የሠርጋቸው ቪዲዮ 'ቫይራል' ሲወጣ በቆዳ ቀለማቸው መሳለቂያ የሆኑት ሕንዳውያን ጥንዶች

ሪሽአብህ ራጅፑት እና ሶናሊ ቾውክሰይ ሰርጋቸው ላይ

የፎቶው ባለመብት, Rishabh Rajput and Sonali Chouksey

የምስሉ መግለጫ, ሪሽአብህ ራጅፑት እና ሶናሊ ቾውክሰይ የተጋቡት ኅዳር ላይ ነበር

ሪሽአብህ ራጅፑት እና ሶናሊ ቾውክሰይ የተዋወቁት ከ11 ዓመት በፊት ኮሌጅ እያሉ ነበር። በፍቅር ወደቁ፤ የአንድ ወር በፊት ደግሞ ተጋቡ።

የሠርጋቸው ፎቶ እና ቪዲዮዎች በማዕከላዊ ሕንድ ከምትገኘው ፕራዴሽ ግዛት የተገኙት ጥንዶች ምን ያህል ደስተኛ እንደነበሩ ያሳያሉ። ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን ሲፈጽሙ እና አብረው ፎቶ ሲነሱ ይ��ያሉ።

ጥንዶቹ ይህንን የደስታቸውን ቀን የሚያሳዩ ምሥሎችን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያጋሩ የደረሳቸው እንኳን ደስ አላችሁ የሚሉ መልዕክቶች ብቻ አልነበሩም። የጥንዶቹን የቆዳ ቀለም የሚያነጸጽሩ እና የሙሽራውን ቀለም የሚተቹ "ቀልዶች እና ሚሞች" በብዛት ተሰራጭቶባቸዋል።

ሕንድ ውስጥ ሰዎች ቀላ ያለ የቆዳ ቀለም ላይ ያላቸው አባዜ በአግባቡ የተሰነደ ነው። አንዳንድ ጊዜም አሰቃቂ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ ምክንያት የሆነ ጉዳይ ነው።

ባለፈው መስከረም ላይ፤ የፊቷ ቆዳ ቀለም "ጠቆረ" ያለ ባል ሚስቱን በሕይወት እያለች በእሳት በማቃጠሉ የሞት ቅጣት ተፈርዶበት ነበር።

በሠርጉ ቪዲዮ ላይ የታየው ባል ሪሽአብህ ራጅፑት "በጠቆረው የቆዳ ቀለሙ" ምክንያት በበይነ መረብ መሸማቀቅ ደርሶበታል፤ በቅጥያ ስሞችም ተጠርቷል። የማኅበራዊ ሚዲያ ተሳላቂዎች ሙሽራዋንም አልተዋትም። "ለገንዘቡ" ብላ እንዳገባችው የሚጠቁሙ ልጥፎችን ሲያጋሩ ነበር።

አንድ ተጠቃሚ፤ "የሆነ ግዴታ ሳኖሮባት ሳይሆን አይቀርም" በማለት ጽፏል። ሌላ ተጠቃሚ፤ በዚህ ዓይነት ሁኔታ በባለቤቷ ደስተኛ እንደማትሆን አስፍሯል።

አንዳንዶች፤ ለሃብቱ ወይም ጥቅማ ጥቅም ያለበት የመንግሥት ሥራ ለማግኘት ብላ እንዳገባችው በመናገር፤ "ጎልድ ዲገር" በማለት ጠርተዋታል። አንድ አስተያየት ሰጪ ደግሞ የራጅፑት አባት "የመንግሥት ሚኒስትር" እንደሆነ የሚጠቁም ምልከታ ሰጥቷል።

በኅዳር 14/2018 ዓ. ም. የተጋቡት ጥንዶች በዚህ ስላቅ እና የሚቀርብባቸውን ትችት በመጋፈጥ በሰጡት ምላሽ የተነሳ መነጋገሪያ ሆነዋል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በርካታ ቃለ መጠይቆችን ሰጥተዋል።

"ሰዎች ቀልዶችን እና ሚሞችን እየሠሩ ነበር፤ በጣም ስህተት እንደሆነ ተሰምቶኛል" ሲል ራጅፑት ጃባልፑር ለቢቢሲ ሂንዲ ተናግሯል። "የእኛ ጊዜ ነበር፤ ለብዙ ዓመታት ጠብቀነዋል። የደስታ ጊዜ ነው መሆን የነበረበት። የሰዎችን ምላሽ ስመለከት ግን እጅግ ደንግጫለሁ" ብሏል።

"አብረን በነበርንባቸው በርካታ ዓመታት፤ እኔ ጠቆር ያለ ቆዳ ስላለኝ እርሷ ቀላ በማለቷ ምክንያት ማንም ሰው አንድ ላይ የማንሄድ ሰዎች እንደሆንን ነግሮን አያውቅም" ሲል ሁኔታው አዲስ እንደሆነበት ያስረዳል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰጡት አስተያየቶች የግል ኩባንያ ውስጥ የሚሠሩትን ጥንዶች ግራ አጋብቷል።

ቾውክሰይ፤ አስተያየቶቹ "እንደረበሿት" አልሸሸገችም። " 'ሰዎች የሚመለከቱን እንደዚህ ነው?' ብለህ ታስባለህ። ስለ እርሱ መጥፎ ነገር ሲናገሩ ወይም እኔን ጎልድ ዲገር ሲሉኝ ያበሳጨኛል" ��ትም ስሜቷን አጋርታለች።

ራጅፑት፤ በገፍ ለመጡት ስላቆች በሰጠው ምላሽ "ስላሳዘንኳችሁ አዝናለሁ። የመንግሥት ሠራተኛ አይደለሁም፤ ነገር ግን ለቤተሰቤ በትጋት እሠራለሁ። ጥሩ እና የተከበረ ሕይወት ልሰጣቸው እፈልጋለሁ" ብሏል።

ሪሽአብህ ራጅፑት እና ሶናሊ ቾውክሰይ ሰርጋቸው ላይ ቁጭ ብለው

የፎቶው ባለመብት, BBC Hindi

የምስሉ መግለጫ, ጥንዶቹ የተዋወቁት በ2006 ዓ. ም. የኮሌጅ ተማሪ እያሉ ነበር
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሶናሊ ከእርሱ ጋር በፍቅር የወደቀችው ምንም ባልነበረው ሰዓት እንደሆነም አስታውሷል። "ከኮሌጅ እስከ ዛሬ ድረስ በእያንዳንዱ ጥሩ እና መጥፎ ጊዜ ከጎኔ ቆማለች። የሰዎች መጥፎ ምልከታ ለእኛ ምንም ማለት አይደለም" በማለት ጽፏል።

ስለቆዳ ቀለሙ ስለተሰጠው አስተያየትም ያነሳው ራጅፑት፤ በሕይወቱ በሙሉ ይህ ዓይነቱም የቀለም ማግለል ሲደረስበት እንደነበር ገልጿል።

"ጠቆር ያለ ቆዳ እንዳ���ኝ በደንብ አውቃለሁ። ነገር ግን በባለቤቴ ዐይን [ስታይ] በቻልኩት መጠን ምርጥ ባል ለመሆን እየሞከርኩ ነው፤ ከሁሉም በላይ ዋጋ የሚሰጠውም ይኸው ነው። ስለ ቤተሰቤ ስህተት ማውራት አስፈላጊ አይደለም" ብሏል።

ተሳላቂዎቹ እናቱ እና የባለቤቱ እህት በሚታዩበት አንድ ፎቶ ላይ ተመሳሳይ አስተያየት መስጠት ሲጀምሩ እርሱም መጋፈጥ ጀምሯል። "ቤተሰቤን ዒላማ እያደረጉ መሆኑን አልወደድኩትም። ማንም እንዳልሆኑ ልነግራቸው እፈልጋለሁ። የማንንም ቤተሰብ ዒላማ ወይም መሳለቂያ ለማድረግ መብት የላችሁም" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ከ2006 ዓ. ም. ጀምሮ አንድ ላይ ያሉት ጥንዶች፤ ከውጭ የሚመለከቷቸው ሰዎች ሕይወታቸውን ሊዳኙ እንደማይገባ ተናግረዋል።

"ግንኙነታችን የጀመረው ከአንድ ዓመት በኋላ ነበር። ከመጀመሪያውን ቀን አንስቶ እንደምንጋባ እናውቅ ነበር። የ30 ሴኮንድ ቪዲዮ ተመልክተው ስለ ግንኙነታችን አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች [ግንኙነታች ላይ] ያፈሰስነውን የ11 ዓመታት ልፋት አያውቁም" ሲል ራጅፑት ያስረዳል።

"ሶናሊ፤ ስንጋባ መንደራችን በሙሉ ምስክር እንደሚሆን ትናገር ነበር። ዛሬ ግን መላው ዓለም እየተመለከተን ይመስላል" ሲልም ያክላል።

ጥንዶቹ ያገኙት ትኩረት በጎ ጎንም እንዳለው ይስማሙበታል። የሚሰጡት አስተያየቶች ግን ቤተሰቦቻቸውን እየጎዳ መሆኑን ቾውክሰይ ትናገራለች።

"ለሰዎች፤ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚመለከቱት ነገር ብቻ ሊሆን ይችላል፤ ለእኛ ግን ሕይወታችን ነው። የሆነ ሰው ቤተሰብን ሊበትን ይችላል" ትላለች።

ጥንዶቹ በሰጧቸው በርካታ ቃለ መጠይቆችም በአገራቸው ያለውን የቆዳ ቀለም መድልዎ ጉዳይ አንስተዋል።

ቾውክሰይ፤ "ከተለያዩ ሃይማኖቶች የመጡ ሰዎች የተለያየ የቆዳ ቀለም ከሚይዙባት ሕንድ ነው የመጣነው። ቀላ ያለ ቆዳ አንድን ሰው ጥሩ ሰው ያደርገዋል ማለት አይደለም። ታድያ እንዴት አንድን ሰው ከቆዳ ቀለሙ ተነስትን እንፈርጀዋለን?" በማለት ትጠይቃለች።

ራጅፑት በበኩሉ "ሕንድ ውስጥ ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ጠቆር ያለ የቆዳ ቀለም ነው ያላቸው። በሕንዳውያን አእምሮ ግን ቀላ ያለ ሰው የተሻለ ነው። ይህንን ዕሳቤ ለመቀየር ጊዜው አሁን ነው" ብሏል።

ጥንዶቹ 'አንድ ላይ አይሄዱም' ለሚሉት ሰዎች ደግም ምላሽ ሳይሆን ጥያቄ ነው ያለው።

"እኛን ስትመለከቱን፤ ትንሽ እንኳ ደስተኛ ያልሆንን እንመስላችኋለን? አይደለንም። ምክንያቱም እኛ ብዙ ሰዎች የሌላቸው ነገር አለን። እኔ እሷ አለችኝ፤ እሷ እኔ አለኋት።"