ከ40 ዓመታት መለያየት በኋላ የወጣትነት ፍቅራቸውን እና ልጃቸውን መልሰው ያገኙት ጥንዶች

የፎቶው ባለመብት, Personal collection
ኬቪን ካሮል እና ዴቢ ዌበር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት በአውሮፓውያኑ 1967 ነበር። ሁለቱም በአስራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቲያትር ቡድኖች አባላት ነበሩ። እንደተያያዩ የፍቅር ስሜት ተሰምቷቸዋል።
"እኔ ወንዶች ብቻ የሚማሩበት ትምህርት ቤት ነበርኩ። ዴቢም የሴቶች ብቻ ትምህርት ቤት ነበረች" ሲሉ ካሮል ለቢቢሲ አውትሉክ ፕሮግራም ተናግረዋል። "የተዋናይ መረጣ ሲካሄድ በጋራ አንድ አዳራሽ ውስጥ ነበርን። ጓደኛዬን 'ያንቺን ልጅ አየሃት? ለትምህርት ቤት የዳንስ ፕሮግራም እወስዳታለሁ' አልኩት" በማለት ያስታውሳሉ።
ዌበርም በበኩላቸው፤ "ለተዋናይ መረጣው ከሌላ ትምህርት ቤት ከመጡት ሴቶች አንዳቸውንም ስለማላውቅ አዳራሹ ውስጥ ብቻዬን ተቀምጬ ነበር። እርሱን እንዳየሁት ግን አስታውሳለሁ። ካየኋቸው ወንዶች በሙሉ ቆንጆው ነበር" ይላሉ።
ካሮል እና ዌበር አንድ ላይ ወደ ዳንስ ፕሮግራሙ በመሄድ ብቻ አላበቁም፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የሚነጣጠሉ ሰዎች አልሆኑም። አንድ ጊዜ ለመጋባት ቀላል የሆነ ሂደት ወዳለበት ሜሪላንድ ለመጥፋት ጭምር አቅደው ነበር።
ኋላ ግን ነገሮች ተቀያየሩ። ዌበር ማርገዟ ህልማቸውን ቀጨው። 40 ዓመት ለሚሆን ጊዜ እንዲለያዩም ምክንያት ሆነ
ዛሬ በድጋሚ ተገናኝተዋል። በወጣትነታቸው ሊቀጥሉት ያልቻሉትን ፍቅር እያጣጣሙ መሆኑን ይናገራሉ። እዚህ የደረሱበት መንገድ ግን የሆሊውድ ፊልም ይወጣዋል።
ያልተጠበቀ ዜና
በወቅቱ ከነበረው ማኅበራዊ ምልከታ አንጻር ሲታይ፤ የዌበር ቤተሰቦች ልጃቸው እንዳረገዘች ሲነገራቸው ያሳዩት ድጋፍ እምብዛም ያልተለመደ ነበር።
"በጣም ፍቅር ነበራቸው። ኬቪንን ይወዱት ነበር። ምርጥ ሰው እንደሆነ ያውቁ ነበር። እናም በጣም እንዋደድ ነበር" ሲሉ ዌበር ለቢቢሲ ተናግረዋል። "የዚያን ጊዜ ግን ለሚያረግዙ ታዳጊ ሴቶች የነበረው ሁኔታ የተለየ ነበር" ይላሉ።
ዌበርን ለብቸኛ እናቶች ወደተጋጀ ቤት ለመላክ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። "እናቴ ኬቪን ቅዳሜ እና እሁድ እየመጣ እንዲወስደኝ ፈቅዳ ነበር። ወጥተን በመኪና ተንሸራሽረን እና አብረን ራት እንበላ ነበር" በማለት ያስታውሳሉ።
በወቅቱ የሚያስቡት፤ ነገሮች ሲመቻቹ እንደሚጋቡ እና የሚትወለደው ልጃቸውን በጋራ እንደሚያሳድጉ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Personal collection
ካሮል በዚህ ሃሳብ እጅጉን አምነውበት ስለነበረ እናታቸውን ጎትጉተው የአሜሪካ ሠራዊት ውስጥ ተመዘገቡ።
"ለወታደርነት ከተመዘገብኩ፤ ባንጋባም እንኳን ለዴቢ ገንዘብ መላክ እንደምችል፣ ሠራዊቱ የእርሷን እና የልጁን ሕክምና እንደሚሸፍን አውቄ ነበር" ሲሉ ይህንን የወሰኑበትን ምክንያት ያብራራሉ። "ሥልጠና ጨርሼ ስወጣ መጋባት እንደምንችል ነበር ተስፋ ያደረግኩት" ይላሉ።
ይህ ሁሉ ግን ተስፋነት አልተሻገረም።
ወታደራዊ ሥልጠና ላይ እያለ ዌበር ልጇን ለማደጎ ልትሰጥ እንደሆነ የሚገልጽ ደብዳቤ ጻፈችለት። "ስሜቱን አስታውሰዋለሁ" ይላሉ ካሮል እምባ በተናነቀው ድምጽ። "ስሜትን ማሳየት በማይቻልበት ስፍራ ከበርካታ ወታደሮች ጋር ሥልጠና ላይ ነበርኩ። በውስጤ ግን ዓለሙ ሁሉ እየተደፋብኝ ነበር" ሲሉ በወቅቱ የተሰማቸውን ገልጸዋል።
ሕይወት ጠመዝማዛ
ወደ ቬትናም ለጦርነት ሊላክ በዝግጅት ላይ ካለው ካሮል ጋር ግንኙነቷን ያቋረጠችው ዌበር፤ ልጇን አሳልፋ የመስጠት ሃሳብ እጅጉን አስጨንቋት ነበር። ኋላ ላይ ልጇን በማደጎ ለመውሰድ ፈቃደኛ የሆነ ቤተሰብ እንዳለ ሐኪሟ ሲነግራት እፎይታ ተሰምቷታል።
"አራት ልጆች ያሉት አንድ ቤተሰብ አለ። እናትየው ተጨማሪ ልጅ መውለድ አልቻለችም። ሴት ልጅ ካለሽ በማደጎነት ሊወስዱ ይፈልጋሉ" ሲል ሐኪሙ ነገራት።
ዌበር፤ ልጇን ከወለደች በኋላ በቅጡ ላማታውቀው ቤተሰብ ሰጥች። ብዙም ሳይቆይ ቤተሰቧ ወደ አዲስ ሕይወት ተሻገረ። ካሮል ደግሞ ቬትናም ውስጥ እየተዋጋ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Personal collection
"ሥራዬ በውጊያ የተመቱ አብራሪዎችን ማዳን ነበር። በአውሮፓውያኑ በጥቅምት 10/1969 ትጥቅ አድራሽ ሄሊኮፕተርን ለማዳን ሄድን" በማለት ጉዳት እንዲደርስባቸው ስላደረገው ዘመቻ ያስታውሳሉ። በዚህ ኦፕሬሽን ወቅት እጅ፣ እግር እና ጀርባቸውን በፍንጥርጣሪ ተመትተዋል።
"ከዚያ ስፍራ በሕይወት የምወጣ አልመሰለኝም ነበር። ከፈጣሪ ጋር ሙግት ገጠምኩ። 'እዚህ፣ ምደረ በዳ መሃል፣ ከቤቴ በሺዎች ኪሎ ሜትር ርቄ፣ ዴቤን ድጋሚ ሳላያት፣ ልጄን ሳላይ እንድሞት እንድታደርገኝ እንደሆነ ማመን አልችልም' አልኩ" ሲሉ ከፈጣሪ ጋር የገቡትን ክርክር ያስረዳሉ።
በድንገት ግን ሌላ ወታደር ደረሰላቸው። ካሮል ለህክምና ወደ ፊሊፒንስ፣ ከዚያም ወደ ጃፓን ተወሰዱ። ወደ አሜሪካ የተመለሱት ካገገሙ በኋላ ነበር።
"በወቅቱ 18 ቀዶ ሕክምና ነው የተደረገልኝ። ከዚያ በኋላ ደግሞ ሌላ 20 ቀዶ ሕክምና አድርጌያለሁ። መጀመሪያ በዊልቼር ነበር፤ ከዚያ ወደ በሁለት እጅ ወደሚያዝ ባለ ጎማ መራመጃ ቀየርኩ። ከእሱ ደግሞ ወደ ክራንች፤ ከክራንች ወደ ከዘራ ተዛወርኩ። በፍጹም ወደ ኋላ አልተመለከትሙም" ይላሉ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ካሮል ዌበርን ለማግኘት እየሞከረ ነበር። ጸጸት ውስጥ ያለችው ዌበር ደግሞ ለመርሳት እየሞከረች ነው። በርካታ ጊዜያት አግብታለች፤ ሦስት ልጆችንም ወልዳለች። መጨረሻ ላይ ግን ባለቤቷ አርፎ ብቸኛ ነበረች።
ሁለቱም ወላጆች ለማደጎ የተሰጠችው ልጃቸውን ለረጅም ዓመታት አግኝተው አያውቁም ነበር።
ፍቅር እንደገና

የፎቶው ባለመብት, Personal collection
በጊዜ ሂደት ዌበር ከነበሯቸው ትዳሮች ለወለዷቸው ሴት ልጆቻቸው እውነቱን ለመናገር ወሰኑ።
"የእናቶች ቀን ነበር። ኩሽና ውስጥ ነበርን። 'የምነግራችሁ ነገር አለ። ወጣት እያለሁ ልጅ ነበረኝ' አልኩ። እኔ እና ኬቪን እንዴት በፍቅር እንደወደቅን ጨምሮ ሁሉንም ነገር አብራራሁ" በማለት ያስታውሳሉ።
አንዷ ልጅ ሕጻኗን ፈልጎ ለማግኘት ዝርዝር መረጃዎች ጠየቀች።
"የመጨረሻ ስማቸውን አውቅ ነበር፣ ቤተሰቡ ውስጥ አራት ልጆች እንደነበሩ አውቃለሁ። እንዲሁም የሚኖሩበትን አካባቢ አውቃለሁ" ሲሉ ለልጃቸው የሰጡትን መረጃ ይዘረዝራሉ።
ከዓመታት በፊት የተሰጠችውን ልጅ ፈልጎ ለማግኘት እነዚህ ፍንጮች በቂ ነበሩ። የዌበር ሴት ልጅ ቤተሰቤን አግኝታ ከወንዶቹ ልጆች አንዱን አነጋገረች። ቀጥሎ ስልክ ተደወለ፤ ሴቷ ልጅ ቫል ነበረች።

የፎቶው ባለመብት, Personal collection
"ጠዋት ሁለት ሰዓት ላይ ነበር የደወልኩት" ትላለች ቫል ለቢቢሲ ስትናገር። "'ብዙ የምንነጋገረው ነገር አለ፤ ያደረግሽውን ነገር አደንቃለሁ' አልኩ። መጥፎ ስሜት አልነበረም" በማለት የመጀመሪያ ንግግራቸውን እንዴት እንደነበር ታስረዳለች።
ይህ ምላሽ ለዌበር እፎይታን የሚሰጥ ነበር። "ያ ሁሉ የእፍረት እና የጥፋተኝት ስሜት ጠፋ" ትላለች። የዚያኑ ምሽት ነበር የተገናኙት። የዚህን ጊዜ አንድ ጥያቄ ተነሳ "የቫል ወላጅ አባት የት ነው?"
ኢንተርኔት ላይ መረጃዎችን ሲፈልጉ ባለቤቱ እንደሞቱ የሚያሳይ መረጃ አገኙ። ከዚያም ለዌበር ደብዳቤ ተጻፈ።
"በቅርቡ ባለቤትህን ስላጣህ አዝናለሁ። ስለ ልጅነት ጊዜያችን ብናወራ ደስ ይለናል። ደህና እንደሆንክ ተስፋ አደርጋለሁ" በማት ወደ ስልክ ቁጥራቸው መልዕክት ላኩ።
ካሮል የደረሳቸውን መልዕክት እንደ ተአምር ነው የቆጠሩት። "ደብዳቤውን ያገኘሁበትን ጊዜ መቼም ቢሆን አልረሳውም። ቀጥታ ወደ ስልኩ ሄጄ፤ እየተነጋገርን እንደሆነ ማመን አልችልም አልኩ" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Personal Collection
በዚህ ሰዓት የቀድሞ ፍቅረኛቸውን ማግኘታቸውን እንጂ ስለ ልጃቸው አልሰሙም ነበር። ዌበር "'የምነግርን ነገር አለ። ልጃችንን አግኝቻታለሁ። ልትተዋወቃት ትፈልጋለህ" በማለት ካሮል ጠየቁ።
በዌበር ቤት ነበር የተገናኙት። ቫል፤ እናቷ አባቷን ሲያዩ የነበራቸው ሁኔታ አስቋታል። "'ኦህ፣ በጣም ቆንጆ ነው' አለች" ሲሉ የልጃቸውን ንግግር ያስታወሳሉ።
ቫል እና አባቷ ለሰዓታት አውርተዋል። ቀጥሎ ደግሞ ካሮል ወደ ቀድሞ ፍቅረኛቸው ዘወር ብለው በዚህ ሁሉ ዓመታት እርሷን ማፍቀር እንዳላቆሙ ተናዘዙ።
ካልተሳካው ተያይዞ የመጥፋት የልጅነት ዕቅድ 40 ዓመታት በኋላ በመጨረሻም ተጋቡ። አሁን በ70ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሆነው በድጋሚ ፍቅራቸውም ማጣጣም ችለዋል።
ዌበር፤ "በዚህ የሕይወታችን ደረጃ ላይ ሆነን አንዳችን ሌላችንን መንከባከብ፣ መውደድ ችለናል። እውነቱን ለመናገር ከዚህ በላይ የምፈልገው ነገር የለም" ሲሉ በዕድሜያቸው ማምሻ በድጋሚ ስላገኙት ፍቅር ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Personal collection















