"በዓለም ዙሪያ በየ10 ደቂቃው አንድ ሴት በፍቅረኛዋ ወይም በቤተሰቧ አባል ትገደላለች"

ፀረ የሴቶች ጥቃት ንቅናቄ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በዓለም ዙሪያ በየ10 ደቂቃው አንዲት ሴት በምታውቀው ሰው ትገደላለች። ገዳዩ የፍቅር አጋሯ፣ ባለቤቷ ወይም ቤተሰቧ ሊሆን እንደሚችል አዲስ የወጣ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ይጠቁማል።

በተመድ ሪፖርት መሠረት በየቀኑ 137 ሴቶች ይገደላሉ። ይህም በመላው ዓለም በአዋቂ ሴቶች እና በታዳጊ ሴቶች ላይ ከሚፈጸም ግድያ 60 በመቶ ነው።

ፀረ የሴቶች ጥቃት ቀን ኅዳር 4/2018 ዓ.ም. ውሏል ታስቦ ውሏል። ሪፖርቱም ቀኑን ታሳቢ አድርጎ ነው ይፋ የተደረገው።

የመንግሥታቱ ድርጅት እንደሚለው ሴቶች በዋነኛነት የሚገደሉት በመኖሪያ ቤታቸው ሳሉ መሆኑ እጅግ አስጊ ነው።

ሴቶች ላይ ያነጣጠረ ግድያ (Femicide) ከመኖሪያ ቤት ውጪም ይፈጸማል። በበቂ ሁኔታ ግን መረጃ አልተሰበሰም።

የተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ጉዳይ ፖሊሲዎች ክፍል ኃላፊ ሳራ ሄንድሪክስ "ሴቶች ላይ ያነጣጠረ ግድያ ድንገት የሚከሰት አይደለም። መነሻው ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ ተከታታይ ጥቃት፣ ትንኮሳ እና ዛቻ ነው። ይህም በበይነ መረብም በአካልም ይፈጸማል" ይላሉ።

ዓለም አቀፍ ቀውስ

በሴቶች ላይ በሚፈጸም ግድያ በዋነኛነት የተስፋፋው በአፍሪካ ነው። ግድያው አብዛኛውን ጊዜ የሚፈጸመው በቅርብ የፍቅር አጋሮቻቸው ወይም በቤተሰቦቻቸው ነው።

ከአፍሪካ በመቀጠል በብዛት ሴቶች የሚገደሉት በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ (1.5 በመቶ)፣ በኦሺኒያ (1.4 በመቶ ) እና በአውሮፓ (0.5 በመቶ) ነው።

በ2024 በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም በአውሮፓ ሴቶች የተገደሉት ከቤተሰቦቻቸው በበለጠ በፍቅር አጋሮቻቸው ነው።

በተመድ ሪፖርት መሠረት ግድያው በአውሮፓ 64 በመቶ ሲደርስ በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ 69 በመቶ ይጠጋል።

በአልባኒያ ከተገደሉ ሴቶች መካከል 90 በመቶው ከመገደላቸው በፊት ጥቃት ደርሶባቸዋል። ጥቃት አድራሾቹ ከእስራት ተለቀው በቀናት ውስጥ የተገደሉም አሉ።

አብዛኞቹ ግድያዎች የተፈጸሙት በመሣሪያ፣ በስለት ወይም በድብደባ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት እንደሚጠቁመው፤ ቅናት፣ የፍቅር ጥያቄዬ ተቀባይነት አያገኝም የሚል ፍርሃት፣ ጥቃት የደረሰባት ሴት ለፖሊስ ጥቆማ በማድረጓ ለበቀል መነሳሳት እና ሴቶች ለምን አዲስ የፍቅር ግንኙነት ጀመሩ የሚል ዕሳቤ ከአብዛኞቹ ጥቃቶች ጀርባ ይጠቀሳሉ።

በሪፖርቱ ውስጥ እናቶቻቸው የተገደሉባቸው 35 ሕጻናትም ተካተዋል።

አፍሪካዊቷ ሌሶቶ በፍቅር አጋር በሚፈጸም ግድያ ቀዳሚ ስፍራ ይዛለች። ከ15 እስከ 49 ዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ሴቶች 44 በመቶ የሚሆኑት በአጋራቸው አካላዊ እና ወሲባዊ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ሪፖርት ማድረጋቸውን የአገሪቱ የወንጀል አሐዝ ያሳያል።

የተደራጀ በቂ መረጃ ባይገኝም እንኳን ሴቶች ላይ ያነጣጡ ግድያዎች የሚፈጸሙት የቅርብ ሰዎች በሆኑ የፍቅር አጋሮች እና የቤተሰብ አባላት መሆኑን ሪፖርቱ ይጠቁማል።

የቤት ውስጥ ጥቃት፣ ከልክ ያለፈ አልኮል እና ግጭት ወደ ግድያ ከሚያመሩ መካከል ተጠቅሰዋል።

የ39 ዓ��ቷ ኡጋንዳዊት የኦሊምፒክ አትሌት ረቤካ ቻፕቴጊ በቀድሞ ፍቅረኛዋ ተገድላለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የ39 ዓመቷ ኡጋንዳዊት የኦሊምፒክ አትሌት ረቤካ ቻፕቴጊ በቀድሞ ፍቅረኛዋ ተገድላለች

ከጥይት እስከ በይረ መረብ

ሴቶች ላይ ያነጣጠረ ግድያ እንዲባባስ ምክንያት ከሆኑ መካከል የመሣሪያ እና ቴክኖሎጂ መስፋፋትን ሪፖርቱ ይጠቅሳል።

"የፍቅር አጋር የመሣሪያ ባለቤት መሆን ለግድያ የመጋለጥ ዕድልን ይጨምራል። ከአንድ በላይ ተጎጂዎች ላይ ግድያ የመፈጸም ዕድሉም 70 በመቶ ከፍ ይላል" ሲል ሪፖርቱ ያትታል።

ቴክኖሎጂም ሴቶችን ለመቆጣጠር እየዋለ ነው።

በበይነ መረብ ሴቶችን መከታተል (online stalking)፣ ያለ ሴቶች ፈቃድ ግላዊ መረጃቸውን በበይነ መረብ ማጋራት (doxing) እና ምሥሎችን ማጋራት በዋናነት ይጠቀሳሉ።

ከግራ ወደ ቀኝ የሉዊስ እናት ሉዊስ እና እህቷ ሃና

የፎቶው ባለመብት, Contributed

የምስሉ መግለጫ, ከግራ ወደ ቀኝ የሉዊስ እናት ሉዊስ እና እህቷ ሃና

ከአውሮፓውያኑ 2011 እስከ 2014 በዩናይትድ ኪንግደም የተፈጸሙ 41 የቤት ውስጥ ጥቃቶች ላይ በተደረገው ምርመራ፤ 58.5 በመቶ በሚደርሱት ክስተቶች ሴቶችን ለመቆጣጠር እንዲሁም ከግድያ በፊት ለተፈጸመ ማስፈራሪያ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ውሏል።

ሴቶችን በበይነ መረብ መቆጣጠር፣ መከታተል እና መሰለል ወደ አካላዊ ጥቃት እንደሚሻገር ሪፖርቱ ያሳያል።

እንደ ጋዜጠኞች፣ የመብት ተሟጋቾች እና ፖለቲከኞች ያሉ በሕዝብ የሚታወቁ ሴቶች በቴክኖሎጂ ለታገሰ ጥቃት በዋነኛነት ተጋላጭ ናቸው።

የ38 ዓመት የቀድሞ ሞዴል  ክርስቲና ጆክሞቪክ ቤቷ አቅራቢያ በባለቤቷ ተገድላለች።

የፎቶው ባለመብት, Kristina Joksimovic/Instagram

የምስሉ መግለጫ, የ38 ዓመት የቀድሞ ሞዴል ክርስቲና ጆክሞቪክ ቤቷ አቅራቢያ በባለቤቷ ተገድላለች።

ሪፖርቱ ባስቀመጠው ምክረ ሐሳብ "አፋጣኝ እና ተገቢ እርምጃ ሊወሰድ" እንደሚገባ አሳስቧል።

የሴቶችን ጥቃት እና ግድያ ለማስቆም የሚውሉ ፖሊሲዎችን ማውጣት አንደኛው የመፍትሔ ሐሳብ ነው።

ለሴቶች ግድያ ምክንያት የሆኑት የመሣሪያ አቅርቦት፣ ሴቶችን መከታተል እና አደንዛዥ ዕጽ መጠቀምን በተመለከተ እርምጃዎች እንዲወሰዱም ጠይቋል።

ጠንካራ ሕጎች እንዲወጡ እንዲሁም እንዲተገበሩም አሳስቧል። ሪፖርቱ፤ ግድያዎች ከመፈጸማቸው በፊት የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው ይላል።

የኖርማ አንድሬስ ልጅ የሆነችው ለይላ በሜክሲኮ ታግታ፣ ስቅይት ተፈጽሞባት ተገድላለች።

የፎቶው ባለመብት, UN Women/Radhika Chalasani

የምስሉ መግለጫ, የኖርማ አንድሬስ ልጅ የሆነችው ለይላ በሜክሲኮ ታግታ፣ ስቅይት ተፈጽሞባት ተገድላለች።

የፆታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶች

  • ረቤካ ቻፕቴጊ - የ39 ዓመቷ ኡጋንዳዊት የኦሊምፒክ አትሌት በምዕራብ ኬንያ፣ ትራንስ ኖዚያ ግዛት በሚገኘው መኖሪያዋ ሳለች በቀድሞ የፍቅር አጋሯ ዲክሰን ንዴማ ጥቃት ደርሶባታል። ጋዝ አርከፍክፎ ካቃጠላት በኋላ ለቀናት ሕክምና ላይ ቆይታ ሕይወቷ አልፏል። ከመሬት ይዞታ ጋር በተያያዘ ጸብ ውስጥ ገብተው እንደነበር ተገልጿል።
  • ሉዊስ ሀንት - በዩናይትድ ኪንግደም የ25 ዓመቷ ሉዊስ እና የ28 ዓመት እህቷ ሃና በሉዊስ የቀድሞ የፍቅር አጋር ካይል ክሊፈርስ በስለት ተወግተዋል። ግለሰቡ መጀመሪያ ላይ እናታቸውን በስለት ወግቶ እህትማማቾቹ ላይ ጥቃት ፈጽሟል። ሉዊስ የፍቅር ግንኙነታቸውን ስታቆም በ2024 ሉዊስን ደፍሮ እሷ እና እህቷን በቀስት ገድሏል። ሦስት የዕድሜ ልክ እስራቶች ተፈርደውበታል። ሉዊስ የቢቢሲ የፈረስ ግልቢያ ዘጋቢ ጆን ሀንት ልጅ ነበረች።
  • ክርስቲና ጆክሞቪክ - የሚስ ስዊዘርላንድ የመጨረሻ ዙር ተወዳዳሪዋ የ38 ዓመት የቀድሞ ሞዴል በ2024 ቤቷ አቅራቢያ በባለቤቷ ተገድላለች። የሁለት ልጇቿ አባት የሆነው ባለቤቷ ግድያውን መፈጸሙን አምኗል። ግድያውን ከመፈጸሙ በፊት ፖሊሶች የቤት ውስጥ ጥቃት መፈጸሙን ሪፖርት ይደርሳቸው ነበር።
  • ለይላ አሌሀንድራ - የኖርማ አንድሬስ ልጅ የሆነችው ለይላ በሜክሲኮ ታግታ፣ ስቅይት ተፈጽሞባት ተገድላለች። እናቷ 'ልጆቻችን ቤታቸው ይመለሱ' የሚል ንቅናቄ ጀምራለች። "ልጄ ለይላ አንድ ቀን ቤት ሳትመጣ ቀረች። ከዚያ ቀን በኋላ አላየኋትም። ዓለሜ ፈረሰ። ልጄ ታፍና፣ ተሰቃይታ ነው የተገደለችው። በሱዳድ ሁራዝ ግዛት ብዙ ሴቶች ተገድለዋል። ለፍትሕ እየታገልን ነው" ትላለች ኖርማ።