አሜሪካ የ10 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ያቀረበችበት የዋይት ሐውስ እንግዳ፡ አህመድ አል ሻራ

የሶሪያው ፕሬዚዳንት አህመድ አል ሻራ

የፎቶው ባለመብት, Louai Beshara/AFP via Getty Images

አዲሱ የሶሪያ ፕሬዝዳንት አህመድ አል ሻራ በአግባቡ የተተኮሰ ሱፍ ለብሰው፣ ፀጉራቸውን ወደ ኋላ አበጥረው ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ሲመጡ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንዳሉ ያ���ታውቃል።

አሁን የትግል ልብሳቸውን ትተው፣ አዲስ ስም ይዘው በዓለም ላይ ካሉት በጣም ኃያላን መሪዎች ጋር ይጨባበጣሉ።

ዩናይትድ ስቴትስ የሶሪያውን ፕሬዚዳንት ስም ከዓለም አቀፍ አሸባሪነት ዝርዝር ውስጥ በይፋ ካወጣች ከሁለት ቀን በኋላ ለሥራ ጉብኝት ዋሽንግተን ገብተዋል።

የቀድሞ እስላማዊ ታጣቂ ይመሩት የነበረው የአማፅያን ጥምረት በሽር አል አሳድን ከሥልጣን ካስወገደ ከ11 ወራት በኋላ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን በዋይት ሐውስ ያገኛሉ።

ታዲያ በአንድ ወቅት አሜሪካ እርሱን ያለበትን ለጠቆመኝ 10 ሚሊዮን ዶላር እከፍላለሁ ያለችለት ሰው እንዲህ አስደናቂ ለውጥ ሊያመጣ ያስቻለው ምንድን ነው?

የሶሪያው ፕሬዚዳንት ወደ ሥልጣን ከመጡ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ሲገናኙ ይህ ሁለተኛቸው ነው

የፎቶው ባለመብት, Bandar Al-Jaloud/Saudi Royal Court/Handout/Anadolu via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሶሪያው ፕሬዚዳንት ወደ ሥልጣን ከመጡ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ሲገናኙ ይህ ሁለተኛቸው ነው

ሻራ ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ ሶሪያን በዓለም መድረክ ላይ ዳግም በአግባቡ ለመወከል እየሰሩ ነው።

አገራቸው አሳድ በሥልጣን ላይ በነበሩበት እና በ13 ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ከዓለም አቀፍ መድረክ ተገልላ ቆይታለች።

ፕሬዚዳንት ሻራ በመስከረም ወር ወደ አሜሪካ ተጉዘው በተባበሩት መንግሥታት አጠቃላይ ጉባዔ ላይ የተገኙ ሲሆን በወቅቱም ሶሪያ "በዓለም ላይ የሚገባትን ስፍራ ዳግም ትይዛለች" በማለት የዓለም መሪዎች የጣሉትን ማዕቀብ እንዲያነሱ ጠይቀው ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ነገር ግን፣ የሻራ ለውጥ ከዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጋር ያደረጓቸውን ቃለ ምልለሳቸውን እና ንግግራቸውን በአግባቡ ለሚመለከት ከአስር ዓመታት በላይ በጥንቃቄ ሲሰሩ የቆዩ መሆኑን እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበቱ የመጡ መሆኑን ያስተውላል።

ስለ ተምሳሌታዊ ኃይል ጥልቅ ግንዛቤ ያላቸው መሆኑ ያስታውቃል።

ከዚህ በፊት የጂሃዲስት ታጣቂዎችን ልብስ ለብሰው ይታዩ የነበሩት ግለሰብ፣ ባለፉት ዓመታት የምዕራባውያን ዓይነት አልባሳትን ለብሰው ታይተዋል።

እናም ባለፈው ዓመት የአሳድ መንግሥትን ለመጣል በተካሄደው ዘመቻ ወታደራዊ አልባሳትን ለበሱ፣ ይህም የዘመቻው አዛዥ በመሆን የነበራቸውን ሚና አሳይተዋል።

ይህ ሁሉ ነገር ሻራ በሶሪያ ውስጥ የሃያት ታህሪር አል ሻም (ኤችቲኤስ) መሪ ሆነው ይጠቀሙበት የነበረበት አቡ መሐመድ አል-ጆላኒ ተብለው ይጠሩ ከነበረበት ጊዜ በጣም የራቀ ነው።

ቡድኑ ግንኙነቱን እስከአቋረጠበት 2016 ድረስ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ነበረው።

ሻራ ኤችቲኤስን ከመምራታቸው በፊት በኢራቅ ውስጥ ላለው አልቃይዳ ሲዋጉ ለተወሰነ ጊዜ በአሜሪካ ጦር ቁጥጥር ስር ውለው ነበር።

በሻራ ዘመን ኤችቲኤስ በሰሜን ምዕራብ የሶሪያ ትልቁ የአማፅያን ይዞታ እና ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች መኖሪያ በሆነችው ኢድሊብ ውስጥ የበላይ ሆኖ ቆይቷል።

አካባቢውን ስለሚያስተዳድረው ታጣቂ ቡድን ያሉ ስጋቶችን ለመፍታት ኤችቲኤስ ፖለቲካውን እና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የሚመራ ሶሪያ ሳልቬሽን ገቨርንመንት (ኤስጂ) ተብሎ የሚጠራ ሰላማዊ ሰዎች የሚመሩት ግንባር አቋቁሟል።

ኤስጂ በሸሪዓ ወይም በእስልምና ሕግ የሚመራ የሃይማኖት ምክር ቤት የነበረው ሲሆን እንደ ትምህርት፣ ጤና እና መል�� ግንባታ ያሉ ዘርፎችን የሚቆጣጠሩ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና የአካባቢ መምሪያዎች ያሉት ራሱን እንደ አገር መሪ ቆጥሮ ስራዎችነ የሚያከናውን ነበር።

ሻራ ቀደም ሲል አቡ መሐመድ አል-ጆላኒ በመባል ይታወቅ የነበረ ሲሆን  ከጊዜ በኋላ ግን ስሙን እና ያለውን ሰብዕና በከፍተኛ ሁኔታ ቀይሯል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሻራ ቀደም ሲል አቡ መሐመድ አል-ጆላኒ በመባል ይታወቅ የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ግን ስሙን እና ያለውን ሰብዕና በከፍተኛ ሁኔታ ቀይሯል

ሻራ በሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ምስል የበለጠ ለማሻሻል፣ ከሕዝቡ ጋር በንቃት ይሳተፋሉ። የተፈናቃይ መጠለያ ካምፖችን በመጎብኘት፣ ዝግጅቶች ላይ በመሳተፍ እና በተለይ እአአ በ2023 በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት የእርዳታ ጥረቶችን በመከታተል ከፊት ተሰልፈው ታይተዋል።

ኤችቲኤስ አገዛዙን ቅቡል ለማድረግ፣ መረጋጋትን እንደሚፈጥር እና አገልግሎቶችን የመስጠት አቅሙን ለማሳየት በአስተዳደር እና በመሠረተ ልማት ውስጥ የተገኙ ስኬቶችን አጉልቷል።

ቀደም ሲል እአአ በ2021 ታሊባን በአፍጋኒስታን ወደ ሥልጣን ሲመለስ የጂሃዲስት ጥረቶችን ከፖለቲካ ምኞቶች ጋር በውጤታማነት ለማመጣጠን፣ ግባቸውን ለማሳካት ስልታዊ ማመቻመች ማድረግን ጨምሮ እንደ መነሳሻ እና አርአያ በማቅረብ አሞካሽተዋቸዋል።

ሻራ በኢድሊብ ያደረጉት ጥረት ኤችቲኤስ ጂሃድ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን በብቃት ለማስተዳደር ያለውን አቅም ለማሳየት ያለውን ሰፊ ስልት አንጸባርቀዋል።

መረጋጋትን፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን እና መልሶ ግንባታን በማስቀደም ኢድሊብን በኤችቲኤስ አገዛዝ የስኬት ተምሳሌት አድርጎ ለማሳየት ያለመ ሲሆን፣ ይህም የቡድኑን ቅቡልነት እና የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት አሳድጓል።

ለእነዚህ የቡድኑ እርምጃዎች ምላሽ አሜሪካ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በኤችቲኤስ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ አንስታለች።

ነገር ግን በእርሳቸው አመራር ኤችቲኤስ ሥልጣኑን ለማጠናከር እና ቦታዎችን ለመቆጣጠር ባደረገው ጥረት ሌሎች ታጣቂ ቡድኖችን፣ ጂሃዲስቶችን እና አማፂያንን በመጨፍለቅ እና በማግለል ተከሷል።

ኤችቲኤስ ከአሳድ መወገድ በፊት ባሉት ወራት ውስጥ በርካታ ማሻሻያዎችን አድርጓል። በሰብአዊ መብት ረገጣ የተከሰሰውን አወዛጋቢ የጸጥታ ኃይል በትኗል ወይንም ዳግም አዋቅሮ ዜጎች በቡድኑ ላይ ቅሬታ እንዲያቀርቡ የቅሬታ መምሪያ አቋቁሟል።

ተቺዎቹ እነዚህ እርምጃዎች ተቃውሞን ለመከላከል የተወሰዱ እርምጃዎች ብቻ ናቸው ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ሻራ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሻራ ከትራምፕ ጋር መገናኘታቸው በዲፕሎማሲያው መስክ ያላቸውን ምስል ለማሻሻል የሚያደርጉት እርምጃ አካል ነው።

ከዚህ ቀደም በግንቦት ወር የሳዑዲ ዋና ከተማን ሪያድ በጎበኙበት ወቅት ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጋር ተገናኝተው ነበር።

ትራምፕ ሻራን "ጠንካራ፣ ያለፈ የኋላ ታሪክ ያለው ሰው" ሲሉ ገልጸውታል።

እናም በመስከረም ወር ላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ለማድረግ ወደ አሜሪካ ተጉዘው ሶሪያ "በዓለም ላይ የሚገባትን ስፍራ ዳግም ትይዛለች" በማለት የዓለም መሪዎች የጣሉትን ማዕቀብ እንዲያነሱ ጠይቀዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመርያ ላይ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት አሜሪካ ማዕቀቦችን ለማንሳት የወሰደችውን እርምጃ ደግፏል።

አሜሪካ በሶሪያ እና በአገሪቱ መሪዎች ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ለማንሳት ወራትን የፈጀ ሂደት ተከትላለች።

ምንም እንኳ ቀደም ሲል ሻራ በአሸባሪነት ከተፈረጁ ታጣቂዎች ጋር ቢሰሩም፣ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ሁሉን አካታች መንግሥት እንደሚመሰርቱ በመናገራቸው የሶሪያ የተለያዩ ብሔሮችን እና አንጃዎችን ድጋፍ ማግኘታቸውን ተከትሎ የአሳድ መንግሥትን የሚቃወሙ አገራት ድጋፍ ችረዋቸዋል።

በግንቦት ወር ከዘ ኢኮኖሚስት ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ሻራ "በበቀል ላይ ወደፊትን መገንባት አንችልም። ሶሪያ የአሸናፊዎች ብቻ ሳትሆን የሁሉም ሕዝቦቿ መኖሪያ መሆን አለባት" ብለዋል።

በእርግጥ ፕሬዚዳንቱ በአሜሪካ ዋና ከተማ ዋሺንግተን ዲሲ ከመድረሳቸው ሰዓታት ቀደም ብሎ የሶሪያ የደኅንነት ባልደረቦች በርካታ የኢስላሚክ ስቴት ቡድን አባላትን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸው ተገልጿል።

ከወራቶች በፊት በፀጥታ መዋቅር ውስጥ የሶሪያ አላዌቴ ህዳጣንን በመግደል የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን መንጥረው እንደሚያወጡ ተናግረው ነበር።

ይህ ግን ቀላል የማይባል ፈተና ገጥሞታል።

ባለፉት ጥቂት ወራት በሱኒ ቤድወኒ ጎሳ ተዋጊዎች እና ድሩዝ ታጣቂዎች መካከል ደም አፋሳሽ ግጭት ተቀስቅሶ ከአስር ዓመታት በላይ በጦርነት የምትታወቀውን አገር የሚመራው የኤችቲኤስ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ መረጋጋትን ያመጣል ወይ የሚል ጥያቄ ፈጥሮ ነበር።