ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መጠቀም የሌሉብን ቃላት እና ብዙ ሰዎች ጋር እንዳይደርሱ የሚደረጉ ይዘቶች አሉ?

የፎቶው ባለመብት, Serenity Strull/ Getty Images
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መጠቀም የማይችሏቸው ዝርዝር ቃላት አሉ። በእርግጥ አንዳንዶች የተወሰኑ ምሥጢራዊ ቃላት ዝርዝሮች መኖራቸውን ማሰብ ይልጋሉ።
ቢያንስ ግን አዘውትረው ማኅበራዊ ሚዲያን የሚጠቀሙ ሰዎች የተወሰኑ ቃላትን ላለማለት ሲጠነቀቁ አስተውለው ይሆናል።
ፈረንጆቹ ተገደለ ከማለት ይልቅ ሕይወቱን አጣ ማለት ይመርጣሉ።
በእንግሊዘኛው "killed" ለሚለው "unalived" ማለት መምረጥን ማለት ነው።
በወንጀል ታሪኮች ውስጥ ጠመንጃ፣ ሽጉጥ ከማለት ደግሞ ፒው ፒውስ (pew pews) የሚለውን ይጠቀማሉ።
የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መጀመሪያ ላይ እንዲህ ዓይነት የቃላት አጠቃቀሞች ረብ የለሽ እንደሆኑ ይሰማቸው ነበር። ነገር ግን አማራጭ የላቸውም።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተወሰኑ የፖለቲካ አጀንዳዎችን ለማሠራጨት ወይም የማስታወቂያ ኩባንያዎች የሚያሻሽጡትን እቃ የበለጠ ስሜት ቀስቃሽ እንዳያደርጉት በሚል መጠቀም የማይቻሉ ቃላትን ወይንም ሐረጋትን እንዲለይ ተደርጎ የተደራጀው አልጎሪዝም 'አልጎስፒክ' ይባላል።
የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪው ይህንን ሃሳብ ያጣጥላል።
የዩቲዩብ ቃል አቀባይ ቡት ቡልዊንክል "ዩቲዩብ የሚከለክላቸው ወይንም ያገዳቸው ቃላት የሉትም" በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
አክለውም "የእኛ ፖሊሲዎች አውዳዊ ጉዳዮች እና ቃላት የተለያየ ትርጉም እና ዓላማ ሊኖራቸው እንደሚችል መረዳታችንን ያንፀባርቃሉ። የዚህ የተዛነቀ አካሄድ ውጤታማነት በዩቲዩብ ላይ በሚለጠፉ ርዕሶች፣ ድምጾች እና አመለካከቶች ልዩነት የሚታይ ነው።"
ሜታ እና ቲክቶክ ተመሳሳይ ምላሽ በመስጠት ይህን በፍፁም አናደርግም፣ ተራ አሉባልታ ነው ብለዋል።
እውነታው ግን የበለጠ ወሰብሰብ ያለ ነው።
የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች በዝምታ ይዘቶች እንዲታዩ እና እንዳይታዩ ሲያደርጉ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል።
አንዳንዴ ገለልተኛ፣ ግልጽ ነን ቢሉም ከዚያ ተቃራኒውን ሲያደርጉ ተስተውለዋል።
ግለሰቦች ራሳቸውን ሳንሱር በማድረግ የሚጠቀሟቸውን ቃላት ከመጠንቀቅ ጀምሮ፣ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጣልቃ ገብተው በለሆሳስ የተወሰኑ ይዘቶች ወደ ሰዎች እንዳይደርሱ ሲያደርጉ እንደነበር ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ችግሩ የተለጠፉት ይዘቶች ለምን ለበርካታ ሰው እንዳልደረሱ አለማወቃችን ነው።
መጥፎ ቪዲዮ ስለሠሩ ነው ወይስ አልጎሪዝሙን ስላበሳጩት? በዚህ መካከል ያለው ግራ መጋባት ይዘት ፈጣሪዎች ራሳቸውን እንዲያርሙ ያደርጋቸዋል።
በአንድ ጽንፍ ሰዎች የሚፈልጉትን እየተጠቀሙ ያሻቸውን ያወራሉ፤ በሌላ ወገን ደግሞ የተወሰኑ ርዕሰ ጉዳዮችን በመተው በርካታ ተመልካች ለማግኘት ይጣጣራሉ።
ማኅበራዊ ሚዲያ ዋነኛ የዜና እና የመረጃ ምንጭ በሆነበት ዓለም የተወሰኑ ሃሳቦችን ፈጽሞ ሰዎች እንዳይሰሟቸው ይደረጋል የሚለው በርካቶች የሚጋሩት ሃሳብ ነው።
አሌክስ ፐርልማን በቲክቶክ፣ በኢንስታግራም እና በዩቲዩብ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሉት ይዘት ፈጣሪ ነው።
ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በሳቅ አዋዝቶ ሸንቆጥ እያደረገ በማቅረቡ ብዙዎች ይከተሉታል።
ፐርልማን የአልጎሪዝም ሳንሱር በሥራዎቹ ላይ በተደጋጋሚ የሚያጋጥመው ነገር አንደሆነ ይናገራል።
"ለመጀመር ያህል ቲክቶክን ብቻ እንመልከት፤ በጣም አልፎ አልፎ ነው 'ዩቲዩብ' የሚለውን የምጠራው። የእኔን አጋጣሚ ብንመለከት እና አናሊቲክሶቼን ብናይ 'ወደ ዩቲዩብ ቻናሌ ሂዱ' ካልኩ ቪዲዮው ተመልካች አያገኝም" ይላል።
ፐርልማን እና ሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጣሪዎች ቲክቶክ ተመልካቾቹ ወደ ተቀናቃኝ ቻናሎች እንዲሄዱ አይፈልግም እንዲሉ አድርጓቸዋል። ስለዚህ ተቀናቃኝ መተግበሪያዎች የሚጠሩበት ቪዲዮ እንዳይታይ ባለመድረግ ይቀጣቸዋል።
ቲክቶክ ግን ይህንን ፈጽሞ አላደርግም ሲል ያስተባብላል።
ፐርልማን በርካታ ቪዲዮዎች በወሲብ ንግድ ወንጀል የተፈረደበት ጄፍሪ ኤፕስቲን ዙሪያ ቢሠራም፣ ግለሰቡ በጣም አከራካሪ ቢሆንም "የሌሎች ቪዲዮ በደንብ ሲታይ የእኔ ግን ከቲክቶክ ላይ እንዲጠፋ ተደርጓል" ይላል።
እነዚያ ተመሳሳይ ቪዲዮዎች ግን በዩቲዩብ እና ኢንስታግራም ገፁ ላይ ያሉ ሲሆን፣ የትኛውን የቲክቶክ መመሪያ እንደጣሰ መረዳት አልቻለም።
የቲክቶክ ቃል አቀባይ በፐርልማን ቪዲዮዎች ላይ አስተያየት መስጠት ባይፈልጉም መተግበሪያው ከሚሠራበት በተቃራኒው የቆመ የተሳሳተ አረዳድ መኖሩን ገልፀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Serenity Strull/ Getty Images
ቲክ ቶክ፣ ሜታ እና ዩቲዩብ ሁሉም ለተጠቃሚዎች የሚደርሱ ቪዲዮዎችን የሚቆጣጠሩባቸው ቀመሮች ውስብስብ መሆናቸውን ይናገራሉ።
እነዚህ አስፈላጊ እና አስደሳች የሆኑ ይዘቶችን እንዲመለከቱ የሚያደርጉት ሥርዓቶች እርስ በርሳቸው የተሳሰሩ ሲሆኑ፣ ቢሊዮኖች ዳታዎችንም ይጠቀማሉ።
ሦስቱም ኩባንያዎች ይህ ሥርዓት እንዴት አንደሚሠራ የሚገልጽ መረጃ በይፋ አስቀምጠዋል።
ቲክቶክ ለምሳሌ እያንዳንዱ ተጠቃሚ ቪዲዮውን ምን ያህል ወዶታል የሚለውን በመውሰድ ለሌሎች እንዲደርስ ያደርጋል።
ኩባንያዎቹ ይዘቶችን የሚያወርዱት ወይም ለሰፊው ተጠቃሚ እንዳይደርስ የሚገድቡት መመሪያዎቻቸውን የሚጥስ ይዘት ካለው ብቻ መሆኑን ይናገራሉ።
ይህ ደግሞ ደኅንነትን እና በነጻነት ሃሳብን መግለጽን ታሳቢ ያደረገ ነው ባይ ናቸው።
ቲክቶክ፣ ዩቲዩብ እና ሜታ ሁሌም ተጠቃሚዎቻቸው መመሪያዎቹን በግልጽ እንዲያውቁት እንደሚያደርጉ ይናገራሉ።
ይህም ብቻ ሳይሆን በየጊዜው ከመተግበሪያዎች ላይ እንዲወርዱ ስለተደረጉ ይዘቶች ወይም ሥርጭታቸው ላይ ገደብ ስለተጣለባቸው ይዘቶች ግልጽነት የተሞላበት ሪፖርት እንደሚያወጡ ያስረዳሉ።
በተግባር ግን የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ድምጾች በሚበዙበት ወይም በሚታፈኑበት ጊዜ በተደጋጋሚ ጣልቃ ገብተው ተገኝተዋል።
ስለ ግልጽነት እና ፍትሃዊ የጨዋታ ሜዳ ያላቸው አቋም ከንግግራቸው ጋር የሚቃረን እንደሆነ ቢቢሲ፣ ተሟጋች ቡድኖች፣ ተመራማሪዎች እና ሌሎች የዜና አውታሮች ባደረጉት ምርመራ ደርሰውበታል።
ቢቢሲ እና ሂዩማን ራይትስ ዋች ባደረጉት ምርመራ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም የሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ የፍልስጤም ተጠቃሚዎችን እና የፍልስጤም ሰብአዊ መብትን የሚደግፉ ይዘቶችን ስልታዊ በሆነ መንገድ መገደባቸውን አረጋግጠዋል።
የሜታ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ኩባንያው "ስህተቶችን" እንደሚሠራ ተናግረው፣ ኩባንያው ሆነ ብሎ የተወሰኑ ድምጾችን አፍኗል የሚለው ግን "በማያሻማ መልኩ ውሸት" ነው ብለዋል።
በአውሮፓውያኑ 2019 ሾልከው የወጡ ሰነዶች ቲክቶክ የይዘት ተቆጣጣሪዎች "አስቀያሚ"፣ ደሃ፣ የአካል ጉዳተኞችን ወይም የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን ይዘቶች በብዛት ወደ ሰው እንዳይደርሱ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ማስተላልፉን አሳይተዋል።
ለዚህም የቀረበው ምክንያት ይዘቶቹ "ዝቅተኛ ሳቢነት እና ማራኪነት" ያላቸው መሆናቸው ነው።
በጊዜው ቲክቶክ ይህ ተግባር አሁን የማይፈጸም "በዘፈቀደ" የተወሰደ የፀረ ነቀፋ እርምጃ ነው ብሎ አስተባብሏል።
ይኸው ሾልኮ የወጣ ሰነድ ተጠቃሚዎች መንግሥትን በመተቸት "አወዛጋቢ" የሆኑ የቀጥታ ሥርጭቶች ሲያስተላልፉ እንደሚያግድ አመልክቷል።
ቲክቶክ ይህ "የአሜሪካ ተጠቃሚዎችን አይመለከትም" ሲል አስተባብሏል።
በ2023 ደግሞ ቲክቶክ የተመረጡ ቪዲዮዎች ለሰፊ ተጠቃሚዎች እንዲደደርሱ የሚያደርግ ምሥጢራዊ ቁልፍ እንዳለው አምኗል።
ይህም የንግድ አጋሮችን ለመሳብ እና አንዳንዴም በሠራተኞች ያለ አግባብ ጥቅም ላይ ውሎ ተገኝቷል።
ቲክቶክ ይህንን ምሥጢራዊ ቁልፍ አሁንም ይጠቀምበት እንደሆን ለቀረበለት ጥያቄ ግን ከመመለስ ታቅቧል።
ዩቲዩብም ተመሳሳይ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ያውቃል። በ2019 የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ የሆኑ ይዘት ፈጣሪዎች በጋራ ዩቲዩብን ከስሰዋል።
በክሳቸውም ላይ "የተመሰሳሳይ ፆታ አፍቃሪ"፣ "ፆታ ቅየራ" የሚሉ ቃላት ያሉባቸውን ቪዲዮዎች ገንዘብ እንዲከፈላቸው አላደረገም የሚል ነበር።
በኋላ ላይ ክሱ ውድቅ የተደረገ ሲሆን፣ ዩቲዩብም ከተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ጋር የተገናኙ ይዘቶችን የሚያግድም ሆነ ገንዘብ እንዳይከፈላቸው የሚያደርግ ፖሊሲ የለኝም ብሏል።
በአእምሯችን ውስጥ ያለ ጉዳይ ይሆን?
አልጎስፒክ አዲስ ነገር አይደለም።
ማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ላይ በወሲብ ንግድ ወንጀል ስለ ተፈረደበት ጄፍሪ ኤፕስቲን፣ ስለ ጋዛ እንዲሁም ስለ ተለያዩ አከራካሪ ርዕሰ ጉዳዮች በርካታ ቪዲዮዎችን እናገኛለን።
ቲክቶክ ስለግድያ የተሠራ ቪዲዮን የሚገድብ ከሆነ ከሞት ጋር ወይንም ከግድያ ጋር የተገናኙ ቃላትን በአጠቃላይ ያግድ ወይም ይገድብ ነበር።
ዝነኛ ይዘት ፈጣሪ የሆነችው አሪያና ጃስሚን "ማንኛችንም ምን እንደሚሠራ እና እንደማይሠራ አናውቅም። ሁላችንም ያለንን በመለጠፍ የሚሠራውን እና የማይሠራውን ለመለየት ነው የምንሞክረው" ትላለች።
ይህ ማለት ግን የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች የማኅበረሰብ ውይይትን መልክ በማስያዝ ረገድ ሚና የላቸውም ማለት አይደለም።
ከ2023 እስከ 2025 ድረስ ባሉት ጊዜያት ውስጥ ሜታ በይፋ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ልጥፎች ለብዙኃኑ እንዳይደርሱ ይገድብ ነበር።
ይህ ፖሊሲ ግን ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ሥራ ላይ እየዋለ አይደለም።
የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች ገንዘባቸውን የሚያገኙት ከማስታወቂያ ነው።
ይህም ማለት ግባቸው በርካታ ተጠቃሚዎች ያሉት መተግበሪያ እንዲኖራቸው ማስቻል ነው።
ከዚያ ማስታወቂያ የሚያሠሩ አካላት ምቾት የሚሰጣቸው ይዘቶች እንዲኖራቸው ማድረግ እና በየትኛውም መንገድ የመንግሥትን ቁጥጥር ማለፍ መቻል ግባቸው መሆኑን በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሴንተር ፎር ክሪቲካል ኢንኳየሪ ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ሳራ ቲ ሮበርትስ ያስረዳሉ።
ፕሮፌሰሯ ስለዚህ የትኛውም የአልጎሪዝም ለውጥ እና የይዘት ቁጥጥር የሚመጣው ከትርፍ ማግኘት ጽንሰ ሃሳብ ነው ይላሉ።
የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች ምክራቸው እና የቁጥጥር ጥረታቸው ዓላማ ለተጠቃሚዎቻቸው ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ምቹ ሁኔታ መፍጠር መሆኑንም ጨምረው ያስረዳሉ።
"እና ብዙ ጊዜ የይዘት ቁጥጥር ፍላጎቶች ከአብዛኞቹ የተጠቃሚዎች ፍላጎት ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸው እውነት ነው። ነገር ግን ማፈንገጥ ካለባቸው እና ከፈለጉ ያደርጉታል" ይላሉ ፕሮፌሰር ሮበርትስ።
"ሰዎች በመደበኛ ሕይወታቸው እርካታ ከሌላቸው፣ ያንን አለመርካታቸውን እና ብስጭታቸውን የሚተነፍሱት በእነዚህ መድረኮች መሆኑ ምርጡ መንገድ ነው?" ሲሉ እጠይቃሉ።
"እንደ ማኅበረሰብ ይህ እኛ የምንሳተፍበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ነው ወይ? የሚለውን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል" ይላሉ።















