ከባሪያዎች ምግብነት እስከ ነገሥታት ማዕድ የዘለቀው፣ የበርካታ ሕመሞች ፈውስ ነጭ ሽንኩርት

ቻይና ነጭ ሽንኩርት በማምረት በዓለም ቀዳሚዋ ነች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቻይና ነጭ ሽንኩርት በማምረት በዓለም ቀዳሚዋ ነች

ነጭ ሽንኩርት ለሺህዎች ዓመታት በምግብ ማጣፈጫነት፣ በመድኃኒትነት አገልግሎት ላይ እየዋለ እገኛል።

በእርግጥ ሽታው በርካቶችን የሚያንገፈግፍ ቢሆንም በመድኃኒትነቱ ላይ ግን ጥያቄ የለም።

በፀረ ባክቴሪያ እና ፀረ ቫይረስ የታወቀው ነጭ ሽንኩርት ከምግብ ማጣፈጫነቱ ባሻገር በባሕላዊ ሕክምና ውስጥ እጅጉን የተለመደ ነው።

ነጭ ሽንኩርት የመጀመሪያ መገኛው በማዕከላዊ እስያ ሲሆን፣ ከዚያም ወደ አውሮፓ እና ዩናይትድ ስቴትስ ተስፋፍቷል።

ዛሬ ቻይና ነጭ ሽንኩርትን በማምረት በዓለማችን ቀዳሚዋ አገር ናት።

ቢቢሲ የነጭ ሽንኩርት ቱባ ታሪክ እና ባህላዊ አበርክቶ ፈትሿል። እንዲሁም ነጭ ሽንኩርት ለጤናችን ጠቃሚ ነውን? ሲልም ጠይቋል።

ምግብ ለማጣፈጥ ወሳኝ የሆነው ግብዓት

የዶሮ ስጋ ከነጭ ሽንኩርት እና ቢላዋ ጋር መክተፊያ ላይ ተቀምጦ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ነጭ ሽንኩርት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በሚገኙ ሰዎች እና ማዕድ ጥቅም ላይ ይውላል

ነጭ ሽንኩርት ስፍር ቁጥር በሌላቸው ምግቦች ውስጥ በጣም አስፈላጊ ማጣፈጫ ነው። በሰሜን ምዕራብ ፈረንሳይ በሚገኝ ትምህርት ቤት ከአሜሪካ፣ ከአውስትራሊያ፣ ከእንግሊዝ እና ከእስያ የመጡ ተማሪዎችን የሚያስተምረው ዴንማርካዊ ሼፍ ፖል ኤሪክ የንሰን ነጭ ሽንኩርትን የማያውቅ ተማሪ አጋጥሞኝ አያውቅም ይላል።

ነጭ ሽንኩርት ምግብን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያጣፍጥ ያምናል፤ እና ያለ እሱ የፈረንሳይ ምግብ ምን እንደሚሆን ሲያስብ ይገረማል።

"እነሱ [ፈረንሳዮቹ] ነጭ ሽንኩርት የሌለበት ማንኛውንም ምግብ ማሰብ የሚችሉ አይመስለኝም" ብሏል። "በሾርባ፣ በአትክልት ወይም በሥጋ ምግቦች ውስጥ በእርግጠኝነት አንድ ቦታ ነጭ ሽንኩርት ይገባል። ምንም አለመጠቀም የማይታሰብ ነው።"

ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ በዴንማርክ ገጠራማ አካባቢ ሲያድግ ነጭ ሽንኩርት ፈጽሞ አይታወቅም ነበር።

ነጭ ሽንኩርት በወቅቱ በጠንካራ ጠረኑ የታወቀ እንደነበር ያስታውሳል። ነገር ግን ቱርካውያን ወደ ዴንማርክ መሰደድ ሲጀምሩ በነጭ ሽንኩርት የጣፈጠ ምግብ እየተለመደ መጣ። አሁን ሼፍ የንሰን በጣልያን ፒዛ ላይ ነጭ ሽንኩርትን ጣል ማድረግ ለምዷል።

"እኔ እና ባልደረባዬ ጠዋት ላይ በእያንዳንዱ ኩባያ ውስጥ አንድ ሙሉ ነጭ ሽንኩርት ተፈጭቶ የተጨመረበት አንድ ኩባያ መረቅ መውሰድ ለምደናል" ይላል።

"ምንም ዓይነት ጉንፋን ወይም የመተንፈሻ አካል ሕመም አላጋጠመንም። እርግጠኛ ነኝ ነጭ ሽንኩርቱ [ምስጋና ይግባውና] ነው።"

ነጭ ሽንኩርት የያዘ እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በ20ኛው ክፍለ ዘመን ነጭ ሽንኩርትን ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያዳረሱት ስደተኞች ናቸው

ረዥም ጉዞ

የነጭ ሽንኩርት ባህላዊ እና መንፈሳዊ ጠቀሜታ ብዙ ሺህ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው።

የጥንቶቹ ግሪኮች የጥንቆላ አምላክ እና የቤተሰብ ጠባቂ ለሆነችው ለሄኬቴ መሥዋዕት አድርገው ነጭ ሽንኩርት በመስቀለኛ መንገድ ላይ ያስቀምጡ ነበር።

በግብፅ ውስጥ ነጭ ሽንኩርት በታዋቂው የፈርዖን ቱታንክሃመን መቃብር ውስጥ ከሞት በኋላ ባለው ሕይወት ይጠብቀዋል በሚል ተገኝቷል።

በቻይና እና ፊሊፒንስ አፈ ታሪክ ውስጥ ሰዎች ቫምፓየሮችን ለመዋጋት ነጭ ሽንኩርት ስለመጠቀማቸው የሚያሳዩ ተረቶች አሉ።

"በዓለም ላይ በጣም ጥንታዊው የምግብ ዓይነት የሜሶፖታሚያን ወጥ ሲሆን ወደ 3,500 ዓመታት ያስቆጠረ ዕድሜ አለው። እና በውስጡ ሁለት ራስ ነጭ ሽንኩርት ይጨመርበታል" ሲል በነጭ ሽንኩርት ላይ መጽሐፍ ያዘጋጀው ሮቢን ቼሪ ተናግሯል።

"በጣም ጥንታዊ የሆነው [የነጭ ሽንኩርት] ሕክምና ወደ 3,500 ዓመታት ገደማ ያስቆጠረ ነው። ይህም ኤበርስ ፓፒረስ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ ነጭ ሽንኩርትን ከበሽታ እስከ ጥገኛ ተውሳኮች እንዲሁም የልብ ወይም የመተንፈስ ችግርን እንዴት እንደሚፈውስ ብዙ ተጠቅሷል" ሲል ታሪካዊ ሂደቱን ያብራራል።

ቼሪ የጥንቷ ግሪክ ሐኪም እና ፈላስፋ ሂፖክራተስ ነጭ ሽንኩርት በተለያዩ የሕክምና ዘዴዎች ይጠቀም እንደነበር ገልጿል።

ከዚህም በላይ እንደ አርስቶትል እና አሪስቶፋንስ ያሉ ታዋቂ ተመራማሪዎች እና ፀሐፊዎች ነጭ ሽንኩርትን በመድኃኒትነት ይገልፁ ነበር።

ነጭ ሽንኩርት የገባበት ፒዛ
የምስሉ መግለጫ, ነጭ ሽንኩርት አዘውትረን በምንመገባቸው እና በምንወዳቸው ምግቦች ውስጥ ማጣፈጫ ሆኖ ይገባል

በባርነት ከተሸጡ ሰዎች ምግብነት ወደ ንጉሥ ማዕድ

ነጭ ሽንኩርት በጥንቷ ሜሶፖታሚያ፣ ግብፅ፣ ግሪክ፣ ሮም፣ ቻይና እና ሕንድ ውስጥ በሰፊው ታዋቂ ነበር። የሮማውያን ወታደሮች ነጭ ሽንኩርት ድፍረትን እና ጥንካሬን እንደሰጣቸው ያምኑ ነበር፤ በወረራዎቻቸው ጊዜ በመላው አውሮፓ አሠራጭተውታል።

ነጭ ሽንኩርት ለምግብም ሆነ ለመድኃኒትነት ሲያገለግል፣ በአንድ ወቅት በምግብ ውስጥ የሚጨመረው ግን ለዝቅተኛ ማኅበረሰብ አባላት ብቻ ነበር።

ሮቢን ቼሪ "በእርግጥ ለድሆች ብቻ የሚሆን ምግብ ነበር" ይላል።

"በግብፅ ውስጥ ፒራሚዶችን ለሚገነቡ ባሪያዎች ወይም የሮማውያን መርከበኞች ጥንካሬን እንዲሰጥ በሚል ነበር ጥቅም ላይ የሚውለው። ዋጋው ርካሽ ነበር፤ የመጥፎ ምግቦችን ጣዕም ሊደብቅ ይችላል። ስለዚህ ድሆች ብቻ የሚበሉት ነገር ተደርጎ ይቆጠር ነበር።"

ከ14ኛው እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን ባለው የአውሮፓ ታሪክ ወሳኝ ወቅት፣ የኪነ ጥበብ እና የሳይንስ ዕድገት በታየበት የሕዳሴ ዘመን የነጭ ሽንኩርት ዝና መቀየር ጀመረ።

"ፈረንሳዊው ሄንሪ አራተኛ በነጭ ሽንኩርት ተጠምቆ ብዙ በልቷል፤ ይህም በመጠኑ ተወዳጅ እንዲሆን አድርጎታል" ሲል ቼሪ ያስረዳል።

አክሎም በ19ኛው ክፍለዘመን የእንግሊዝ ቪክቶሪያን ዘመን ነጭ ሽንኩርት ዝናው ናኘ።

ነጭ ሽንኩርት ብዙ ቆይቶ በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ ውስጥ ከስደተኞች ጋር የተቆራኘ ታሪክ ኖረው። ይህም አሉታዊ አመለካከቶችን ለመቀልበስ ረድቷል።

"ነጭ ሽንኩርት አይሁዶችን፣ ጣሊያናውያን እና ኮሪያውያን ለማንቋሸሽ ጥቅም ላይ ይውል ነበር። ሁሉም 'ነጭ ሽንኩርት በሊታዎች' ተብለው ይጠሩ ነበር፤ እና አሉታዊ ትርጉም ነበረው" ሲል ሮቢን ቼሪ ተናግሯል።

ነጭ ሽንኩርትን እንደ መድኃኒት

ከነጭ ሽንኩርት የተዘጋጁ መድሃኒቶች እና ዘይቶች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጋርሊክ ለተለያዩ ሕመሞች መድሃኒት መሆኑ በስፋት ይታመናል

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከ600 በላይ የነጭ ሽንኩርት ዝርያዎች አሉ። አንዳንዶቹ፣ ልክ ከኡዝቤኪስታን እና ከጆርጂያ እንደተገኙት ዝርያዎች በቅርቡ ነው በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁት።

ነጭ ሽንኩርት በዘመናዊ ምግቦች ውስጥ ከሚጫወተው ጉልህ ሚና ባሻገር፣ በተለምዶ የጉንፋን ምልክቶችን ለማከም ወይም ለመቀነስ ያገለግላል።

ክሊኒካዊ ሙከራዎች በደም ግፊት፣ በኮሌስትሮል እና በካንሰር ላይ ያለውን ተጽእኖ መርምረዋል፤ ነገር ግን ውጤቶቹ አንድ ወጥ አይደሉም።

በኢራን የተካሄደ አንድ አነስተኛ ጥናት ነጭ ሽንኩርት እና የሎሚ ጭማቂ በስድስት ሳምንታት ውስጥ የኮሌስትሮል እና የደም ግፊትን ለመቀነስ ረድተዋል።

ይሁን እንጂ በዩናይትድ ስቴትስ በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ 200 ጤናማ ግለሰቦችን በስድስት ወራት ውስጥ ያሳተፈ ትልቅ ጥናት ተካሄዶ ምንም የኮሌስትሮል መቀነስ አላገኘም።

የደረቀ ነጭ ሽንኩርት

የፎቶው ባለመብት, Press Association

የምስሉ መግለጫ, ነጭ ሽንኩርትን በባዶ ሆድ መውሰድ ጨጓራን ሊያስቆጣ ይችላል

በአውሮፓውያኑ 2014 በአውስትራሊያ ሲድኒ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት ደግሞ የነጭ ሽንኩርት ጠንካራ ፀረ-ተህዋስያን፣ ፀረ ቫይረስ እና ፀረ ፈንገስ ቅመሞች እንዳሉት አረጋግጧል።

"ነጭ ሽንኩርት ከፍተኛ መጠን ያለው ፖታስየም፣ ፎስፎረስ፣ ዚንክ፣ ሰልፈር እና መጠነኛ ማግኒዢየም፣ ማንጋኒዝ እና አይረን ይዟል። በጣም የሚያስደንቅ አትክልት ነው" ብለዋል የብሪታኒያ የአመጋገብ ህክምና ማህበር ቃል አቀባይ እና የሕፃናት የአመጋገብ ባለሙያ የሆኑት ባሂ ቫን ደ ቦር።

"አሊሲን የሚባሉ ደስ የሚሉ ሰልፈር የያዙ ውህዶች አሉት። በፕሪባዮቲክ ፋይበር የበለፀገ ነው፤ ለሆዳችን ተስማሚ በመሆኑ ለአንጀታችን ጤና ጠቃሚ ነው። በተጨማሪም አንዳንድ ፀረ ጀርም መድኃኒቶች አሉት" ሲሉ የነጭ ሽንኩርት ፋይበር ጠቃሚ የአንጀት ባክቴሪያን እንዲዳብር እና የሆድ ድርቀትን እና መነፋትን ለመከላከል እንደሚረዳ አብራርተዋል።

በቀን አንድ ወይም ሁለት ፍሬ ነጭ ሽንኩርት መመገብ ለአዋቂዎች መልካም ነው ተብሎ ይታሰባል።

ነገር ግን አሜሪካን ፋሚሊ ፊዚሺያን በተባለ ጆርናል ላይ በታተመው ጥናት መሠረት በተለይ በባዶ ሆድ ከመጠን በላይ ነጭ ሽንኩርት መውሰድ የጨጓራ መረበሽ፣ የሆድ መነፋት እና በአንጀታችን ውስጥ በሚገኙ ጠቃሚ ተህዋሲያን ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።