በመካከለኛው ምሥራቅ ኃያል የሆነችው የአይሁዶች አገር እስራኤል እንዴት ተመሠረተች?

ዴቪድ ቤንጎሪዮን በዙሪያቸው ሌሎች ሰዎች ተቀምጠው የእስራኤል መመሥረትን ሲያውጁ የሚያሳይ ባለ ነጭ እና ጥቁር ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዴቪድ ቤንጎሪዮን የእስራኤል መመሥረትን ሲያውጁ

በመካከለኛው ምሥራቅ በእስራኤል እና በፍልስጤማውያን መካከል የሚካሄደው ግጭት ዘመናት ቢያስቆጥርም መቋጫ ከማግኘት ይልቅ እየተወሳሰበ የዓለማችን አሳሳቢ ጉዳይ ከሆነ ዘመናት ተቆጥረዋል።

ከ75 ዓመታት በፊት የተመሠረተችው እስራኤል የአካባቢው ኃያል በመሆን የበላይነትን ስትይዝ፤ ፍልስጤማውያን ደግሞ በስደት እና በጦርነት ውስጥ ሆነው የራሳቸውን አገር ለመመሥረት ሳይችሉ አስካሁን ደርሰዋል።

ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል እያካሄደችው ያለው ወታደራዊ ዘመቻ የፍልስጤማውያንን ስቃይና መከራን ከማባባሱ በላይ ኅልውናቸውንም አደጋ ላይ ጥሎታል።

የእስራኤል ባለሥልጣናት ጋዛን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር እንዲሁም በዌስት ባንክ ውስጥ የአይሁዳውያንን ሰፈራዎች ለማስፋፋት መወሰናቸው ሌላ ዙር መፈናቀል እና ስደትን በፍልስጤማውያን ላይ ያስከትላል ተብሎ ተሰግቷል።

ለመሆኑ ፍልስጤም ለሁለት ተከፍላ የእስራኤል እና የፍልስጤም መንግሥታት እንዲመሠረት እንዴት ተወሰነ? የአይሁዳውያን አገር የሆነችው እስራኤል እንዴት ተመሠረተች?

የ YouTube ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን Google YouTube ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በGoogle YouTube. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የGoogle YouTube ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም። YouTube] ማስታወቂያ ሊኖረው ይችላል።

የ YouTube ይዘት መጨረሻ

ግንቦት 14/1984 ልክ 10 ሰዓት. . . በመቶዎች የሚቆጠሩ አይሁዶች ቴል አቪቭ በሚገኘው የሥነ ጥበብ ሙዚየም ደጃፍ ተሰብስበዋል።

ዴቪድ ቤን-ጎሪዮን ደግሞ ሙዚየሙ ውስጥ ሆነው የመካከለኛው ምሥራቅን ታሪክ እስከ ወዲያኛው የሚቀይር ንግግር እያደረጉ ነው።

ይህም በፍልስጤም የእስራኤል ድርጅት ሊቀመንበር የሆኑት ዴቪድ ቤን-ጎሪዮን የእስራኤልን በነፃነት አገርነት መመሥረትን ያወጁበትን ንግግር አያሰሙ ነበር። ከዚህ ክስተት ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ የብሪታንያ ወታደሮች አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል።

ቀኑ አይሁዶች ሁሌም እያስታወሱ በደስታ የሚዘክሩት፤ አረቦች ደግሞ "የጥፋት ቀን" (ናቅባ) ሲሉ የሚብሰለሰሉበት ነው።

ዛሬ በወታደራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃያላን ከሚባሉት አገራት አንዷ ለመሆን የበቃችው እስራኤል በዚህ መልኩ ነበር የተመሠረተችው።

የፊዚክስ ሊቁ አልበርት አንስታይን ከእስራኤል የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ቤን ጎሪዮን ጋር ተቀምጠው የሚያሳይ ባለ ነጭ እና ጥቁር ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የፊዚክስ ሊቁ አልበርት አንስታይን ከእስራኤል የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ቤን ጎሪዮን ጋር

ጽዮናዊነት እና የአይሁዶችን አገር ፍለጋ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በ1880ዎቹ ፍልስጤም የኦቶማን ኢምፓየር እና "ታላቋ ሶሪያ" ተብሎ የሚጠራው አካባቢ አካል ነበረች።

የፍልስጤም ሕዝብ በአብዛኛው ሙስሊም ሲሆን፣ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ክርስቲያኖች እና አይሁዶችም ነበሩ። አይሁዶች ከጠቅላላው ሕዝብ 5 በመቶ አካባቢ የሚሆነውን እንደሚሸፍኑ ይገመታል።

በዓለም ዙሪያ የተበተኑት አይሁዳውያን የራሳቸውን አገር ለመመሥረት ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ ዋነኛ ትኩረታቸው መካከለኛው ምሥራቅ ነበረ።

ከዚያም አሊያህ እየተባለ በሚጠራው የአይሁዶች የፍልሰ�� እንቅስቃሴ የተስፋይቱ ምድር ብለው ወደ ሚጠሯት ፍልስጤም መፍለስ የጀመሩት አካባቢው በኦቶማኖች ቁጥጥር ሥር ሳለ ነው።

የአብዛኛዎቹ አይሁዳውያን ፍልሰት መነሻ ደግሞ ሩሲያ ነበረች። ሩሲያ ውስጥ በነበሩበት ወቅት፤ የአገሪቱን ንጉሥ ዛር አሌክሳንደር 2ኛን ለመግደል ተሳተፋችኋል በሚል ተከሰው በርካቶች ተፈርዶባቸዋል።

በዚህም የተነሳ በሚገጥማቸው ከፍተኛ የሆነ የፀረ-ሴማዊነት ጥቃት እና መሳደድ ምክንያት ይፈጸምባቸው የነበረው ጥቃት 'ፖግሮምስ' በመባል ይታወቃል።

በወቅቱ ወደ ፍልስጤም የደረሱት አይሁዶች ለእርሻ የሚሆን መሬት ለማግኘት እና አነስተኛ የመኖሪያ መንደር ለመመሥረት ችለዋል። እነዚህም 'ኪቡትዝ' በመባል ይጠራሉ።

እነዚህ ቀደምት ፍልሰቶች በጽዮናዊነት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸው ነበሩ። ጽዮናዊነት አውሮፓን እያጥለቀለቀ ለነበረው ፀረ-ሴማዊነት ምላሽ ሲሆን፣ በኋላም በአይሁዶች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ እንቅስቃሴ ለመሆን በቃ።

የዚህ እንቅስቃሴ ዋነኛው መሪ ደግሞ የኦስትሮ-ሃንጋሪው ጋዜጠኛ ቴዎዶር ሄርዝል ነበር።

የታሪክ ምሁሩ ዮርጌ ራሞስ እንደሚሉት ሄርዝል "የአይሁዶችን ፈተና ሃይማኖታዊ ሳይሆን የማንነት እንደሆነ ያምን ነበር። የጽዮናውያን እንቅስቃሴ ያደረገው ነገር ቢኖር አይሁድነት ተቀባይነት እንዲያገኝ እና አይሁዶች እንደ ሕዝብ ተቆጥረው በአውሮፓ የሚደርስባቸውን ፈተና የሚያሳልፉበት ሌላ መሸሸጊያ አገር መፍጠር ነበር።"

ጽዮናዊነት ዓለም አቀፍ ድጋፍ አስፈልጎታል። በወቅቱ የነበሩት ታላላቅ አገራትም አዲሷን አይሁዳዊት አገር ለመመሥረት ብዙ ቦታዎችን ከግምት አስገብተዋል። ከአርጀንቲና እስከ ኡጋንዳ፤ ከማዳጋስካር እስከ ሩቅ ምሥራቅ ሩሲያ ድረስ ያሉ ቦታዎችን ተመልክተዋል።

ሆኖም አይሁዳዊነት ከፍልስጤም ጋር ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ጥብቅ ቁርኝት ነበረው። በዚህም ምክንያት ፍልሰቱ ወይም አሊያህ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ቀጠለ። በዚህ ወቅት ነበር ቴል አቪቭ የተቆረቆረችው።

የፍልስጤምን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የወሰነው ክስተት ግን የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ነበር።

በተጨናነቀ መርከብ ላይ ሆነው ከአውሮፓ የመጡ አይሁዳውያን ስደተኞችን የሚያሳይ ጥቁር እና ነጭ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጦርነት ከወደመችው አውሮፓ ተሰደው በ1947 (እአአ) ሃይፋ ወደብ የደረሱ አይሁዳውያን ስደተኞች

ከኦቶማን ወደ ብሪታንያ የተዛወረችው ፍልስጤም

ከአውሮፓውያኑ 1914 እስከ 1918 ባለው ጊዜ ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት በዳረገው በዚህ ደም አፋሳሹ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት፤ መካከለኛው ምሥራቅ ልዩ ትኩረት አግኝቷል።

ከኦቶማን ኢምፓየር በተቃራኒ የቆመችው ብሪታኒያ በኦቶማኖች እጅ የነበረውን አካባቢ ለመንጠቅ ከፍተኛ ፍላጎት ነበራት። በወቅቱ ብሪታኒያ ገንዘብ የምትሰበስብበትን የስዊዝ ካናልንም ትቆጣጠር ነበር።

"ዩናይትድ ኪንግደም በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በዋናነት በኦቶማን ባለሥልጣናት ላይ ውስጣዊ አመጽን በማነሳሳት የኦቶማን ግዛትን እና የኦቶማንን ጥንካሬ ለማዳከም ሞክራለች" ሲሉ የታሪክ ተመራማሪው ዮርጌ ራሞስ ይናገራሉ።

ለዚህም ሲባልም ብሪታኒያ በአካባቢው ትልቅ የአረብ መንግሥት እንዲመሠረት ድጋፍ እንደምትሰጥ በመግለጽ ፊቷን ወደ አረቦች አዞረች።

ይህ ሃሳብ የቀረበው በ1915 እና 1916 የመካው ገዢ ሁሴን ቢን አሊ እና በካይሮ የብሪታኒያ አምባሳደር በነበሩት ሄንሪ ማክማሆን መካከል በተደረጉ የደብዳቤ ልውውጦች ላይ ነው።

በወቅቱም የፍልስጤም አረቦች እና ��ሎችም ለዘመናት አካባቢው በተቆጣጠረው በኦቶማን ጦር ላይ አመጽ ጀመሩ።

ብሪታኒያም ደብዳቤ በመጻፍ ለአይሁዶች አንድ ሃሳብ አቀረበች።

በ1917 የባልፎር ስምምነት ተብሎ የሚጠራው ደብዳቤ በብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አርተር ጀምስ ባልፎር በኩል፤ በዩናይትድ ኪንግደም መቀመጫቸውን ላደረጉት የአይሁድ ማኅበረሰብ መሪ ባሮን ሊዮኔል ዋልተር ሮትሽልድ ተላከ።

በዚህ ደብዳቤ ላይ የብሪታንያ መንግሥት ፍልስጤም ውስጥ "አይሁዶች አገር" እንዲመሠርቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል። ነገር ግን በአካባቢው ያሉትን አይሁድ ያልሆኑ ማኅበረሰቦች መብት እንደሚከበርም በግልጽ አስፍሯል።

ከአረቦች እና ከአይሁዶች ጋር ከሚደረጉት ድርድሮች ጎን ለጎን ብሪታኒያ በ1916 ከፈረንሳይ ጋር የሳይክስ-ፒኮት ስምምነትን በድብቅ ተፈራረመች። በስምምነቱ መሠረት ሁለቱ ኃያላን ጦርነቱን ካሸነፉ በኦቶማን ግዛቶች ላይ ያላቸውን ተጽእኖ እና ቁጥጥር የሚመለከት ነው።

አገራቱ በ1918 ድል ቀናቸው። የኦቶማን ግዛት የነበረውን መካከለኛው ምሥራቅን የተከፋፈሉትም በዚህ ስምምነት መሠረት ነው።

መጀመሪያ ላይ ፍልስጤም በዓለም አቀፍ ቁጥጥር ስር ሆና ቆየች። በኋላ ላይ ግን ብሪታኒያ ፍልስጤምን ለማስተዳደር ዝግጁ ነኝ ስትል ሃሳብ ቀረበች።

እናም ገና መቋቋሙ የነበረው የዓለም መንግሥታት ማኅበር (የሊግ ኦፍ ኔሽን) በ1922 ብሪታንያ ፍልስጤምን ለማስተዳደር ያቀረበችውን ሃሳብ ተቀበለ።

የማስተዳደር ኃላፊነቱን መውሰድ የራሱ መልዕክት ነበረው። አንድ አስተዳደር ሌላውን ካሸነፈ በኋላ አካባቢውን ለማስተዳደር ተረከበ ማለት የአካባቢው ነዋሪዎች ራሳቸውን ማስተዳደር አይችሉም የሚል መልዕክትን ያስተላልፋል።

በዚያን ወቅትም ከፍልስጤም ነዋሪዎች አብዛኞቹ ሙስሊሞች ነበሩ። የአይሁዶች ቁጥር ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ወደ 11 በመቶ አካባቢ ደርሶ ነበር።

ብሪታኒያ በፍልስጤም ላይ የነበራት አገዛዝ በይፋ አብቆቶ ወታደሮቿ ሰንደቅ ዓላማቸውን በ1948 ሲያወርዱ የሚያሳይ ባለ ጥቁር እና ነጭ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Bettmann via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ብሪታኒያ በፍልስጤም ላይ የነበራት አገዛዝ በይፋ አብቆቶ ወታደሮቿ ሰንደቅ ዓላማቸውን በ1948 ሲያወርዱ

አመጽ እና ውጥረት

በአውሮፓውያኑ 1931 በፍልስጤም የተደረገው የሕዝብ ቆጠራ የአይሁዶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ደጋሚ አሳየ።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት በአውሮፓ እየጨመረ የነበረው በአይሁዳውያን ላይ የሚያነጣጥረው የፀረ-ሴማዊነት እንቅስቃሴ ሲሆን፣ ቁጥራቸውንም 16 በመቶ አደረሰው።

የቁጥራቸው መጨመርን ተከትሎ በአካባቢው በአረቦች እና በአይሁዶች መካከል ያለው ውጥረትም ከፍ እያለ መጣ።

በ1936 ደግሞ በፍልስጤም ብሪታኒያን የሚቃወም የአረብ አመፅ ተቀሰቀሰ። ይህም ለስድስት ወራት የሚቆይ አጠቃላይ የሥራ ማቆም አድማ ነበር። የአረቦችን ነፃነት እና አይሁዶች በአካባቢው የሚያደርጉት ሰፈራ እንዲያበቃም ተጠይቋል።

ይሁን እንጂ አመፁ ከሸፈ። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመሞታቸውም በተጨማሪ የፍልስጤም ብሔራዊ ንቅናቄም በኋላ ላይ በተፈጠሩ ክስተቶች ምክንያት ክፉኛ ተዳከመ።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አይሁዶች ወደ ፍልስጤም የሚያደርጉት ፍልሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨመረ። በተለይም የናዚ ማጎሪያ ካምፖች ነፃ መውጣታቸውን ተከትሎ የጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸሙ ሲታወቅ የሚፈልሱት አይሁዶች ቁጥሩ ከፍ አለ።

የፍልስጤም ችግር እልባት እንዲያገኝ በብሪታኒያ ላይ የሚደርሰው ዓለም አቀፍ ጫናም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ መጣ። ብሪታንያ በአካባቢው መኖሯ በአይሁዶችም ሆነ በአረቦች ዘንድ ያለው ተቀባይነት ቀነሰ።

ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ በፍልስጤም የብሪታኒያ አስተዳደር መቀመጫ በሆነው በኪንግ ዴቪድ ሆቴል ላይ ሐምሌ 22/1946 የተፈጸመው ጥቃት ነው።

ጥቃቱ 'ኢርጉን' በተባለው የጽዮናውያን ታጣቂ ድርጅት የተፈፀመ ሲሆን፣ የ92 ሰዎች ሕይወት የጠፋበት ጥቃት ሆኖ በብሪታኒያ ዘንድ ድንጋጤን ፈጥሯል።

በመርከብ ወደ ግብፅ የተሰደዱ ፍልስጤማውያንን የሚያሳይ ጥቁር እና ነጭ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ምሥረታን ተከትሎ በርካታ ፍልስጤማውያን ለስደት ተዳርገዋል። በመርከብ ወደ ግብፅ የተሰደዱ ፍልስጤማውያን

የፍልስጤም ለሁለት መከፈል

በአካባቢው እየጠነከረ የመጣው ውጥረት ብሪታኒያ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት እንድትወስደው ምክንያት ሆኗል። ይህንንም ተከትሎ 11 ገለልተኛ አገራትን ያቀፈ የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ልዩ ኮሚቴ ተቋቋመ።

ኮሚሽኑ ግዛቱን ለሁለት በመክፈል አንዱን ለአረቦች ሌላኛወን ደግሞ ለአይሁዶች ሰጠ። እያንዳንዳቸው ሦስት ዞኖች የሚኖራቸው ሲሆን፣ ኢየሩሳሌም ደግሞ በልዩነት በዓለም አቀፍ ቁጥጥር ስር እንድትሆን ሐሳብ አቅርቧል።

'ፕሮፖዛል 181' የተሰኘው ይህ ሃሳብ፣ የግዛቱን 55 በመቶ ለአይሁዶች ቀሪውን 45 በመቶ ለአረቦች ሰጠ። በወቅቱ የነበረው የአይሁዶች ቁጥር፤ ከጠቅላላው ሕዝብ አንድ ሦስተኛ ገደማ ብቻ ነበር።

ሃሳቡ ኅዳር 29/1947 (እአአ) በተካሄደው በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ቀርቦ ድምጽ እንዲሰጥበት ተደረገ።

በወቅቱ የጉባዔው ሰብሳቢ የነበሩት ኦስቫልዶ አራንሃ የፍልስጤም ልዩ ኮሚቴ ያቀረበው የውሳኔ ሃሳብ "በ33 ድጋፍ፣ በ13 ተቃውሞ እና በ10 ድምጸ ተአቅቦ" ተቀባይነት ማግኘቱን በማሳወቅ ነበር ውጤቱን ይፋ ያደረጉት።

አሜሪካ እና ሶቪየት ኅብረትን ጨምሮ አብዛኞቹ የአውሮፓ እና የላቲን አሜሪካ አገራት ፍልስጤም ለሁለት ተከፍላ የአይሁዶች እና የአረቦች አገራት እንዲመሠረቱ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

ግብፅን ጨምሮ የአረብ አገራት ሃሳቡን ውድቅ አደረጉ። ኢትዮጵያ፣ ብሪታኒያ እና ቻይናን ጨምሮ 10 አገራት ድምጸ ተአቅቦ ማድረግን መረጡ።

ውሳኔው በአይሁዶች ዘንድ ታላቅ ፈንጠዝያን የፈጠረ ነበር። ክፉኛ በተበሳጩት በአረቦች ዘንድ ግን ውሳኔው የሚዋጥላቸው አልነበረም።

ይህ ውሳኔም ቴል አቪቭ በሚገኘው የሥነ ጥበብ ሙዚየም ውስጥ ግንቦት 14/1948 ለተካሄደው የእስራኤል ምሥረታ ምክንያት ሆነ።

በዕለቱ ጠዋት 5 ሰዓት ላይ የብሪታኒያ የሩብ ክፍለ ዘመን አገዛዝ ተጠናቆ የአገሪቱ ወታደሮች ፍልስጤምን ለቀው ወጡ።

ከአምስት ሰዓታት በኋላ ደግሞ የእስራኤል የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ቤን-ጎሪዮን እስራኤል በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ የአይሁዳውን አገር ሆና መመሥረቷን በይፋ አወጁ።

ይህም ዕለት ለፍልስጤማውያን የ'ናቅባ' ወይም የጥፋት ቀን መጀመሪያ ሆነ። ተከትሎም አብዛኛዎቹ ፍልስጤማውያን ከመኖሪያ ቤታቸው ለመባረር ወይም ለመሸሻቸው የመጀመሪያው ምክንያት እንደሆነ ይታሰባል።

እነሆ ከሰባ አምስት ዓመታት በኋላ እስራኤል በወታደራዊ እና በቴክኖሎጂ አቅሟ ከዓለማችን ታላላቅ ኃያላን አገራት አንዷ ለመሆን ስትበቃ፤ ፍልስጤማውያን አሁንም ዓለም አቀፍ እውቅና ለማግኘት በመታገል ላይ ናቸው።

በዚህ ሂደት ውስጥ አካባቢው በጎረቤት አገራት መካከል የሚደረግ ተደጋጋሚ ጦርነት የማያጣው፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሞቱበት እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ስደተኞች ያሉበት ሆኗል።