እስራኤል በሶሪያ ላይ ጥቃት እንድትፈጽም ምክንያት የሆኑት ድሩዞች እነማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አዲሱ የሶሪያ መንግሥት የተበታተነውን ግዛት አንድ ለማድረግ በሚጥርበት በዚህ ወቅት የአገሪቱ ደካማ የፀጥታ ሁኔታ እና በሶሪያ የተቀሰቀሰው ከባድ ሃይማኖት ተኮር ግጭት ፈተና ሆኖበታል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሐምሌ13/2025 የድሩዝ ጎሳ አባላት የሆኑ ነጋዴዎች መታፈናቸው ተሰማ።
ከዚያም በደቡባዊ ሶሪያ በድሩዝ ታጣቂዎች እና በሱኒ ቤዱዊን ተዋጊዎች መካከል ለቀናት የዘለቀ ግጭት ተቀሰቀሰ።
በኋላ ማክሰኞ ሐምሌ 15/2025 የእስራኤል ጦር ድሩዞችን ለመከላከል እና በሱዌይዳ ጥቃት ፈጽመዋል የተባሉትን የመንግሥት ደጋፊ ኃይሎችን ለማጥፋት በሚል ጥቃት ፈጽሟል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ የአገሪቱ ጦር "ድሩዝ ወንድሞቻችንን ለማዳን እና የሥርዓቱን ወንበዴዎች ለማስወገድ እየሠራ ነው" ብለዋል።
ከእሁድ ጀምሮ በሱዌይዳ ቢያንስ 350 ሰዎች መሞታቸውን የሶሪያን የሰብዓዊ መብቶች የሚከታተለው ተቋም ይፋ አድርጓል።
በሚያዝያ እና በግንቦት ወር በድሩዝ ተዋጊዎች እና በሶሪያ አዲሱ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መካከል ውጊያ ተቀስቅሶ በርካታ ሰዎች ከተገደሉ በኋላ፣ የድሩዝ ጎሳ አባላት በብዛት በሚገኙበት የሱዌይዳ ግዛት ዳግም ግጭት ሲቀሰቀስ ይህ የመጀመሪያው ነው።
ከዚህ ቀደም ብሎ በመጋቢት ወር በሶሪያ የባሕር ጠረፍ ግዛቶች በተቀሰቀሰው ግጭት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድ ወገን የሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአላዋይት ጎሳ አባላት መገደላቸው ተነግሯል።
ይህ ከፍተኛ ግጭት ከእስራኤል ጥቃት ጋር ተደምሮ በሶሪያ የፀጥታ ችግር ሊፈጠር ይችላል የሚል ፍራቻን በድጋሚ ፈጥሯል።
ከአስር ዓመታት በላይ በዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የቆየችው ሶሪያ በቅርቡ እስላማዊ መራሹ የአማፅያን ቡድን በታኅሣሥ 2024 ደማስቆን ከተቆጣጠረ ወዲህ የታየ ከፍተኛ ግጭት ነው።
የአሁኑ የሶሪያ መሪ የቀድሞ ጂሃዲስት አህመድ አል ሻራ፣ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን የሶሪያን ኃይሎች ለመከላከል ቃል ገብተዋል።
ድሩዝ እነማን ናቸው?
ድሩዝ በሶሪያ፣ በሊባኖስ፣ በእስራኤል እና እስራኤል በወረራ በያዘችው የጎላን ተራሮች የሚገኙ አረብኛ ተናጋሪ ሕዝቦች ናቸው።
ድሩዞች የሚከተሉት ሃይማኖት የራሱ የሆነ መለያ እና እምነት ያለው የሺዓ እስልምና አካል ነው።
በግምት ወደ አንድ ሚሊዮን ከሚጠጉ ተከታዮቹ ውስጥ ግማሽ ያህሉ የሚኖሩት በሶሪያ ውስጥ ሲሆን፣ ከአጠቃላይ ሕዝቡ 3 በመቶ ብቻ ናቸው።
በእስራኤል ውስጥ የሚገኙት የድሩዝ ማኅበረሰብ አባላት ለእስራኤል መንግሥት ታማኝ እንደሆኑ የሚነገር ሲሆን፣ በአገሪቱ የውትድርና አገልግሎት ውስጥም ይሳተፋሉ።
እንደ የእስራኤል ማዕከላዊ የስታትስቲክስ ቢሮ መረጃ ከሆነ 152 ሺህ የድሩዝ ማኅበረሰብ አባላት በእስራኤል ውስጥ እና በእስራኤል በወረራ በተያዘው የጎላን ተራሮች ላይ ይኖራሉ።
እነዚህ ማኅበረሰቦች በሶሪያ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ በታሪክ አደገኛ የሆነን ቦታ ይዘዋል።
ለ14 ዓመታት ያህል በዘለቀው የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ድሩዞች በደቡባዊ ሶሪያ የራሳቸውን የታጣቂ ቡድን አደራጅተዋል።
በታኅሣሥ ወር የአሳድ መንግሥት መውደቁን ተከትሎ ድሩዞች በደቡባዊ ሶሪያ ማዕከላዊ መንግሥቱ አስተዳደሩን ለመመሥረት የሚያደርገውን ሙከራ ተቃውመዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሶሪያ ውስጥ ያሉት የድሩዝ አንጃዎች የሶሪያን አዲሱን መንግሥት በጥርጣሬ ከመመልከት እስከ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አስከማድረግ የተከፋፈሉ ሲሆኑ፣ ብዙዎቹ የሶሪያን የፀጥታ አካላት ወደ ሱዌይዳ መግባቱን ይቃወማሉ።
በተጨማሪም ከሶሪያ ጦር ጋር መቀላቀልን የተቃወሙ ሲሆን፣ በምትኩ በአካባቢው ባሉ ሚሊሻዎች ላይ መተማመንን መርጠዋል።
የሶሪያ መንግሥት በቅርቡ በድሩዝ ማኅበረሰብ አባላት ላይ የተፈፀመውን ጥቃት በማውገዝ፣ በደቡባዊ ሶሪያ ያለውን ፀጥታ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ ቃል መግባቱ ቢገልጽም፣ ጦሩ ህዳጣን የሆኑትን ድሩዞች በማጥቃት ተከስሷል።
መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የሶሪያ የሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ ባደረገው ክትትል በድሩዝ ማኅበረሰቦች ላይ በመንግሥት ኃይሎች "ግድያ" መፈጸሙን ይፋ አድርጓል።
እንደነዚህ ያሉት ሪፖርቶች በአንዳንድ የድሩዝ ማኅበረሰብ አባላት እና ደማስቆ ባለው መንግሥት መካከል አለመተማመንን አስፍነዋል።
ከአሳድ ድንገተኛ ውድቀት በኋላ እስራኤል በሰሜናዊ ድንበሯ አቅራቢያ ከሚገኙት የድሩዝ ማኅበረሰብ ጋር ጥምረት ለመፍጠር ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።
የእስራኤል መንግሥት በሶሪያ የሚገኙ ወታደራዊ ሥፍራዎችን እና የመንግሥት ኃይሎች ላይ ጥቃት እየፈጸመ በሶሪያ የሚገኙ ኩርዶችን፣ ድሩዞችን እና አላዋይቶችን በመከላከል የህዳጣን ቡድኖች ጠባቂ ለመሆን ይሞክራል።
በግንቦት ወር በተካሄደው የጎሳ ግጭት እስራኤል በደማስቆ በሚገኘው ፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ጥቃት ፈጽማለች።
ይህም በድሩዝ ማኅበረሰብ ላይ ለሚሰነዘረው ጥቃት ማስጠንቀቂያ መሆኑን ገልጻለች።
ነገር ግን አንዳንድ የሶሪያ እና የሊባኖስ ድሩዝ ተወላጆች እስራኤል በቀጠናው የራሷን የመስፋፋት ምኞት ለማራመድ የጎዛ መከፋፈልን ታስፋፋለች ሲሉ ከስሰዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል ሶሪያን አሁን ለምን አጠቃች?
እስራኤል በቅርብ ጊዜ የፈጸመቻቸው ጥቃቶች በዋነኛነት የሶሪያ ጦር ወደ ደቡባዊ ሶሪያ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለማስተጓጎል እና እንደ ማስጠንቀቂያ ነው።
እስራኤል በአካባቢው ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ የሆነ ቀጠና ለመፍጠር ትፈልጋለች።
በተለይም እስራኤል በሰሜናዊ ድንበሯ አቅራቢያ፣ በኃይል በተቆጣጠረችው የጎላን ተራሮች አካባቢ እስላማዊ ተዋጊዎች መኖራቸው ያሰጋታል።
ሐምሌ 15/2025 የእስራኤል አየር ኃይል የፈጸመው ድብደባ በሱዌይዳ የፀጥታ ኃይሎች እና ተሽከርካሪዎች ላይ በማነጣጠር ላይ ብቻ የተገደበ ቢሆንም፣ በቀጣዩ ቀን የጥቃቱን ወሰን በማስፋት በደማስቆ የሚገኘውን የመከላከያ ሚኒስቴርን ዋና መሥሪያ ቤት መትቷል።
ሶሪያ ጥቃቱን አውግዛለች።
እስራኤል ሶሪያን ብዙ ጊዜ ደብድባለች። ከታኅሣሥ 2024 ወዲህ እስራኤል በመቶዎች የሚቆጠሩ የሶሪያ ወታደራዊ ጣቢያዎችን በመላ አገሪቱ አውድማለች።
በተባበሩት መንግሥታት ስር የነበረውን የሶሪያ ጎላን ተራሮች ግዛት በቁጥጥሯ ስር አድርጋለች።
ይህ የአሁኑ ጥቃት ደግሞ አዲሶቹ ባለሥልጣናት ወታደራዊ አቅማቸውን እንዳይገነቡ ለመከላከል በማሰብ ሲሆን፣ ለእስራኤል ደኅንነት ስጋት ሊሆን እንደሚችልም ተቆጥሯል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትስ ሐምሌ 16/2015 ጦራቸው በደማስቆ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ "ለደማስቆ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ አክትሟል። አሁን ከፍተኛ ውድመት የሚያደርሱ ድብደባዎች ይከተላሉ" ሲሉ ጽፈዋል።
የሶሪያ ወታደራዊ ዋና መሥሪያ ቤት በእስራኤል ጦር ጥቃት ሲደርስበት ስቱዲዮው ከሕንጻው ባሻገር የሚገኘው የሶሪያ ቴሌቪዥን በቀጥታ አስተላልፏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተቀረው ዓለም ምን አለ?
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ አገራቸው ግጭቱ "በጣም አሳስቧታል" ያሉ ሲሆን፣ "ይህንን አሳሳቢ እና አስፈሪ ሁኔታ ለማስቆም በሚያስችሉ የተለዩ እርምጃዎች ላይ ተስማምተናል" ሲሉ አክለዋል።
ሊባኖስ፣ ኢራቅ፣ ኳታር፣ ዮርዳኖስ፣ ግብፅ እና ኩዌትን ጨምሮ በርካታ የአረብ አገራት የእስራኤል ጦር የሶሪያ መንግሥት እና የፀጥታ ኃይሎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈፀሙን አውግዘዋል።
የሳውዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "እስራኤል በሶሪያ ላይ ያደረሰችው ግልጽ ጥቃት ነው" በማለት ተቃውሟል።
ኢራን ግን ጥቃቱን "ሁሉም ሊገመት የሚችል" ብላዋለች።
በድኅረ አሳድ ሶሪያ ውስጥ ቁልፍ ባለድርሻ የሆነችው ቱርክ ጥቃቱን "ሶሪያ ሰላምን፣ መረጋጋትን እና ደኅንነትን ለማስጠበቅ በምታደርገው ጥረት ላይ የተደረገ የሸፍጥ ተግባር" ስትል ገልጻዋለች።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም እስራኤል በሱዌይዳ እና በደማስቆ የምታደርገውን ጥቃት "አባባሽ" ሲሉ አውግዘውታል።
ቀጥሎ ምን ሊሆን ይችላል?
ሁከቱ በሶሪያ ከእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ ያለውን ደካማ የፀጥታ እና የፖለቲካ ሁኔታ አጉልቶ አሳይቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች በሶሪያ አለመረጋጋት እና የሃይማኖት ጥቃት እንደገና ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ፍራቻን ፈጥሯል።
አል ሻራ የሶሪያን ግዛት ለመቆጣጠር እና የተለያዩ ቡድኖችን አንድ ለማድረግ እየሞከሩ ባለበት በአሁኑ ወቅት በእስላማዊ የበላይነት የሚመራው መንግሥት ለዓመታት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት የተነሳ የሶሪያን ስር የሰደደ የሃይማኖት ክፍፍል ማስታረቅ ይችሉ እንደሆነ ወደፊት የሚታይ ይሆናል።
የሃይማኖት ግጭት ከእስራኤል ጥቃት ጋር ተደምሮ በመንግሥት ግንባታ እና ከጦርነቱ በኋላ ለማገገም የሚደረጉ ሙከራዎችን እንዳያደናቅፈው ተሰግቷል።
እስራኤል በበኩሏ አዲሶቹን ባለሥልጣናት እና በደቡብ የሚገኙትን ተባባሪ እስላማዊ ተዋጊዎቹን እንደ ትልቅ የደኅንነት ስጋት መቁጠሯን ቀጥላለች።
ይህ ደግሞ በአዲሶቹ ባለሥልጣናት የተገለሉ ከሚመስላቸው ቡድኖች ጋር ትስስር እንድትፈጥር ይገፋፋታል።















