የሱዳን አየር ኃይል በከተሞች፣ በገበያዎች እና በትምህርት ቤቶች ላይ በፈጸመው ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው ይፋ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የሱዳን አየር ኃይል በመኖሪያ አካባቢዎች፣ በገበያዎች፣ በትምህርት ቤቶች እና በተፈናቀሉ ሰዎች መጠለያች ላይ በፈጸመው ድብደባ ቢያንስ 1700 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።
ሱዳን ዊትነስ የተባለ እና በአገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚመረምር ፕሮጀክት ግጭቱ ከጀመረበት ከሚያዚያ 2023 ጀምሮ የተካሄዱ ወታደራዊ የአየር ጥቃቶችን በመሰነድ ምርመራ ማድረጉን ገልጿል።
የአገሪቱ አየር ኃይል በርካታ ሰዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ያለምንም በቂ ልየታ የቦምብ ድብደባ መፈጸሙን የተደረጉ ምርመራዎች ያሳያሉ።
መረጃዎች የተሰባሰቡት በጦር አውሮፕላኖች የተፈጸሙ ጥቃቶች ላይ ብቻ ሲሆን፣ የዚህ አቅም ያለው የሱዳን ጦር አየር ኃይል ብቻ ነው ተብሏል።
ተቀናቃኙ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ይህ አቅም የለውም።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የሚጠቀመው ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ሲሆን፣ ይህ ደግሞ በጥናቱ ውስጥ አልተካተተም።
አርኤስኤፍ በምዕራብ የዳርፉር ግዛት ጎሳ ተኮር ጭፍጨፋ በማድረግ ይወነጀላል።
በዚህም የተነሳ የአሜሪካ መንግሥት የዘር ማጥፋት ክስ መሥርቶበታል።
"አርኤስኤፍ ለበርካታ ውድመቶች እና ጥሰቶች ተጠያቂ ነው፤ ያም ተገቢ ይመስለኛል" ብለዋል ፕሮጀክቱን በኃላፊነት የሚመሩት ማርክ ስኖይክ ። አክለውም "ነገር ግን የአገሪቱ ጦርም ለሚፈጽማቸው ድርጊቶች ተጠያቂ መሆን አለበት" ብለዋል።
የአገሪቱ ጦር በዘፈቀደ የአየር ጥቃቶችን በመፈጸም ከዓለም አቀፍ አካላት ትችት ይቀርብበታል።
ቢቢሲ ከሱዳን ጦር ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ነገር ግን ከዚህ ቀደም ሰላማዊ ዜጎችን ዒላማ ያደርጋል የሚለውን ውንጀላ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።
የሚፈጽማቸው የአየር ጥቃቶች የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ተሰብሰብበው የሚገኙባቸው ስፍራዎች እና ካምፖቻቸው ላይ ብቻ ያነጣጠረ መሆኑን በመግለጽ ማስተባበያ ሰጥቷል።
ሱዳን ዊትነስ የተሰኘው ፕሮጀክት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማጋለጥ በሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት 'ሴንተር ኦፍ ኢንፎርሜሽን ሪዚሊያንስ (ሲአይአር)' የሚመራ ነው።
ቢቢሲ የተመለከተው የድርጅቱ ሪፖርት ሱዳን ዊትነስ ከሚያዚያ 2023 እስከ ሐምሌ 2025 ድረስ የተፈጸሙ 384 የአየር ጥቃቶችን መርምሯል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በዚህ ሪፖርት ላይ የሱዳን ጦር በፈጸማቸው የአየር ድብደባዎች ከ1700 በላይ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን እና 1120 ደግሞ መጎዳታቸው ተገልጿል።
ቡድኑ ሪፖርት የተደረጉት አነስተኛ ቁጥሮች በመሆናቸው ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ እንደሚልቅ ይገልጻል።
135 የአየር ጥቃቶች የተፈጸሙት በመኖሪያ አካባቢዎች ሲሆን፣ በቤቶች እና ሌሎች የሰላማዊ ዜጎች መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ተረጋግጧል።
35 የአየር ጥቃቶች ደግሞ የመገበያያ ሥፍራዎች ላይ የደረሱ ሲሆን እነዚህ የገበያ ቦታዎች ብዙ ጊዜ በገበያተኞች የሚጨናነቁ ናቸው ተብሏል።
ቡድኑ ከተመለከታቸው የአየር ድብደባዎች መካከል 19 የሚሆኑት የተፈጸሙት በጤና ተቋማት፣ የተፈናቀሉ ሰዎች በተጠለሉባቸው ሥፍራዎች እና በትምህርት ተቋማት ላይ ነው።
ሱዳን ዊትነስ ጥናቱን ያከናወነው ባገኛቸው መረጃዎች ላይ ብቻ ተመሥርቶ በመሆኑ አጠቃላይ የተፈጸሙ የአየር ድብደባዎችን እንደማያሳይ እና በዚህም የተነሳ ክፍተት እንዳለበት ገልጿል።
ጦርነት ከሚካሄድባቸው የአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች መረጃ ለማግኘት ደካማ የስልክ ግንኙነት በመኖሩ እና ተዓማኒነት ያላቸው የመረጃ ምንጮችን ለማግኘት ፈታኝ በመሆኑ ከባድ ነው።
በዚህም የተነሳ በጦሩ የተፈጸሙ የአየር ድብደባዎችን በሚገባ የሚያሳዩ መረጃዎች ላይሆኑ ይችላሉ ብሏል።
ቡድኑ የአገሪቱ ጦር የፈጸማቸው የአየር ጥቃቶች ላይ በቂ መረጃ ለማግኘት የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀሙን ይናገራል።
"እኛ የሱዳን ጦር ኃይሎች በተወሰነ ቦታ ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙን ለመናገር ይብዛም ይነስ ጦሩ ድርጊቱን ሲፈጽም ሊያረጋገጥ የሚችል ቀረጻ ማግኘትን እንደ ግዴታ አስቀምጠናል" ይላሉ ስኖይክ ።
"ይህ ደግሞ በጣም በከፍተኛ ደረጃ እውነታውን ያሳያል፤ ምክንያቱም እንደዚህ ዓይነት ምሥሎች በሱዳን ውስጥ በጣም ብርቅ ናቸው። ስለዚህ እኛ ያደረግነው በመቶዎች የሚቆጠሩ የአየር ድብደባዎችን በመፈተሽ ትልቁን ምሥል ማሳየት ነው።"
ስኖይክ እንደሚሉት በተደጋጋሚ ያስተዋሉት ጦሩ የሰላማዊ ዜጎች መኖሪያዎች እና ገበያዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ነው።
ከዚህም በተጨማሪ በሰብዓዊ እርዳታ እና ሕክምና ተቋማት ላይ ጥቃቶች ስለመፈጸሙ መረጃዎች መኖራቸው ተገልጿል።
"እነዚህ የተደጋገሙ ጥቃቶች የሱዳን ጦር የሰላማዊ ዜጎችን ጉዳቶች ለመቀነስ በቂ ጥረት እንደማያደርግ ነው" ብለዋል።
ከተለያዩ አገራት ወደ ሱዳን የሚገቡ የጦር መሣሪያዎችን የሚከታተለው 'ኮንፍሊክት ኢንሳይት ግሩፕ' ዳይሬክተር የሆኑት ጀስቲን ሊንች ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሱዳን ሰላማዊ ዜጎች በጦሩ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል በሚካሄደው ውጊያ ያለውን ትልቅ ጉዳት የተሸከሙ ናቸው ይሏቸዋል።
"የሱዳን ጦርነት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተቃጣ ግጭት ነው" ያሉት ዳይሬክተሩ "የአየር ኃይል እና ሌሎች የከባድ መሣሪያ ጥቃቶች ከወታደራዊ ዒላማዎች ይልቅ ሰላማዊ ዜጎች ላይ በዘፈቀደ ተፈጽመዋል።"

የፎቶው ባለመብት, Facebook
ባለፈው ዓመት በሰሜን ዳርፉር በሚገኘው እና ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ስደተኞች በሚገኙበት ዘምዘም የስደተኞች መጠለያ ላይ የደረሰ የአየር ጥቃትን የሚያሳዩ በርካታ ቪዲዮዎች እና ምሥሎች ወጥተዋል።
ይህ ያልፈነዳ ቦምብ ኤስኤች-250 የሚባል ሲሆን የሱዳን ጦር ወታደራዊ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ያመረተው እንደ��ነ ማወቅ ተችሏል።
ስኖይክ "ለምን ተፈናቅለው በመጠለያ ካምፕ ውስጥ ላይ ባሉ ሰዎች ላይ ዒላማውን የማይለይ ቦምብ ትጥላለህ? በወቅቱ ይህ አካባቢ በአርኤስኤፍ ታጣቂዎች እጅ እንኳ አልነበረም። ለጥቃቱ መፈጸም በምክንያትነት የቀረበው እስካሁን ድረስ ግራ ያጋባኛል" ብለዋል።
ሱዳን ዊትነስ የተመለከተው እና ትክክለኛነቱን ያረጋገጠው ሌላ የአየር ጥቃት ላይ 30 ያህል ሰዎች ሲገደሉ ከ10 በላይ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው በሰሜን ኮርዶፋን ግዛት በሚገኝ በሐምረት አል ሼክ ገበያ ነው።
በርካታዎቹ የሱዳን ጦር የፈጸማቸው የአየር ጥቃቶች የደረሱት በአርኤስኤፍ ቁጥጥር ስር በምትገኘው ዳርፉር ነው።
ይህም በነሐሴ ወር 2024 በኤል ዳይን ሆስፒታል ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ያካትታል።
ሱዳን ዊትነስ በቦምብ ጥቃቱ ጉዳት የደረሰበትን ሕንጻ ከተለቀቁት ምሥሎች ላይ ማረጋገጥ ችሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት እና የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት ኤጀንሲ፣ ዩኒሴፍ፣ 16 ሰላማዊ ዜጎች ሕጻናትን እና የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ መገደላቸውን ይፋ አድርጓል።
ጥቃቱን ከጦሩ ጋር አብረው የሚዋጉ ታጣቂዎችም አውግዘውታል።
በደቡብ ዳርፉር የምትገኘው ኒያላ በተደጋጋሚ ጥቃት ከደረሰባቸው ከተሞች መካከል አንዷ ናት።
በከተማዋ የሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የምትልካቸው የጦር መሣሪያ እና ድሮኖችን ለማስገባት ያገለግላል የሚሉ መረጃዎች ይሰማሉ።
ኤምሬትስ ግን አርኤስኤፍን ትደግፋለች የሚለውን ክስ አትቀበልም።
የሱዳን ጦር ደግሞ በከተማዋ የሚገኝ ወታደራዊ አቅርቦትን ዒላማ ማድረጉን ይናገራል።
እንደ ሱዳን ዋር ሞኒተር ግን ጥቃቱ ዒላማቸውን ለይተው በሚመቱ መሣሪያዎች ያልታገዘ በመሆኑ ሰው በሚበዛባቸው አካባቢዎች ጉዳት አድርሷል።
ሱዳን ዊትነስ በበኩሉ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ በከተማዋ በተፈፀመ ጥቃት የመኖሪያ አካባቢዎች እና በዐይን ሆስፒታል አቅራቢያ የሚገኝ መደብር ላይ ጥቃት አድርሶ 63 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።
ቡድኑ በመኖሪያ እና በንግድ ሥፍራዎች የሚደርሱ ጥቃቶች የሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት ከመቅጠፍ ባለፈ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ይገድባሉ።
በጥቅምት ወር በሰሜን ዳርፉር አልኩማ የገበያ ሥፍራ በደረሰ ጥቃት 65 ሰዎች ሲገደሉ 200 ያህል ደግሞ ቆስለዋል።
የሱዳን ጦር የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ታጣቂዎች በመኖሪያ አካባቢዎች ይደበቃሉ በማለት ይወነጅላል።
ከዚህ በተጨማሪም በጦርነት ወቅት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕጎችን እና ደንቦችን እንደሚያከብር፣ የሰላማዊ ዜጎችን እና ንብረታቸውን እንደሚከላከል ይገልጻል።
በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ሁለቱም ወገኖች በጦር ወንጀል ይከሰሳሉ።















