"ከሃይማኖቴ፣ ከአስተዳደጌ...ጋር አይሄድም" በማለት በስህተት የገባላቸውን 8.4 ሚሊዮን ብር የመለሱት ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, AMC
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የፋይናንስ ባለሙያ የሆኑት አቶ ቻላቸው ጌጡ ኅዳር 20/2018 ዓ.ም. ወደ ባንክ አካውንታቸው 8.4 ሚሊዮን ብር መግባቱን የሚገልጽ መልዕክት በእጅ ስልካቸው ላይ ደረሳቸው።
አቶ ቻላቸው ይህን ያህል ገንዘብ የሚልክ ዘመድም ሆነ ወዳጅ በአገር ውስጥም ሆነ ከባሕር ማዶ የለኝም ይላሉ።
ስለዚህ ግራ ተጋቡ፤ በሥራ ገበታቸው ላይ ላሉ ባልደረቦቻቸው የሆነውን ነገሩ።
ማንም ግን የተ���ጠረውን የሚያብራራ ሳይሆን በግርታው ላይ መደናገር የሚጨምር ብቻ ነው።
ስለዚህ ባሕር ዳር ወደ ሚገኘው የንግድ ባንክ ቤዛዊት ቅርንጫፍ ደወሉ።
ከዕኩለ ቀን በፊት 5፡15 ሰዓት ላይ "8.4 ሚሊዮን ብር ወደ ባንክ ሒሳቤ መግባቱን የሚገልጽ መልዕክት ደርሶኛል" በማለት ያን ያህል መጠን ያለው የገንዘብ ዝውውር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ጥያቄ አቀረቡ።
አቶ ቻላቸው ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ወደ ባንክ ደውለው ፈጽመው አስበውት የማያውቁት መጠን ያለው ገንዘብ ወደ አካውንታቸው ስለመግባቱ የደረሳቸው የአጭር ጽሑፍ መልዕክት ትክክል መሆኑን ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
አስከትለውም "ከየት ነው የመጣው?" ብለው ሲጠይቁ "ከአዋሽ ባንክ ወደ ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ሲያስተላልፉ ከዚያ የመጣ ነው" የሚል ምላሽ በማግኘታቸው የበለጠ ጉዳዩን ተወሳሰበባቸው።
የእርሳቸው የባንክ አካውንት የሚገኘው ንግድ ባንክ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ቻላቸው፣ ከሌላ ባንክ ወደ እርሳቸው አካውንት እንዴት ገንዘቡ ሊገባ እንደቻለ ግር ብሏቸው የባንኩን ሠራተኛ በድጋሚ ጠየቁ።
ነገር ግን በወቅቱ ደውለው ያናገሩት የባንኩ ባልደረባ ይህ ክስተት እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ ማስረዳት አልቻለም።
አቶ ቻላቸው "የሚቻል ከሆነ ከባንኮቹ ጋር ተነጋግራችሁ አስተካክሉ���ኝ" ብለው በድንገት የባንክ ሂሳባቸው ውስጥ የተገኘው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ባለቤቱ እንዲገባ ጠየቁ።
ነገር ግን አቶ ቻላቸው "ብሩ የእኔ አይደለም፤ ከላከው ባንክ ጋር ተነጋግራችሁ መልሱ እና ውጤቱን አሳውቁኝ" ሲሉ ላቀረቡት ጥያቄ "እንደዚያ እንኳን አይቻልም" የሚል ምላሽ አገኙ።
ገንዘቡን ወደ ላከው ባንክ ለመመለስ "አንተ ራስህ መጥተህ አመለክተህ ነው የምትመልሰው" መባላቸውን ይናገራሉ።
"አስገባልኝ አላልኩት፤ እንደዚህ ዓይነት ገንዘብ የሚያስገባልኝ ዘመድ ከውጭም ከውስጥም የለኝም" ሲሉ የግራ መጋባታቸውን ልክ ያስረዳሉ።
"ዞሮ ዞሮ የሕግ አካል ብሩን አይቶ መርምሮ ይመልሰው" በሚል ወደ ባሕር ዳር ፖሊስ መምሪያ እና ስምንተኛ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ አቤቱታቸውን አቀረቡ።
አቶ ቻላቸው "የእኔ ሀብት ያልሆነ ወደ አካውንቴ በመግባቱ ተጣርቶ ወደ ባለቤቱ ይመለስልኝ" የሚለው ማመልከቻቸው ተቀባይነት አግኝቶ ፖሊስ ለባንኩ ገንዘቡ እንዳይንቀሳቀስ የሚል ደብዳቤ ጻፈ።
የፖሊስ ደብዳቤን ተከትሎ ገንዘቡ እንዳይንሳቀስ ተደርጎ ምርመራ ከተደረገ በኋላ ፖሊስ ዳግም አቶ ቻላቸውን ጠራቸው።
"ገንዘቡ የማጭበርበር ነገር የለበትም። ነጻ ነው፤ ለሚመጣው ሁሉ እኛ ኃላፊነት እንወስዳለን" የሚል ምላሽ አገኙ።
ከዚያ በመቀጠል ተመልሰው ወደ ባንካቸው በመሄድ "ብሩ ጤናማ ነው ተብሏል። በስህተት የመጣ ብር ነው ተብሏል። እንዲመለስላቸው ብዬ አመለከትኩኝ፤ ብሩ በዚህ መልኩ ተመለሰላቸው" ብለዋል።
አንድ የአዋሽ ባንክ ደንበኛ የሆነ ግለሰብ ከባንኩ ወደ ሌላ ባንክ ለማስተላለፍ ፈልጎ በስህተት ወደ አቶ ቻላቸው ጥሩነህ አካውንት የላከው 8.4 ሚሊዮን ብር ተመለሰ።
አቶ አብዱሰመድ መሐመድ የተባሉ ግሰለብ ለአዋሽ ባንክ ለአቶ መሐመድ ኢብራሒም በኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ አካውንታቸው 8.4 ሚሊዮን ብር እንዲያስገባላቸው አዘው ነው ስህተቱ የተፈጠረው።
ይህ ገንዘብ ወደ ተሳሳተ አካውንት ሊተላለፍ የቻለው ጥያቄው የቀረበለት የባንኩ ሠራተኛ ወደ አቶ ቻላቸው የንግድ ባንክ አካውንት በስህተት ገንዘቡን በማስገባቱ መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጻፈው የምስጋና ደብዳቤ ላይ ተጠቅሷል።
አቶ ቻላቸው የራሳቸው ያልሆነውን ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ በታማኝነት ወደ ላኪው ባንክ እንዲመለስ በማድረጋቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኅዳር 29/2018 ዓ.ም. የምስጋና ደብደቤ ጽፎላቸዋል።
ከማያውቁት ምንጭ የተላከው 8.4 ሚሊዮን ብር እጅግ ብዙ ነው፤ ሚሊዮኖች ድንገት ሰተት ብለው ወደ አካውንታቸው የገባላቸውን አቶ ቻላቸው ግን ከመነሻው "የእኔ አይደለም" ነበር ያሉት።
አቶ ቻላቸው ይህን ያህል ዳጎስ ያለ መጠን ያለው ገንዘብ ወደ አካውንትዎ ሲገባ "ይህንን ነገር ላስብበት ያሉበት" ጊዜ የለም ተብለው ሲጠየቁ ፈገግ ብለው "የለም" ብለዋል።
አቶ ቻላቸው "ሥጋዊ ነኝ" ይላሉ የገንዘቡን አጓጊነት ለማስረዳት ሲሞክሩ፤ "ዛሬ ማንም ቀምቶ እየበላ፣ ይህንን ያህል ገንዘብ አምጣ እየተባለ በሚገደድበት ክልል እና አገር ላይ እንዲህ ዓይነት ገንዘብ መጥቶ እንዴት ዝም አልከው" የሚል አስተያየትም ደርሷቸዋል።
እርሳቸው ግን ይህ የራ�� ያልሆነ ገንዘብን መውሰድ ቀርቶ መመኘት "ከሃይማኖቴ፣ ከአስተዳደጌ፣ ከመጣሁበት ማኅበረሰብ ባህል ጋር አይሄድም" ይላሉ።
"ድሮም የእኔ ያልሆነ ነገር የእኔ አይደለም ብዬ ስለማስብ ዕድገቴም ይህንን ስለማይፈቅድልኝ ነው [ፈገግታ] የመለስኩት እንጂ ብዙ ያዝ የሚያደርጉ፣ ሃሳብ የሚያስቀይሩ ነገሮች ከጓደኞቼም ከሁሉም አሉ" ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።
ባለትዳር እና የአራት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ቻላቸው በፋይናንስ ባለሙያነታቸው በቅርቡ ከተደረገው የደሞዝ ጭማሪ በፊት 9 ሺህ ወርሃዊ ደሞዝ እንደሚያገኙ ይናገራሉ።
በሥራ ገበታቸው ላይ ሆነው ገንዘቡ መግባቱን የሚያሳይ መልዕክት በእጅ ስልካቸው ላይ ሲደርሳቸው ለሥራ ባልደረቦቻቸው ተናግረዋል።
በኋላም ከጓደኞቻቸው እና ከጎረቤቶቻቸው ጋር በመሆን ወደ ፖሊስ መምሪያው በመሄድ አመልክተዋል።
በዚህ መካከል "አንተ ሞኝነት አለብህ፤ ሰው ይሰርቃል አንተ እግዚአብሔር የሰጠህ ሥራ፣ ብላ፣ ተለወጥ ብሎ ነው። ይህችን ደካማ ቤትህን ሥራ ብሎ ነው የሰጠህ የሚለኝ ብዙ ነበር፤ ይሄን ይሄን ተቋቁሜ ነው" ይላሉ።
ወደ ፖሊስ ጣቢያ ስሄድ ለሥጋዬ ላላደላ ወስኜ ስለሆነ ምንም ፀፀት አልተሰማኝም ሲሉ ወደ አካውንታቸው የገባውን ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ መመለሳቸው ምንም ዓይነት ቁጭት እንዳልፈጠረባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
መልካም ተግባራቸውን የሰሙ በርካታ ሰዎች "አኮራኸን፤ ተባረክ፤ ልጆችህ ይደጉ" በሚል የመመረቃቸውን ያህል "አይለፍልህ" የሚሉ አሉታዊ አስተያየቶችም እንደደረሳቸው እየሳቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በስልክ እየደወሉ "ተለወጥ ስትባል የማትለወጥ፤ ከአሁን በኋላ እግዜርን ገንዘብ ስጠኝ ብለህ እንዳታማርር፤ እንዳትጠይቀው፤ ሰጥቶህ አንተ ራስህ ገፍተኸዋልና" ሲሉ የነቀፏቸው እና "ወደ እኔ አካውንት ብታስገባው" ያሉም መኖራቸውን አቶ ቻላቸው ይናገራሉ።
ቢቢሲ -ይህ ተሳስቶ ብሩን ያስገባው ሰው በታማኝነት ሲመልሱት ምንም አላደረገልዎትም?
አቶ ቻላቸው- [ሳቅ] እንግዲህ የሁሉም ጥያቄ እርሱ ነው። እኔ አንዴ ለመድሃኒያለም ነው ስለሰጠሁት፤ የሚመጣ ነገር ካለ ግን 'እግዜር ይስጥልኝ' ብዬ እቀበላለሁ። አልቀበልም አልልህም፤ እስካሁን ግን ያለኝ ነገር የለም።















