በርካታ ወጣቶች ለምን በለጋ ዕድሜያቸው ፀጉራቸው ይሸብታል? የሸበተውን ፀጉር መመለስስ ይቻላል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሽሊ ስኩሩ በ14 ዓመቷ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለች ነበር ነጭ ፀጉር ማውጧን ያወቀችው። ጓደኛዋ ነጭ የሆኑ ዘለላ ፀጉሯን ለቅማ አሳየቻት። ይቺ ቅፅበት ስለ መልኳ የነበራትን ስሜት ለበርካታ ዓመት የቀየረች ናት።
"ወዲያውኑ አይሆንም አልኩ፤ ሽበት ሊኖረኝ አይችልም፤ ገና 14 ዓመቴ ነው" ማለቷን ታስታውሳለች።
"በምሳ ሰዓት ወደ ቤቴ ተመልሼ ፀጉሬን እየለቀምኩ ሳይ ብዙ ነጭ ፀጉሮች እንዳሉኝ ተረዳሁ። ሀፍረት ተሰማኝ።"
ቤተሰቦቿን ፀጉሯን ቀለም ለመቀባ እንደለመነቻቸው የምታስታውሰው አሽሊ ካናዳዊ ስትሆን አሁን 28 ዓመቷ ነው።
"ሁሉንም ሰው ጋር ለመመሳሰል ስትሞክሪ ሽበት ፀጉር ከሌላው ጋር የሚያመሳስል አይደለም፤ ለመሸፈን እሞክር ነበር" ስትል ትገልፃለች።
ሰዎች ያለ ዕድሜያቸው እየሸበቱ ነው?
ተመራማሪዎች መቼ እንደምንሸብት ለመወሰን ዘር (ጄኔትክስ) ትልቁ ወሳኝ ነው ይላሉ። አሽሊ ያደረገችው ምርመራም ይሁኑ ያመለክታል። እናቷም በ14 ዓመቷ ሽበት የወጣባት ሲሆን፤ አያቷ ደግሞ በ17 ዓመታቸው ነው ሽበት የጀመራቸው።
ሐኪሞች ቁጥራቸው እየጨመረ ያሉ በአብዛኛዎች በ20ዎቹ እና በ30ዎቹ ያሉ ወጣት ታካሚዎች ፀጉራቸው ያለ ዕድሜያቸው መሸበት በመጀመሩ እየተጨነቁ ነው ይላሉ።
ጤናማ የሕይወት ዘይቤ የሚመሩ የቆዳ ቀለማቸው ነጭ የሆኑ ሰዎች ሽበት የሚጀምራቸው በ35 ዓመታቸው ነው። ለአፍሪካዊያን እና እስያዊያን ደግሞ ከዚህ ከ10 ዓመት በኋላ የሚመጣ ነው።
ከዚህ ዓመት በፊት የሚታይ ሽበት ያለ ዕድሜ የሚመጣ ሽበት ሲሆን፤ ይህም ማለት ለነጮች ከ20 ዓመታቸው በፊት፤ ለአፍሪካዊያን ከ30 ዓመታቸው በፊት እንዲሁም ለእስያዊያን ከ25 ዓመታቸው በፊት።
እነዚህ የዕድሜ መደቦች የወጡት የፀጉር እድገት በተለያዩ ዘሮች የተለያየ መሆን ነው።
በዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላላ ሐኪም የሆኑት ሰርመድ መዚሂር "በዚህ መንገድ ሌሎች መንስኤዎችን መቼ መፈለግ እንዳለብን እና በመደበኛ የዕድሜ ክልል መቼ ይከሰታል የሚለውን እናውቃለን" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Ashley Sukru
ፀጉር ለምን ይሸብታል?
አዲስ ፀጉር 'ሜላኖክተስ' የተባሉ አሳዳጊ ሕዋሶች ባሉበት ስፍራ በቆዳ ጥቃቅን ቀዳዳዎች ይበቅላል።
'ሜላኖክተስ' ሁለት የለተያዩ ቀለሞችን የሚያመርት ሲሆን፤ አንደኛው የፀጉርን ጥቁረት የሚወስን ሌላኛው ደግሞ ቀይ አሊያም ቢጫ ቀለም መሆኑን የሚወስን ነው። እነዚህ ማቅለሚያዎች የቆዳ እና የዓይን ቀለምንም የሚወስኑ ናቸው።
በኒው ዮርክ ዩኒቨርስቲ የተመራማሪዎች ቡድን በሕዋስ የእድገት ሂደት ላይ የተሠራ አንድ ጥናት ፀጉር እያደገ ሲሄድ በርካታ ቁጥር ያላቸው የ'ሜላኖክተስ' ሕዋሶች ሥራቸውን እንዳይሠሩ ቀርፋፋ ያደርጋቸዋል።
በጥቃቅን ቀዳዳዎች የተሰባሰቡት ሕዋሶች እድገታቸው ይገታ እና ሙሉ ለሙሉ 'ሜላኖክተስ' መሆን ይሳናቸዋል።
የፀጉርን ጥቁረት የሚወስነው 'ፒግመንት' ካልተመረተ ፀጉር ወደ ሽበት፣ ወደ ነጭ አሊያም ወደ ግራጫነት ይቀየራል።
የንጥረ ነገሮች እጥረት ያለ ዕድሜ ሽበትን ሊያስከትል?
የዩናይትድ ስቴትስ እና የብራዚል ተመራማሪዎች የቆዳ እና የፀጉርን ቀለም የሚወስኑት ሕዋሶች በከባድ ጭንቀት ወቅት እንደሚጎዱ በጥናታቸው አረጋግጠዋል።
ነገር ግን ባለሙያዎች ያለ ዕድሜ መሸበት የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘት ወይም እጥረት ምልክት ሊሆን ይችላል ይላሉ።
የቫይታሚን ዲ እና ቢ12 እጥረት፣ የኮፐር፣ አይረን፣ ዚንክ እና የፎሊክ አሲድ መጠን መቀነስ ያለ ዕድሜ ከሚከሰት ሽበት ጋር ይያያዛሉ። ከእነዚህ ውስጥ የቢ12 እጥረት ያለ ዕድሜ ለመሸበት ትልቁ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል።
'ኮባላሚን' ተብሎም የሚታወቅ ቢ12 ንጥረ ነገር ለፀጉት ጥቃቅን ቀዳዳዎች ጨምሮ ለሰውነት ኦክስጂን የሚያቀርበውን ጤናማ ቀይ የደም ሕዋስን ለማምረት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
በደንብ ኦክስጂን የሚያገኝ የቆዳ ቀዳዳ 'ፒግመንት' የተባለውን የፀጉርን ቀለም የሚወስነውን ክፍል በበቂ ሁኔታ እንዲመረት ያደርጋል።
ዶ/ር መዚሂር "ቢ12 በአብዛኛው ከእንስሳት ተዋፅኦ የሚገኝ እና አንድ ሰው ሙሉ ለሙሉ የእንስሳት ተዋፅኦ የማይመገብ ከሆነ [ቪገን ከሆነ] እና አጋዥ ንጥረ ነገሮች ካልወሰደ በዋናነት መንስኤ ብለን ከምንዘረዝራቸው ነገሮች ሁሉ ከፊት የሚመጣው ይህ ነው" ይላሉ።
ከዚህ በተጨማሪ የባሕር ምግቦች፣ ሰሊጥ፣ የበሬ እና የበግ ጉበት መመገብ የፀጉርን ቀለም የሚወስነውን እና ከብርሃን ጉዳት የሚከላከለውን ሚላኒን ለማምረት የሚያግዝ ነው።
ይሁን እንጂ ባለሙያዎች ከመጠን በላይ ዚንክ እና ቫይታሚን ሲ ከወሰድን ከእነዚህ ምግቦች የምናገኘው የኮፐር ንጥረ ነገር ሊዋጥ አሊያም ሊያሳጥር ይችላል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
በ20ዎቹ ዕድሜ መሸበት የጀመረችው የሥነ ምግብ ባለሙያ እና ፀሐፊ ማሪያ ማርሎው በቅርብ ዓመታት በተለይም በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ሰዎች በሽታ የመከላከል አቅማቸውን ለማጎልበት የዚንክ አጋዦችን መውሰድ እንደጀመሩ ጠቁማለች።

የፎቶው ባለመብት, Maria Marlowe
"በደንብ ካልተመጣጠነ በተመሳሳይ ሁኔታ ኮፐርን ሊያሟጥጥ ይችላል" ትላለች።
"የዚንክ አጋዥ መውሰድ ከፈለጋችሁ ዚንክን ከኮፐር ጋር አብሮ መውሰድ አለባችሁ፤ ስለዚህ ተቀላቅለው።"
ከፍተኛ መጠን ያለው አይረን እና ቫይታሚን ሲ መውሰድም የኮፐር መጠንን እንደሚቀንስም ታክላለች።
ሐኪሞች ያለ ዕድሜ መሸበት በንጥረ ነገሮች እጥረት ከተከሰተ ከሌሎችንም ምልክቶች ጋር ብቅ እንደሚል ይናገራሉ።
ዶ/ር መዚሂር እንደሚሉት "ከኮፐር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ክብደት መቀነስ፣ የፀጉር መሳሳት እና ሽፍታዎች ሊያስተውሉ ይችላሉ። በጣም መድከም እና መሰላቸት እንዲሁም ብርድ አለመቻል ሊሰማም ይችላል።"
ማሪያ ማርሎች ከምርመራ በኋላ የኮፐር፣ የአይረን እና የአዮዲን እጥረት እንዳለባት አውቃለች።
የተመጣጠነ ምግብ ያለ ዕድሜ የሚከሰት ሽበትን ይቀለብሳል?
በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የተደረገ ጥናት ጭንቀት ከተፈታ አዲስ ፀጉር በተፈጥሯዊ ቀለሙ መልሶ እንደሚበቅል አረጋግጧል።
ሐኪሞቹ ፀጉር በንጥረ ነገር ማነስ ምክንያት ከሸበተ ወደ ቀደመው ሁኔታው በተመሳሳይ መመለስ ���ቻላል ይላሉ።
ዶ/ር መዚሂር "ለአብዛኛው ሰው ሽበቱ ከዘር ጋር የተያያዘ ከሆነ አይመለስም" ይላሉ።
በንጥረ ነገር የበለፀጉ ምግቦችን በመመገብ የሚመከር ሲሆን፤ አንዳንድ ምግቦች በአማራጭነት መመገብ ካልተቻለ አጋዦችም መውሰድ እንደሚረዳ ይመከራል።
"ፀጉር ወደ ነበረበት ቦታ ባይመለስ እንኳ መሸበቱን ቢያንስ ይቀንሰዋል ወይም የመሸበት ሂደቱን ያስቆመዋል. . ።"
ይሁን እንጂ ባለሙያዎች ሽበትን ለመቀልበስ ሚያስችል የተረጋገጠ ፈውስ የለም ይላሉ።
ማሪያ ማርሎው የአመጋገብ ሥርዓቷን ስታስተካክል እና ከባድ ብረት እንዳላቸው የሚታወቁ ምግቦችን ስትቀንስ በሽበቶ ፀጉሯ ላይ ለውጥ ማየቷን ትናገራለች።
ለውጥ ለማየት ግን ቢያንስ በትንሹ ሦስት ወራት ያህል እንደጠበቀች የምትናገረው ማሪያ የሸበተውን ፀጉሯን ሙሉ ለሙሉ ወደ ነበረበት መልኩ ግን መመለስ አልቻለችም።
በአትክልት እና ፍራፍሬ የሚገኘው 'አንቲኦክሲደንት' የተጎዳ ዘረመል እና ያለ ዕድሜ የሚከሰትን መመለጥ እና መሸበት ለመከላከል ያግዛል።
ሲጋራ ማጨስ፣ የሥነ ልቦናዊ ጭንቀት፣ ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት ወይም በጣም በሕዝብ በተጨናነቀ አካባቢ መኖር ለፀጉር ጉዳት አስተዋጽኦ አላቸው።
ማሪያ ባለፈው ዓመት የልጅ እናት ከሆነች በኋላ መደበኛ ልማዷን ገታ ማድረጓን ተከትሎ ተጨማሪ የሽበት ዘለለላዎች ዳግም መመለሳቸውን ተናግራለች።

የፎቶው ባለመብት, Ashley Sukur
ለአሽሊ ግን የአመጋገብ ሥርዓቷን ማስተካከል የዘር ግንዷን የሚቀይረው አይደለም። ነገር ግን ዕይታዋ ተቀይሯል።
ግራጫ ፀጉሯ አሁን የማንነቷ አካል ሆኗል። አሁን በኦንላይን ስለ ወጣትነት እና ቁንጅና ነባር ዕይታዎችን የሚቀናቀን ማኅበረሰብ መገንባት ችላለች።
"በቲክቶክ እና በኢንስታግራም [ይዘቶችን] መለጠፍ ስጀምር በእኔ ዕድሜ ያሉ ፀጉራቸው እየሸበተ ያሉ በርካታ ሴቶችን አግኝቻለሁ" ትላለች።
"'ሽበታም ፀጉር ያስጠላል፣ ሽበት ለሽማግሌዎች ነው' ከማለት ፈንታ ተጨማሪ ሴቶች ሽበታማ ፀጉራቸውን እንዲቀበሉት አነሳሳለሁ ብዬ ተስፋ አለኝ።















