የእስራኤል ፕሬዝዳንት እንዲሆን ተጠይቆ የነበረው ታዋቂው የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አንስታይን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩሲያ ውስጥ የተወለደው ብሪታንያዊ ቻይም ዌይዝማን (1874-1952) በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነ የባዮኬሚስትሪ ሊቅ ነበር።
የእሱ ግኝት በአውሮፓውያኑ 1910ዎቹ ውስጥ ስትራቴጂካዊ ወታደራዊ አገልግሎት ለነበረው የአሴቶን ምርት በጣም ወሳኝ ነበረ።
በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በዩናይትድ ኪንግደም በሰፊው ጥቅም ላይ የዋለውን ፈንጂ ለማምረት አገለግሏል።
የዊዝማን የፖለቲካ ሕይወትም የበለጠ ልዩ ነበር።
በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ብቅ ያለው እና በፍልስጤም የአይሁድ መንግሥት መመሥረትን የሚደግፍ ብሔራዊ ንቅናቄ የጽዮናዊነት መሪዎች መካከል አንዱ ነበሩ።
በአውሮፓውያኑ 1947 ከሆሎኮስት አስከፊ እልቂት በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በብሪታኒያ አገዛዝ ስር የነበረችውን ፍልስጤምን በሁለት ግዛቶች እንድትከፈል ውሳኔ አሳለፈ።
ምንም እንኳ ከ140 በላይ አገራት ፍልስጤምን እንደ አገር እውቅና ቢሰጧትም እስካሁን ድረስ ግን አገር ሆና አልተመሠረተችም።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በሚቀጥለው የመስከረም ወር በሚካሄድበት ወቅት አንዳንድ አገራት ለፍልስጤም መንግሥት እውቅና እንደሚሰጡ በመናገራቸው ይህ ቁጥር ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል።
በአንፃሩ እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1948 ነፃነቷን ያወጀች ሲሆን፣ በ1949 ዌይዝማን ለጽዮናዊነት ዓላማ ለነበረው ቁርጠኝነት እና ተሳትፎ የአዲሲቷ አገር ፕሬዝዳንት ሆኖ ተመረጠ።
እስራኤል ፓርላሜንታዊ ሥርዓትን ስለምትከተል እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱን ሥልጣን በበላይነት ስለሚይዝ የተሰጠው ሥልጣን ከውሳኔ ሰጪነት ይልቅ የበለጠ ተምሳሌታዊ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዌዝማን በ77 ዓመቱ በአውሮፓውያኑ 1952 ሲሞት አደሲቷ አገር እስራኤል ሌላ አዲስ ፕሬዝዳንት ያስፈልጋታል።
የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለቦታው ይመጥናሉ ያላቸውን ታዋቂ እና ወደ እስራኤል ስደተኞች እንዲመጡ የሚያበረታቱ አይሁዶችን ስም ዘረዘረ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ቤን ጉርዮን መንግሥት ወዲያውኑ በጣም ታዋቂ በሆነው ሳይንቲስት ላይ ዓይኑን በማሳረፍ ለፕሬዝዳንትነት ሹመት አጨው።
"ያስደስተኛልም፤ ያሳፍረኛልም"
በዩናይትድ ስቴትስ የእስራኤል አምባሳደር አባ ኢባን ለእስራኤል ፕሬዝዳንተንት የታጨውን አልበርት አንስታይንን እንዲያነጋግር ተደረገ።
ጀርመናዊው የፊዚክስ ሊቅ አዶልፍ ሂትለር ሥልጣን በያዘበት እና በአገሪቱ የአይሁዶች ስደት ከጀመረበት ከ1933 ጀምሮ በአሜሪካ ውስጥ ይኖር ነበር።
ኢባን፣ የእስራኤልን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤን ጉርዮንን ወክሎ ለአንስታይን ደብዳቤ ጻፈ።
"እስራኤል በመልከዓ ምድራዊ ሁኔታዋ ትንሽ ግዛት ነች" ይላል በደብዳቤው። አክሎም "ነገር ግን የአይሁድ ሕዝቦች ጥንትም ሆነ ዛሬ ጥልቅ መንፈሳዊ እና ባህላዊ ማንነታቸውን በልባቸው እና በአእምሯቸው ስለመሠረቱ ታላቅ ነገርን ሊያሳኩ ይችላሉ።"
አምባሳደሩ በተጨማሪም አንስታይን የሳይንስ ሙያውን መተው እንደሌለበት አፅንዖት ሰጥቷል። ነገር ግን ከሚኖርበት እና የሚያስተምርበት ዩኒቨርስቲ ከሚገኝበት ከኒው ጀርሲ ወደ እስራኤል መሄድ ይኖርበታል።
በወቅቱ የ73 ዓመት አዛውንት የነበረው አንስታይን ምላሽ የሰጠው በበዛ ትህትና ነው።
ምንም እንኳ በግብዣው የተደሰተ ቢመስልም፣ ጥሪውን ተቀብሎ መሄድ አልፈለገም።
በኢየሩሳሌም በሚገኘው የሂብሩ ዩኒቨርስቲ የአንስታይን መዝገብ ቤት ኃላፊ የሆኑት ዘዬቭ ሮዝንክራንዝ፣ የፊዚክስ ሊቃውንት ደብዳቤዎችን እና የግል ፎቶግራፎችን በያዘው 'አንስታይን ስክራፕቡክ' በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ስለሰጠው ምላሽ አስፍሯል።
ታዋቂው ሊቅ አንስታይን እስራኤልን የፐሬዝዳንትነት ሥልጣን እንዲይዝ የቀረበለትን ጥያቄ ለቦታው የሚያስፈልጉ ክህሎቶች እንደሌሉት በመግለጽ ውድቅ ማድረጉን አስፍሯል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንስታይን "የእስራኤል መንግሥት ባቀረበልኝ ግብዣ የላቀ ደስታ ተሰምቶኛል።በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ መቀበል ባለመቻሌ አዝኛለሁ፤ አፍራለሁም" ሲል መለሰ።
"በሕይወቴ በሙሉ ተጨባጭ ጉዳዮች ላይ አትኩሬ ሠርቻለሁ፤ ስለዚህ ከሰዎች ጋር በትክክል የመገናኘት እና ኃላፊነት በሚጠይቁ ቦታዎች ላይ ለመሥራት ተፈጥሯዊ ችሎታ እና ልምድ የለኝም።
"በእነዚህ ምክንያቶች ብቻ በዚህ ከፍተኛ የሥልጣን ቦታ ኃላፊነቴን ለመወጣት ብቁ አይደለሁም።
"በዓለም አገራት መካከል ያለንን አደገኛ ቦታ ሙሉ በሙሉ ካወቅኩበት ጊዜ ጀምሮ፣ ከአይሁዶች ጋር ያለኝ ግንኙነት በጣም ጠንካራ ትስስር ያለው በመሆኑ፣ በሚፈጸሙት ሁኔታዎች የበለጠ ተበሳጭቻለሁ።"
በሳይንቲስቱ ላይ በርካታ መጽሐፎች የጻፈችው አሊስ ካላፕሪስ እንዳለችው ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤን ጎሪዮን እምቢ በማለቱ እፎይታ ተሰምቷቸዋል።
በአንስታይን ኢንሳይክሎፔዲያ ላይ "ከሕሊናው ጋር የሚቃረኑ ፖሊሲዎችን በተመለከተ አንስታይን ባለው ግልጽነት የተነሳ ፈርቼ ነበር" ሲሉ ጽፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጽሕፈት ቤታቸው ኃላፊ ይትዛክ ናቮን (ከ1978 እስከ 1983 የእስራኤል ፕሬዚዳንት ሆነው ላገለገሉት) "አዎ ካለ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ንገረኝ" በማለት አዝዘዋቸው እንደነበር ተጽፏል።
"ሹመቱን መስጠት ነበረብኝ፤ ምክንያቱም አለመስጠት የማይቻል ነበር። እሱ ከተቀበለ ግን ችግር ይገጥመናል።"
አንስታይን እና እስራኤል
አንስታይን ሥልጣኑን አልተቀበለም ማለት፣ለእስራኤል ፖለቲካ ደንታ ቢስ ነበር ማለት አይደለም፤እንደውም በተቃራኒው ነው።
የታሪክ ባለሙያው ማይክል ጌህርማን "አንስታይን የጽዮናዊነት እንቅስቃሴ አባል ነበር።ከ1921 ጀምሮ ከዊዝማን ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበረው፤ የጽዮናዊነትን ግራ ክንፍ በመወከል በፍልስጤም ላሉ አረቦች እና አይሁዶች ብሔራዊ መብት የሚሰጥ የሁለትዮሽ መንግሥት መፈጠርን የሚደግፍ ነው" በማለት ያብራራሉ።
አሁንም የአንስታይን የደብዳቤ ልውውጥ ይህንን እንድንረዳ ያግዘናል።
በአውሮፓውያኑ 1947 ከሕንድ ከነፃነት በኋላ ሳይንቲስቱ ለአዲሱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለጃዋሃርላል ኔህሩ ደብዳቤ ፃፈ።
የሕንድ ስኬትን አድንቆ በጽዮናዊነት ላይ ያለውን አቋም "የጽዮናውያንን ጉዳይ ተቀብያለሁ፤ ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ የሆነ ስህተትን ለማስተካከል መንገድ ስላየሁ ነው" ሲል በግልጽ ተናግሯል።
በሚቀጥለው ዓመት እስራኤል ስትመሠረት ሳይንቲስቱ ከብዙ አሥርተ ዓመታት የጽዮናውያን ትግል በኋላ እርካታ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል።
ነገር ግን ይበልጥ አክራሪ በሆነው የእስራኤል ሕዝብ የሚፈጸመውን በደል አውግዟል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በ1948 መገባደጃ ላይ እሱ እና ሌሎች የአይሁድ ምሁራን ፖለቲከኛ ሜናሂም ቤጊን ወደ አገሪቱ ያደረጉትን ጉብኝት በመተቸት ለኒው ዮርክ ታይምስ ግልጽ ደብዳቤ ጽፈው ነበር።
ቤጊን በቅድመ እስራኤል ዘመን ፍልስጤማውያን እና እንግሊዛውያን ላይ በሚፈጽመው የሽብር ጥቃቶች የሚታወቀው ኢርጉን የተባለው የጽዮናውያን ደጋፊ ድርጅት መሪ ነበር።
በዚያው ዓመት የኢርጉን ቡድን በኢየሩሳሌም አቅራቢያ በምትገኘው የዴይር ያሲን መንደር ከ100 የሚበልጡ የፍልስጤም ሰላማዊ ወንዶችን፣ ሴቶችን እና ሕጻናትን ጨፈጨፈ።
ብዙም ሳይቆይ ድርጅቱ ሄሩት (በዕብራይስጥ "ነጻነት" ማለት ነው) የሚል አዲስ ፓርቲ አቋቋመ።
አንስታይን ለኒው ዮርክ ታይምስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ "የዚህ ፓርቲ መሪ ሜናሂም ቤጊን ወደ አሜሪካ ያደረገው ጉብኝት በእስራኤል በሚካሄደው ምርጫ የአሜሪካን ድጋፍ እንደሚያገኝ በመገመት የተሰላ መሆኑ ግልጽ ነው።
ደብዳቤውን የጻፉት ምሁራን በመጀመሪያው አንቀጽ ላይ ስለ ሄሩት ፓርቲ ያላቸውን አመለካከት በግልፅ አስቀምጠዋል።
"በአደረጃጀቱ፣ በአሠራሩ፣ በፖለቲካዊ ፍልስፍናው እና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ለናዚ እና ለፋሽስት ፓርቲዎች ይቀርባል።"
በ2024 የብራዚል የግራ ክንፍ ፖለቲካ ደጋፊዎች የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ከሐማስ ጋር የምታካሄደውን ጦርነት ከሆሎኮስት ጋር ካነፃፀሩ በኋላ ይህንን ደብዳቤ በማኅበራዊ ሚዲያዎቻቸው ላይ ለቅቀውታል።
ደብዳቤው ከአውድ ውጪ ጥቅም ላይ ሲውል ሳይንቲስቱ የእስራኤል ተቃዋሚ መሆኑን ሊጠቁም ይችላል።
ብሪታኒያዊው የታሪክ ምሁር ሪቻርድ ክሮካት 'አንስታይን ኤንድ ዘ ቴዌንቲንዝ ሴንቸሪ ፖለቲክስ' በተባለው መጽሐፋቸው ላይ "አንስታይን የራሳቸውን አጀንዳ ለመደገፍ በሚጥሩ ዘንድ የጽዮናዊነት እና የእስራኤል መንግሥት ተቺ እና ደጋፊ ሆኖ ተስሏል" ብለዋል።
ለክሮካት፣ሳይንቲስቱ የእስራኤል መንግሥት ምን መምሰል እንዳለባት በሚያስቀምጣቸው መሠረታዊ እሳቤዎች የተመሰረተው በሰፋፊ ማዕቀፎች ላይ ባለው ቁርጠኝነት ነው።
"ከሁሉም በላይ ብሔርተኝነት ይጠላ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊነትን ይደግፍ ነበር።ይህም ሁልጊዜ ለጽዮናዊነቱ እና ለእስራኤል ያለውን አቋም ላይ እንደ ልጓም በመሆን ያገለግለው ነበር" ሲሉ አብራርተዋል።
ይህ እአአ በ1952 የአገሪቱ ፕሬዝዳንት እንዲሆን የተጋበዘው አንስታይን ነበር።
የታሪክ ባለሙያው ጌህርማን ከ1948-1949 እስራኤል ከአረብ ሊግ ጋር ተዋግታ ለወደፊቷ ፍልስጤም የታቀደውን መሬት መውሰዷን በመጥቀስም "ዓላማው ከጥቂት ዓመታት በፊት ከደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ለወጣችው ለአዲሲቷ አገር ዓለም አቀፍ እውቅና ማስገኘት ይሆናል" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"ከዳተኞች"
የታሪክ ምሁሩ ሚሼል ጌህርማን ምንም እንኳን በእስራኤል ውስጥ የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት የበለጠ ተምሳሌታዊ ተግባር ያለው ቢሆንም "እጅግ በጣም ፖለቲካዊም ነው"ይላሉ።
"አንስታይን የተጋበዘው አይሁዳዊ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከጽዮናዊነት እንቅስቃሴ እና የእስራኤልን መፈጠር በመደገፍ ሂደት ወቅት በነበረው ፖለቲካዊ ተሳትፎ ነው" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ሌሎች ታዋቂ አይሁዳውን እስራኤልን እንዲወክሉ ተጋብዘው እንደነበር በመግለጽም "በተምሳሌታዊ ቦታ የአገሪቱን ገጽታ ለማሻሻል በማሰብ" እንደነበር ያስታውሳሉ።
በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺሞን ፔሬዝ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ ደራሲው አሞስ ኦዝ ወደ ፖለቲካ መግባት እንዳለበት ተከራክረዋል።
እአአ በ1952 አንስታይን አባል የሆነበት ብሪቲ ሻሎም አነስተኛ ተጽዕኖ ቢኖረውም በጭራሽ የተገለለ አልነበረም ሲሉ ጌህርማን ያስረዳሉ።
አባላቶቹ እንደ ፈላስፎች ሃና አረንት፣ማርቲን ቡበር እና ጌርሾም ሾለም ያሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበሩ እና የተደነቁ ምሁራን ነበሩ።
ሂብሩ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ጄሩሳሌምን የመሠረቱት የብሪቲ ሻሎም ተሳታፊዎች ነበሩ።
ዛሬ ግን የቡድኑ አባላት አሁን ባለው የእስራኤል መንግሥት እንደ "ከሃዲ" ይቆጠራሉ ሲሉ ጌህርማን ይናገራሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አስተዳደር ለሁለት አገራት መፍትሄ መሻትን ለመሳሰሉት ተቃራኒ አስተያየቶች ቦታ የለውም ሲሉም አክለዋል።
"የዘመናችን አንስታይን ማን ሊሆን ይችላል? ያ ሰው ሥልጣኑን ቢቀበል ብላችሁ አስቡት። በኬሚስትሪ የኖቤል ተሸላሚ እና የፍልስጤም ግዛቶችን ወረራ እና ዛሬ በጋዛ እየሆነ ያለውን የሚተቸው አዳ ዮናት ይቀበል ይሆን? አይመስለኝም።"
አንስታይን የቀረበለትን የፕሬዝዳንትነት ሥልጣን ሹመት ውድቅ ስላደረገ፣ በዚያ ዓመት የእስራኤል ፕሬዝዳንት የሆነው የታሪክ ምሁሩ ይስሃቅ ቤን ዝቪ ነው።
አሜሪካን የጎበኘው እና በሳይንቲስቱ የተተቸው ፖለቲከኛው ሚናሂም ቤጊን በእስራኤል ውስጥ ያለው ተጽዕኖ እየጨመረ መጥቷል።
ሄሩት በቀጣዮቹ አስርት ዓመታት ውስጥ የሌበር ፓርቲ ሥልጣን በያዘበት በቅት ዋነኛው የእስራኤል ወግ አጥባቂ ፓርቲ ነበር።
ቤጊን እአአ በ1977 የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታን ያገኘ ሲሆን፣ እስከ 1983 ድረስ በሥልጣን ቆይቷል።
ከአምስት ዓመት በኋላ ሄሩት በሌላኛው የቀኝ ክንፍ ፓርቲ ሊኩድ ተገፋ።
እአአ ከ2006 ጀምሮ መሪው ኔታንያሁ በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ ረዥም ዓመት ሥልጣን ላይ የቆዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
በአጠቃላይ በሥልጣን ላይ የቆዩበት ዘመናቸው ሲሰላ ወደ 18 ዓመታት ሊደርስ ይችላል።















