የሩሲያ ዩክሬንን ጦርነት የተቀላቀሉ ደቡብ አፍሪካዊያን መውጫ ማጣታቸውን ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ቅጥረኛ ወታደራዊ ኃይሎችን ከተቀላቀሉ 17 ዜጎቹ የአደጋ ጊዜ ጥሪ እንደደረሰው የደቡብ አፍሪካ መንግሥት አስታወቀ።
ከ20 እስከ 39 ዓመት ይሆናሉ የተባሉት ደቡብ አፍሪካዊያኑ በዩክሬን ጦርነት ክፉኛ በተጎዳው ዶንባስ ክልል ይገኛሉ።
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ቃል አቀባይ እንዳሉት ስሪል ራማፎሳ "ወጣቶቹ ቅጥረኛ ወታደር ለመሆን እንዲመለመሉ የተደረጉበት ሁኔታ" እንዲመረመር ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
መግለጫው ደቡብ አፍሪካዊያኑ የግጭቱን የትኛውን ወገን ወግነው እየተዋጉ እንደሆነ አልጠቀሰም።
በደቡብ አፍሪካ መንግሥት ካልፈቀደው ውጭ እንደ ቅጥረኛ ወታደር ወይም ተዋጊ ለሌላ አገር መንግሥት መዋጋት ሕገ ወጥ ነው።
የአገሪቱ መንግሥት ወጣቶቹ በሚያማልል የሥራ ቅጥር ተታልለው የቅጥር ውትድርና ኃይሉን እንደተቀላቀሉ ጠቅሷል።
ቃል አቀባዩ ቪንሰንት ማግወይና አክለው የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ተዋጊ ዜጎችን ለመመለስ "የዲፕሎማሲ መንገዶችን" ተጠቅሞ እየሰራ ነው ብለዋል።
ቃለ አቀባዩ 16ቱ ቅጥረኛ ተዋጊዎች ከዋዙሉ ናታል አካባቢ ሲሆኑ አንዱ ደግሞ ከምሥራቅ ኬፕ መሄዱን ጨምረው ተናግረዋል።
"ፕሬዝዳንት ራማፎሳ እና የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ከውጭ አገር ወታደራዊ ተቋማት ጋር የሚሰሩ አካላት ወጣቶች ላይ የሚያደርጉትን ብዝበዛ ያወግዛሉ" ብለዋል።
በደቡብ አፍሪካ የሥራ አጦች ቁጥር ከ30 በመቶ በላይ ሲሆን እነዚህ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ለሐሰተኛ የሥራ ምልመላ ተጋላጮች መሆናቸውን ተንታኞች ይናገራሉ።
ቢቢሲ ሩሲያ በአፍሪካ ያላትን ተፅዕኖ ለማስፋት እየሰራች መሆኑን ማስረጃ አግኝቷል።
በምዕራብ አፍሪካ ይንቀሳቀስ የነበረው ዋግነር ቡድን መሪ ከተገደለ በኋላ በሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር የሚመራ አፍሪካ ኮርፕስ የተባለ የቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን ሙሉ ለሙሉ ተክቶታል።
ባለፈው ነሐሴ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ለወጣት ሴቶች በዋናነት ወደ ሩሲያ እና ሌሎች የውጭ አገራት በማኅበራዊ የትስስር ገፆች በሚደረጉ የሥራ ምልመላዎች ላይ ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።
የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ ወጣት ሴቶች ወደ ሩሲያ አላቡጋ ልዩ የኢኮኖሚ ���ን ተወስደው ድሮን ፋብሪካ ውስጥ እንዲሰሩ መደረጉን አረጋግጧል።
አንድ ሺህ ይጠጋሉ ተብሎ የሚገመቱ ሴቶች ከመላው አፍሪካ እና ደቡብ እስያ ተመልምለው በጦር መሣሪያ ፋብሪካ እንዲሰሩ ተደርገዋል።
ባለፈው መስከረም የኬንያ መንግሥት ሩሲያ ሥራ እንቀጥራለን በሚል ግን ወደ ዩክሬን ሊዘዋወሩ የነበሩ 20 ሰዎችን ማትረፉን አስታውቋል።
ዩክሬን ከዚህ ቀደም የሶማሊያ፣ ሴራ ሊዮን፣ ቶጎ፣ ኩባ እና ሲሪላንካ የመሰሉ የበርካታ አገራት ዜጎችን በጦር እስረኞች ማቆያ እንደሚገኙ ገልፃለች።
አገሪቱ አፍሪካዊያንን ጨምሮ በጦርነቱ የሚዋጉ የውጭ አገር ዜጎችን ለመመልመል ሙከራ ማድረጓን ተከትሎ ትችት ገጥሟትም ነበር።















