ሰዎች በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንኳን በፍጹም ፍርሃት እንዳይሰማቸው የሚያደርገው ሕመም

የፎቶው ባለመብት, Serenity Strull/ BBC
ፍርሃት ራሳችንን ከአደጋ የምንጠብቅበት ዝግመተ ለውጣዊ ባህሪ ነው። ፍርሃት ደመ ነፍሳዊ ነው።
ፍርሃት የሌለው ሕይወት ምን ይመስል ይሆን? ለብዙዎቻችን ይሄንን ስሜት መገመት ከባድ ነው።
እጅግ ጥቂት ሰዎች ግን ይሄንን እውነታ ይኖሩታል። ከአውሮፕላን ቢዘሉም እንኳን ቅንጣት ያህል ፍርሃት አይሰማቸውም።
በሰውነታቸው አድሬናሊን ሆርሞን አይዘዋወርም፤ ፈርተው የልብ ምታቸው አይጨምርም።
ጆርዲ ክረንክ ከጥቂቶቹ አንዱ ነው። አድሬናሊን ሆርሞን የሚያመነጨው ዕጢ ከመጠን በላይ ሆርሞን ሲያመርት የሚያስከትለው ሕመም (Cushing's syndrome) ነበረበት።
በዚህ ሕመም ምክንያት ከፍተኛ የጭንቀት ሆርሞን (cortisol) ያመነጭ ስለነበር ዕጢውን አስወጥቷል።
ኮሪስትሮል አምራች ዕጢ ከሰውነቱ ከወጣ በኋላ አንዳችም ፍርሃት ከማይሰማቸው ሰዎች አንዱ ሆኗል።
በከፍታ ላይ ሆኖ የሚሽከረከር መጫወቻ (rollercoaster) ላይ ሲወጣ ምንም አልፈራም። ከአውሮፕላን ላይ ሲዘልም ፍርሃት አልገባውም።
ሰዎችን ከፍርሃት ነጻ የሚያደርገው ሕመም ኧርባች ዌይዝ (Urbach-Wiethe) ወይም ሊፖይድ ፕሮቲኖሲስ (lipoid proteinosis) ይባላል።
እስካሁን በበሽታው የተያዙ ሰዎች 400 ብቻ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሕመሙ ያለባት አንዲት ግለሰብ ላይ በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ በዩታ ዩኒቨርስቲ ምርምር ተካሂዷል።
በ2000 ጀስቲን ፈርንቲን የጥናት ቡድኑን ተቀላቀለ።
"አስፈሪ ፊልሞችን በአጠቃላይ ብናሳያትም በፍጹም ፍርሃት አላሳየችም" ይላል የሥነ ልቦና ባለሙያው።
ለጭንቀት እና ፍርሃት ሕክምና የሚሰጥ የሥነ ልቦና ዘዴ ላይ ምርምር ያደርጋል።
በርካቶችን የሚያሸብሩ እባቦች እና ሸረሪቶች ቢያሳዩዋትም ፍርሃት አልፈጠሩባትም።
እንዲያው��� አስፈሪዎቹን እንሰሳት ተጠጋቻቸው።
"በጣም በቅርበት ልታያቸው እና ልትነካቸው ፈለገች" ሲል ይገልጻል ባለሙያው።
ሕመሙ በዘረ መል የሚተላለፍ ነው። ኢሲኤም1 የተባለው ዘረ መል ውስጥ ነው የሚገኘው።
ሕዋሳትን አንድ ላይ ተሳስረው እንዲሠሩ የሚያደርገውን ፕሮቲን በማመንጨት የሚታወቅ ዘረ መል ነው።
ኢሲኤም1 (ECM1) ሲጎዳ የካልሽየም እና ኮሎኝ ክምችት ይፈጠራል። የሕዋሳት ሞትም ያስከትላል።
ፍርሃት የሚፈጠረው አሜግድላ በተባለው የአንጎል ክፍል ነው። በሽታው አሜግድላን ሲጎዳ ሰዎች ፍርሃት ያቆማሉ።
"ምርምሩ የተደረገባት ሴት ፍርሃት ባይሰማትም ሌሎች ስሜቶች አሏት" ሲል ባለሙያው ይናገራል።
አሜግድላ የተለያዩ ዓይነት ፍርሃቶች መነሻ ነው። አይጦች ላይ በተሠራ ጥናት መሠረት፤ አይጦች የኤሌክትሪክ ንዝረት እንዲሰማቸው ተደርጎ ድምጽ ከሰሙ በኋላ ንዝረቱን ከድምጹ ጋር ስለሚያስተሳስሩ ድምጹን ሲሰሙ ፍርሃት ያሳያሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምርምር የተደረገባት ሴት በሰውነቷ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ትኩስ መጥበሻ መንካትን የመሰሉ ድርጊቶችን የማትፈጽመው ስለምትፈራ ሳይሆን ምክንያታዊ ውሳኔ ላይ በመድረስ ነው።
ሕመም ሊፈጥርባት የሚችል ነገር ሲገጥማት የፈራ ሰው የሚያሳያቸውን ምልክቶች አታሳይም።
ሌሎች ሰዎች ፍርሃት ሲሰማቸው መረዳትም አትችልም። ደስታ እና ሐዘንን ከሰዎች ፊት ማንበብ ብትችልም ፍርሃትን አትረዳም።
በቀላሉ ከሰው ጋር የምትግባባ ደግ ሰው ብትሆንም ፍርሃት መፍጠር ያለባቸው ድርጊቶችን አታስተውልም።
ስለት ወይም ሽጉጥ የያዘ ሰው ቢገጥማት አትፈራም።
"ልትቀርባቸው የማይገባትን ሰዎች ትቀርባለች። ማንን ማመን እንዳለባት ስለማትገነዘብ አደጋ ውስጥ የመውደቅ ዕድሏ ሰፊ ነበር" በማለት የሥነ ልቦና ባለሙያው ያብራራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታማሚዋ ከሌሎች በጎ ፈቃደኞች ጋር በመሆን በተሳተፈችበት ጥናት፤ የማታውቀው እንግዳ ሰው እስከ 1 ጫማ እንዲቀርባት ፈቅዳለች። የተቀሩት የጥናቱ ተሳታፊዎች ግን ርቀታቸውን መጠበቅ መርጠዋል።
"አሜግድላቸው የተጎዳ ሰዎች ከሰዎች ጋር አፍንጫ ለአፍንጫ ገጥመው ሊቆሙ ይችላሉ" ሲል በአሜሪካ፣ ሜሪላንድ የሥነ ልቦና መምህር አሌክሳንደር ሻክማን ይናገራል።
በማኅበራዊ ግንኙነታችን ምን ዓይነት ባህሪ እንደምናሳይ የሚወስነው አሜግድላ ነው።
ከአሜግድላ ውጭ የሚከሰቱ የፍርሃት ዓይነቶችም አሉ።
በታካሚዋ ላይ የተሠራው አንድ ጥናት ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ ሰውነቷ እንድታስገባ አድርጓል።
ካርቦን ዳይኦክሳይድ ሰዎች ፍርሃት እንዲሰማቸው የሚያደርግ ንጥረ ነገር ነው።
አሜግድላቸው የተጎዳ ሌሎች ሁለት ታካሚዎች ካርቦን ዳይኦክሳይድ ሲሰጣቸው ፍርሃት ተሰምቷቸዋል። በዋነኛነት ምርምሩ የተደረገባት ሴት ግን ጭንቀት እንጂ ፍርሃት አላሳየችም።
"የተሰማት ጭንቀት በሕይወት ዘመኗ አይታው የማታውቀው ዓይነት ፍርሃት ነበር" ሲል ባለሙያው ጀስቲን ፈርንቲን ያስረዳል።
አንጎል ውስጥ ሁለት የፍርሃት መስመሮች አሉ። አንደኛው ለውስጣዊ ስጋት ሌላኛው ደግሞ ለውጫዊ ስጋት የሚሰጥ ምላሽ ናቸው።
ውጫዊ ስጋት ሲፈጠር አሜግድላ በሚያስተላልፈው ትዕዛዝ አማካኝነት ሰውነት ምላሽ ይሰጣል።
አንጎል ውስጥ ምሥል፣ ድምጽ፣ ሽታ እና ንክኪን የሚገነዘበው ክፍል መረጃውን አብላልቶ ለሰውነት መልዕክት ያስተላልፋል።
አሜግድላ ሌባ ቤት ሰብሮ ሲገባ ወይም እባብ ሲቃረብ ሰውነት ራሱን እንዲከላከል ትዕዛዝ ይሰጣል።
"የልብ ምት እና የደም ግፊት የሚጨምረው ከአንጎል መልዕክት ሲተላለፍ ነው" ሲል ባለሙያው ይናገራል።
ውስጣዊ ስጋት የሚባለው ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ ሰውነት ሲገባ የሚሰማው ስሜት ነው።
ሰውነት ሊታፈን እንደሆነ ይታወቀዋል። አእምሮ የኦክስጂን መጠንን የሚለካበት መንገድ ስለሌለው አተነፋፈስን ለመቆጣጠር ይጣጣራል። ድንጋጤ የሚፈጠረውም በዚህ ወቅት ነው።
አሜግድላቸው የተጎዳ ሰዎች ፍርሃት የማይሰማቸውም ለዚህ ነው። አንዳንድ ታካሚዎች ደግሞ ከመጠን ያለፈ የፍርሃት ምላሽ ይሰጣሉ።
"አሜግድላ ሁሉንም ዓይነት ፍርሃት አይፈጥርም። ለሌባ፣ ለእባብ ወይም ለሸረሪት የሚሰጠው ምላሽ የተለየ ከውስጣዊ ፍርሃት ነው" በማለት ባለሙያው ያስረዳል።
ሙሉ በሙሉ አሜግዳቸውን ያጡ ሰዎች ያላቸው የፍርሃት ማጣት እንደ ሌሎች ፍርሃት አልባ ሰዎች አይደለም።
አጥቢ እንሰሳት፣ ወፎች እና ዓሣ ፍርሃት የሚያሳዩት በዝግመተ ለውጥ ምክንያት ነው።
ራሳቸውን ለመከላከል እና በሕይወት ለመቆየት ፍርሃት የግድ ያስፈልጋቸዋል።
"አሜግድላ የሌለው እንሰሳ ዱር ውስጥ ቢለቀቅ በሰዓታት ይሞታል። አደጋ ሲቃረብ ማየት አለመቻሉ ሕይወቱን ያሳጣዋል" ይላል የሥነ ልቦና ባለሙያው።
በእርግጥ አሜግድላ የሌላት ታካሚ ለረዥም ዓመታት ኖራለች።
ምናልባትም በዘመናዊው ሕይወት ፍርሃት እንደቀደመው ጊዜ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል የሚል ዕሳቤ መነሻም ሆናለች።















