ከልጅነቷ ጀምሮ በፈተናዎች ውስጥ ያለፈችው የአወዛጋቢው የሚስ ዩኒቨርስ ውድድር አሸናፊ

ፋጢማ ቦርሽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፋቲማ ቦሽ ሁልጊዜ ታይላንድን መጎብኘት ትፈልግ ነበር። ስለዚህ የ74ኛው የሚስ ዩኒቨርስ የቁንጅና ውድድር በዋና ከተማዋ ባንኮክ እንደሚካሄድ ስታውቅ፣ ህልሟን ለማሳካት እንደተቃረበ ት ተገነዘበች።

"አንድ ከተማ ቀልብሽን ከሳበው እና ሁልጊዜ ስለ ከተማው የምታስቢ ከሆነ፣ እዚያ በጽሁፍ ለመስፈር የሚጠብቅ ታሪክ እና ያልተጠናቀቀ ነገር ስላለሽ ነው" ስትል በታባስኮ ግዛት በምትገኛው ቲያህፓ የተወለደችው ሜክሲካዊቷ ባለፈው መስከረም በተደረገ ቃለ ምልልስ ተናግራለች።

ኋላ ላይ ያሳካችውን በዓለም ላይ ትልቁ የቁጅና ውድድር አሸናፊ ለመሆን ምን ያህል ጊዜ እንዳሰበች እሷ ብቻ ናት የምታውቀው።

በኅዳር መጀመሪያ ላይ እንደ ሚስ ዩኒቨርስ ድርጅት ፕሬዝዳንት ራውል ሮቻ ገለጻ ከአዘጋጆቹ ከወድደሩ ካስወጣት በኋላ በተነሳው ውዝግብ በዓለም ዙሪያ የመገኛኛ ብዙኃንን ቀልብ ለመሳብ ችላለች።

ከአዘጋጁ ጋር ያደረጉት ተደጋጋሚ እንካ ሰላንትያ ሌሎች ተወዳዳሪዎች ውድድሩን ጥለው እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል።

ሽልማቱን ከተረከበች በኋላ "የወይዘሪት ዩኒቨርስን አብነት የቀየረች እና ልቧን የምትሰጥ እውነተኛ ሰው እንደሆንኩ መታወስ እፈልጋለሁ" ብላለች።

ነገር ግን፤ በአወዛጋቢው ውድድር ላይ ያልተጠበቀች ኮከብ እና ውድድሩን በማሸነፍ አራተኛዋ ሜክሲኳዊት የሆነችው ይህች የ25 ዓመት ሴት ማን ናት?

ፋጢማ ቦሽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የልጅነት ጊዜ

ልጅነቷ ሁልጊዜ ቀላል አልነበረም።

በፍቅር በተሳሰረ ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደገች ቢሆነም እንደ ቦሽ ገለጻ፣ በትምህርት ቤት የተደጋጋሚ የሥነ ልቦና እና አካላዊ ጥቃት ሰለባ ነበረች።

በለጋ ዕድሜዋ፣ ትኩረት ማድርግን በሚፈታተን በሽታ (ADHD) እንዳለባት ታውቋል፣ ይህም በትምህርት ዘመኗ ውስብስብ ፈተናዎ��ን አስከትሎባታል።

ነገር ግን ይህ ለስኬት ያላትን ጉጉት እንዳልገደበው ትናገራለች። ከጊዜ በኋላ ደስተኛ እና በራስ የመተማመን ባህሪ እንዳዳበረች ተናግራለች።

ቦሽ በሜክሲኮ ሲቲ በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኢቤሮ አሜሪካና የፋሽን ዲዛይን አጥናለች። በጣሊያን ሚላን እና በዩናይትድ ስቴትስ ተመሳሳይ ትምህርት ተከታትላለች።

እንደ አሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ፣ ወጣቷ ሴት የሙያዋን ዘላቂ ዲዛይኖችን በመፍጠር እና ከተጣሉ ቁሳቁሶች ጋር በመሥራት ላይ የተመሠረተ ነበር።

በተጨማሪም የታመሙ ሕጻናትን ለመርዳት በበጎ ፈቃደኝነት ሠርታለች፤ የአካባቢ ጥበቃ ላይ ግንዛቤ እንዲጨምር እንዲሁም ከስደተኞች እና ከአእምሮ ጤና ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ትሠራለች።

"ሁልጊዜ ሌሎችን መርዳት እወዳለሁ። ከ14 ዓመቴ ጀምሮ በፕሮጀክቶች እና በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ተሳትፌያለሁ። ነገር ግን ከልጅነቴ ጀምሮ ሳላስበው ወደዚህ ሥራ እንደተሳብኩ ተገንዝቤያለሁ" ስትል ተናግራለች።

ቦሽ ፈረስ መጋለብ፣ ቴኒስ መጫወት፣ ሙዚቃ ማዳመጥ፣ ሥዕል መሳል እና ማንበብ እንደምትወድም ጠቅሳለች።

በእግዚአብሔር ላይ ጥልቅ እምነት እንዳላት ትናገራለች። በሜክሲኮ ያሉ አንዳንድ ሰዎች የውድድሩን ዘውድ ከጫነች በኋላ ጣቶቿን ወደሰማይ ቀስራ ያሳየችውን የደስታ ምልክት እንደ መንፈሳዊ ተግባር ተርጉመውታል።

የሚስወ ዩኒቨርስ የመጨረሻ አምስት ዕጩዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቁንጅና ውድድሮች የሚታወቀው ቤተሰብ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አዲሷ ሚስ ዩኒቨርስ ከሜክሲኮ ታዋቂ ቤተሰብ የተገኘች ሲሆን፣ ቤተሰቧ በቁንጅና ውድድሮችም ሆነ በፖለቲካ ረጅም ታሪክ አለው።

እንደ የአካባቢው ሚዲያዎች ገለጻ፣ የእናቷ የቫኔሳ ፈርናንዴዝ ቤተሰብ ገና በጅምሩ ከቁንጅና ውድድር ዓለም ጋር አስተዋውቋታል።

ሁለት የእናቷ እህቶች እሷ በ2018 ባሸነፈችው እና በሜክሲኮ በሚገኘው የፍሎር ደ ታባስኮ ውድድር ላይ ተወዳድረዋል።

ወጣቷ ሴት ስታድግ ቁንጅና ውድድሮች በቤተሰቧ እንደ ትልቅ ነገር ይታይ እንደነበር እና ቤተሰቧ በየዓመቱ የሚስ ዩኒቨርስ ውድድርን ለመመልከት የመሰብሰብ ባህል እንደነበረው ተናግራለች።

ይሁን እንጂ ቦሽ እያደገች ስትሄድ የቁንጅና ውድድሮችን በጥርጣሬ መመልከት እንደጀመረች አስተውላለች።

"ስለ ቁንጅና ውድድሮች ያን ያህልም አዎንታዊ አመለካከት አልነበረኝም። ነገር ግን ከሚስ ዩኒቨርስ ሜክሲኮ ዳይሬክተ የመነጋገር ዕድል ካገኘሁ በኋላ ወዲያውኑ በቀላሉ መግባባት ቻልን እና ትርክቱን እየቀየሩ ስለሆነ ታሪክ እየሠሩ እንደሆነ ተገነዘብኩ።"

"የሚናገሩት ነገር ያላቸው እውነተኛ ሴቶች ይፈልጋሉ። እናም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ነን። ያንን በጣም ወድጄዋለሁ።

"ይህ ድምፄን ለበጎ ነገር መጠቀም የምችልበት ቦታ መሆኑን ያየሁት ያኔ ነው። እዚህ መሆን አለብኝ፣ እርምጃ መውሰድ አለብኝ" ስትል ተናግራለች።

የእናቷ እህት አክስቷ ሞኒካ ፈርናንዴዝ በሜክሲኮ ፖለቲካ ውስጥ ታዋቂ ሰው ነች። የገዢው ሞሬና ፓርቲ የኮንግረስ አባል እና ሴናተር ነበረች እና የሴኔት ፕሬዝዳንት ሆና አገልግላለች።

ከ2024 ጀምሮ ባልቦአ የተዘረፈን ንብረት ወደ ሕዝብ እንዲመለስ የሚሠራን ኢንስቲትዩት መርታለች፣ ይህም ተቋም ከወንጀል ድርጊቶች የተወሰዱ ንብረቶችን ለጨረታ ለማቅረብ የተፈጠረ የሜክሲኮ የመንግሥት ኤጀንሲ ነው።

ከዚህም በላይ ቦሽ ከአባቷ ከበርናርዶ ቦሽ ሄርናንዴዝ ጋር በጣም ትቀራረባለች፣ ሐሙስ ምሽት በባንኮክ በተደረገው የመጨረሻ ውድድር ላይ አብሯት ነበር።

ፋጢማ ቦሽ ሚስ ዩኒቨርስን ዘውድ ስትጭን

የፎቶው ባለመብት, EPA / Shutterstock

የፋጢማ ቦሽ ድምጽ

ወጣቷ ሚስ ዩኒቨርስ ከአዘጋጆቹ አንዱ የሆነው ናዋት ኢሳራግራሲል ከውድድሩ ውጭ እንደሚያደርጋት ማስፈራራቱን ከተናገረች በኋላ የውድድሩ ያልተጠበቀች ኮከብ ሆነች።

የታይላንድ የሚዲያ ባለቤት እና የውድድሩ አዘጋጅ ቦሽን ከውድድሩ ጋር የተያያዙ የማስታወቂያ ይዘቶችን በማኅበራዊ ሚዲያ አልለጠፍሽም በሚል በደርዘን የሚቆጠሩ ተወዳዳሪዎች ፊት ገስጿታል።

እሷም "እኔ ድምጽ አለኝ። እንደ ሴቶችም ክብር ይገባናል። እዚህ ያለሁት አገሬን ወክዬ ነው፣ እና በድርጅቴ ላይ ችግር ስላጋጠመህ የእኔ ጥፋት አይደለም" ስትል በወቅቱ ናዋት የጥበቃ አባላትን እስኪጠራ ድረስ ተጋፍጣዋለች።

የአዘጋጁ ድርጊት በሌሎች ተወዳዳሪዎች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል፣ እነሱም ለሜክሲካዊቷ ፋጢማ ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት ክፍሉን ለቅቀው ወጥተዋል።

ከዚያ በኋላ የቦሽ ምሥል በዓለም ዙሪያ በመገኛኛ ብዙኃን በኩል ተሠራጭቷል።

በሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሼንባም በወቅቱ ቦሽ "ሴቶች ድምፃቸውን እንዴት ከፍ ማድረግ እንዳለባቸው የምታሳይ ምሳሌ" ሲሉ አወድሰዋታል።

ያሳየችው አቋም በሜክሲኳዊያን ዘንድም ተወድሷል።

ፋጢማ ቦሽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጥርጣሬዎች

የፋቲማ ቦሽ የአሸናፊነቱን ዘውድ መጫን ጥርጣሬዎችን አስነስቷል። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ፣ አንዳንድ አድናቂዎች ከመድረክ ጀርባ ያለው ድራማ ውድድሩን እንድታሸንፍ እንደረዳት ተናግረዋል።

ከስምንቱ ዳኞች አንዱ የሆነው የፈረንሳይ እና ሊባኖስ ዜግነት ያለው ሙዚቀኛ ኦማር ሃርፎች ውድድሩ የተጭበረበረ ነው በሚል ከኃላፊነቱ ከለቀቀ በኋላ ስለ አሸናፊዋ ምርጫ ጥርጣሬ ተነስቷል።

የሚስ ዩኒቨርስ ድርጅት ማክሰኞ ዕለት የኦማር ሃርፎችን ትችቶች ውድቅ ለማድረግ ባወጣው መግለጫ፤ "ተወካዮችን ለመገምገም ወይም የመጨረሻ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ ምንም ዓይነት የውጭ ቡድን አልተፈቀደለትም" ብሏል።

"ግልጽ የሆነው ነገር ሚስ ዩኒቨርስ 2025 በድርጅቱ ታሪክ ውስጥ እጅግ ትርምስ እና አወዛጋቢ ከሆኑ ውድድሮች አንዱ እንደሆነ ይታሰባል" ብለዋል የቢቢሲ ጋዜጠኛ ፓኒሳ አኤሞቻ።

"በሁሉም ደረጃዎች የሚነሱ አለመግባባቶች አሉ። በፕሬዝዳንቱ እና በብሔራዊ ዳይሬክተሩ መካከል፤ በብሔራዊ ዳይሬክተሮች እና በተወካዮች መካከል፤ በውድድሩ ዳኞች እና በድርጅቶች መካከል አለመግባባቶች ይኖራሉ፤ አሁን ደግሞ በንግሥቲቱ እና በሕዝቡ መካከል እየተነጋገርን ነው።"

በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹ ላይ፣ ሚስ ዩኒቨርስ ድርጅት ቦሽ "ጸጋዋ፣ ጥንካሬዋ እና ብሩህ መንፈሷ የዓለምን ልብ እሸንፏል" ሲል አውድሷታል።

ከውድድሩ በፊት ቦሽ "ያንን ዘውድ ጨለማ ወደ ነበረበት ቦታ ብርሃን ለማምጣት፣ ሴቶች በድምፃቸው ኃይል እንዲያምኑ ለማነሳሳት መጠቀም እወዳለሁ።

"ከሁሉም በላይ ግን የዛሬ ማንነታቸው በቂ መሆኑን እንዲያምኑ ማድረግ እፈልጋለሁ" ብላለች።