ሁለት የጀርመን ድምጽ ዘጋቢዎች 'ዘላቂ ዕገዳ' ሲጣልባቸው፣ የሰባቱ የሥራ ፈቃድ ተመለሰ

የጀርመን ድምጽ መሥሪያ ቤት

የፎቶው ባለመብት, dw

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ሁለት የጀርመን ድምጽ (ዶይቸቬለ) ዘጋቢዎች ላይ ዘላቂ ዕገዳ በመጣል በሌሎቹ የሬዲዮ ጣቢያ ዘጋቢዎች ላይ የጣላውን ዕገዳ ማንሳቱን ጣቢያው አስታወቀ።

ባለሥልጣኑ ጥቅምት 13/2018 ዓ.ም. ለዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ የተለያዩ ከፍሎች ውስጥ ወኪል ሆነው በሚሠሩ ዘጠኝ ዘጋቢዎች ላይ ዕገዳ መጣሉን በወቅቱ ዶይቸቬለ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ተቆጣጣሪዉ ባለሥልጣን ለዶይቸ ቬለ (ዲደብሊው) የአማርኛ ክፍል በጻፈው ደብዳቤ እንዳሳወቀው የመገናኛ ብዙኃኑ ዘጋቢዎችን የሥራ ፈቃድ "ለጊዜው" ማገዱን ካስታወቁ በኋላ ነበር መደበኛ ሥራቸውን ያቆሙት።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዕገዳውን ባሳወቀበት ደብዳቤ ላይ ጣቢያው የጥላቻ ንግግር እና የሐሰት መረጃ ሥርጭትን የሚያግደውን የመገናኛ ብዙኃን ደንቦችን እና አዋጆችን ጥሷል በማለት ቢከስም "ምንም ዓይነት ተጨባጭ ክስ" አላቀረበም ሲል ዲደብሊው በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቶ ነበር።

የመገናኛ ብዙኃኑ ዋና ዳይሬክተር ባርባራ ማሲንግ "ከኢትዮጵያ በሚሠራዉ ዘገባ ላይ የተጣለው እገዳ በጣም ያሳስበናል" ያሉ ሲሆን ተቋሙ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የገለጹትን የመገናኛ ብዙኃን አዋጆች ጥሰዋል ስለተባሉት ዘገባዎች ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጡ እና እገዳው በአስቸኳይ እንዲያነሱ ጠይቀዋል።

ዲደብሊው በጋዜጠኞቹ ላይ ከ40 ቀናት በላይ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ ጥያቄ ሲየቀርብ የቆየ ሲሆን፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣኑ ታኅሣሥ 01/2018 ዓ.ም. ከዘጠኙ ዘጋቢዎች መካከል የሰባቱን የሥራ ፈቃድ መመለሱን፣ ነገር ግን "ሁለቱ በዘለቂነት ከሥራ መታገዳቸውን" ጣቢያው አስታውቋል።

አክሎም ይህንን በሁለቱ ጋዜጠኞች ላይ የተጣለውን ዘላቂ ዕገዳ "አጥብቆ በማውገዝ" በተደጋጋሚ አቅርቦ ምላሽ አላገኘሁላቸውም ላላቸው እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ስህተት አለባቸው ያላቸው ዘገባዎች አለያም የኢትዮጵያ ሕግን ስለመጣሳቸው ማስረጃ እንዲያቀርብ በድጋሚ ጠይቋል።

ስለ ዕገዳው መነሳትም ሆነ በጀርመን ድምጽ የቀረቡለት ጥያቄዎች በተመለከተ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አስካሁን በይፋ የሰጠው መግለጫ የለም።

ከአንድ ወር በላይ በቆየው ዕገዳ የሬዲዮ ጣቢያው ኢትዮጵያ የሚመለከቱ ዘገባቸዎችን ዋና መቀመጫው ከሆነው ቦን በሚገኙ ጋዜጠኞቹ አማካኝነት በስልክ ከርቀት ሲዘግብ ቆይቷል።

እገዳው መጣሉን ተከትሎ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ የሆነው ኮሚቲ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ (ሲፒጄ) መግለጫ አውጥቶ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚሠሩት የዶይቸ ቬሌ ጋዜጠኞች ላይ የተጣለው ዕገዳ በአስቸኳይ እንዲነሳ እና ጋዜጠኞች በነጻነት ያለ ስጋት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርቦ ነበር።

ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በጋዜጠኞች አያያዝ በአሉታዊ ሁኔታ ስሟ በተደጋጋሚ ሲነሳ የቆየ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በፕሬስ ነጻነት ይዞታዋ በ2025 በዓለም የፕሬስ ነጻነት መመዘኛ ደረጃ ከ180 አገራት 145ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል።