ሻምፑ የተጎዳ ፀጉርን ይጠግናል? የፀጉር እንክብካቤን የተመለከቱ አራት እውነታዎች

ፀጉሯ ፍሪዝ የሆነ የምትስቅ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሁላችንም ጤናማ የሆነ ፀጉር እንዲኖረን እንፈልጋለን - የሚያንፀባርቅ፣ ዞማ፣ ዛላው የሚያምር እና ለስላሳ።

ለዚህ ሌላ ማስረጃ ማቅረብ አያስፈልግም።ቲክቶክን ጨምሮ በየማኅበራዊ ሚዲያው የሚተዋወቁ የፀጉር ውበት እና ጤንነት መጠበቂያ ምርቶች መበራከትን ማንሳት በቂ ነው።

በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) 5.8 ቢሊዮን ፓውንድ ዋጋ ባለው ኢንደስትሪ ውስጥ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው የፀጉር መንከባከቢያ ምርቶች፣ ልምዶች እንዲሁም መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን እንድንዘነጋ የሚያደርጉ በቲክቶክ የሚዘዋወሩ መረጃዎች ይተዋወቃሉ።

እውነታው ግን ሌላ ነው።ጤናማ ፀጉር እንዲኖረን የሚያስፈልገው ለምርቶች ብዙ ገንዘብ ማውጣት ወይም ውስብስብ ልማዶችን መከተል ሳይሆን ቀላል ነገሮችን ብቻ ማስተካከል ነው።

በዩኬ የፀጉር እና የራስ ቅል ስፔሻሊስት የሆኑት ኢቫ ፕራውድማን እና የፀጉር እና የራስ ቅል ሕክምና አገልግሎት በሚሰጥ ክሊኒክ የሚሠሩት ትሬሲ ዎከር፣ ከፀጉር እንክብካቤ ጋር በተያያዘ ያሉ አራት እውነታዎችን ነቅሰው አውጥተዋል።

1. ቀዝቃዛ ውሃ ፀጉርን አንፀባራቂ እንዲሆን አያደርግም

ፀጉሯን የምትታጠብ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አንፀባራቂ ፀጉር እንዲኖርዎት እንደ በረዶ በሚቀዘቅዝ ውሃ ታጥባችሁ ታውቃላችሁ?

አሁን ግን ይህንን ማድረግ ማቆም እና በሚመቻችሁ ውሃ መታጠብ ትችላላችሁ።ፕራውድማን እንደሚሉት ቀዝቃዛ ውሃ ፀጉርን እንዲያንፀባርቅ አያደርግም።

"ምንም የሚጨምረው የተለየ ነገር ስለሌለ ፀጉርን በቀዝቃዛ ውሃ መታጠብ አያስፈልግም" ይላሉ።

በመሆኑም ለፀጉራችሁ ጤንነት ሊያሳስባችሁ የሚገባው ወሳኙ ጉዳይ ከኬሚካል፣ከሙቀት እና ምቹ ካልሆነ የአየር ሁኔታ እንዴት መጠበቅ እንዳለባችሁ ነው።

ነገር ግን በጣም በሞቀ ውሃ መታጠብም ፀጉራችን እንዲደርቅ እና የራስ ቅል ቆዳችን እንዲጎዳ ሊያደርግ ስለሚችል በጣም በሞቀ ውሃ መታጠብ እንደሌለብንም ፕራውድማን ይመክራሉ።

2. ምንም ዓይነት ምርት የተጎዳን ፀጉር አይጠግንም

ረዥም ፀጉር ያላት ሴት፣ የፀጉር መጠበቂያ ምርት ስትጠቀም የሚያሳይ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፀጉር ባለሙያ ጋር ሳትሄዱ የተሰነጣጠቀውን የፀጉራችሁን ጫፍ ለመጠበቅ የምትፈልጉ ከሆነ እና ብቸኛ መፍትሔው ፀጉርን መቁረጥ እንደሆነ ስታውቁ ቅር ልትሰኙ ትችላላችሁ።

ፕራውድማን የፀጉር ጫፍ መሰንጠቅ ከጠባብ ልብስ ጋር የሚመሳሰል ነው ይላሉ።በቀላሉ ለመጠገን የሚያስችል ምንም ዓይነት መንገድ የለም።

ዎከር በበኩላቸው ፀጉራችሁ እየተሰነጣጠቀ እንደሆነ ተሰምቷችሁ በአጉሊ መነጽር ብትመለከቱት ሁለት ወይም ሦስት መንታዎች (ቅርንጫፎች) ያሉት ነው የሚመስለው ይላሉ።

በርካታ ሰዎችም ይህንን ለማስተካከል ይረዳሉ ያሏቸውን ምርቶች ይጠቀማሉ።

"እንደ ሙጫ የማጣበቅ ባሕርይ ያላቸው በገበያ ላይ ያሉ የፀጉር ምርቶች ተሰነጣጥቆ የተበታተነውን ፀጉር አንድ ላይ በማድረግ ፀጉራችን ጥሩ ሆኖ እንዲታይ ያደርጋሉ" የሚሉት ዎከር፣ይህ ግን ጊዜያዊ ጥገና መሆኑን ይናገራሉ።

በመሆኑም ዘላቂ መፍትሔ በማይሰጡ ምርቶች ላይ ብዙ ገንዘብ በማውጣት መታለል እንደማይገባ ዎከር ያስጠነቅቃሉ።

ፀጉርን መቁረጥ በፍጥነት እንዲያድግ ያደርጋል የሚለው አመለካከትም ከእውነት የራቀ መሆኑንም ፕራውድማን ተናግረዋል።

"ፀጉራችንን በፍጥነት እንዲያድግ ማድረግ አይቻልም፤ በመሆኑም ይህንን አደርጋለሁ የሚሉ የምርቶች ማስታወቂያዎች ሐሰት ናቸው" ይላሉ።

3. ፀጉራችን እራሱን አያፀዳም

ፀጉሯን በሻምፑ የምትታጠብ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፀጉራቸው ራሱን እንዲያፀዳ ማለማመድ እንደቻሉ የሚናገሩ ሰዎች አጋጥመዋችሁ ሊሆን ይችላል። ይህም ፀጉራቸውን ቶሎ ቶሎ አሊያም ጭራሽኑ እንዳይታጠቡ እንዳስቻላቸው ይናገራሉ።

ሆኖም ይህንን ማድረግ ለፀጉር ጤንነት ጥሩ እንዳልሆነ ፕራውድማን ይናገራሉ።

"የራስ ቅል ቆዳ 180 ሺህ ቅባት የሚያመነጩ ዕጢዎች አሉት፤ በመሆኑም በየጊዜው ካልታጠበ ቆሻሻ ይሰበስባል" ይላሉ።

ዎከርም በፕራውድማን ሃሳብ ይስማማሉ።

ቅባትነት ያለውን ወይም ቆሻሻን ያለ ሳሙና በውሃ ብቻ በማጠብ ከልብስ ላይ ማስወገድ አይቻልም የሚሉት ዎከር፣ፀጉርን በየጊዜው አለመታጠብ መጥፎ ጠረን እና እንደ ፎረፎር ያሉ የራስ ቅል ቆዳ ችግሮችን እንደሚያባብስም አክለዋል።

ምክንያቱም ፀጉርን ቅባታማ ሆኖ እንዲቆይ ማድረግ ፈንገስ እና ባክቴሪያዎች እንዲያድጉ የሚያደርግ ሲሆን፣ ይህም ማሳከክ በመፍጠር የራስ ቅል ቆዳ እክልን ያባብሳል።

በመሆኑም ፀጉራችሁ ቅባታማ ከሆነ በየሁለት ቀኑ መታጠብ ወይም ብዙ የፀጉር ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች መጠቀም እንደሚገባ ፕራውድማን ይመክራሉ።

በሃደርስፊልስ ዩኒቨርሲቲ የመድኃኒት ምርምር ፕሮፌሰር የሆኑት ላውራ ዎተር እንደሚሉት በጣም ቅባታማ የሆነ ፀጉር ያላቸው ሰዎች የማጽዳት አቅማቸው ጠንካራ የሆኑ ምርቶችን በመገልገል አትራፊ ሊሆኑ ይችላሉ።

ደረቅ ፀጉር ያላቸው ሰዎች ደግሞ በአንጻሩ ��ዋጋ የተወደደ እና የፀጉር ወዝን የማያጠፋ ከሰልፌት ነጻ የሆነ ሻምፑ መጠቀም ይችላሉ ብለዋል።

4. ደረቅ ሻምፑ መጠቀም መታጠብን አይተካም

ፀጉሯ ላይ ደረቅ ሻምፑ የምታደርግ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሥራ፣ በስፖርት እና በማኅበራዊ ግንኙነት መካከል ፀጉርን በሙሉ ለመታጠብ፣ ለማድረቅ እና በቅጡ ለመንከባከብ ሁልጊዜ የሚቻል አይደለም።

በመሆኑም ብዙ ሰዎች የፀጉራቸውን ሥር ለማጽዳት እና ሳይታጠቡ ፀጉራቸውን ለማደስ ደረቅ ሻምፑን መጠቀም እንደ ፈጣን መፍትሔ ይወስዱታል።

በእርግጥ ደረቅ ሻምፑ መጠቀም ችግር የለውም ይላሉ ፕራውድማን። ነገር ግን መጠቀም ያለብን ፀጉራችንን በምንታጠብባቸው ጊዜያት መካከል አንድ ጊዜ ብቻ ነው።

ደረቅ ሻምፑን መጠቀም ችግር የሚሆነው ፀጉራችንን ሳንታጠብ ለብዙ ቀናት በተከታታይ ስንጠቀም ነው።

"የራስ ቅል ቆዳችን ተፈጥሯዊ ቅባት ሻምፑው ውስጥ በመግባትና ለፈንገሶች ምግብ በመሆን እንዲራቡ ያደርጋል" ይላሉ።

በመሆኑም ጥንቃቄ ካላደረግን የሚያሳክክ እና የተሰነጣጠቀ የራስ ቅል ቆዳ እንዲኖረን ያደርጋል።

ፕራውድማን ፊታችንን በምንከባከብበት መንገድ የራስ ቅላችንን መንከባከብ ላይ እንድናተኩርም ይመክራሉ።

"ከሥር ያለውን ቆሻሻ ሳናፀዳ እና ሳንታጠብ በቆዳችን ላይ የውበት መጠባቂያ ምርቶችን ( ሜካፕ) መደራረብ አይገባም" ብለዋል ፕራውድማን።