በደቡብ ኢትዮጵያ የተከሰተው ደም መፍሰስ የሚያስከትለው በሽታ ምንድን ነው? ሕክምናስ አለው?

የላብራቶሪ ምርመራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጂንካ ከተማ ውስጥ ምንነቱ በውል ባልታወቁ በሽታ የተያዙ የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ቢቢሲ በአካባቢው ካለ የሕክምና ተቋማት እና ባለሙያዎች ተረድቷል።

በበሽታው ከሞቱት ስድስት ሰዎች መካከል ለታማሚዎች ሕምክና ሲሰጡ የነበሩ ሁለት የጤና ባለሙያዎች እንደሚገኙበት ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በበሽታው የተያዙ ሰዎች የተለያዩ ምልክቶችን የሚያሳዩ ሲሆን የበሽታው ምልክታ የታየባቸው ታማሚዎች ላይ "በፍጥነት የኩላሊት ሥራ የማቆም" እንደሚያጋጥማቸው ተገልጿል።

የፌደራል ጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በደቡብ ኢትዮጵያ "ምንነቱ በመረጋገጥ ላይ ያለ የሔሞራጂክ ፊቨር" በሽታ መከሰቱን ኅዳር 3/2018 ዓ.ም. በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

እንዲህ ያለው በሽታ ምንድን ነው? ከሌሎች በሽታዎች ጋር ይዛመዳል? ምልክቶቹ ምንድን ናቸው? እንዴት ይተላለፋል? ሕክምናስ አለው?

ቫይራል ሔሞራጂክ ፊቨር ምንድን ነው?

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ቫይራል ሔሞራጂክ ፊቨር (Viral haemorrhagic fever) ለተለያዩ የቫይረስ ሕመም ዓይነቶች የተሰጠ የወል ስም ነው። ቢጫ ወባ፣ የደንጊ ትኩሳት (dengue fever) እና ኢቦላ ተጠቃሽ ናቸው።

ክሪሚያን-ኮንጎ ሔሞረጂክ ፊቨር (Crimean–Congo haemorrhagic fever) እና ሪፍት ቫሊ ፊቨር (Rift Valley fever) የተባሉት በሽታዎችም እዚህ ውስጥ እንደሚካተቱ የዓለም የጤና ድርጅት በድረ ገጹ ያሰፈረው መረጃ ያስረዳል።

ሔሞራጂክ ፊቨር፤ በዋናነት የሰውነትን የደም ዝውውር (vascular system) የሚጎዳ እና ሰውነት ራሱን የሚቆጣጠርበትን አቅም የሚያሳጣ ነው። ሕይወትን እስከመቅጠፍ የሚደርስ ሕመም እንደሆነም ተገልጿል።

የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ትናንት ባወጡት መግለጫ፤ በጂንካ ከተማ የተከሰተው ሔሞረጂክ ፊቨር "ምንነቱ በመረጋገጥ" ላይ እንደሆነ አስታውቀዋል።

የሕመሙ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

የጤና ሚኒስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ባወጡት መግለጫ ላይ የሕመሙ ምልክቶች እንደሆኑ ከዘረዘሯቸው ውስጥ "በአፍ፣ አፍንጫ እና ሌሎች የሰውነት ክፍሎች መድማት" የሚለው ይገኝበታል። "ትኩሳት፣ ማስቀመጥ እና ማስመለስም" በምልክትነት ተጠቅሰዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ ድንገተኛ የጡንቻ ሕመም፣ ራስ ምታት እንዲሁም እና ከደም መፍሰስ ጋር የተያያዘ ሾክን በተጨማሪ ምልክትነት አስፍሯል። ሕመሙ የሰውነት ክፍሎችን መደበኛ ሥራ የሚያስተጓጉል (organ failure የሚያስከትል) እንደሆነም የተቋሙ መረጃ ያሳያል።

የሕመሙ የመጀመሪያ ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ድካም፣ የጡንቻ ሕመም እና ምቾት አለመሰማት ናቸው። ሕመሙ እየተባባሰ ሲሄድ የሆድ ሕመም፣ ማስመለስ፣ ማስቀመጥ፣ የቆዳ መቆጣት እንዲሁም ፊት እና ደረት ላይ የሚሰማ ሙቀት ያስተዋላል።

ሕመሙ በተባባሰባቸው ሰዎች ላይ ከመጠን ያለፈ ደም መፍሰስ (haemorrhaging) ይከሰታል። ከአፍ እና ከአፍንጫ እንዲሁም ከሌሎች የሰውነት ክፍሎችም ደም ይፈሳል።

የሕመሙ የመጀመሪያ ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ድካም፣ የጡንቻ ሕመም እና ምቾት አለመሰማት ናቸው።

ሕመሙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ከፍተኛ ደም መፍሰስ እና ሞት ያስከትላል።

እንዴት ይተላለፋል?

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፤ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ቀጥተኛ የአካል ንክኪ ወይም በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ሰውነት የሚወጣ ፈሳሽ ወይም ደም መንካት ሕመሙ እንዲተላለፍ ያደርጋል።

ክሪሚያን-ኮንጎ ሔሞረጂክ ፊቨር እና ሪፍት ቫሊ ፊቨር በተባሉት የሕመሙ ዓይነቶች በበሽታው የተያዙ እንሰሳትን ጥሬ ሥጋ እና ወተት መመገብ ለበሽታው እንደሚያጋልጥ ተጠቅሷል።

እንደ ሪፍት ቫሊ ፊቨር እና ደንጌ ፊቨር ባሉት የሕመሙ ዓይነቶች ደግሞ የወባ ትንኝ ንክሻ በሽታውን እንደሚያስተላልፍ ተገልጿል።

ሮደንትስ (rodents) የተባሉት የአይጥ ዝርያዎችም በሽታውን እንደሚያስተላልፉ ተጠቅሷል።

ሕመሙን እንዴት መከላከል ይቻላል?

የጤና ሚኒስቴር "ምልክት ከታየበት ሰው ጋር ንክኪ በሚኖርበት ጊዜ ራስን የመከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም" እንደሚያስፈልግ አሳስቧል። "ሁልጊዜ እጅን በሳኒታይዘር ወይም በውሃ እና ሳሙና በመታጠብ ማጽዳት" እንደሚያሻም ተገልጿል።

የዓለም ጤና ድርጅት 'viral haemorrhagic fevers' ወይም በምጽሐረ ቃሉ 'VHFs' በሚል አጠቃላይ መጠሪያ የጠቀሰውን ሕመም "በመላው ዓለም እየተባባሰ የመጣ ስጋት ነው" ሲል ይገልጸዋል።

አጠቃላይ የሕመሙን ዓይነቶች ለማከም የሚውል መድኃኒት እንደሌለ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ይጠቁማል።

ሆኖም ግን የቢጫ ወባ እና ኢቦላ ክትባቶች የሕመሙን ዝርያዎች ለመከላከል እንደሚረዱ ተገልጿል። በሕመሙ የተያዙ ሰዎች ትኩሳታቸው እንዲቀንስ በማድረግ፣ የመተንፈሻ አካላቸው በአግባቡ እንዲሠራ ኦክስጅን በመስጠት እና በሌሎችም መንገዶች የሕክምና እርዳታ ይሰጣቸዋል።