በሀዋሳ የ14 ዓመት ታዳጊ 'መጠለፏ' ተነገረ

እገታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሀዋሳ ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ሜላት መሀመድ ትላንት ሰኔ 5/2015 ዓ.ም ቀትር ላይ በሁለት ተሽከርካሪ በመጡ ግለሰቦች 'መጠለፏን' ቤተሰቧቿ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የ14 ዓመት ከ 8 ወር ታዳጊዋ ሜላት ከትምህርት ቤት ወደ ወደ መኖሪያ ቤቷ በመመለስ ላይ እያለች በሀዋሳ ከተማ ሞኖፖል ተብሎ በሚጠራው አከባቢ “ቤት ልትደርስ ጥቂት ሜትሮች ሲቀራት” በሃይል ታግታ መወሰዷን የሜላት የቅርብ ዘመዶች ገልጸዋል።

የሜላት የአክስት ልጅ የሆነችው ትዕግስት ብስራት ስለሁኔታው ስትገልጸ “እኔና እናቴ ለቅሶ ላይ ስለነበርን [ለሜላት] ቁልፉን አስቀምጠንላት ነበር. . .[ቁልፉን] ከስራ ቦታዬ ወደመኖሪያ ቤት ይዛ እየሄደች ነበር። ከዚያ እንደጥበቃ የሚሰራልኝ ልጅ በግምት 6 ሰዓት ተኩል ይሆናል ደውሎ ‘ሁለት ዳማስ [መኪና] ቆሞ ነበር፣ እየጮኸች ልጅሽን አፍነው አስገቧት’ አለኝ” ስትል ታስረዳለች።

የሜላት እናት ከዓመታት በፊት በማለፋቸው ምክንያት ከሶስት ዓመቷ ጀምሮ ታዳጊዋ ከሷ ቤተሰቦች ጋር እንዳደገች የምትገልጸው ትዕግስት ነገሩ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ ከሌሎች ቤተሰቧቿ ጋር ፍለጋ ላይ እንደሆኑ ጠቅሳለች።

ትዕግስት ሀዋሳ ከተማ ውስጥ አንስተኛ ምግብ ቤት አላት። “[የአጋቾቹን ማንነት] ሳጣራ እኔጋ ምግብ የሚበሉ ልጆች ናቸው። ለሊቱን ሙሉ እየፈለኳቸው ነው። ወደ ቤት አልገባሁም” ስትል ገልጻለች።

ትዕግስት ‘ጠላፊውን’ እንድምታወቀውና ጥሩ ግንኙነት እንደነበራቸው የገለጸች ሲሆን ይህ የምግብ ቤት ደንበኛዋ የተለየ ምንም ነገር እንደማያሳይ ጨምራ ተናግራለች።

ሌላኛው የሜላት የአክስት ልጅ እንዳልካቸው ብስራት ከዚህ በፊት ሜላትን ‘ያስቸግረኛል’ ብላ የተናገረችው ሰው እንደሌለ ገልጿል።

“እኛ ግራ ገብቶኖናል። ማንም ፍንጭ የሚሰጠን አጣን” የሚለው እንዳልካቸው በእንባ ጭምር ቤተሰቡ ጭንቅ ላይ እንዳለ ገልጿል።

ትዕግስት በበኩሏ ጠላፊውእን በተመለከተ ስትናገር ከሜላትና “ከልጆቼ ጋር ያለኝ ነገር ያውቃሉ። ሲናገሯቸው እንኳን በጣም ነው የምቆጣው። አይደፍሩም. . . ሙሉ ቤተሰብ ለቅሶ ላይ ስለነበር አለመኖራችንን አይቶ ነው [ይህንን ያደረገው]” ብላለች።

እንዳልካቸውና ትዕግስት ከፖሊስ ጋር በመሆን ሜላትን እያፈላለጉ እንደሚገኙ ገልጸው ጥሩ ትብብር እየተደረገልን ይገኛል ብለዋል። ሆኖም ቢቢሲ ከሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ክልል ፖሊስ መምሪያዎች መረጃ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም የስልክ ጥሪዎቹ ምላሽ ማግኘት አልቻሉም።

ሜላትን በኃይል ወደ ተሽከርካሪ እንድትገባ ሲደረግ የአካቢው ሰው ሊታደጋት መሞከሩንም ቤተሰቦቿ አመላክተዋል።

“[ሜላት] ስትጮህ ይዟት የጠፋውን መኪና የፊትለፊቱን መስታወት የአከባቢው ሰው ሰብሮበታል። ከዛ በኋላ እየበረረ አመለጠ” ሲል እንደላካቸው ገልጿል።

በሌላ በኩል ትዕግስት የጠለፏትን ሰዎች ማንነት ካጣራች በኃላ መረጃ ለመጠየቅ ወደ የቤተሰቧቻቸው ቤት ቢሄዱም ሊተባበሯት እንዳልቻሉ ገልጻለች።

እንደ ትዕግስት ገለጻ ሜላት ከመጠለፏ አስቀድሞ ከእሷ ጋር የምትማርና ‘የጠላፊው’ ዘመድ ሜላትን አናግራታለች። “እሷም ቤቷ ሄደን አላገኘናትም። ሸሽተዋል” ብላለች።

ትዕግስት “መርዳት የሚችል አካል እንዲረዳኝ በጣም እፈልጋለሁ” ስትል በእንባ ተማጽና ለቢቢሲ ተናግራለች።

ሜላት የተወለደችው ያቤሎ ከተማ ሲሆን ከእናቷ ህልፈት በኃላ ወደ ጉጂ ዞን ዋደራ ሄዳ ዓመታትን ቆይታለች። ከአራት ዓመታት በፊት ወደ ሀዋሳ ከተማ ከቤተሰቦቿ ጋር በማቅናት ትምህርቷን እየተከታተለች ነው።

ጸጋ ከቀናት እገታ በኃላ ወደ ቤተሰቧቿ መቀላቀሏንና አጋቹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋለ ተዘግቧል።