖር ለጋሽ የተገኘ ከሆነ ዘሩ ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ ውሎ እንደሆነ መጠየቅ ጠቃሚ ነው። ወይም ምን ያህል ጊዜ ጥቅም ላይ ውሏል? ብሎ ማወቅ ተገቢ ይመስለኛል ብለዋል።















