በሴቶች ላይ እየበረታ ከመጣው የማኅበራዊ ሚዲያ ጥቃት እንዴት ራስን መጠበቅ ይቻላል?

በቻርጀር ገመድ የታሰሩ እጆች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዲጂታል ጥቃት ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ እያደገ የመጣ ስጋት ነው

የበይነ መረብ ጥቃት ወይንም ዲጂታል ቫዮለንስ በጣም በፍጥነት እያደጉ ካሉ የጥቃት ዓይነቶች አንዱ ሲሆን ሴቶችን ከኦንላየን እያስወጣ ነው።

ይህ ጥቃት በኦንላይን ተጠቃሚ ሴቶች ላይ ዘለፋን መፈጸም፣ ክትትል ማድረግ፣ ሐሰተኛ ቪዲዮዎች ማሠራጨት፣ ምሥልን ተጠቅሞ ስም በማጥፋት በሚሊዮን የሚ���ጠሩ ሴቶች እና ልጃገረዶች በየዓመቱ በርካታ ትንኮሳ ይደርስባቸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ 6 ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ከሴቶች በ280 ሚሊዮን የሚበልጡ ወንዶች በኦንላየን ተጠቃሚ ነበሩ ሲል የዓለም አቀፍ ቴሌኮምዩኒኬሽን ኅብረት የተባበሩት መንግሥታት የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ልዩ ኤጀንሲ አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሴቶች፣ ልጃገረዶች እና ፆታቸውን መግለጽ የማይፈልጉ ግለሰቦች በፆታቸው ምክንያት ዒላማ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ገልጾ የበለጠ ከባድ እና ዘላቂ መዘዝ ያጋጥማቸዋል ይላል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት እስከ 58 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች እና ልጃገረዶች በኦንላይን ለሚፈጸሙ ጥቃቶች ዒላማ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ድርጅት አስታውቋል።


በስልክ ስክሪን ላይ ተገቢ ያልሆነ ባህሪን ለማሳየት የተቀመጡ የጽሑፍ ምልልስ ምልክቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዝነኛ ሴቶች፣ አክቲቪስቶች እና ጋዜጠኞች በተሳዳቢዎች ዒላማ ከሚደረግባቸው መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው

በዲጂታል የሚደርሱ አምስት የተለመዱ ጥቃቶች

1. መዝለፍ

ዘለፋ ሆን ተብሎ ቀስቃሽ ወይም አፀያፊ መልዕክቶችን በኦንላይን ላይ በመለጠፍ አንድን ሰው ለማናደድ፣ ምላሽ እንዲሰጥ ለመቀስቀስ ወይም ችግር ለመፍጠር መሞከርን ያካትታል።

በኦንላይን ላይ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰት መረጃ ሥርጭትን ለማስቆም ያለመው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት (ሲሲዲኤች) እንደሚለው ሁለት ዋና የዘለፋ ዓይነቶች አሉ። እነሱም. . .

  • ጥቃትን ለማጉላት ትልቅ የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታዮች ያላቸውን ዝነኛ ሰዎች ዒላማ ያደረገ ዘለፋዎች፣
  • "አሉታዊ ማኅበራዊ ሁኔታን" በሚያነሳሱ ዘለፋዎች የተነሳ በሌሎች ላይ በሚደርስ ጉዳት መደሰት።

ሰዎች በኦንላይን ላይ የሚዘልፉበት ብዙ ምክንያቶች ሊኖራቸው የሚችል ሲሆን፣ አንዱ ዘለፋ ከሌላኛው የተለየ ነው።

ዘላፊዎች ብዙውን ጊዜ የሚያጠቋቸው ሰዎች በመበሳጨታቸው ይደሰታሉ፤ ስለዚህ ዒላማ ያደረጓቸው ሰዎች ምላሽ ከሰጡ ጥቃታቸውን እንዲቀጥሉ ይበረታታሉ።

ዘለፋ ጭንቀትን የሚያባብስ ሲሆን፣ የተጎጂውን በራስ የመተማመን ስሜትን ይቀንሳል።

2. የሌሎችን ግላዊ መረጃ ሆን ብሎ ማሠራጨት

 ያዘነች ሴት መስኮት አጠገብ ቁጭ ብላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የግላዊ ምሥልን ያለፈቃድ ለሰፊው የኦንላይን ተጠቃሚ ማጋራት ጭንቀትን የሚፈጥር ሲሆን ወደ ጥቃት ሊያመራም ይችላል

የግለሰቦችን መረጃ በመጥፎ ልቦና በመነሳሳት በኦንላይን ማሠራጨት በኦንላይን የሚደርስ የጥቃት ሌላ መልክ ነው።

ይህም ክትትል ማድረግ፣ ማስፈራራት እና አካላዊ ጥቃትን የመሳሰሉ ጉዳዮችን ሊያስከትል ይችላል።

በአውሮፓውያኑ 2021 የሃሪ ፖተር ደራሲ ጃኪ ሮውሊንግ አድራሻዋን የያዘ ከቤቷ ውጪ የተነሳችው ፎቶ በኦንላይን ላይ ከተሠራጨ በኋላ የዚህ ዓይነት ጥቃት ሰለባ እንደነበረች ተናግራለች።

ነገር ግን ፖሊስ እሷን ዒላማ ባደረጉት አክቲቪስቶች ላይ ምንም ዓይነት እርምጃ እንደማይወሰድ ተናግሯል።

ከሚያዚያ 2022 ጀምሮ በሜታ ባለቤትነት ሥር የሚተዳደሩት ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ምንም እንኳን ይፋ የሆነ መረጃ ቢሆንም ወይም በዜና ዘገባዎች ላይ ቢቀርብም የአንድን ሰው የቤት አድራሻ ማጋራት ከልክለዋል።

ተጠቃሚዎች አሁንም የራሳቸውን አድራሻ ማጋራት የሚችሉ ቢሆንም ሌሎች ግን እንደገና ማጋራት አይችሉም።

ይህ ለውጥ የተደረገው የግላዊ መረጃ ጥበቃን ለማጠናከር እና የግል መረጃን በክፋት የመልቀቅ ስጋቶችን ለመቀነስ ከሜታ ቁጥጥር ቦርድ የተሰጡ ምክሮችን ተከትሎ ነው።

3. ዲፕፌክ

ላፕቶፕ እየተመለከተች የመትጨነቅ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በርካታ ሴቶች ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ ከኦንላይን ይርቃሉ

ዲፕፌክ የሚባሉት ቪዲዮዎች ምሥሎች ወይም የድምጽ ቅጂዎች እውነተኛ እንዲመስሉ ተደርገው በሰው ሠራሽ አስተውሎት ሲሠሩ ነው።

እነዚህም ለመዝናኛነት ወይም ለሳይንሳዊ ምርምርም ሊያገለግሉ ይችላሉ።

ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ሕዝቡን ሆን ብለው ለማሳሳት ፖለቲከኞች ወይም የዓለም መሪዎች በማስመሰል ይሠራሉ።

ልቅ የሆኑ የወሲብ ቪዲዮዎችን ወይም የታዋቂ ሰዎችን ምሥሎችን ወይም ተራ ሰዎችን ምሥሎችን ለመፍጠር በስፋት ጥቅም ላይ ውለዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም በቅርቡ በፖሊስ የተካሄደ የዳሰሳ ጥናት "ከአራት ሰዎች አንዱ የሚታየው ሰው ፈቃደኛ ባይሆንም እንኳ ወሲብ ነክ የሆኑ ዲፕፌኮች መፍጠር እና ማጋራት ምንም ስህተት እንደሌለው ወይም ግድ እንደማይሰጣቸው" ያሳያል።

ያለፈቃድ ምሥሎችን ማጋራት ወይም ለማጋራት ማስፈራራት በዩናይትድ ኪንግደም ወንጀል ነው። በዚህ ሕግ መሠረት ይዘታቸው የተቀየረ ምሥሎችን ዲፕፌኮችን ጨምሮ ማጋራት ያስቀጣል።

እንደ አውስትራሊያ እና አየርላንድ ያሉ ሌሎች ብዙ አገራት ግለሰቦችን በምሥላቸው የተነሳ ከሚደርስባቸው ጥቃት ለመጠበቅ ተመሳሳይ ሕጎች አሏቸው።

ኮምፒውተሩ ፊት ለፊት ራሱን ሸፋፍኖ የተቀመጠ ወንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በበይነ መረብ አንዳንድ ሰዎች የወጣት ልጃገረዶችን እምነት ለማግኘት ማንነታቸውን ደብቀው ይቀርባሉ

4. ማባበል

ልጆች እና ወጣቶች በኦንላይን ዒላማ ሊደረጉ እና የተለያዩ የማባበያ ስልቶች ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ።

ወንጀለኞች ልጅቷ ላይ ጥቃት ከመፈጸማቸው በፊት እምነቷን ለማግኘት የተለያዩ ነገሮችን ያደርጋሉ።

ይህ ጥቃት በኦንላይን ሊፈጸም ወይም አጥፊው ​​ልጅቷን ለማጥቃት በማሰብ በአካል እንዲገናኙ ሊያመቻች ይችላል። በኦንላይን ላይ ጎጂ ይዘቶች ሲቀዱ፣ ሲለጠፉ ወይም ሲጋሩ ለተጨማሪ ጥቃት ያጋልጣሉ።

ጥቃቶች በኦንላይንም ተፈጸሙ ከዚያ ውጪ በታዳጊ ልጆች ላይ ዘላቂ የሆነ ጉዳት ያደርሳሉ።

ይህም ወደ ጭንቀት፣ ራስን መጉዳት፣ የአመጋገብ መዛባት፣ ራስን የማጥፋት ማሰብ እና ከሃሳብም አልፎ ራስን ማጥፋትን ያስከትላል።

5. የበይነ መረብ ተሳዳቢዎች

የሳይበር ተሳዳቢዎች ወይንም የኦንላይን ተሳዳቢዎች አንድ ግለሰብ በማኅበራዊ ሚዲያ፣ በመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች፣ በኦንላየን ጌሞች እና ሌሎች የኢንተርኔት ስፍራዎች ላይ የሚደርሱ ስድቦችን ያካትታል።

ይህ በመሳደብ የሚደርስ ጥቃት በተመሳሳይ ወቅት በኦንላይንም ሆነ ከኦንላይን ውጪ ሊደርስ ይችላል።

አንዳንድ ጊዜ በኦንላይን የሚሳደብ ሰው ጥቃቱ በሚደርስበት ሰው የሚታወቅ ይሆናል።

በመደበኛ ሕይወት ውስጥ ተገናኝተው የማያውቁ ነገር ግን በኦንላይን ማኅበረሰቦች ዘንድ በሚገባ የሚታወቅ ሰው፣ በጌሞች ወይም በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚያውቁት ሰው ትንኮሳን ሊያደርስ ይችላል።

ጥቃት ፈጻሚውም ስም አልባ ሊሆንም ይችላል።

ደኅንነትን እንዴት መጠበቅ ይቻላል?

“Scam Alert” የሚል ፍሑፍ ያለበት ስልክ የያዘ እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የበይነ መረብ ተቆጣታሪዎች እና የቴክ ኩባንያዎች የሳይበር ወንጀልን ለመቀነስ እርምጃ እየወሰዱ ነው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኦንላይን ከሚደርስ ጥቃት ራስን ለመከላከል ወይንም ለመቀነስ የሚረዱ በሚል ያጋራቸው አንዳንድ ምክሮች የሚከተሉት ናቸው።

  • በኦንላይን ላይ ማንኛውንም ነገር ከመለጠፍ ወይም ከማጋራትዎ በፊት ደጋግመው ያስቡ፤ ያጋሩት ነገር በኦንላይን ላይ ለዘላለም ሊቆይ እና በኋላ ላይ እርስዎን ለመጉዳት ሊያገለግል ይችላል።
  • በኦንላይን ላይ የሚለጥፉትን መረጃዎች በተለይም እንደ አድራሻ እና የስልክ ቁጥርን የመሳሰሉ የግል መረጃዎችን ይገድቡ።
  • ጓደኞችዎ እና ወዳጆችዎ ስለእርስዎ የግል መረጃ እንዳይለጥፉ ያስጠነቅቁ።
  • በማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች ላይ ማን መረጃዎን ማየት እንደሚችል እና የይዘት አማራጮችን ማገድ/መደበቅ እንደሚችል ጨምሮ የግላዊ መረጃ አያያዝ (ሴቲንግ) አጠቃቀምን በደንብ ይረዱ።
  • በሁሉም አካውንቶችዎ ላይ የሚገኙበትን አካባቢ መጠቆሚያ ያጥፉ።
  • አጠራጣሪ ወይም አስጊ አካውንቶችን ሪፖርት ያድርጉ።

አሳሳቢ አደጋ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኦንላይን እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጥቃትን በብቃት ለመከላከል ድርጊቱ ምን እንደሆነ እና በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ ያለውን ተጽእኖ በአግባቡ መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው ይላል።

በአውሮፓውያን 2021 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአረብ አገራት ውስጥ ያደረገው ጥናት እንዳመለከተው 60 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ለኦንላይን ጥቃት በዚያው ዓመት ተጋልጠዋል።

አንድ የአውሮፓ ጥናት ደግሞ ሴቶች በኦንላይን ከወንዶች በ27 እጥፍ ለትንኮሳ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍ ያለ ሲሆን፣ በሌላ ትንታኔ ደግሞ 92 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች በኦንላይን ላይ የሚፈጸም ጥቃት ደኅንነታቸውን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ገልጿል።

በሕዝብ ሕይወት ውስጥ በይፋ ተሳትፎ የሚያደርጉ ሴቶች እንደ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በተለይ ዒላማ ተደርገዋል።

ለነጭ ያልሆኑ ሴቶች፣ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች እና የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ላይ አደጋው ከፍ ያለ ነው ሲል የመንግሥታት ድርጅት ገልጿል።

ድርጅቱ በሁሉም ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ ዲጂታል ጥቃትን ለማስቆም ዘመቻ ጀምሯል።

ዘመቻው መንግሥታት የግል መረጃን እንዲከላከሉ እና ዲጂታል ጥቃትን ወንጀል እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ሲሆን፣ ትላልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጎጂ ይዘቶችን እንዲያስወግዱ አሳስቧል።