አሜሪካ የኮሎምቢያ ተዋጊዎችን ለሱዳን ጦርነት መልምለዋል ባለቻቸው ላይ ማዕቀብ ጣለች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
አሜሪካ በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት እንዲሳተፉ የቀድሞ የኮሎምቢያ ተዋጊዎችን መልምሏል ያለችው 'ኔትዎርክ' ላይ ማዕቀብ ጣለች።
የውጭ ሃብትን የሚቆጣጠረው የአሜሪካ ግምጃ ቤት እንዳስታወቀው በዋናነት የኮሎምቢያ ዜጎች የሆኑ ስምንት ተቋማት እና ግለሰቦች ከሱዳን ጦር ጋር እየተፋለመ ላለው የሱዳንን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስ ኤፍ) ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ የኮሎምቢያ ተዋጊዎች አርኤስኤፍን በውትድርና ለማገልገል እና ለድሮን አብራሪነት ከአውሮፓውያኑ 2024 ጀምሮ ወደ ሱዳን መጓዛቸውን ቢሮው በመግለጫው አስታውቋል።
ባለፈው ዓመት የኮሎምቢያው ፕሬዝደንት ጉስታቮ ፔትሮ ለገንዘብ ሲሉ "በውጭ አገር የወጣቶችን ደም የሚያፈሱ በወንጀል ሊቀጡ ይገባል" ብለዋል።
በውጭ አገር ግጭቶች የቀድሞዎቹም ሆኑ አዲስ ተመልማይ ወታደሮች ተሳትፎ አሜሪካ ከአስርተ ዓመታት በፊት በአፍጋኒስታን እና ኢራቅ ወዳደረገችው ጦርነት የሚመልስ ነው።
በትምህርት ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ እና ጡረታ የወጡ የጦር መኮንን "በእነዚያ ጦርነቶች ተሳትፈው የነበሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው የኮሎምቢያ ወታደሮች ከሁለት አስርተ ዓመታት በኋላ ያለ ምንም በቂ የገቢ ምንጭ ጡረታ መውጣት ጀምረዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ሙንዶ ተናግረዋል።
አልፎንሶ ማንዙር እንደሚሉት በዚህም ምክንያት የቀድሞ የኮሎምቢያ ወታደሮች በውጭ አገር ተልዕኮ ተሰማርተው ይታያሉ።
ጡረታ የወጡ የኮሎምቢያ ወታደሮች እንደ የሩሲያ እና ዩክሬን እንዲሁም እንደ ሱዳን ባሉ ጦርነቶች ከመሳተፋቸው በፊት "ብዙም ለአደጋ የማያጋልጥ ሥራ" ላይ እንደሚሠማሩ በሚገባላቸው የሐሰት ቃል እንደሚመለመሉ ማንዙር ተናግረዋል።
በአውሮፓውያኑ 2024 የኮሎምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጎቹ "ውስብስብ በሆኑ የሰዎች አዘዋዋሪ ሰንሰለቶች" ተታለው በዓለም አቀፍ ጦርነቶች ላይ ቅጥረኞች እንደሆኑ እንደሚያውቅ ገልጿል።
የውጭ ሃብቶችን የሚቆጣጠረው የአሜሪካ ግምጃ ቤት ባወጣው መግለጫም ከሁለት ዓመታት በፊት ከአገሪቱ ጦር ጋር ለሚፋለመው አርኤስኤፍ ተዋጊዎችን የሚመለምል 'ኔትወርክ'ን ዒላማ ማድረጉን ነው የገለጸው።
የቢሮው የሽብር እና የገንዘብ ደኅንነት ምክትል ኃላፊ ጆን ሃርሊይ " አርኤስኤፍ ጨቅላ ሕፃናትን እና ታዳጊዎችን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ የማድረግ ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ አሳይቷል" ብለዋል።
ጭካኔው "ግጭቱን በማባባስ ቀጣናውንም አፈራርሷል" ያሉት ምክትል ኃላፊው፣ ሽብርተኛ ቡድኖች እንዲጠናከሩ ማድረጉንም ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በበኩሉ ቡድኑ እና አጋር ሚሊሻዎቹ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን እና "ስልታዊ በሆነ መንገድ አዋቂ እና ወጣት ወንዶችን ገድለዋል፤ ሴቶች እና ልጃገረዶችን ሆነ ብለው ደፍረዋል" ብሏል።
ምንም እንኳን ጦሩም ሆነ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በጦር ወንጀል ቢከሰሱም እየተገባደደ ባለው የኣውሮፓውያኑ ዓመት መጀመሪያ ላይ የአርኤስኤፍ አባላት "የዘር ጭፍጨፋ" መፈጸማቸውን መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።
ቡድኑን በመርዳት የተከሰሰው 'ትራንዚሽናል ኔትወርክ' አራት ተቋማት እና የኮሎምቢያ እና ጣልያን ጥምር ዜግነት ያለውንና አሁን በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ተቀማጭነቱን ያደረገ የቀድሞ የጦር መኮንን ጨምሮ አራት ግለሰቦችን የያዘ ነው።
ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ አርኤስኤፍን በማስታጠቅ የምትከሰስ ሲሆን፣ አገሪቷ ግን ይህንን በተደጋጋሚ አስተባብላለች።
ነሐሴ ወር ላይ የሱዳን የመንግሥት ቴሌቪዥን የአገሪቷ አየር ኃይል ቢያንስ 40 የኮሎምቢያ ተዋጊዎች ያሳፈረች የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስን አውሮፕላን መትቶ መጣሉን እና ሁሉም መሞታቸውን ዘግቧል።
ምንም እንኳን በወቅቱ የኮሎምቢያ ፕሬዝደንት ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ እና አስክሬናቸውን መመለስ ይቻል እንደሆነ ለማረጋገጥ እየሞከረ እንደሆነ ገልጸው የነበረ ቢሆንም፣ ኤምሬትስ ክሱን ውድቅ አድርገዋለች።
አሜሪካ ለአርኤስኤፍ "ስልታዊ እና ቴክኒካዊ" ሙያዎችን እንዲሰጡ ወታደሮችን በመመልመል የኮሎምቢያ ኔትወርክን ከሳለች።
በመሆኑም በዚህ ላይ የተሳተፉ አካላት እንዲሁም በአሜሪካ ግለሰቦች ይዞታ ሥር የሚገኙ ሁሉም ንብረቶች እና የንብረት ወለዶች መታገዳቸውን ጠቅሶ፣ ሪፖርት መደረግ እንዳለባቸው ገልጿል።
መግለጫው እንዳለው ከሆነ የኮሎምቢያ ተዋጊዎች መዲናዋን ካርቱም፣ ኦምዱርማን፣ ኮርዶፋን እና ኤል ፋሽርን ጨምሮ በሱዳን የተለያዩ ግንባሮች ላይ ተሳትፈዋል።
በምድር ጦር አርኤስኤፍ ድልን እየተቀዳጀ ሲሆን ከ500 ቀናት ከበባ በኋላ ኅዳር ወር ላይ ኤል ፋሽርን ተቆጣጥሯል።
የሱዳን ጦር ጠንካራ ይዞታ በነበረው ዳርፉር በተደረገው ውጊያም ከአምስት ሺህ በላይ ሰዎች እንደተገደሉ ይገመታል።
የስምንት ሚሊዮን ሰዎች መኖሪያ እንደሆነች የምትገመተው እና በካርቱም እና ዳርፉር መካከል የምትገኘው ኮርዶፋን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዋነኛ የጦር ግንባር ሆናለች።
ሰኞ ዕለት በደቡባዊ ኮርዶፋን በሕጻናት ትምህርት ቤት እና ሆስፒታል ላይ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት 63 ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 114 ሰዎች መገደላቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ጥቃቱን "ትርጉም የለሽ" ሲሉ የተኩስ አቅም እንዲደረግ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።
አርኤስኤፍ "አገሪቷን ነጻ ለማውጣት ወሳኝ" ያለውን የሱዳን ትልቁን የነዳጅ መገኛ ሄግሊግን መቆጣጠሩን ገልጿል።
ባለፈው ወር የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከግብፅ፣ ከሳዑዲ አረቢያ እና ከአረብ ኤምሬትስ ጋር በመሆን የሱዳን ሰላም ጥረት ለመጀመር ቃል ገብተው ነበር።
ትራምፕ "መጠነ ሰፊ ጥቃቶች ተፈጽመዋል" ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ገልጸዋል።
በአገሪቷ የተወሰኑ ክፍሎች ወደ 12 ሚሊዮን ሕዝቦች በረሃብ ምክንያት ቤታቸውን ለቅቀው ለመውጣትም ተገድደዋል።















