ከሦስት ልጆቿ ጋር ጎዳና ከመውጣት ተነስታ ታዋቂ ሳይንቲስት የሆነችው ሴት

የፎቶው ባለመብት, photos of the palace
በአውሮፓውያኑ 1990 ኢጄዎማ ኡቼግቡ ሦስት ልጆቿን እና አንድ ሻንጣ ይዛ ከናይጄሪያ ለንደን ገባች።
የተወለደችው ለንደን ነበር። ከ30 ዓመታት በኋላ ሦስት ልጆች ይዛ ወደ ለንደን ተመለሰች።
ለንደን በገባች በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከልጆቿ ጋር ጎዳና ወጡ።
ከጎዳና ሕይወት ወጥታ የናኖፓርቲክልስ ሳይንቲስት ሆናለች። ታሪኳ ፈተናዎችን ድል የመንሳት እና የጀግንነት ነው።
ኢጄዎማ ለንደን እንድትቆይ ወላጆቿ መስዋዕትነት ከፍለዋል።
"ወላጆቼ የሰጡኝ ስም 'መልካም መንገድ' ማለት ነው። ዩናይትድ ኪንግደም ሁሉም ነገር ቀና እንዲሆንላቸው አስበው ነው ይሄን ስም የሰጡኝ" ትላለች።
እናቷ ለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ይማሩ ነበር። አባቷ ደግሞ ኤሌክትሪካል ኢንጂነር ነበሩ።
ወላጆቿ ትምህርት ላይ ስለነበሩ በኬንት ከተማ ለሚኖሩ ልጆች አሳዳጊዎች ተሰጠች።
ምዕራብ አፍሪካውያን ወላጆች ልጆቻቸውን ለአሳዳጊዎች ሰጥተው ትምህርታቸውን መቀጠላቸው የተለመደ ነው።
ለአራት ዓመታት ከአሳዳጊዎቿ ጋር በፍቅር ኖረች። ከዚያም አባቷ ወሰዳት።
"አሳዳጊዬን አክስቴ ፓት ነበር የምላት። አባቴ ከአክስቴ ፓት ወሰደኝ። ከእናቴ ጋር ተለያይቶ ከሌላ ሴት ጋር ይኖር ነበር" ስትል ታስታውሳለች።
የእንጀራ እናቷ የትውልድ እናቷ አለመሆኗን ያወቀችው 10 ዓመት ሲሞላት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Courtesy of Ijeoma Uchegbu
ሌላዋ እናት
ወላጅ እናቷን የተዋወቀችው በ13 ዓመቷ ነበር።
"ስታገኘኝ በጣም ደስተኛ ሆና ነበር። ፈርታም ነበር። ስንተቃቀፍ ተንቀጠቀጠች። ለእኔ እንግዳ ሰው ነበረች። ግን ውብ ቅዳሜ እና እሑድ አሳለፍን" በማለት ታስታውሳለች።
የእነ ኢጄዎማ ቤተሰብ ስድስት ነበር። ከዚያም ከእናቷ ጋር እየኖረች የነበረችውን ታናሽ እህቷን ተዋወቀች።
"ገበያ ስንወጣ አንድ እቃ ስመለከት ካየችኝ 'ትፈልጊዋለሽ?' ብላ ትጠይቀኝና ይገዛልኛል። ነገር ግን እናቴ ለምን በሕይወቴ እንዳልነበረች አልነገረችኝም።"
እናቷን ይሄንን ጥያቄ ብትጠይቅ በመልሱ ደስተኛ እንደማትሆን አሰበች። እናቷን በተዋወቅ በዓመቱ እናቷ አሜሪካ ሄደች።
ብዙም ሳትቆይ በ33 ዓመቷ ሞተች።
"እናቴ መሞቷን ስሰማ ጮህኩ። ዳግመኛ ሳላያት ቀረሁ" ትላለች ኢጄዎማ።
እናቷን ብቻ ሳይሆን የእንጀራ እናቷን እና አሳዳጊ እናቷንም ማጣቷ ጎድቷታል።

የፎቶው ባለመብት, Courtesy of Ijeoma Uchegbu
አባቷ 11 ልጆች ነበሯቸው።
"አባቴ ድንቅ ሰው ነው። አንድ ቀን ልደቴን ረስቶ አያውቅም። ሁላችንንም ያጫውተናል፤ ተረት ያነብልናል፤ መካነ እንሰሳት ይወስደናል" ስትል አባቷን ትገልጻለች።
ወደ ናይጄሪያ መመለስ የሁሌም ሕልሟ ነበር። በእርስ በርስ ጦርነቱ ምክንያት ግን ሕልሟ ሳይሳካ ቆይቷል።
ናይጄሪያ ካለው ቤተሰቧ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ነበራት። ከዓመት ዓመት ወደ ናይጄሪያ ለመመለስ ቃል ትገባላቸውም ነበር።
በአወሮፓውያኑ 1960ዎቹ እና 1970ዎቹ በዩናይትድ ኪንግደም ነው ያደገችው። ዘረኝነት የተስፋፋበት ፈታኝ ወቅት ነበር።
መምህሯ በጣም ይተማመኑባት እንደነበር ትናገራለች። ማንኛውንም ነገር ማድረግ እንደምትችል ይነግሯታል።
እሷ ግን ሱቅ ተቀጥራ መሥራት ጀመረች።
"እንደ እኔ ያሉ ሰዎች በሙያ መስክ ተሰማርተው ስለማላይ ራሴን እንደ ባለሙያ መቁጠር አልቻልኩም" ትላለች።
አባቷ ወደ ናይጄሪያ ለመመለስ ፈቃድ ሲያገኙ ሕይወቷ ተለወጠ።
"ወደ ማላውቀው አገር ስሄድ ጓደኞቼን ትቼ ነበር። ግን ደፋር ለመሆን ወሰንኩ። ለመሄድ መወሰኔን ለትምህርት ቤቱ ኃላፊ ስናገር እያለቀስኩ ነበር። 'ናይጄሪያ ፀሐያማ የገና በዓል ይጠብቅሻል' ብለው ሲሰናበቱኝ የበለጠ አለቀስኩ።"
ጉዞ ወደ ናይጄሪያ
ናይጄሪያ እንደተመለሰች በፀሐይ አለርጂ ምክንያት ከቤት መውጣት አልቻለችም።
ኢጄዎማ በናይጄሪያ ትምህርት ቀጠለች። ነገሮች ቀላል ሊሆኑላት ግን አልቻሉም።
"ተቀባይነት ለማግኘት ከበደኝ። አነጋገሬ ከእነሱ የተለየ ነበር። በጦርነት ውስጥ ሲያልፉ እኔ ዩናይትደ ኪንግደም ነበርኩ። ሁሉም ነገር ሲረጋጋ በመሄዴ ደስተኛ አልነበሩም።"
የሁለት የተለያዩ ባህሎች መጋጨትም ገጠማት።
በእርስ በርስ ጦርነት በተጎዳችው አገር የሚታየው ሁሉ ውድመት ነው። መብራት አና ውሃ ማግኘት እንደ ቅንጦት ሆነ።
በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ከለመደችው ሕይወት እና ትምህርት የተለየ ሕይወት በናይጄሪያ ጠበቃት።
ዩኬ ሳለች ከክፍሏ ጎበዟ ተማሪ ነበረች። ናይጄሪያ ግን የአውሮፓን ታሪክና ጂኦግራፊ መማር ነበረባት።
"በሁለቱም አገሮች ተመሳሳይ ትምህርት የነበረው ሳይንስ እና ሒሳብ ነው። እነዚህን ትምህርቶች ስለማውቃቸው ወደእነሱ አዘነበልኩ" ትላለች።
የሱቅ ተቀጣሪ ሆና ለመሥራት ታስብ የነበረቸው ኢጄዎማ፤ ናይጄሪያ ከሄደች በኋላ ሐሳቧን ለወጠች።
"እንዴት የሱቅ ተቀጣሪ ለመሆን እመኛለሁ? ብዬ ራሴን ወቀስኩ። ዩኒቨርስቲ ለመግባት ወሰንኩ" ትላለች።
መጀመሪያ አካባቢ ነገሮች ቀላል ባይሆኑላትም ናይጄሪያ መሄድ አዲስ ሕልም እንድትሰንቅ አገዛት።

የፎቶው ባለመብት, Courtesy of Ijeoma Uchegbu
ከጎዳና ወደ ፍቅር
በ16 ዓመቷ የፋርማሲ ትምህርት ጀመረች።
ሁለተኛ ዲግሪዋን ከጨረሰች በኋላ አግብታ ሦስት ልጆች ወለደች። ከዚያም ወደ ዩኬ ተመለሰች።
ሕልሟ ሳይንቲስት መሆን ነበር። ናይጄሪያ ሆና ይሄንን ሕልም ለማሳካት ቀላል አልሆነም።
"ሁሉም ሰው እንደማይሳካልኝ ነገረኝ። በድህነት ምክንያት ወደ ናይጄሪያ ትመለሻለሽ አሉኝ" ትላለች።
በቂ ገንዘብ ባይኖራትም ልጆቿን ይዛ ለንደን ገባች። ብዙም ሳትቆይ ለጎዳና ተዳዳሪዎች የተዘጋጀ መጠለያ ገባች።
"11 ቤተሰቦች አንድ መፀዳጃ ይጠቀሙ ነበር። አንዳንዴ ጓዳው ስለሚዘጋ ምግብ አናበስልም። ለሰባት ወራት ቆይቼ ስወጣ ከእስር ቤት የመለቀቅ ያህል ነበር።"
ፈተናው ቢበረታም ወደ ናይጄሪያ ለመመለስ አላሰበችም። በዩኬ የዶክትሬት ዲግሪዋን ለመቀጠል መሞከር ጀመረች።
ስለ ጥቃቅን ቅንጣቶች (tiny particles) ጥናት የሚደረግበትን ዘርፍ መረጠች። በዘርፉ ምንም ዕውቀት አልነበራትም።
ከመንግሥት በሚደረግላት ድጎማ ቤተሰቧን እያስተዳደረች ጥናቷን ቀጠለች።
ከሦስት ዓመታት በኋላ ሕይወቷን የለወጠ ኮንፈረንስ ላይ ተሳተፈች።
ጀርመናዊው ሳይንቲስት አንድሬስ ጂ ሻልትዘን ጋር ተዋወቀች። "ለአራት ሰዓታት ካወራን በኋላ በፍቅሩ ወደቅኩ" ትላለች።
ከኮንፈረንሱ በኋላ ሲሰነባበቱ ዳግመኛ እንደማታገኘው እያሰበች ነበር።
"ስልኬን መስጠት ስላሳፈረኝ የፖስታ አድራሻዬን ሰጠሁት። እወድሻለሁ ብሎ ተሰናበተኝ።"
ከሳይንቲስቱ ስትጠብቀው የነበረው ደብዳቤ ደረሳት።
"ደብዳቤው ላይ ማንበብ የምፈልገውን ሁሉ ጽፏል። ግን የምንኖረው የተለያየ አገር ነው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከእኔ ጋር ለመኖር ወደ ዩኬ መጣ" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Phil Mynott
ከሰዎች ፀጉር በአንድ ሺህ በሚያንሱ ጥቃቅን ቅንጣቶች አማካይነት ለሰዎች መድኃኒት መስጠት ላይ ያተኮረውን ጥናቷን እያካሄደች ነበር።
"መድኃኒት በእንክብል ወይም በመርፌ ሲወሰድ የደም ሕዋስ ውስጥ ይገባል። የሰውነት ክፍሎችንም ያልፋል። ሁሉንም የሰውነት ክፍሎች እንዲያዳርስ ተፈልጎ ላይሳካ ይችላል። ስለዚህ ቅንጣቶችን በመጠቀም መድኃኒት ማድረስ ይቻላል" ስትል ታስረዳለች።
ለካንሰር ሕክምና የሚውለውን ኬሞቴራፒ እንደሚያዘምን ይታመናል። ለከፍተኛ ሕመም በታዘዘላቸው አደንዛዥ መድኃኒት ሱስ የተያዙ ሰዎችንም ይረዳል።
አሁን መድኃኒቱ ሙከራ እየተደረገበት ነው። በጠብታ አማካይነት ዐይነ ስውርነትን ለማዳን ሙከራዎች ተደርገዋል።
ኢጄዎማ ኡቼግቡ አሁን ላይ በዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ኦፍ ለንደን ውስጥ በፋርማሱቲካል ናኖሳይንስ ፕሮፌሰር ሆናለች።
በዩኒቨርስቲ ኦፍ ኬምብሪጅ ውስጥ የዎልፍሰን ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ናት።
ከሳይንስ በተጨማሪ ኮሜዲ ትወዳለች። የ10 ሳምንታት የኮሜዲ ትምህርትም ወስዳለች። በለንደን ቴአትር የኮሜዲ ትርኢት አቀርባለች።
"ያስፈራ ነበር፤ ግን ተዝናንቻለሁ" ስትል ትገልጸዋለች።
አናሳ ማኅበረሰቦች የተሻለ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ለማበረታታት በተለያዩ ትምህርት ክፍሎች ንቅናቄ ታደርጋለች።
"የአናሳ ማኅበረሰብ ተማሪዎች በማዕረግ እምብዛም አይመረቁም። ሴቶች ላይ ደግሞ የበለጠ ጫነው ይበረታል" ትላለች።
"አንድ ሴት መጣችና 'አካል ጉዳተኛ ነበርኩ፤ ስላደረግሽልን ድጋፍ አመሰግናለሁ' አለችኝ። በጣም ነው ስሜቴ የተነካው" ስትልም ትናገራለች።
ከሕይወት ተሞክሮዋ ተነስታ አንድ የምትሰጠው ምክር፤ ገንዘብ ለማግኘት ብቻ አንድ ሙያ አለመምረጥን ነው።
"የምትወዱትን ምረጡ። ሰው የሚወደውን ነገር ከተከተለ ሕልሙን ያሳካል።"















