የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሳዑዲ አረቢያ በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ የበለጠ ተሳትፎ እንዲኖራት ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Yemane G. Meskel/X
የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ ሳዑዲ አረቢያ እንደ ናይል ተፋሰስ እና ቀይ ባሕር ባሉ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ያላትን ተሳትፎ እንድታሳድግ እንዲሁም ለቀጣናው ሰላም "ከፍተኛ አስተዋፆ" እንድታደርግ ጠየቁ።
ሳዑዲ አረቢያም በእነዚህ "በወሳኝ ቀጣናዊ ጉዳዮች" ላይ ምክክር ለማድረግ ወደ ኤርትራ ልዑክ እንደምትልክ ገልጻለች ተብሏል።
ለአራት ቀናት የሥራ ጉብኝት በሪያድ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ይህንን ጥያቄ ያቀረቡት፤ ትናንት ረቡዕ ታኅሣሥ 1/2018 ዓ.ም. ከሳውዲው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን ጋር ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደሆነ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል አስታውቀዋል።
ኢሳያስ፤ ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ዕለት ወደ ሳዑዲ ያቀኑት በንጉሥ ሰልማን ቢን አብዱላዚዝ አል ሳዑድ ግብዣ እንደሆነ ተገልጿል። በሪያድ ከሳውዲ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ስብሰባዎችን እንደሚያደርጉ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ጠቅሰው ነበር።
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ረቡዕ በኤክስ ገጻቸው ያጋሩት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ኢሳያስ በአል ያማማህ ቤተ መንግሥት ተገኝተው ከሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ ጋር "ሰፊ ንግግር" አድርገዋል።
የሁለቱ መሪዎች ንግግር "በሁለትዮሽ ግንኙነቶች እንዲሁም ለሁለቱ አገራት ወሳኝ ጥቅም ባላቸው ሌሎች ጉዳዮች" ላይ ያተኮረ እንደነበር አመልክተዋል።
"ሞቅ ያለ" እንደነበር የተገለጸው የሁለቱ መሪዎችን ውይይት፤ አገራቱ ያላቸው "ታሪካዊ እና ወንድማማቻዊ ግንኙነት" የተነሳበት እንደነበረም ጠቅሰዋል።
ሁለቱ አገራት "ኢኮኖሚያዊ ትብብሮች ላይ ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማስፋት ያላቸው ተስፋ እና ዕድል" ላይ ተኮረም እንደነበር ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እና ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቀጣናዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያደረጉት ውይይት "ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ ምልከታ መለዋወጥ ላይ" ያጠነጠነ እንደነበረ የማነ በልጥፋቸው አስረድተዋል።
ቀጣናዊ ጉዳዮች ተብለው የተጠቀሱት "የአባይ ተፋሰስ፣ የአፍሪካ ቀንድ፣ ቀይ ባሕር እና የአረቢያን ባሕረ ሰላጤ" ናቸው።
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ በልጥፋቸው፤ "ሁለቱ ወገኖች ሳዑዲ አረቢያ በእነዚህ ሁሉ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ስለሚኖራት ተገቢ ሚና ተወያይተዋል" ሲሉ ጽፈዋል። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፤ ሳዑዲ አረቢያ "ከዚህ ቀደም" በእነዚህ ጉዳዮች ላይ "ንቁ ሚና እንዳልነበራት" አንስተዋል ተብሏል።
የማነ ገብረ መስቀል "የዳበረ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት [እንዲኖር] ለማድረግ ዘላቂ ቀጣናዊ ሰላምን [ማስፈን] አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ መሆኑን አስምረውበታል" ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ያነሱትን ነጥብ አስረድተዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አክለውም፤ "በጠቅላላው በሰፊው ቀጣና እና በተለይም በጎረቤቶቻችን ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን ሳዑዲ አረቢያ ከፍተኛ ሚና እንድትጫወት ጠይቀዋል።"
ይህ ጥያቄ የቀረበላቸው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን በበኩላቸው፤ "በቅርቡ ልዑካቸውን ወደ ኤርትራ እንደሚልኩ" መናገራቸውም የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
ወደ ኤርትራ የሚጓዘው ልዑክ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ባነሷቸው "ወሳኝ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ምክክር" እንደሚያደርግ ልዑል አልጋ ወራሹ መግለጻቸውን ተጠቅሷል።
ባለፉት ወራት ኢትዮጵያ የይገባኛል ጥያቄ ያነሳችበትን የአሰብ ወደብ ኤርትራ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር በጋራ ለማልማት ፍላጎት እንዳልት የሚገልጹ ሪፖርቶች መውጣታቸው ይታወሳል።

የፎቶው ባለመብት, Yemane G. Meskel/X
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ሦስተኛ የሆነውን የውጭ ጉዞ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያደረጉት፤ የሪያድ ተቀናቃኝ ከሆነችው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ጥሩ ግንኙነት ያላት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የገቡበት ውጥረት በቀጠለበት ወቅት ነው።
ደም አፋሳሹን የትግራይ ጦርነት ካስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ወዲህ የሻከረው የአዲስ አበባ እና አሥመራ ግንኙነት፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር ለማግኘት ያለውን ፍላጎት መግለጹን ተከትሎ ይበልጡኑ ውጥረት ውስጥ ገብቷል።
የባሕር በር ለኢትዮጵያ "የኅልውና ጉዳይ" መሆኑን የሚገልጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በቀይ ባሕር ላይ "የተፈጸመው ስህተት እንደሚታረም" መናገራቸው ይታወሳል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጤሞቲዮስ በበኩላቸው የአሰብ ወደብ በኢትዮጵያ መንግሥት "በዋነኛነት ቅድሚያ የሚሰጠው" ጉዳይ እንደሆነ ባለፈው ኅዳር ላይ በተዘጋጀ አንድ መድረክ ላይ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ከባሕር በር ጋር ተገናኘ እንቅስቃሴ እንደ ትንኮሳ እየገለጸች ያለችው ኤርትራ በበኩሏ ከአዲስ አበባ ጋር ግንኙነታቸው ከተሻከረ እና ከተቀዛቀዘ አካላት ጋር ያላትን ትስስር አጠናክራለች።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ባለፈው ዓመት መጋቢት ላይ ወደ ግብፅ በተጓዙበት ወቅት ቀይ ባሕር ዳርቻ ተጎራባች ያልሆኑ አገራት በውሃ አካሉ "ደኅንነት እና አስተዳደር ላይ" መሳተፍ እንደሌለባቸው መስማማታቸው ተገልጾ ነበር።
የጅቡቲ እና ሶማሊያ ባለሥልጣናት ወደ ግብፅ በተጓዙበት ወቅትም ተመሳሳይ አቋም ተንጸባርቆ እንደነበር አይዘነጋም።












