'ባሕል እና ሥነ ምግባር' ጥሰዋል የተባሉት ቲክቶከሮች ምን ዓይነት ክስ እና ቅጣት ሊገጥማቸው ይችላል?

አዶናይ ብርሃነ ኃ/ሚካኤል የቲክቶክ አዋርድ ካሸነፈ በኋላ ደስታውን ሲገልጽ

የፎቶው ባለመብት, Kirnfud Digitals

የምስሉ መግለጫ, አዶናይ ብርሃነ ኃ/ሚካኤል ለሦስተኛ ጊዜ የተዘጋጀውን የቲክቶክ አዋርድ ካሸነፈ በኋላ ደስታውን ሲገልጽ

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አዶናይ ብርሃነ ኃ/ሚካኤል የተባለ ተጠርጣሪ ቲክቶከርን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ገልጿል።

ሐሙስ ኅዳር 1/2018 ዓ.ም. አዶናይ በቁጥጥር ስር ከመዋሉ አስቀድሞ ማክሰኞ ኅዳር 30/2018 ዓ.ም. የፌደራል ፖሊስ በቲክቶክ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ "ከኢትዮጵያ ሕዝብ ባህልና ሥነ-ምግባር ያፈነገጠ" ሰውነትን የሚያጋልጥ ልብስ በአደባባይ ለብሰው የታያዩ ያላቸውን "ተጠርጣሪዎችን እና ግብረ-አበሮቻቸውን" ማሰሩን አስታውቆ ነበር።

አዶናይ ብርሃነ ረቡዕ ዕለት የታሰረው ‎ማክሰኞ በቁጥጥር ስር ከዋሉ አምስት ተጠርጣሪዎች የወንጀል ጉዳይ ጋር በተያያዘ መሆኑንም ፌደራል ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።

ከፍተኛ ተከታይ ያላቸው እና ታዋቂ የሆኑ ቲክቶከሮች መያዛቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል።

አዶናይ በቲክቶክ ላይ 3.9 ሚሊዮን ተከታዮች ያሉት ሲሆን፣ ማክሰኞ ዕለት በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል ወንጌል በቲክቶክ ስሟ ኢቫን 700 ሺህ ገደማ እንዲሁም ዮሐንስ ወይንም በቲክቶክ ስሙ ጃኒ 434 ሺህ ገደማ ተከታዮች አሏቸው።

ፖሊስ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ባህል እና መልካም ሥነ-ምግባር በተቃራኒ የሆነ አለባበስ ለብሰው ታይተዋል ያላቸው ወንጌላዊት ገብረ እንድርያስ፣ ዮሐንስ መኮንን እና ግብረ አበሮቻቸው ናቸው የተባሉት በረከት ፀጋዬ፣ መቅድም ደረጄ፣ ግሩም ገዛኽኝ በቁጥጥር ስር መዋላቸው የተገለጸው ማክሰኞ ዕለት ነው።

እነዚህ የማኅበራዊ ሚደያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት ስለመቅረባቸው የተባለ ነገር የለም።

ፖሊስ ረቡዕ ዕለት የአዶናይን በቁጥጥር ስር መዋል በገለጸበት የፌስቡክ ልጥፉ ላይ "እውቅና እና ገንዘብ ለማግኘት ብቻ በማሰብ" ሚዲያዎችን ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የሚጠቀሙ ያላቸው ወጣቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።

በተለይ ወጣቱ ትውልድ በመልካም ሥነ ምግባር ተቀርጾ አገርን የሚጠቅሙ ተግባራትን እንዳያከናውንና በተቃራኒው በትውልዱ ላይ ርካሽ ባህልን ለመጫን የሚደረገውን ተግባር ለመከላከል ፖሊስ ሥራውን እንደሚቀጥል ገልጿል።

አዶናይ በቅርቡ ከሚኖርበት ካናዳ ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ሲሆን "ሰግጥ ፈምስ" በሚለው ንግግሩ በበርካቶች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

አዶናይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን ተከትሎ እናቱ ለቢቢሲ ትግርኛ "ልጄ ያጠፋው ነገር የለም። ያሰረው መንግሥት ሁኔታውን አጣርቶ እንደሚለቅቀው አምናለሁ" ብለዋል።

"የራሱን ምቹ ሕይወት ትቶ መጥቶ ሰዎችን የሚያግዝ እኔንም የሚያበረታን ልጄ ነው።"

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባልደረቦች በተገኙበት ንግግር ማድረጉ ለሌላ ተጨማሪ ውዝግብ መነሻ ሆኖ ነበር።

ቲክቶክ ክሬቲቭ አዋርድ 2025 ኅዳር 21/2018 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ የተካሄደ ሲሆን ዝግጅቱም በቀጥታ በአርትስ ቲቪ ላይ ተላልፏል።

ረቡዕ ዕለት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለው አዶናይ በዚህ "የቲክቶክ ክሬቲቭ አዋርድ" ላይ አሸናፊ በመሆን መኪናን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ሽልማቶችን አግኝቷል።

ቲክቶክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቲክቶከሮቹ እስር ምን ያመለክታል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጉዳዩን በሚመለከት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሃሳቦቹን ያጋራው በፍቃዱ ኃይሉ ቲክቶከሮቹ ከመታሰራቸው አስቀድሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ተከፍቶባቸው አንደነበር ያስታውሳል።

የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻን ተከትሎ መንግሥት ምላሽ የሚሰጥበት አጋጣሚ እየተፈጠረ ነው የሚለው በፍቃዱ፣ ይህ ግን "ሕጋዊ መሠረት ያለው አይመስለኝም" ብሏል።

የሽልማት ሥነ ሥርዓቶች ላይ ሰዎች በዲዛይነር አሠርተው በተለያየ ዓይነት አለባበስ መገኘታቸው የተለመደ ነው የሚለው በፍቃዱ በዚህም "ራሳቸውን ይገልጻሉ ወይንም መልዕክት ያስተላልፋሉ" ሲል ያስረዳል።

በፍቃዱ ፖሊስ ማክሰኞ ዕለት ተጠርጥረዋል ብሎ ስማቸውን ከዘረዘራቸው ቲክቶከሮች መካከል አንዱን በመጥቀስ "እናቴ ብቻዋን ነው ያሳደገችኝ" በማለት "የሴቶችን ተፈጥሯዊ ፈተና እና ጥንካሬ ማስታወስ እፈልጋለሁ" በሚል ቀይ ልብስ ለብሶ መገኘቱን ጠቅሷል።

ይኽው ወጣት ሴቶች በየወሩ "በወር አበባ የሚሰቃዩትን ለማስታወስ" በሚል ልብሶን አሰፍቶ መልበሱን መግለጹን ያስታውሳል።

በዚህ ልጅ እንዲሁም የእጁ ቦርሳ የያዘው ቲክቶከር ልጅ ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ "ከተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ጋር ተያይዞ" ዘመቻ ተከፍቶባቸው እንደነበር በፍቃዱ ይናገራል።

ይህ የማኅበራዊ ሚዲያ ውንጀላ ሀቅ ላይ የተመሠረተ አይደለም የሚለው በፍቃዱ "ስሜታዊነት እና ግምት ላይ የተመሠረተ ፍርሃት" ነው ሲል ያጣጥላል።

በፍቃዱ በእኔ እምነት የፀጥታ ኃይሎች ምላሽ የሰጡት ለዚህ ዘመቻ ነው ሲል ተናግሯል።

ዐቃቤ ሕግ የትኛውን የሕግ አንቀጽ እንደሚጠቅስ ገና አልታወቀም የሚለው በፍቃዱ "አስረን እየመረመርን ነው" ማለቱን በማስታወስ "የለበሱት በአደባባይ የሚታይ ነገር በመሆኑ አስረው ምን አንደሚመረምሯቸው ራሱ አላውቅም" ብሏል።

ቲክቶከሮቹ የተላለፉት የሕግ አንቀጽ ካለ በቀጥታ ክስ ቢመሰርትባቸው የተሻለ እንደነበርም ጨምሮ ገልጿል።

ምን ዓይነት ክስ እና ቅጣት ሊገጥማቸው ይችላል?

ቢቢሲ በቲክቶከሮቹ በየትኛው የወንጀል ሕግ ሊጠየቁ አንደሚችሉ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች የተመሠረተባቸው ክስ እስካልታወቀ ድረስ መናገር አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል።

ነገር ግን ፖሊስ ከሰጠው መግለጫ በመነሳት በ1996 የወጣው የወንጀል ሕግ አንቀፍ 639 አንቀፍ 1 መሠረት ሊከሰሱ ይችላሉ ብሎ መገመት አንደሚቻል ተናግረዋል።

ይህ አንቀጽ "ማንም ሰው አስቦ ሕዝብ በሚበዛበት ቦታ ወይም በሕዝብ ፊት የግብረ ሥጋ ድርጊትን ወይም ለመልካም ጠባይ ወይም ለመልካም ሥነ ምግባር በብርቱ ተቃራኒ የሆነውን ማናቸውንም ሌላ ፀያፍ ድርጊት የፈጸመ ወይም በአኳኋን ያሳየ አንደሆነ ከሦስት ወር እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከአንድ ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል" ይላል።

ረቡዕ ዕለት የአዶናይ መታሰርን አስመልክቶ ፖሊስ የሰጠው መግለጫ ላይ ቀደም ብለው ከታሰሩት ተጠርጣሪዎች ወንጀል ጋር በተያያዘ መታሰሩን መናገሩን በማስታወስ የማኅበራዊ ወጀብን ተከትሎ በቲክቶክ ላይ የወጣቶች ድምጽ ከፍ እያለ ስለሆነ "ያንን ለማፈን እና ለማስደንገጥ የፈለገ ነው የሚመስለው" ብሏል።

ቲክቶክ ክሬኤቲቭ የውድድርና የሽልማት ሥነ ሥርዓት የወጣቶችን የፈጠራ ችሎታ ከማበረታታት ባለፈ የአገርን ገፅታ በመገንባት ረገድ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አዘጋጆቹ በወቅቱ ተናግረው ነበር።

የውድድሩ አዘጋጆች የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ የወጣቶችን የፈጠራ ችሎታ ከማበረታታት ባለፈ የአገርን ገፅታ መገንባት ረገድ አስተዋጽኦ እንዳለው አዘጋጆቹ ይናገራሉ።

በችሎታቸው አገርን በጥሩ ስም ማስጠራት የሚችሉ እንዲሁም ሰላምን በዲጂታል መረብ የሚያስተዋውቁ ወጣቶችን ለማበረታታት ያለመ ነው በተባለው በዚህ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ለሽልማት መዋሉ ተገልጿል።

መድረኩ አርቲስቶች፣ ኮሚዲያኖች፣ ዳንሰኞች እና ሌሎች ተሰጥኦዋቸውን እንዲያሳዩበት 26 የመወዳደሪያ ዘርፍ የተዘጋጀ ነበር።

የፀጥታ አካላት የወሰዱት እርምጃ ቲክቶክ ላይ እየጎለበቱ የመጡ ድምጾችን ለማፈን ይመስላል የሚለው በፍቃዱ "እነዚህ ድምጾች ፖለቲካም አይደሉም።ባህልንም ከመጠበቅ የሚመጣ ይመስላል። ወግ ጠባቂነትንም ደግፎ ከሆነ ሊብራልነት ወንጀል አይደለም" ሲል ይሞግታል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ወጣት ቲክቶከሮች ተጽዕኖ የመፍጠር አቅማቸው ከፍተኛ እየሆነ እና እያደገ በመጣ ቁጥር መንግሥት ስጋት ሊገባው እንደሚችል ያለውን ግምት ይናገራል።

እነዚህ አሁን በቁጥጥር ስር የዋሉ ቲክቶከሮች እንኳን ባይሆኑ እነርሱን የሚመለከቱ እና ያላቸውን ተፅዕኖ የሚረዱ ሌሎች ለዚህ ተግባር ሊያውሉት ይችላሉ የሚል ስጋት መንግሥት ሊያድረበት እንደሚችል ያለውን ግምት ያስቀምጣል።

መንግሥት ቲክቶክ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣ "እኔን ያየህ ተቀጣ" ለማለት እነዚህን በማሰር ሌሎቹን የሚያስፈራራበት ዕድል ይኖራል ሲልም ያብራራል።