ሕፃናትን ከማኅበራዊ ሚዲያ ማገድ እንችላለን? ከጉዳትስ የሚጠብቃቸው እንዴት ነው?

የፎቶው ባለመብት, BBC/Jessica Hromas
ለ13 ዓመቷ ኢሶቤል በዓለም የመጀመሪያ የሆነውን እና አውስትራሊያ በሕፃናት ላይ የጣለችውን እገዳ ጥሳ ለመሄድ የወሰደባት ከአምስት ደቂቃ በታች ነው።
በእገዳው ከተካተቱ 10 ማኅበራዊ ሚዲያዎች መካከል አንዱ ሆነው ስናፕቻት በዚህ ሳምንት ሕጉ ተግባራዊ ሲሆን ከ16 ዓመት በላይ መሆኗን ማረጋገጥ ካልቻለች አገልግሎቱን እንደማታገኝ የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ወደ ስልኳ ልኮ ነበር።
ከዚያም "የእናቴን ፎቶ አገኘሁ እና በካሜራው ፊት ለፊት አደረኩት። እንድገባ ፈቀደልኝ. . . " የምትለው ኢሶቤል፣ 'እድሜሽን ስላረጋገጥሽልን እናመሰግናለን' የሚል ምላሽ ከማኅበራዊ ሚዲያው እንዳገኘች ትገልጻለች።
ወደ ማኅበራዊ ሚዲያው ለመግባት "የቢዮንሴን ፊት የተጠቀመ እንዳለም ሰምቻለሁ" ብላለች ኢሶቤል።
ከዛሬ ጀምሮ በአውስትራሊያ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲጠቀሙ አይፈቀድላቸውም።
የአገሪቷ መንግሥት በዓለም የመጀመሪያ የሆነው ፖሊሲው ታዳጊዎቹን ከጎጂ ይዘቶች እና በሳይበር ከሚፈፀሙ ዘለፋዎች እና ጥቃት ለመጠበቅ ያለመ እንደሆነ ገልጿል።
ከዚህም ባሻገር ሕፃናቱ ጥሩ እንቅልፍ እንዲያገኙ፣ አካላዊ እና የአዕምሮ ጤናቸውን ለማሻሻል ያስችላል ብሏል።
የኢሶቤል እናት ሜል ልጇ ቲክቶክ እና ስናፕቻትን እንድትጠቀም ትፈቅድላት የነበረው ጥብቅ ክትትል በማድረግ የነበረ ቢሆንም እገዳው እንደ እርሷ ያሉ ወላጆች መስመራቸውን እንደገና እንዲያሰምሩ ይረዳል ብላ ተስፋ ስታደርግ ቆይታለች።
አሁን ላይ ግን ይህ ተስፋ ተመናምኗል። በርካታ ባለሙያዎች እና ሕፃናቱ ዓለም በቅርበት እየተመለከተው ያለውን እና የተወሰኑ ተፅዕኖ ፈጣሪ ኩባንያዎችም በስጋት እየተከታተሉት ያለው ፖሊሲ ተጨባጭነት እና ደኅንነት ላይ ጥያቄ እያነሱ ነው።
ፖሊሲው እንዴት ተግባራዊ ሊሆን ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, BBC/Jessica Hromas
ኅዳር ወር ላይ በቀረበው እና ከታኅሣሥ 1 ጀምሮ ተግባራዊ በሚሆነው ፖሊሲ መሠረት ወላጆች እና ሕፃናት ማኅበራዊ ሚዲያ በመጠቀማቸው የሚጣልባቸው ቅጣት የለም።
በምትኩ እገዳ የተጣለባቸው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች አካውንት ያላቸው ተጠቃሚዎች ቢያንስ 16 ዓመት መሆናቸውን ለማረጋገጥ "ምክንያታዊ እርምጃዎችን" መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።
ይህን ሳያደርጉ የከፋ ጥሰት ከተፈፀመም የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹ 33 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ይገጥማቸዋል።
በመንግሥት የሚደገፈው ኢንደስትሪ ሙከራ እያካሄደ ሲሆን፣ ዋነኛ የዕድሜ ማረጋገጫ መንገዶችን ተመልክቷል። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ቴክኒካዊ በሆነ መንገድ ይህንን ማድረግ እንደሚቻል ተገልጾ ነበር። ሆኖም ሁሉም ዘዴዎች አስተማማኝ እና ከአደጋ የፀዱ አይደሉም።
መታወቂያ ካርድን በመጠቀም ዕድሜን ማረጋገጥ በጣም ትክክለኛው መንገድ ቢሆንም ተጠቃሚዎች ጥንቃቄ የሚያሻቸውን እና ወሳኝ የሆኑ ግላዊ ሰነዶችን መስጠት ይጠበቅባቸዋል።
በተጠቃሚዎች የኦንላይን እንቅስቃሴ መሠረት ድምዳሜ ላይ የሚደርሰው በዕድሜ ደረጃ እና በቴክኖሎጂ የሚደረግ የፊት ገጽ ግምገማም ታዳጊዎቹ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ትክክለኝነት ይጎድላቸዋል።
ሆኖም የዕድሜ ማረጋገጫ ቴክኖሎጂዎች "ግላዊነታቸው የተጠበቀ፣ ጤናማ እና ውጤታማ" እንደሚሆን ሪፖርቱ አሳይቷል።
በዩናይትድ ኪንግደም ተቀማጭነቱን ያደረገው የዕድሜ ማረጋገጫ ፕሮግራም መሪ እና ይህንን ሙከራ የመሩት ቶኒ አለን ስለ ዘዴዎቹ ሲያብራሩ፣ ለታዳጊዎች የአልኮል ሽያጭን ከሚከለክለው አሠራር ጋር አመሳስለውታል።
"ልክ ወደ መጠጥ መሸጫ ሱቆች ስትሄዱ ከላይ እስከ ታች ተመልክተዋችሁ 'ሂዱ' ሊሏችሁ ይችላሉ፤ እርግጠኛ ካልሆኑ ድገሞ መታወቂያ ካርድ ይጠይቋችኋል። ይህም ተመሳሳይ መርኅ ነው" ብለዋል።
ግኝቱ ግን አሁንም ከአወዛጋቢነት የፀዳ አልነበረም።
ሁለት የቀድሞ አማካሪ የቦርድ አባላት ዘዴውን አግላይ እና ግላዊነትን የሚያሳጣ ነው ሲሉ ከሰውታል። ምንም እንኳን ሙከራው ታዳጊዎች ክልከላዎችን ጥሰው ሊያልፉ የሚችሉባቸውን መንገዶች ከግምት ቢያስገባም፣ የማረጋገጥ ኃላፊነት የለውም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እገዳውን እንዴት መጣስ እንደሚቻል የሚያሳዩ መንገዶችም ማኅበራዊ ሚዲያዎችን አጥለቅልቀዋል።
የዕድሜ ማረጋገጫውን የሚደግፉ እገዳውን ጥሰው እንዳያልፉ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች አሉ ይላሉ። ኢሶቤልም ተጠቀምኩት ያለችው ፎቶም እነዚህን ማረጋገጫዎች መሸወድ አይችልም።
ቢቢሲ በዚህ ላይ ስናፕቻትን የጠየቀ ሲሆን ቃል አቀባዩ ድርጅቱ እገዳውን ተግባራዊ ለማድረግ ሊገጥሙት የሚችሉ ቴክኒካዊ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ያለውን ስጋት በተደጋጋሚ ገልጿል ብለዋል።
በስናፕቻት በኩል የዕድሜ ግምገማ የሚያካሂደው የኬ አይዲ ኃላፊ ሉክ ዲላኒይ "ዕድሜን የሚያረጋገጡ ቴክኖሎጂዎች እንዳይጣሱ በየጊዜው መከላከያዎች እየተሻሻሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ፈታኝ ነው" ሲሉ አስረድተዋል።
ኢሶቤል ግን በእርሷ ልምድ እገዳው እንደማይሠራ በጣም እርግጠኛ ናት።
"ክልከላውን ማለፍ ካልቻልኩ ሌላ መተግበሪያ እፈልጋለሁ" ብላለች።
ይህ ለውይይት ክፍት መሆኑን የምትገልጸው እናቷ ሜልም የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹ እና ተቆጣጣሪዎቹ ታዳጊዎቹ ሌሎች መድረኮችን እንዳይጠቀሙ ያሉ ቀዳዳዎችን ሁሉ እንዳይደፍኑ ስጋት አላቸው።
ከአውሮፓውያኑ 2013 እስከ 2017 ድረስ በአውስትራሊያ እና ኒው ዚላንድ ፌስቡክን የመሩት ስቴፈን ስችለር፣ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹ ምንም እንኳን የሚጣልባቸው ቅጣት ፖሊሲውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ በመጠኑም ቢሆን ቢያስገድዳቸው እገዳውን አሳንሰው ሊመለከቱት ይችላሉ ከሚሉት ወገኖች ይገኙበታል።
ለምሳሌ ፌስቡክ የሚጣልበትን ያህል ቅጣት ገንዘብ የሚያገኘው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሁለት ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው።
"ያልተገባ ቦታ ተሽከርካሪ በማቆም የሚጣል የፓርኪንግ ቅጣት እንደማለት ነው" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሌላኛው ደግሞ ሕጋዊ ተግዳሮት ነው። እገዳው ኢ- ሕገ መንግሥታዊ እና ጨቋኝ ነው በማለት ሁለት ታዳጊዎች በአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መሥርተዋል።
የዩቲዩብ እና ጉግል ባለቤት የሆነው አልፋቤት የገጠመውን ተግዳሮት እያጤነ ነው። የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድኖች እና የሕግ ባለሙያዎችም ያላቸውን ቅሬታ አሰምተዋል።
አንዳንድ ስጋት የገባቸው ወላጆችም እገዳው ሕገ ወጥ እንደሆነ ይገልጻሉ። ልጆቻቸው ማኅበራዊ ሚዲያን ለመጠቀም በልዩ ሁኔታ እንዲታዩ አሊያም ጫና እንዲደረግባቸው አይፈልጉም።
አለን "ውጤታማ ፖሊሲ እንዲሆን መቶ በመቶ ሕፃናት ማኅበራዊ ሚዲያን እንዳይጠቀሙ ማድረግ አይገባም። 80 በመቶዎቸ ላይ እንዲሆን ማደረግ አለበት ከዚያ ሌሎቹ ይከተላሉ" ብለዋል።
ጉዳትን ይቀንሳል?
እንዴት ተግባራዊ ሊሆን ይችላል የሚለውን ጥያቄ ወደ ጎን አስቀምጠው ጉዳትን ሊቀንስ ይችላል ወይ? ሲሉ በርካቶች ይጠይቃሉ።
መጀመሪያ ፖሊሲው ሕፃናቱን ለባሰ ጉዳት ወደሚዳርጋቸው ድረ ገጾች ሊገፋቸው ይችላል የሚሉ ስጋቶች አሉ። እነዚህ ገጾች ደግሞ በእገዳው ውስጥ አልተካተቱም።
ሕፃናት አሁንም አካውንት መክፈት ሳይጠበቅባቸው እንደ ቲክቶክ እና ዩቲዩብ ያሉ በርካታ መተግበሪያዎችን መጠቀም ይችላሉ። ይህም ላልተጣሩ ይዘቶች እና ማስታወቂያዎች የመጋለጥ ዕድላቸውን ይጨምረዋል።
ብዙ የማኅበራዊ መድረኮች ግን በልጆች አካውንቶች ላይ እነዚህን ይዘቶች ይገድባሉ።
በእርግጥ እንዲህ ያሉ ይዘቶችን በመቆጣጠር ረገድ ትላልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጭምር ትችት ይቀርብባቸዋል፤ ነገር ግን እነዚህ ትላልቅ መድረኮች ከአነስተኞቹ ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ጥንቃቄ ያደርጋሉ።
ለምሳሌ ፌስቡክ አዋቂ የሆነ ሰው ወደ አንድ ታዳጊ ተደጋጋሚ መልዕክት ሲልክ የሚያስጠነቅቅበት ሥርዓት አለው።
ከማኅበራዊ ሚዲያ እና ከጤና ጋር የተያያዙ ሳይንሶች ውስብስብ እና እየተሻሻሉ የሚመጡ ናቸው።
ማኅበራዊ ሚዲያ የሚያስገኘው ውጤት ደካማ ነው የሚሉ ጥናቶች ቢኖሩም፣ በተለይ ከተመሳሳይ ፆታ ቤተሰቦች የተገኙ፣ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ካለባቸው ወይም ገጠር ማኅበረሰብ ውስጥ ላሉ የተወሰኑ ሕፃናት የሚረዳ ሊሆን ይችላል።
በመሆኑም ትኩረት መደረግ ያለበት ማኅበራዊ ሚዲያዎች ጎጂ ይዘቶችን እንዲከላከሉ እና የአልጎሪዝሙን አቅም ውስን እንዲያደርጉ ማስገደዱ የተሻለ እንደሆነ በርካቶች ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ልጆችን ለድረ ገጽ እውነተኛ ሕይወት ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አክለዋል።
የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር የሆኑት አኒካ ዌልስም መንግሥታቸው እነዚህ ነገሮች ማድረግ እንደሚፈልግ ለቢቢሲ ተናግረዋል። እገዳው ፍፁም ባይሆንም ���ቃሚ እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል።
"ይህ መዳኛ አይደለም። ሕክምና ነው፤ የሕክምና ዕቅዱ ደግሞ ሁልጊዜም እየተሻሻለ፤ እያደገ ይመጣል" ብለዋል።















