በሂትለር ዘረ መል ላይ የተደረገው ጥናት ያስገኘው ውጤት እና የፈጠረው ሙያዊ ውዝግብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአዶልፍ ሂትለር ደም ላይ የተደረገው የዘረ መል (ዲኤንኤ) ትንታኔ ስለ አምባገነኑ የዘር ግንድ እና ሊኖሩ ስለሚችሉ የጤና ሁኔታዎች አንዳንድ ያልተለመዱ ግኝቶች ላይ ደርሷል።
የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ቡድን የተደረገው አስደናቂ ሳይንሳዊ ሙከራ ሂትለር የአይሁዶች የዘር ግንድ ነበረው የሚለውን ውድቅ ያደረገ ሲሆን፣ የመራቢያ አካል እድገት የሚጎዳ የዘረመል መታወክ እንደነበረበትም አሳይቷል።
ይህን ሁሉ ምርመራ ማድረግ የተቻለው በአንዲት እራፊ ጨርቅ ላይ ፈስሶ ከተገኘው ደም ላይ ከተወሰደ ናሙና ነው።
ትኩረት ለመሳብ የሚሞክሩ ዜና ርዕሶች የናዚው አምባገነን በጣም አነስተኛ ብልት እና አንድ የወንድ የዘር ፍሬ ብቻ ነበረው የሚል ላይ ያተኮሩ ቢሆንም፣ የእርሱ ዲኤንኤ "በጣም ከፍተኛ" ውጤት ያሳየበት ከአንድ በመቶ በላይ ለኦቲዝም፣ ለስኪዞፍሪኒያ እና ለባይፖላር ዲስኦርደር ተጋላጭ እንደነበር ያሳያል።
ይህ ማለት እነዚህ የነርቭ በሽታዎች ነበሩት ማለት ነው?
"በፍጹም አይደለም" ይላሉ ባለሙያዎቹ፤ ይህ የጤና ምርመራ አይደለም።
ሆኖም ግን፣ ስለ መገለል እና ጥናቱ ምን ያህል ሥነ ምግባራዊ ነበር የሚል ጥያቄ አስነስቷል፤ ይህም ጥናቱ መደረግ ነበረበት? የሚል ጥያቄ አስነስቷል።
ፕሮፌሰር ቱሪ ኪንግ በቻናል 4 ላይ በቀረበው ዘጋቢ ፊልም ላይ "በውሳኔው በጣም ተጨነቅኩ" ብለዋል።
የዘረ መል ባለሙያ የሆኑት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከበርካታ ዓመታት በፊት በፕሮጀክቱ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፉበት ወቅት እንደ አዶልፍ ሂትለር ያለ ሰውን ዲኤንኤ በማጥናት ላይ ሊኖረው የሚችለውን አንድምታ ጠንቅቀው ያውቁ ነበር።
"እኔ ነገሮችን የማራገብ ፍላጎት የለኝም።"
ነገር ግን በአንድ ወቅት በሆነ ሰው ሊሠራ እንደሚችል ይናገራሉ። እና ቢያንስ በእርሳቸው ክትትል ሥር ጥናቱ የተደረገው ጥብቅ በሆነ መስፈርት፣ በሁሉም "ማስጠንቀቂያዎች እና መከላከያ መንገዶች ተቀምጠው" መሆኑን ማረጋገጥ ይችላሉ።
ፕሮፌሰር ኪንግ ከፍተኛ ስም ላላቸው እና ትኩረትን በቀላሉ ለሚስቡ ፕሮጀክቶች እንግዳ አይደሉም።
በአውሮፓውያኑ 2012 በሌስተር የመኪና ማቆሚያ ሥር ተቀብሮ የተገኘው የሪቻርድ ሳልሳዊ አጽም ማንነት ከተረጋገጠ በኋላ የዘረ መል ምርመራውን መርተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Gettysburg Museum of History
ደም ነካው ጨርቅ አሁን 80 ዓመት ሞልቶታል፣ በሂትለር የመሬት ውስጥ መኖሪያ ውስጥ ካለው ሶፋ ተቆርጦ የተወሰደ ነው።
ይህ ሶፋ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ የኅብረቱ ኃይሎች ወደ በርሊን ሲቃረቡ ራሱን ያጠፋበት ነው።
የአሜሪካ ጦር ኮሎኔል ሮዝዌል ፒ ሮዘንግሬን ከመሬት በታች የተገነባውን ዋሻ ሲፈተሹ ልዩ ወታደራዊ ሽልማት የማግኘት ያህል ስለቆጠሩት ጨርቁን ወሰዱት። አሁን በመስታወት ተደርጎ በአሜሪካ በሚገኘው በጌቲስበርግ የታሪክ ሙዚየም ውስጥ ለዕይታ በቅቷል።
ሳይንቲስቶቹ የሂትለር ደም መሆኑን እርግጠኞች ናቸው። ምክንያቱም ከአስር ዓመታት በፊት ከተሰበሰበው የወንድ ዘመድ ከተወሰደውን የ‹ዋይ-ክሮሞዞም› የዲኤንኤ ናሙና ጋር በትክክል ማዛመድ ችለዋል።
አሁን በሌሎች ባለሙያዎች እየተደረገ ባለው ግምገማ በእርግጥም አስደናቂ ነው።
የሂትለር ዲኤንኤ ሲታወቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን በአራት ዓመታት ውስጥ ሳይንቲስቶች በዓለም ላይ ካሉት እጅግ ዘግናኝ አምባገነኖች አንዱ የሆነውን ግለሰብ የዘረመል ስሪት ለማየት ችለዋል።
ከአውሮፓውያኑ 1920ዎቹ ጀምሮ ሲሠራጭ እንደ ነበረው መረጃ ሂትለር የአይሁድ የዘር ግንድ ነበረው የሚለው ያልተረጋገጠ ሐሰተኛ ወሬ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ሌላው ቁልፍ ግኝት ካልማን ሲንድሮም የተባለ በጉርምስና እና በመራቢያ አካላት እድገት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው የዘረ መል መታወክ ነበረበት።
ይህ የዘረ መል መታወክ በጣም አነስተኛ የብልት መጠን እንዲኖር እና የዘር ፍሬ ከረጢቱ ባዶ እንዲሆን ወይም ወደ ውስጥ የገባው የዘር ፍሬው እንዳይወርድ ያደርጋል።
ይህም በብሪታኒያ ጦር ዘንድ በወቅቱ በሰፊው የሚወራ ነበር።
የካልማን ሲንድረም የወሲብ ፍላጎትን ሊጎዳ ይችላል፤ ይህም በተለይ ትኩረት የሚስብ ነው ሲሉ የታሪክ ምሁሩ እና የፖትስዳም ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር አሌክስ ኬይ በዘጋቢ ፊልሙ ላይ ተናግረዋል።
"ስለግል ሕይወቱ ብዙ ይነግረናል፤ ወይም በትክክል የግል ሕይወት እንዳልነበረው ያሳየናል" ሲሉ ያስረዳሉ።
ሂትለር ሙሉ በሙሉ ሕይወቱን ለምን ለፖለቲካ ሰጠ የሚለው የየታሪክ ተመራማሪዎች ለረጅም ጊዜ ሲከራከሩበት ኖረዋል።
"ከምንም በላይ ከማንኛውም ዓይነት የግል ሕይወት ራሱን አግልሎ ኖሯል" እና ይህ ደግሞ ለዚያ ማስረጃ በመሆን ያገለግላል።
ባለሙያዎቹ እንደዚህ ዓይነት ግኝቶች ናቸው ማራኪ እና ጠቃሚ የሚያደርጉት ይላሉ።
ፕሮፌሰር ኪንግ እንዳሉት "የታሪክ እና የዘረ መል ጋብቻ።"

የፎቶው ባለመብት, Tom Barnes/Channel 4
በጣም የተወሳሰቡ እና አወዛጋቢ የሆኑ ግኝቶች ሂትለር አንድ ወይም ከዚያ በላይ የነርቭ ወይም የአእምሮ ጤንነት ችግሮች ሊኖሩበት እንደሚችል የሚጠቁሙ ናቸው።
የእሱን ዘረ መል እና ሌሎች የተፈጥሮ መረጃ ውጤቶችን በማነፃፀር ሂትለር ለተለያዩ የእድገት ውስንነቶች እና ለአእምሮ ጤና ችግሮች የመጋለጥ ከፍተኛ አዝማሚያ እንደነበረው ደርሰውበታል።
ሳይንስ ውስብስብ የሚሆነው እዚህ ላይ ነው።
ፖሊጄኒክ የውጤት መለያ ከአንድ ሰው ዲኤንኤ ጋር ይያያዛል እናም ግለሰቡ ምን ያህል ለበሽታ ሊጋለጥ እንደሚችል ያሰላል።
ግለሰቡ እንደ የልብ ሕመም እና የተለመዱ ካንሰሮች የመጋለጥ አዝማሚያ ለማወቅ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የእሱን ዲኤንኤ ከብዙ ሰዎች ናሙና ጋር ማወዳደር ይጠይቃል። እና ስለዚህ ግኝቶቹ ወደ ግለሰብ ሲወርዱ በጣም ያነሰ እርግጠኝነት ሊኖራቸው ይችላል።
ቢቢሲ በተመለከተው ዘጋቢ ፊልም ላይ ባለሙያዎቹ የዲኤንኤ ትንታኔው የበሽታ ምርመራ ሳይሆን የተጋላጭነት አዝማሚያ አመላካች ነው በማለት ተናግረዋል። ይህም ሂትለር እነዚህ የጤና እክሎች አሉበት ማለት አይደለም።
ነገር ግን አንዳንድ የዘረ መል ሳይንቲስቶች ግኝቶቹን ከመጠን በላይ አቅልሎ ማቅረብ ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።
በለንደን በኪንግስ ኮሌጅ የፎረንሲክ ዘረ መል ፕሮፌሰር የሆኑት ዴኒስ ሲንደርኮምቤ ኮርት "በግምታቸው በጣም ርቀው እንደሄዱ" ይሰማቸዋል።
በአውሮፓውያኑ 2018 ተመሳሳይ የደም ናሙና ላይ ምርምር ያደረጉት ፕሮፌሰር ኮርት "በጠባይም ሆነ በባህሪ፣ ያ ምንም ፋይዳ እንደሌለው አስቤ ነበር" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንድ ሰው ከውጤቶቹ በመነሳት የተለየ ሁኔታ አለበት በሚል ምንም ዓይነት ትንበያ መስጠት እንደማይፈልጉ በመናገር ምክንያታቸውን ሲያስረዱ "ያልተሟላ የዘረመል ጥናት ነው" ብለዋል።
ሌላዋ የዘረመል ሳይንቲስት ዶ/ር ሳንዲያ ራማን ደግሞ በቀላል አነጋገር "በዲኤንኤ ውስጥ የሆነ ነገር ስላለህ ብቻ ትገልፀዋለህ ማለት አይደለም" ይላሉ።
በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የኦቲዝም ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ሲሞን ባሮን ኮኸን "ከባዮሎጂ ወደ ባህሪ መሄድ ትልቅ እመርታ ነው" ሲሉ ዘጋቢ ፊልሙ ላይ ተናግረዋል።
"እንደዚህ ዓይነት የዘረ መል ውጤቶችን በመመልከት የመገለል አደጋ አለ። በተለያዩ የዓለም ክፍል ያሉ ሰዎች ምርመራዬ 'እንደዚህ ዓይነት አሰቃቂ ነገሮችን ካደረገ ሰው ጋር የተያያዘ ይሆን?' ብለው ያስቡ ይሆናል።"
ሌሎች ሊታሰብባቸው የሚገቡ ብዙ ምክንያቶች መኖራቸውን በመጥቀስ "አደጋው ሁሉንም ነገር ወደ ዘረ መል የሚያውረድ ነው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ ኦቲስቲክ ማኅበር ምላሽ ለመስጠት ፈጣን የነበረ ሲሆን፣ ግኝቶቹን "ርካሽ ዋጋ" ያላቸው ሲል በይኖታል።
የጥናት እና ምርምር ክፍል ረዳት ዳይሬክተር የሆኑት ቲም ኒኮልስ "ከአስደናቂው ሳይንስ የባሰ [በዘጋቢ ፊልሙ] ለኦቲስቲክ ሰዎች ስሜት የታየው ግድየለሽነት በጣም ያስደንግጠናል" ሲሉ ጠንከር ያለ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቢቢሲ የማኅበሩን ስጋት ዘጋቢ ፊልሙን ለሠራው ቻናል 4 እና ብሊንክ ፊልምስ አቅርቧል።
በመግለጫ በሰጡት ምላሽ እንደ ፕሮፌሰር ባሮን-ኮኸን ያሉ ባለሙያዎች "የሰው ልጅ ባህሪ በዘረ መል ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ምክንያቶች የሚቀረጽ መሆኑን ያብራራሉ። ይህም አካባቢ፣ የልጅነት ገጠመኞች፣ አስተዳደግ፣ ለትምህርት ያለው ተጋልጦ እና በዙሪያው ባለው የባህል ተጽዕኖ የተፈጠረ መሆኑን ያስረዳሉ።"
"ፕሮግራሙ አፅንዖት የሚሰጠው በፊልሞቹ ላይ የተገለጹት የዘረ መል ምልከታዎች በሂትለር ላይ ብርሃን እንደሚፈነጥቁ ነው፤ ነገር ግን እሱ በተለየ መንገድ ባህሪ እንዲኖረው በሥነ ሕይወት አስቀድሞ ተወስኖ እንደነበር አይነግሩንም።"

የፎቶው ባለመብት, Stephanie Bonnas
ሰዎች የዘጋቢ ፊልሙን ርዕስ ገና ሲመለከቱ መጠየቅ ይጀምራሉ። በተለይ ሁለተኛው ክፍል 'ብሉፕሪንት ኦፍ ኤ ዲክታተር' የሚለው ለሁሉም ግርምትን የፈጠረ ነው።
ፕሮፌሰር ኪንግ የሚመርጡት ርዕስ አለመሆኑን ሲናገሩ በፊልሙ ላይ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ቶማስ ዌበር ደግሞ "አምባገነን ዘረ መል የለም" ሲሉ በመግለጻቸው ርዕሱ እንዳስገረማቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ለቢቢሲ ቃለ መጠይቅ ከመስጠታች በፊት ዘጋቢ ፊልሙን ያላዩት ፕሮፌሰሩ የዲኤንኤ ትንታኔውን ትኩረት የሚስብ እና አሳሳቢ ሆኖ አግኝተውታል።
"አስገራሚ ነው፤ ምክንያቱም በሂትለር ላይ የጠረጠርኳቸውን ብዙ ነገሮችን ስላረጋገጠኝ. . .ነገር ግን ሰዎች 'ክፉውን ዘረመል' ለማግኘት በመሞከር ስለ ዘረ መል ብዙ ማንበብ ይችሉ እንደሆነ ስጋት ነበረኝ።"
በተለይም በፕሮግራሙ ውስጥ ለተጠቀሱት ኦቲዝም እና ሌሎች የጤና አክሎች ያለባቸው ሰዎች ��ንዴት እንደሚቀበሉት አሳስቧቸው እንደነበርም ተናግረዋል።
ስለ ውስብስብ ሳይንስ ለሠፊው ሕዝብ ትክክለኛ ፕሮግራም ለመሥራት ስትሞክር ብዙ ችግሮች እና ውድቀቶች አሉት።
እንደ ሳይንቲስት ኃላፊነታቸውን ከሚዲያ እውነታዎች ጋር በማመጣጠን ብዙ ልምድ ያላቸው ፕሮፌሰር ኪንግ "ቴሌቪዥን ነው - አልፎ አልፎ ቀለል ይላል" ብለዋል።
"እነሱ [ዘጋቢ ፊልሙን የሰሩት] የተለየ መንገድ ወስደዋል እና በጣም ስሜት ቀስቃሽ ሊሆኑ ይችሉ ነበር፤ ነገር ግን አላደረጉም፤ አንዳንድ ጥቃቅን ነገሮችን ለመያዝ ሞክረዋል. . . እና መከላከያዎ ግንቦችን አስገብተናል።"
ቻናል 4 "ዲኤንኤ የሚለው 'የሕይወት መዝገብ' በመባል ይታወቃል" በማለት ለዝግጅቱ የተሰጠውን ስም ትክክለኛነት አብራርቷል።
በተጨማሪም ኃላፊነቱ "ለሰፊ ታዳሚ የሚደርሱ ፕሮግራሞችን መሥራት እና ውስብስብ ሳይንሳዊ ሀሳቦችን እና ታሪካዊ ምርምሮችን ለሁሉም ተመልካቾች ተደራሽ ማድረግ ነው።"

የፎቶው ባለመብት, Alamy
በፕሮጀክቱ ሥነ ምግባር ላይ የተነሱ ብዙ ጥያቄዎች አሉ።
የሂትለር ዲኤንኤ እርሱ ወይንም ፈቃድ መስጠት የሚችል ቀጥተኛ ዝምድና ያለው ሰው ሳይገኝ መመርመር ነበረበት?
እና ይህ በታሪክ ውስጥ ከፈጸመው አስከፊ ጭካኔዎች ለአንዱ ተጠያቂ መሆኑን እንዴት ይገለጻል? ያ የግላዊነት መብቱን ይጥሳል?
"ይህ ሂትለር ነው፤ እሱ ማንም ሰው የዲኤንኤ ምርምር ሊያደርግበት የማይችል አንድ ተዓምራዊ ገጸ ባህሪ አይደለም። ይህን ውሳኔ የሚያደርገው ማን ነው?" በማለት ፕሮፌሰር ኪንግ ይከራከራሉ።
የታሪክ ምሁሩ ሱብሃድራ ዳስ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ።
"ሳይንቲስቶች የሚያደርጉት ይህ ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ከሞቱ ረዥም ጊዜ የሆናቸው ሰዎች ዲኤንኤያቸው የተወሰዱ ሰዎች አሉ። በሳይንስ እና በአርኪኦሎጂ ውስጥ ይህ የተለመደ ተግባር ነው፤ ችግር የሚጀምረው እንዴት እናነበዋለን የሚለው ላይ ነው።"
የታሪክ ምሁሩ ዶ/ር ኬይ "እውነታው እስካለ ድረስ እና ሁሉም ነገር በሚገባ መረጋገጡን እስካረጋገጥን ድረስ" ሥነ ምግባር እንደማያስባቸው ተናግረዋል።
እና የሂትለር ዲኤንኤ መነካት ነበረበት ወይ ለሚለው "ሂትለር ለ80 ዓመታት ሞቷል። ቀጥተኛ ዘሮች የሉትም፤ ልጅም አልነበረውም። ላልተነገረ ስቃይ ተጠያቂ ነው፤ ያንን ዲኤንኤውን ከመተንተን የሥነ ምግባር መርሆዎች ጋር መመዘን አለብን።"
የሚገርመው በአውሮፓ ውስጥ ያሉ በርካታ ቤተ ሙከራዎች የፕሮጀክቱ አካል መሆን አልፈለጉም። እና ሙከራውን ያደረገው በአሜሪካ የሚገኝ ተቋም ነው።
ዘጋቢ ፊልሙን የሠሩት ድርጅቶች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጥናቱ "ለአካዳሚክ ሥራ አስፈላጊ የሆነውን መደበኛ የሥነ ምግባር ግምገማ ሂደት አልፏል" ይህም በሁለት አገራት የተደረጉ ግምገማዎችን ያካትታል።

የፎቶው ባለመብት, General Photographic Agency/Hulton Archive/Getty Images
ታዲያ ይህ ጥናት መካሄድ ነበረበት? ቢቢሲ የተለያዩ የዘረመል ሳይንቲስቶችን እና የታሪክ ተመራማሪዎችን አነጋግሯል። እና መልሱ ጥያቄውን በሚያነሳው አካል ላይ እንደሚወሰን ምላሽ አግኝቷል።
በዘጋቢ ፊልሙ ውስጥ ያሉት ያለማወላወል አዎ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የሂትለርን ማንነት ያለማወላወል ለማሳየት ይረዳል፤ እርሱ የሚያስፈራም የሚያስደንቅም ሰው ነው ይላሉ።
"ያለፈውን ጽንፍ ለመረዳት የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን" ሲሉ ፕሮፌሰር ዌበር ያምናሉ።
ዶ/ር ኬይ "እውነት እንነጋገር ከተባለ፣ እነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ቀደም ብለው እዚያ ነበሩ… ይህንን ሀሳብ በድንገት በሰዎች አእምሮ ውስጥ አልተከልነውም። ሰዎች ሂትለር አንዳንድ ችግሮች ነበሩት ብለው ለብዙ አሥርተ ዓመታት ሲገምቱ ቆይተዋል።"
ሁሉም የታሪክ ምሁራን ግን በዚህ አይስማሙም።
በዩትሬች ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ታሪክ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ኢቫ ቩኩሲች "የሂትለርን ድርጊት ያነሳሳውን ለማብራራት መሞከር በጣም አጠራጣሪ መንገድ ይመስለኛል" ብለዋል።
በጅምላ ግጭቶች ላይ ምርምሮቻቸውን የሠሩት ዶ/ር ቩኩሲች ሰዎች ለምን ፍላጎት እንደሚያድርባቸው መረዳት እንደሚችሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ነገር ግን "የምንፈልገው የትኛውም መልስ በዲኤንኤ ምርመራ አይገኝም" ብለዋል።
እና ጥናቱ አስደሳች ቢሆንም፣ የታሪክን እውነተኛ ትምህርቶችን የመደበቅ አደጋን ይፈጥራል ሲሉ በአምስተርዳም የኤንአይዲ ኢንስቲትዩት የታሪክ ምሁር የሆኑት አን ቫን ሞሪክ ይናገራሉ።
ያ ትምህርት "በተወሰኑ አውዶች ውስጥ ያሉ መደበኛ ሰዎች ዘግናኝ ጥቃት ሊፈጽሙ፣ ሊያነሳሱ ወይም ሊቀበሉ ይችላሉ" የሚል ነው።
በሂትለር አነስተኛ የብልት መጠን ላይ ማተኮር፣ የጅምላ ጥቃት እና የዘር ማጥፋት እንዴት እንደሚፈጸም እና ለምን እንደሚከሰት ምንም አያስተምረንም ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጥናቱ ሲጠናቀቅ እና በሌሎች ባለሙያዎች ግምገማ እየተደረገበት፣ የሆነ ጊዜ ሙሉ ግኝቶቹ ይፋ ይደረጋሉ።
ፕሮፌሰር ዌበር "በጣም በጥንቃቄ እና በስክነት" ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው ይላሉ። ነገር ግን በሆነ መንገድ ጠቃሚ እንደሚሆን ተስፋ ያደርጋሉ።
"የምርምር ውጤቶች ጥሩ ጎናቸው እርሱ ነው። በአምስት፣150፣ 500 ዓመታት ውስጥ ሊከሰት ይችላል። ይህ ምርምር ለትውልድ የሚያገለግል ነው፤ እናም ለወደፊቱ ብልህ ሰዎች እንደሚጠቀሙባቸው እርግጠኛ ነኝ።"
ግን እነዚህን ውጤቶች እንዴት እንደምንጠቀም ሁላችንም ኃላፊነት አለብን።
ዶክተር ኬይ ሁሉም ሰው "ሳይንስን መከተል" እና የምናውቀውን እና የማናውቀውን ግልጽ ማድረግ አለበት ይላሉ።
ይህ ደግሞ መገናኛ ብዙኃን እንዴት እንደሚዘግቡት ያካትታል።
"ይህን ዘጋቢ ፊልም የሚመለከት ማንኛውም ሰው ለመገለል አስተዋፅኦ አለማድረጉን ለማረጋገጥ በትክክል የመፃፍ ኃላፊነት አለበት። እንዲህ ያለ ዘጋቢ ፊልም ዝም ብሎ ከባዶ ተነስቶ አይሠራም።"















