"በቆሰሉ ሰዎች ላይ መኪና ሲነዱ ተመልክቻለሁ" – ከአስከፊው የሱዳን ጦርነት ለማምለጥ የሚደረገው አደገኛ ጉዞ

የፎቶው ባለመብት, Ed Habershon / BBC
አብዱልቃድር አብዱላህ አሊ፤ በሱዳኗ ኤል ፈሸር ከተማ ላይ በተደረገው ከበባ ምክንያት ላለባቸው የስኳር ሕመም የሚሆን መድኃኒት ሳያገኙ ወራትን አሳልፈዋል። በዚህም ምክንያት እግራቸው ላይ የነርቭ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በትክክል ለመራመድ የሚቸገሩት የ62 ዓመቱ አሊ፤ የሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ከተማዋን ሲቆጣጠር እጅጉን መደንገጣቸውን ያስረዳሉ። በምዕራባዊ ዳርፉር የምትገኘውን ይህቺን ከተማ በፍጥነት ለቅቀው ሲወጡ ምንም ሕመም አልተሰማቸውም።
"አርኤስኤፍ በመጣበት ጠዋት የጥይት ተኩስ ነበር፤ ብዙ ተኩስ። ፈንጂም እየፈነዳ ነበር" ይላሉ።
"ሰዎች [በፍርሃት] ከቁጥጥር ውጪ ሆነው ነበር። ከቤታቸው ወጥተው ሮጡ። ሁሉን ሰው ወደ ተለያየ አቅጣጫ ነበር የሚሮጠው፤ አባት፣ ወንድ ልጅ፣ ሴት ልጅ እየሮጡ ነበር" ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ።
ለ18 ወራት በከበባ ውስጥ የቆየችው ኤል ፋሸር ከተማ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የተያዘችበት ሁኔታ የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት አንድ አስከፊ ምዕራፍ ነው።
ቢቢሲ፤ ከኤልፋሸር ያመለጡ ሰዎች እማኝነትን ለመስማት በሰሜናዊው አገሪቱ ክፍል የሱዳን ጦር ወደሚቆጣጠራቸው ግዛቶች ተጉዟል። የቢቢሲ ጉዞዎች በሙሉ በአገሪቱ ባለስልጣናት ክትትል እየተደረገባቸው ነበር።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ከአገሪቱ መደበኛ ጦር ጋር ውጊያ ውስጥ ነው። የኤልፋሸር መያዝ ለቡድኑ ትልቅ ድል ነበር። የሱዳን ጦር ዳርፉር ውስጥ የነበረውን ብቸና ይዞታ ለቅቆ እንዲያፈገፍግ ማድረግ አስችሎታል።
በከተማዋ የተፈጸሙትን ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚያሳዩ ማስረጃዎች መውጣታቸው ግን ቡድኑ ዓለም አቀፍ ውግዘት እንዲደርስበት እና አሜሪካ ጦርነቱን ለመቋጨት የበለጠ ትኩረት እንድትሰጥ ምክንያት ሆኗል።
ማስጠንቀቂያ፦ ይህ ዘገባ አንዳንድ አንባቢያን ሊረብሹ የሚችሉ ገለጻዎችን ይዟል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቢቢሲ ጋዜጠኞች፤ አሊን ያገኟቸው ከኤልፋሸር በ770 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከአል ዳባህ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ በረሃ ውስጥ በተመሰረተ መጠለያ ካምፕ ውስጥ ነው። በወቅቱ ቤተሰባቸው ድንኳን እንዲያገኙ ለማስመዝገብ እየሞከሩ ነበር።
"[የአርኤስኤፍ ተዋጊዎች] ሰዎች ላይ ጥይት እየተኮሱ ነበር፤ አዛውንት፣ ንጹኃን ላይ። ጥይታቸውን የሚጨርሱት እነርሱ ላይ ነበር" ይላሉ።
"የተወሰኑት የአርኤስኤፍ [ተዋጊዎች] በመኪና ነው የመጡት። አንድ ሰው እየተነፈሰ ከተመለከቱ በላዩ ላይ ይነዱ ነበር" ሲሉ የተመለከቱትን ተናግረዋል።
አሊ እንደሚያስረዱት አካባቢው ያመለጡት በቻሉት ጊዜ ሁሉ ሲሮጡ፣ መሬት ላይ እየዳሁ አልያም አደጋ በሚቃረብበት ሰዓት እየተደበቁ ነው። መኖሪያቸው ከኤል ፋሸር ጥቂት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ጉርኒ መንደር ነች።
ከኤል ፋሸር ከተማ የሚሸሹ ሰዎች የመጀመሪያ መዳረሻቸው ጉርኒ ነች። በአቅራቢያው በሚገኘው ዘምዘም የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ኃላፊ የነበረው መሀመድ አባክር አደምም ከከተማዋ ከሸሸ ኋላ ያመራው ወደዚች መንደር ነበር።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሚያዝያ ወር ላይ ዘምዘምን ሲይዙ ነበር ወደ ኤልፋሸር የሸሸው። ጥቅምት ላይ ደግሞ ከኤልፋሸር በወጣ በማግስቱ ከተማዋ በአርኤስኤፍ ተይዛለች።
"መንገዱ በሙሉ በአስከሬን ተሞላ ነበር" ይላል ራሱን የሸመገለ ሰው አስመስሎ በሸሸበት ሰዓት የተመለከተውን ሲያስታውስ።

የፎቶው ባለመብት, Ed Habershon / BBC
የተወሰኑ ሰዎችን ፊት ለፊታችን ቀጥታ በጥይት ደብድበው ወሰዷቸውና ሩቅ ቦታ ወረወሯቸው። መንገድ ላይም ያልተቀበሩ ሬሳዎችን ሜዳ ላይ አይተናል። አንዳንዶቹ ለሁለትና ለሦስት ቀን ያህል እዚያው የተተዉ ነበሩ" በማለት ይናገራል።
"ብዙ ሰዎች ተበታትነዋል። የት እንዳሉ አናውቅም" ሲልም ያክላል።
ወደ አል ዳባህ በሚወስደው ረዥም መንገድ ያልተጓዙ ተፈናቃዮች ከኤል ፋሸር በ70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው የሰብዓዊ እርድታ ማዕከሏ ታዊላ አምርተዋል። ሌሎች ወድሞ ወደ ጎረቤት አገር ቻድ ሸሽተዋል።
በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሠረት፤ ከተማዋ ከመያዟ በፊት ነበሩ ተብለው ከሚገመቱት 260,000 ነዋሪዎች ውስጥ ከግማሽ በታች የሚሆኑት በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ አይታወቅም።
የእርዳታ ድርጅቶች፤ በርካታ ሰዎች በተጋረጠባቸው አደጋ ወይም በተፈጸመባቸው እስር ወይም ገንዘብ ስለሌላቸው ርቀው መሄድ እንዳልቻሉ ያምናሉ።
የመጠለያ ካምፕ ኃላፊ የነበረው አደም የአርኤስኤፍ ተዋጊዎች ሴቶች መደፈራቸውን በማንሳት በበርካታ መልኩ የተገለጸውን የወሲባዊ ጥቃት ጉዳይ ያጠናክራል።
"ሴቷን ከዛፍ ጀርባ ወይ ከእኛ እይታ አርቀው ይወስዳሉ፤ ስለዚህ [የተደረገውን] በአይንሽ አትመለከቺም። ነገር ግን 'እርዱኝ፣ እርዱኝ' እያለች ስትጮህ ትሰሚያታለሽ። ኋላም ትመጣና 'ደፈሩኝ' ትለናለች" ሲል ለቢቢሲ ዘጋቢ ተናግሯል።
በመጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚበዙት ሴቶች ናቸው። ብዙዎቹም በከተማዋ ለሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ወይም ወዳጆቻቸው ደህንነት ሲሉ ማንነታቸው እንዲገለጽ አይፈልጉም።
አንዲት የ19 ዓመት ልጅ፤ በቡድን እየተጓዙ በነበሩበት ሰዓት የአርኤስፍ የፍተሻ ኬላ ጋር ሲደርሱ ተዋጊዎቹ አንዲት ሴትን ነጥለው ስለወሰዱ ያለ እርሷ ጉዟቸውን ለመቀጠል እንደተገደዱ ተናግራለች።
"የፍተሻ ኬላው ጋር ከመኪናው አስወርደው እንደወሰዷት ስመለከት በምንደርስበት ኬላ በሙሉ ሴት ልጅ ይወስዳሉ ብዬ ፈርቼ ነበር። ግን እዚህ እስከምንደርስ ድረስ የወሰዷት እሷን ብቻ ነው" ብላለች።

የፎቶው ባ��መብት, Ed Habershon / BBC
ወደ መጠለያ ጣቢያው የመጣችው ከታናሽ እህቷ እና ወንድሟ ጋር ተጉዛ ነው። ወታደር የነበረው አባቷ በጦርነት ተገድሏል። ኤልፋሸር ስትያዝ እናቷ ከተማ ውስጥ አልነበረችም።
ሦስቱ ልጆች በእግር የሚደረገውን የሽሽት ጉዞ የጀመሩት ከአያታቸው ጋር ነበር። ነገር ግን አያታቸው ጉርኒ ከመድረሳቸው በፊት ሕይወታቸው በማለፉ እሳቸውን ጥለው ጉዟቸውን ቀጥለዋል።
"በጣም ሩቅ እንደሆነ ስላላወቅን በቂ ውሃ አልያዝንም ነበር" ትላለች የ19 ዓመቷ ልጅ።
"የልብ ምቷ መኖሩን አረጋገጥኩ፤ እሷ ግን አልነቃችም። በአቅራቢያ ያለ መንደር ውስጥ ሐኪም አገኘሁ። እርሱም መጥቶ 'አያትሽ ነፍሷን ሰጥታሻለች' አለኝ። ለእህቴ እና ለወንድሜ ስል ራሴን ለመቆጣጠር እየሞከርኩኝ ነበር። እንዴት ብዬ ለእናቴ እንደምነግራት ግን አላወቅኩም ነበር" በማለት በወቅቱ የተሰማትን አስረድታለች።
ሁሉም ሰው ግን ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች አላመለጠም። የ62 ዓመቱ አሊ፤ የአርኤስኤፍ ወታደሮች በቡድን የነበሩ በርካታ ወንዶች ላይ ተኩስ ሲከፍቱ ከርቀት መመልከታቸውን ተናግረዋል።
"ሁሉንም ወንዶች ገድለዋቸዋል። ሴቶችን አልገደሉም። ወንዶች ሁሉ ግን ተገድለዋል። ብዙ የሞቱ ሰዎች ነበሩ፤ እኛ ሮጠን" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ብዙዎቹ ወደ ተፈናቃዮች ካምፑ የመጡ ሰዎች የደረሱት ባዶ እጃቸውን ነው። ከተማውን ለቅቀው የወጡት ጥቂት ነገር ይዘው ነው፤ በየመንገዱ ያሉ የፍተሻ ኬላዎችን ለማለፍም ገንዘብ መክፈል ነበረባቸው።

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
የመጠለያ ጣቢያ ኃላፊ የነበረው አደም፤ "የአርኤስኤፍ ተዋጊዎች ያለንን ገንዘብ፣ ስልክ ሁሉ፣ ጥሩ ልብሶቻችንን እንኳ ወስደውብናል። በቆምንበት በእያንዳንዱ ቦታ ወደ ቀጣዩ ኬላ ከማለፍችን በፊት ወደ ቤተሰብ ደውለን ወደ ገንዘብ እንድናስተላለፍ አድረገውናል" ሲል ያጋጠመውን አስረድቷል።
ስለእነዚህ ክሶች ምላሽ እንዲሰጥ ጥያቄ የቀረበለት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በንጹኃን ላይ ስልታዊ በደል እየፈጸመ ነው መባሉን አስተባብሏል።
የአርኤስኤፍ አዛዥ ጄነራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ኢብራሂም ሙክሃይር፤ "የተነሳው ይህ የዘረፋ፣ ግድያ፣ ወሲባዊ ጥቃት ወይም ንጹኃንን የማንገላታት ክስ የእኛን መመሪያ አያንጸባርቅም" በማለት ተከላክለዋል።
"የማይገባ ድርጊት መፈጸማቸው የተረጋገጠ ማንኛውም የአርኤስኤፍ አባል ሙሉ ተጠያቂነት ይረጋገጥበታል" ሲሉም አክለዋል።
በቡድናቸው ላይ የሚቀርበው ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክስ፤ በሱዳን ወታደራዊ በሚመራው አስተዳደር ውስጥ ያሉ ኢስላማዊ አካላት በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ቡድኑ ላይ የከፈቱት ፖለቲካዊ ዘመቻ አካል ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።















