ማርበርግ ቫይረስ: የመጀመሪያው ታማሚ እና ሦስት መሪዎቿን ያጣችው የጂንካ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን

"ከአንድ አጥቢያ እንዴት ሦስት አባቶች በአንድ ጊዜ ይሞቱብናል?" ሲሉ ይጠይቃሉ የጸሎት አባቱ ያዕቆብ ቡችሌ ግራ መጋባት እና ሐዘን በተጫነው ድምጽ።
"የሰይጣን ሥራ ይሁን፤ የእግዚአብሔር ጥሪ ይሁን ምንም ማወቅ አልቻልንም። ለጌታ ሰጥተን ሁላችንም ቁጭ ብለናል" ይላሉ።
አቶ ያዕቆብን እንዲህ ያስመረራቸው በጂንካ ከተማ የምትገኘው "ቁጥር 6" ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ሦስት መሪዎች በቀናት ልዩነት ሕይወታቸው ማለፉ ነው።
በመላው ኢትዮጵያ የምትገኘው ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ቅርንጫፍ ሆነችው ይህቺ አጥቢያ የተመሠረተችው በ2011 ዓ.ም. ነበር። ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያኗ አባላት ሐዘን እና ድንጋጤ ውስጥ ናቸው።
አንዳንዶች፤ የቤተ ክርስቲያን አባቶቹ ሕይወት ለማለፉ ምክንያት ይሆናል ያሉትን ግምት ያስቀምጣሉ። ሌሎች ደግሞ ከዚህም ከዚያም ከሚሰሙት ማብራሪያ በስተቀር 'እንዲህ ነው' የሚሉት ነገር የላቸውም።
ይህ ሁሉ የተጀመረው የቤተ ክርስቲያኗ ምዕመን የሆነው ኢንጂነር አለማየሁ (የግለሰቡ ስም ተቀይሯል) ሲታመም ነው። አለማየሁ በግንቦት 2010 ዓ.ም. ከባለቤቱ ጋር ወደ ጂንካ የመጣው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በከተማዋ የሚያስገነባው ሕንጻ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ነው።
በከተማዋ "መሃል አራዳ" አካባቢ እየተካሄደ ያለው የሕንጻ ግንባታ የማጠናቀቂያ ሥራዎች ብቻ ቀርተውታል።
የፕሮጀክት ማናጀሩ ባለቤት እመቤት እንየው ደግሞ አካባቢው ላይ አነስተኛ ምግብ ቤት አላት። የስድስት ዓመት ዕድሜ ያላት ልጃቸውን የወለዱት ወደ ጂንካ ከሄዱ በኋላ ነው።

የንግድ ባንኩን ሕንጻ "አፍርሶም፣ ቀይሶም የሠራው እሱ ነው፤ ማንም ያውቃል" ትላለች ባለቤቱ እመቤት። ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጂንካ ከተማ ነዋሪዎችም የሚያስረዱት ይህንኑ ነው። በተለይም ምዕመን ከሆነባት ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ጋር በተያያዘ በጥሩ ያነሱታል።
አለማየሁ በጥቅምት መጀመሪያው ህመሙ ሲጀምረው 'የብርድ በሽታ ይሆናል' የሚል ግምት እንደነበረው እመቤት ታስታውሳለች። ረቡዕ ጥቅምት 5/2018 ዓ.ም. ወደ ጤና ተቋም ሄዶ መርፌ ቢወጋም፤ ይብስኑ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና ትኩሳት ማሳየት ጀመረ።
ሐኪሞች የፈሳሻ እጥረት እንዳጋጠመው፣ ቆይቶ ደግሞ የኩላሊት 'ኢንፌክሽን' እንደሚታይበት ተናገሩ። "ወባ ተደብቆ ሊሆን ይችላል ብለን ወባ ስናሠራ 'የጭንቅላት ወባ ነው' አሉን። ከእሁድ በኋላ ማስመለስ [ጀመረ]፤ የሚገባ ምግብ አይቀመጥም። የትኛውንም ፈሳሽ ይወጣል" ስትል በሽታው እየተባባሰ መሄዱን ታስረዳለች።
አለማየሁ ወደ ጂንካ ጠቅላላ ሆስፒታል የገባው ከሳምንት በኋላ ረቡዕ ጥቅምት 13 ቀን ነበር። መታመሙን የሰሙ የቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን አባቶች ብቻውን አልተዉትም። ምዕመን የሆነባት "የቁጥር 6" አጥቢያ መሪዎች መምህር ጳውሎስ ማቴዎስ፣ ፍሬሁን ፈቃዱ እና መምህር እቃሌ ጋልኮ ሊያስታምሙ እና ሊጸልዩ አጠገቡ ተገኝተዋል።
በከተማው የምትገኘው ሌላኛው ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ መጋቢ የሆኑት ፓስተር ሚልኪያስ አምባዬም በሆስፒታሉ የተገኙ ሌላኛው የሃይማኖት አባት ናቸው። ፓስተር ሚልኪያስ፤ አለማየሁ "ይወራጭ" እንደነበር ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Fikreab Lukas
በዚህ ምክንያት የጤና ባለሙያዎች ሕክምና ለማድረግ ተቸግረው እንደነበር የሚያስታውሱት ፓስተር ሚልኪያስ፤ ታማሚውን "በመያዝ" ሲያግዙ እንደነበር ይገልጻሉ። በታማሚው ላይ "እጃቸውን ጭነው" ጸሎት ማድረጋቸውም ያስረዳሉ።
ፓስተር ሚልኪያስ እና መምህር እቃሌ ጸሎት አድርገው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ቀሪዎቹ ሁለት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እያስታመሙ በሆስፒታል አድረዋል።
ከምሽት 12 ሰዓት ጀምሮ የአለማየሁ ሁኔታ እየተባባሰ ከሄደ በኋላ፤ ሌሊት ስድስት ሰዓት ገደማ ላይ "ሰውነቱ እየቀዘቀዘ" መጣ።
እመቤት፤ "እስከ [ሌሊት] ስድስት ሰዓት ድረስ 'መድኃኒትም ግዙ' እየተባለን ውጪ እየሮጥን ነበር። 'ይተርፋል፣ ምንም አይሆንም' [ብለው] ተስፋ እየሰጡን ነበር። ነገር ግን 'ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል ይግባ' አሉን፤ ሮጠን ይዘን ሄድን። ሾክ በሚያደርጉበት ሲሉት ሕይወቱ አልፏል" በማለት ቅጽበቱን ታስታውሳለች።
በማግስቱ ጠዋት ወደ ቤተ ክርስቲያኗ በማምራት የአለማየሁ ሕይወት ማለፉን ለምዕመናን የተናገሩት በሆስፒታል ያደሩት መምህር ጳውሎስ እና ፍሬሁን ናቸው። ቀጥሎ የነበሩት ነገሮች የተከናወኑት በፍጥነት ነው። ብዙ ምዕመናንም የግለሰቡን ሞት አልሰሙም። አስከሬኑ በመኪና ተጭኖ ወደ ቢሾፍቱ ከተማ ተሸኘ።
ምክንያቱ በውል ካልታወቀው የአለማየሁ ሞት በኋላ የከተማዋ እንቅስቃሴ ከወትሮው የተለየ ነገር አልታየበትም። የቤተ ክርስቲያኗ መሪዎችም የዘውትር አገልግሎታቸውን ቀጥለው ነበር፤ ቢያንስ እስከ ቀጣዩ ሳምንት ድረስ።

የፎቶው ባለመብት, Jinka Town Communication
የመጀመሪያውን ታካሚ በሆስፒታል የጎበኙት የሃይማኖት አባቶች የሕመም ምልክት ማሳየት የጀመሩት ከአለማየሁ ህልፈት አንድ ሳምንት በኋላ ነበር።
ከፍተኛ ትኩሳት፣ ማስመለስ እና ማስቀመጥ በአራቱም የሃይማኖት አባቶች ላይ የታዩ ምልክቶች እንደነበሩ ከሃይማኖት አባቶቹ አንዱ የሆኑት ፓስተር ሚልኪያስ፣ የታማሚዎቹ ቤተሰቦች እና የጤና ባለሙያዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የቃለ ሕይወት ቁጥር 6 ቤተ ክርስቲያን ሰብሳቢ የሆኑት ፍሬሁን በሽታው እየባሰባቸው ሲሄድ ወደ ጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል መወሰዳቸውን እህታቸው ፋናዬ ፍቃዱ ታስረዳለች።
"ሆስፒታል ሲወሰድ በጣም ከባድ ሙቀት፣ ይሄ ነው የማይባል ራስ ምታት [ያዘው]። ሰውነቱ ላይ ውሃ ስንጨምር ውሃው የባሰ እየጋለ እንፋሎት ሁሉ ከሰውነቱ ላይ ይነሳል" ስትል የወንድሟን ሁኔታ ገልጻለች።
ፋናዬ እንደምትናገረው፤ የቤተ ክርስቲያኗ ዋና ፀሐፊ ከሆኑት መምህር ጳውሎስ እና ከሂሳብ ሹሙ መምህር እቃሌ ጋር ሲነጻጸር የፍሬሁን ሁኔታ የተሻለ ነበር። ከሁለቱ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች "በነስር መልክ ብዙ ደም ይወርድ" እንደነበር ታስታውሳለች።
ፓስተር ሚልኪያስም እንደሌሎቹ ታማሚዎች ደም መፍሰስ እንዳላጋጠማቸው ተናግረዋል። አራቱም ግለሰቦች ግን በተመሳሳይ ከኩላሊት ጋር የተያያዘ ህመም ታይቶባቸዋል።
በሽታው እጅጉን የጠናው በቤተ ክርስቲያኗ የሂሳብ ሹሙ እቃሌ ላይ ነበር። መምህር እቃሌ ጥቅምት 29/2018 ዓ.ም. ጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ሕይወታቸው አለፈ።
የዚህ ጊዜ ቀሪዎቹ የሃይማኖት አባቶች ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ሐዋሳ ከተማ ተላኩ። መምህር ጳውሎስ እና ፍሬሁን በሐዋሳ ከተማ የተደረገላቸው ሕክምና ሕይወታቸውን ሊታደግ አልቻለም። በአንድ ቀን ልዩነት ኅዳር 1 እና ኅዳር 2/2018 ዓ.ም. አርፈዋል።
ቀጥሎ ደግሞ ሕክምና ያደረጉላቸው የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ሐኪም ዶ/ር ጌታሁን አብዩ እና ነርስ አማኑኤል ካሳ የህመሙን ምልክቶች አሳይተው አርፈዋል።
የነርስ አማኑኤል ባለቤት ቤተልሔም ገበየሁ፣ የመምህር ጳውሎስ ነፍሰ ጡር ባለቤት ፀሐይ ማቲዮስ እንዲሁም የመምህር እቃሌ ወንድም እንዲሁ በተመሳሳይ መልኩ ሕይወታቸው አልፏል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የማርበርግ ቫይረስ
ሁለቱ የጂንካ ጠቅላላ ሆስፒታል የጤና ባለሙያዎች ሕይወታቸው ያለፈው "በሽታው ምን እንደሆነ ባለማወቃቸው ምክንያት ያለ ጥንቃቄ ሕክምና" በመስጠታቸው እንደሆነ አንድ የአካባቢው ጤና ዘርፍ ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ኃላፊው፤ ጤና ሚኒስቴር ከበሽታው ጋር በተያያዘ የሚወጡ መረጃዎች ላይ ባስቀመጠው አሠራር ምክንያት ስማቸውን እንዳይጠቀስ ጠይቀዋል።
ኃላፊው እንደሚናገሩት፤ የጤና ባለሙያዎቹ ሕይወት ማለፍ የአሪ ዞን እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጤና ቢሮ ኃላፊዎች ለበሽታው የተለየ ትኩረት እንዲሰጡት አድርጓል። ከዚህ ክስተት በኋላ የታማሚዎች ናሙና ወደ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተልኮ ምርመራ መደረጉን ያስረዳሉ።
የጤና ሚኒስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምንነቱ በውል ያልታወቀ የሔሞራጂክ ፊቨር በሽታ በጂንካ ከተማ መከሰቱን ያሳወቁት የአለማየሁ ሕይወት ካለፈ ከ20 ቀናት በኋላ ኅዳር 3/2018 ዓ.ም. ነበር። ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ በሽታው የማርበርግ ቫይረስ እንደሆነ መረጋገጡን ይፋ አድርገዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጤና ዘርፍ ኃላፊ እንደሚያስረዱት ሕይወታቸው በቀናት ልዩነት ያለፈው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መምህር ጳውሎስ፣ መምህር እቃሌ እና ፍሬው በማርበርግ ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል። የመምህር ጳውሎስ ባለቤት እና የመምህር እቃሌ ወንድምም በተመሳሳይ ሕይወታቸው ያለፈው በቫይረሱ ተይዘው ነው።
ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ሐዋሳ ተልከው የነበሩት ፓስተር ሚልኪያስ ቫይረሱ እንዳልተገኘባቸው ተናግረዋል።
የመጀመሪያው ታማሚ እና ሁለቱ ጤና ባለሙያዎች የበሽታውን ምልክት አሳይተው ሕይወታቸው ቢያልፍም፤ በማርበርግ ቫይረስ መያዛቸው በላብራቶሪ ምርመራ እንዳልተረጋገጠ ኃላፊው አስረተድተዋል።

ይህም ቢሆን ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ለተከሰተው የማርበርግ ቫይረስ የመጀመሪያው ታማሚ (index case) ተብሎ የሚቆጠረው አለማየሁ እንደሆነ ገልጸዋል። "አለማየሁ ኢንዴክስ ተደርጎ የተወሰደው ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች ታምመው፤ ቫይረሱ የተገኘው ሰዎቹ ላይ ስለሆነ ነው" በማለት አብራርተዋል።
እመቤትም፤ ከፌደራል እና ከክልል ተቋማት የመጡ የጤና ባለሙያዎች ወደ ቤቷ መጥተው ከባለቤቷ ህመም ጋር የተያያዙ መረጃዎችን መሰብሰባቸውን ለቢቢሲ ተናግራለች።
ቢቢሲ፤ ስለ መጀሪያው ታማሚ እንዲሁም ንክኪ ስለነበራቸው የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ከጤና ሚኒስቴር መረጃ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም። የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ቡድን መሪ ዮርዳኖስ አለባቸው፤ በሽታው የተገኘባቸው ወይም ምልክት የታየባቸውን ሰዎች ዝርዝረው መናገር እንደማይችሉ አስረድተዋል።
እነዚህም መረጃዎች የሚገለጹት "በጤና ተቋም ደረጃ" እንደሆነም ጠቁመዋል። የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ እንዲሁም የጂንካ ከተማ ጤና ጽህፈት ቤት እና የአሪ ዞን ጤና መመሪያ በበኩላቸው መረጃዎች የሚገለጹት በጤና ሚኒስቴር ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።

ጂንካ ውስጥ ማርበርግ ቫይረስ ከየት መጣ?
በ1959 ዓ.ም. በሽታው ለመጀመሪያ ጊዜ ከተከሰተባት የጀርመኗ ማርበግ ከተማ ስያሜውን ያገኘው ይህ ቫይረስ፤ ከ24 በመቶ እስከ 88 በመቶ የመግደል ምጣኔ አለው። ማርበርግ እና ኢቦላ፤ ምንም እንኳ በተለያዩ ቫይረሶች የሚፈጠሩ ቢሆኑም፤ "ተመሳሳይ ቤተሰብ" ውስጥ እንደሚካተቱ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
በድንገት የሚከሰት የሰውነት ሙቀት መጨመር፣ ከፍተኛ ራስ ምታት እና የጡንቻ ህመም ከቫይረሱ ዋነኛ መገለጫዎች መካከል ናቸው። በበሽታው የተያዘ ሰው ከሦስተኛው ቀን አንስቶ ከፍተኛ የሆነ ማስቀመጥ፣ የሆድ ህመም እና ማስመለስ ይታይበታል።
ከአምስተኛው ቀን ጀምሮ ደግሞ ትው��ት ላይ ደም ሊታይ ይችላል። ከአፍ፣ ከአፍንጫ እና ከሴቶች መራቢያ አካል ደም መፍሰስ የሚጀምረውም ከዚህ በኋላ ነው።
የማርበርግ ቫይረስ መነሻው "ሩሰተስ (ኢጂፕትያን) ፍሩት" የተሰኙት የሌሊት ወፎች ናቸው። የሌሊት ወፎቹ በብዛት ለሚገኙባቸው "የማዕድን ቦታዎች ወይም ዋሻዎች ለረጅም ጊዜ የተጋለጡ ሰዎች" ቫይረሱ ሊተላለፍባቸው እንደሚችል የዓለም የጤና ድርጅት ይገልጻል። ከእንስሳቱ ወደ ሰው የገባው ቫይረስ ደግሞ በንክኪ ወደ ሌሎች ሰዎች ይተላለፋል።
ለምሳሌ በጥቅምት 2010 ዓ.ም. በዩጋንዳ የተከሰተው የማርበርግ ቫይረስ የመጀመሪያ ታማሚ፤ የሌሊት ወፎች በከፍተኛ ብዛት በሚገኙበት ዋሻ አቅራቢያ ይኖር የነበረ ግለሰብ ነው።
በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የነበረው ይህ ግለሰብ ወደ ሆስፒታል ሪፈር በተደረገበት ዕለት ሕይወቱ ያለፈ ሲሆን፣ በቫይረሱ መያዙ በምርመራ አልተረጋገጠም። ከእርሱ ሞት በኋላ በእህቱ ላይ የማርበርግ ቫይረስ ተገኝቷል።

የፎቶው ባለመብት, WHO
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ታማሚ ይሠራ በነበረበት የግንባታ ስፍራ ላይ የሚገኙ የሌሊት ወፎች ለመጀመሪያ ጊዜ በጂንካ ለተከሰተው የማርበርግ ቫይረስ መነሻ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቢቢሲ ካደረጋቸው ቃለ መጠይቆች የተገኙ መረጃዎች አመላክተዋል።
ግለሰቡ በፕሮጀክት ማናጀርነት በሚያስገነባው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንጻ ውስጥ የሌሊት ወፎች መገኘታቸውን ባለቤቱ እመቤት፣ አንድ የጤና ዘርፍ ኃላፊ እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በግንባታው ስፍራ አነስተኛ ምግብ ቤት ያላት እመቤት እንደምታስረዳው፤ የሕንጻው ምድር ቤት ውስጥ "የሌሊት ወፍ ይቀመጣል።"
"ሁሌም ሌሊት ሌሊት፤ የሌሊት ወፍ [ከሕንጻው] በጀርባ በኩል ይወጣል። እኛ የምንሠራው በፊት ለፊት ነው። የሌሊት ወፍ አለ፤ ሕንጻው ስርም ውሃ አለ" ትላለች። ከዚህም በተጨማሪ በተደጋጋሚ የሌሊት ወፎች ተንጠልጥለው እና ከሕንጻው መስታወት ጋር ተጋጭተው ይገኙ እንደነበር ታስረዳለች።
"ማታ ማታ ከሕንጻው መስታወት ጋር ተጋጭተው በምንሠራበት በኩል ይሞታሉ። በዚያ ሰዓት ጠርገን እናነሳለን። እርሱም [ባለቤቷ] ከእኛ ጋር ይገባል። ጠዋት ላይ ምግቡን ስለሚያስተባብርልኝ ይገባል። ያው በእጅ አንነካም በመጥረጊያ እናነሳለን" ስትል የሌሊት ወፎች ለግንባታው አካባቢ አዲስ አለመሆናቸውን ትገልጻለች።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጤና ዘርፍ ኃላፊም በሕንጻው ላይ የሌሊት ወፎች "በብዛት" መገኘታቸውን አረጋግጠዋል። "የሌሊት ወፎቹ እሳቸው [የመጀመሪያው ታማሚ] ሲሠሩ በነበሩበት ግንባታ ውስጥ በጣም በብዛት [ተገኝተዋል]" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Samson Ayele
የቫይረሱ ተሸካሚ የሆኑት እንስሳት በመጀመሪያው ታማሚ የሥራ ቦታ "ቀጥታ መገኘታቸው በኋላ ለተደረገው ምርመራ ትልቅ ፍንጭ" እንደሰጠ አብራርተዋል።
ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ያለው የንግድ ባንክ ሕንጻ በአሁኑ ወቅት ጥበቃ እየተደረገለት እንደሆነ እመቤት እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል። እመቤት፤ "አሁን በፖሊስ ተከልሎ ጥበቃ እየተደረገ ነው። መድኃኒት ረጭተዋል። መጀመሪያ ከመርጨታቸው በፊት ለናሙና የሌሊት ወፍ ተወስዷል። ግራውንድ ላይ አሉ" ብላለች።
የጤና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ቡድን መሪው ዮርዳኖስ፤ "እዚያ አካባቢ 'የሌሊት ወፎች አሉ' ተብሎ እየተጠና ነው" ሲሉ የቫይረሱን መነሻ የማረጋገጥ ሥራ በሂደት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
ማርበርግን በተመለከተ የሚደረጉት ጥናቶች ቫይረሱ "እንዴት ሊመጣ ቻለ? መነሻው ምንድነው? አሁንስ የመራባት መጠኑ ምንያህል ነው?" የሚሉት ጉዳዮች እንደሚዳሰሱ ጠቅሰዋል።
ጥናቱ ሲጠናቀቅ ግኝቶቹ ይፋ እንደሚደረጉም አክለዋል። የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ኅዳር 8/2018 ዓ.ም. የማርበርግ ቫይረስን በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅትም ተመሳሳይ ሀሳብ አንስተው ነበር።
ቫይረሱ 'እንዴት ከሌሊት ወፍ ወደ ሰው ተላለፈ?' የሚለውን የሚያጠና "አንድ አጠቃላይ ቡድን" ወደ ስፍራው መላኩን ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ በአካባቢው የሚገኙ የሌሊት ወፎችን የሚያድን የባለሙያዎች ቡድን መሠማራቱንም አስታውቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Jinka Town Communication
"'መድኃኒት አብልታቸው ነው' ተብዬ ታሰርኩ"
እመቤት፤ ባለቤቷን የቀበረችው በትውልድ ከተማው ቢሾፍቱ ነው። ከ10 ቀናት ገደማ በኋላ ወደ ጂንካ ተመልሳለች። የአካባቢው ነዋሪዎች እና የሚያውቋቸው ሰዎችም ለቅሶ ደርሰዋታል።
ከሳምንት ገደማ ቆይታ በኋላ ሦስቱ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም በጽኑ መታመማቸውን ተከትሎ ጥርጣሬ ይነሳባት ጀመር። "እሷ ቤት መድኃኒት በልተዋል" የሚል ውንጀላ እንደመጣባት ትናገራለች።
"ሻይ፣ ቡና ይዘው መጥተው፣ ዳቦ አስደፍተው 'እግዚአብሔር ያጽናሽ' ብለውኝ ሄደዋል። 'አይ እሷ ባሏንም ገድላ ይሆናል' የተባልኩት ከዚያ በኋላ ነው" ትላለች። የሁለተኛው የቤተ ክርስቲያን መሪ ሕይወት ባለፈበት ኅዳር 1 ቀን ፖሊስ በቁጥጥር እንዳዋላት አስረድታለች።
የጤና ሚኒስቴር በአካባቢው የማርበግር ቫይረስ መከሰቱን ይፋ ያደረገው እመቤት በእስር ላይ እያለች ነበር። ይህንን ተከትሎም ከ10 ቀናት እስር በኋላ ፍርድ ቤት በ20 ሺህ ብር ዋስትና እንድትለቀቀ ወስኖላታል።
ባለቤቷን ባጣች በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለእስር የተዳረገችው እመቤት፤ "'እውነቱን አውጣልኝ ብዬ' ፈጣሪዬን አምርሬ እየጠየኩ ነበር" ብላለች።
"[የቤተ ክርስቲያን መሪዎቹ] መልካም ሰዎች ናቸው፤ አፈሩን ያቅልላቸው። ለእኔ ግን በጣም ያስጠላል፤ ከሐዘንም ሐዘን የጨመረብኝ እርሱ ነው" ስትል የቀረበባት ውንጀላ የፈጠረባትን ስሜት አስረድታለች።

የፎቶው ባለመብት, South Ethiopia Health Bureau
ምንም እንኳ ባለቤቷ የበሽታው ምልክቶች የታዩበት የመጀመሪያው ታማሚ ስለመሆኑ የጤና ባለሙያዎች እና ኃላፊዎች ቢናገሩም፤ እመቤት አታምንበትም። እርሷ እና የስድስት ዓመት ልጇ እንዲሁም ያስታመሙት እና አስከሬኑን የገነዙ ሰዎች በበሽታው አለመያዛቸው በመጥቀስ ትከራከራለች።
"እኔ ለማመን እቸገራለሁ። '[እሱ] ነው' ከተባለም ችግር የለብኝም። እሱን ከአፈር የሚመልስልኝ ምንም ነገር የለም። ይሄ ህመም ከላይ ጥቁር ለብሰህ እንደምትገልጸው ሳይሆን የውስጥ በሽታ ስለሆነ በጣም ያምማል። ስጠየቅ ሁሉ ያመኛል" በማለት ለቢቢሲ ተናግራለች።
በአሁኑ ሰዓት እመቤት ከሰዎች ጋር ያላትን ግንኙነት እንድትገድብ በጤና ባለሙያዎች ተነግሯታል። የሌሎች ሟቾች ቤተሰቦችም ተመሳሳይ የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወስዱ እንደተደረጉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ማርበርግ ቫይረስ የተገኘባት ጂንካ ከተማ በሽታውን ለመቆጣጠር የምታደርገውን ጥረት አጠናክራለች። ከተማዋ የምትገኝበት አሪ ዞንም እስከ ኅዳር 26 ቀን የቆየ የአንድ ሳምንት የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች ገደብ አድርጎ ነበር።
ትናንት እሁድ ኅዳር 28 የወጣው የጤና ሚኒስቴር ዕለታዊ መረጃ እንደሚያሳየው 13 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ ተረጋግጧል። ከእነዚህ ውስጥ ስምንቱ ሕይወታቸው አልፏል። አራት ሰዎች ደግሞ አገግመዋል።















