ልጆች መውለድ ዕድሜን ሊያሳጥር ይችላል? ታሪክ ምን ይነግረናል?

ስድስት ልጆችን አቅፋ የተቀመጠች እናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ታሪካዊ ሰነዶች አንዳንድ እናቶች በእያንዳንዱ በሚወልዷቸው ልጆች ስድስት ወር ከዕድሜያቸው ላይ እንደሚቀንሱ ያሳያሉ

ልጆች የያዙትን በቁጣ ሲወረወሩ፣ አልበላም ሲሉ ወይም ለመተኛት ሲያስቸግሩ እናቶች 'አቃጠላችሁኝ፤ ያለ ዕድሜዬ አስረጃችሁኝ' በማለት ይማረሩ ይሆናል።

አዲስ የሚወጡ ጥናቶችም የሚያሳዩት ይህ ልጆችን በማሳደግ ፈተና ውስጥ ለሚያልፉ ሴቶች ከእውነታው ብዙም የራቀ ላይሆን እንደሚችል ነው።

የታሪክ መዛግብት የአንዳንድ እናቶች ሕይወት በሚወልዱት በእያንዳንዱ ልጅ እስከ ስድስት ወር ሊቀንስ እንደሚችል ሲተነተኑ፣ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ሴቶች ላይ ደግሞ ይህ ጫና ከፍ እንደሚል ይጠቁማል።

የዝግመተ ለውጥ ተመራማሪዎች ደግሞ የልደት እና የሞት መረጃዎችን የያዙ የቤተ እምነቶች መዛግብትን ፈትሸዋል። መዛግብቱ በአውሮፓውያኑ 1866 እና 1868 መካከል በታላቁ የፊንላንድ ረሃብ ወቅት በሕይወት የነበሩ 4,684 ሴቶችን ሰንደዋል።

በኔዘርላንድስ የግሮኒንገን ዩኒቨርሲቲ የጥናቱ መሪ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ኢዩን ያንግ ቲ ይህ "በአውሮፓ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ ከታዩት እጅግ ዘግናኝ ረሃቦች አንዱ ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።

በረሃብ ወቅት የወለዱ እናቶች ዕድሜያቸው ለእያንዳንዱ ልጃቸው በስድስት ወር መቀነሱን ዶ/ር ያንግ እና ባልደረቦቻቸው ተመልክተዋል።

ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት እናቶች ከፍተኛ መጠን ያለው አቅማቸውን የራሳቸውን ህዋሳት ከመጠገን ወደ መውለድ በማዘዋወራቸው እና በኋላ ላይ በበሽታ የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ እንደሆነ ግኝቶቹ ጠቁመዋል።

ነገር ግን ከረሃቡ በፊትም ሆነ በኋላ በነበሩት ሴቶች ዕድሜ እና መውለድ መካከል ምንም ግንኙነት አልነበረም።

"ይህን ልውውጥ የምናየው ረሃቡ በተከሰተበት በዚህ ወቅት በወሊድ ውስጥ በነበሩት ሴቶች ላይ ብቻ ነው" ብለዋል ዶክተር ያንግ።

ይህ የሚያሳየው ሴቶች በወሊድ ጊዜ የሚኖሩበት አካባቢ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ነው።

መውለድ ለምን በዕድሜ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል?

አንዱ ማብራሪያ በአስቸጋሪ የአካባቢ ሁኔታዎች ውስጥ ልጅ መውለድ የረዥም ጊዜ የጤና ችግሮችን ሊያባብስ ይችላል የሚል ሊሆን ይችላል።

ከረዥም ጊዜ በፊት እናቶች የልብ እና የደም ሥር እንዲሁም ከምግብ መፈጨት ጋር ለተያያዙ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍ ያለ እንደሆነ ይታወቃል።

ይህ ደግሞ በከፊል በክብደት መጨመር እና በአካላዊ ውጥረት ምክንያት የሚመጣ ነው።

ዶ/ር ያንግ አክለውም "በዚህ ጊዜ ውስጥ እርግዝና፣ ጡት ማጥባት እና ልጆች ማሳደግ በእናቲቱ ውስጥ ያለውን አቅም እንደሚያሟጥጥ ተጨባጭ ማስረጃ አለ።"

እርግዝና እና ጡት ማጥባት ብዙ ጉልበት ይጠይቃሉ።

ይህም ማለት አዲስ እናት በረሃብ ወቅት በኋለኛው ሕይወቷ በሽታ እንዳይከሰት የሚከላከለውን የሰውነት አቅም ለማደርጀት ጉልበት ያንሳታል ማለት ነው።

"ረሃብ ባለበት አካባቢ ብዙ ልጆች የሚወልዱ እናቶች በቂ የማገገሚያ ጊዜ ሳያገኙ በመቅረታቸው የሚደርስባቸው የጤና ተጽእኖ ሊባባስ ይችላል" ሲሉ ዶ/ር ያንግ ያብራራሉ።

ነገር ግን ጥናቱ ታሪካዊ መረጃዎችን ብቻ በመመርመሩ፣ በላብራቶሪ ተጨማሪ ሙከራ በማድረግ አዲስ መረጃ እስኪያመጣ ድረስ እርግጠኛ መሆን እንደማይችል ተናግረዋል።

አንዲት እናት ሴት ልጇን ታቅፋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በ2023 በሱዳን የምትኖር አንዲት እናት 4.32 የወሊድ ምጣኔ ነበራት፤ በሚቀጥለው ዓመት በአገሪቱ የተወሰኑ ክፍሎች ድርቅ መከሰቱ ታወጀ

ከልጅ ቁጥር ጋር ያለው 'የዕድሜ ልውውጥ'

ግኝቶቹ ብዙ ልጆች ባሏቸው ሴቶች ላይም ጎልቶ ይታያል። ነገር ግን ሁሉም ሴቶች በእኩልነት አልተጎዱም ሲል የዶ/ር ያንግ ጥናት አመልክቷል።

"በእርግጥ በጣም ትልቅ ቤተሰብ ያላቸው እና የረሃብ ክስተቶች የሚሉ ሁለት ጽንሰ ሃሳቦች አሉ" በማለት ዶክተር ያንግ ያብራራሉ።

ለአስርት ዓመታት ሳይንቲስቶች ዕድሜያቸው አጭር በሆኑ እና ብዙ ልጆችን በወለዱ እንስሳት (አይጥ እና ነፍሳት) እንዲሁም ትንሽ ወልደው ረዥም ዓመታት በኖሩ ፍጥረታት (ዝሆኖች፣ አሳ ነባሪ እና ሰው) ግራ ሲጋቡ ቆይተዋል።

አንዱ መሪ ​​ንድፈ ሐሳብ ለህዋሳት ጥገና ይውል የነበረውን አቅም ለመውለድ በመዞሩ እንደሆነ ያሳያል፤ ይህም ለእርጅና አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ዘመናዊ ሴቶች በተመሳሳይ መንገድ ይጎዳሉ?

ከ200 ዓመታት በፊት ከነበሩ ሴቶች የተወሰዱት ግኝቶች በ 21ኛው ክፍለ ዘመን እናቶች ላይ ተፈጻሚ ሊሆኑ ይችላሉ?

"የዘመናዊ የጤና አጠባበቅ ሥርዓቶች ያን ያህል ጠንካራ ባልሆኑበት በዚህ ታሪካዊ ጊዜ ውስጥ ይህንን አውድ ማየቱ አስፈላጊ ነው" ብለዋል ዶክተር ያንግ።

"በዚህ ጊዜ ውስጥ የኖሩ ሴቶች በአማካኝ አራት ወይም አምስት ልጆች የሚኖራቸው ሲሆን፣ ይህም አሁን ካለው የልጆች ብዛት በጣም የራቀ ነው።"

ከአውሮፓውያኑ 1800ዎቹ ጀምሮ፣ በቤተሰብ ውስጥ ያሉ ልጆች ቁጥር በዓለም ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

በ2023 በአማካኝ አንድ ሴት ከሁለት በላይ ልጆች ነበሯት።

ይህ ለውጥ በትምህርት ተደራሽነት፣ ከሥራ ቦታ፣ ከእርግዝና መከላከያ አቅርቦት እንዲሁም ከሕፃናት ሞት መጠን መቀነስ ጋር ��ተዛመደ ነው።

ሆኖም እንደ ኒጀር፣ ቻድ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ባሉ አገራት የሚኖሩ ሴቶች አሁንም ቢያንስ አራት ልጆች ይወልዳሉ።