በአሜሪካ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች አቋም ላይ አስደንጋጭ ለውጥ ስላስከተለው ጥቃት እስካሁን የምናውቀው
የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሁለት የብሔራዊ ዘብ አባላት ረቡዕ ዕለት ከዋሽንግተን ዲሲ ዋይት ሐውስ በቅርብ ርቀት በጥይት ተመትተው ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐሙስ ዕለት አንደኛው ሲሞት ሁለተኛው ደግሞ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ጥቃቱን ያደረሰው ተጠርጣሪ አፍጋኒስታናዊ በእስር ላይ ይገኛል።
ለጥቃቱ ምላሽ ለመስጠት ትራምፕ ሌሎች 500 ወታደሮችን ወደ አገሪቱ ዋና ከተማ ጎዳናዎች እንደሚያሰማሩ ተናግረዋል።
በዋይት ሐውስ አቅራቢያ በተፈፀመው የተኩስ ልውውጥ ምን ተከሰተ?
ረቡዕ ከሰዓት በኋላ ሁለት የብሔራዊ ዘብ አባላት በዋሽንግተን ዲሲ መሃል ከተማ በሚገኘው ፋራጋት አደባባይ አቅራቢያ በቅርብ ርቀት ላይ ተኩስ ተከፍቶባቸው ተመትተዋል።
ወታደሮቹ ብዙ የቢሮ ሠራተኞች በምሳ ሰዓት የሚንቀሳቀሱበት በ17ኛው እና 1ኛው ጎዳናዎች ጥግ ላይ ነበሩ።
የዋሽንግተን ከተማ ሜትሮፖሊታን ፖሊስ ረዳት አዛዣ የሆኑት ጄፍ ካሮል ተጠርጣሪው "ከጥግ በኩል መጥቶ" "ወዲያውኑ መተኮስ ጀመረ" ሲሉ ወታደሮቹ "ደፈጣ" እንደተደረገባቸው አክለዋል።
የዋሽንግተን ዲሲ ከንቲባ ሙሪኤል ቦውሰር፣ ክስተቱ የታቀደ ጥቃት እንደነበር ተናግረዋል።
ጥቃቱ የደረሰበት ቦታ ከዋይት ሐውስ በቅርብ ርቀት የሚገኝ መሆኑ በርካታ የሕግ አስከባሪ አካላት ለሁለቱ ተጎጂዎች የሕክምና እርዳታ ለማድረግ እና እና ታጣቂውን ለመያዝ በፍጥነት በቦታው ደርሰው ነበር።
ጥቃት የደረሰባቸው የብሔራዊ ዘብ አባላቱ ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱ በኋላ አንዷ ሕይወቷ አልፏል።
ጥቃቱ ሲፈጸም ትራምፕ ከአሜሪካ የምስጋና በዓል በፊት በፍሎሪዳ በሚገኘው የማር-አ-ላጎ መኖሪያ ቤታቸው ነበሩ፤ በወቅቱ በዋይት ሐውስ አልነበሩም።
የፎቶው ባለመብት, Reuters
ስለ ተጎጂዎቹ ምን እናውቃለን?
ተጎጂዎቹ የ20 ዓመቷ ሳራ ቤክስትሮም እና የ24 ዓመቱ አንድሪው ዎልፍ እንደሆኑ ተገልጿል። ሁለቱም የምዕራብ ቨርጂኒያ ብሔራዊ ዘብ ዩኒፎርም የለበሱ አባላት ናቸው።
ቤክስትሮም፣ ሐሙስ ዕለት ሕይወቷ ማለፉን ትራምፕ ተናግረዋል።
ሌላኛው ተጎጂ ዎልፍ ብዙ ጊዜ ከተተኮሰበት በኋላ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፓም ቦንዲ ለፎክስ ኒውስ እንደተናገሩት ሳራ ቤክስትሮም፣ 'በታንክስጊቪንግ' በዓል ወቅት ፈቃደኛ ሆና በአገሪቱ ዋና ከተማ ተሰማርታለች።
"እሷም እንደ ብዙዎቹ [ብሔራዊ] ዘቦች ወንዶችና ሴቶች ሁሉ ሌሎች ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ቤት እንዲውሉ በፈቃደኝነት ትሰራ ነበር" ሲሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጓ ተናግረዋል።
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ስለ ተጠርጣሪው ምን እናውቃለን?
የአገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት ተጠርጣሪው ራህማኑላህ ላካንዋል የተባለ "ከአፍጋኒስታን የመጣ ወንጀለኛ" ሲል ገልጾታል።
በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት ተጠርጣሪው አራት ጊዜ በጥይት እንደተመታ የጸጥታ አካላት ምንጮች መናገራቸውን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘግቧል።
የ29 ዓመቱ ላካንዋል ለመተባበር ፈቃደኛ አለመሆኑን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
እኤአ በ2021 ወደ አሜሪካ እንደመጣ የሚነገረው ላካንዋል፤ ከሚስቱ እና ከአምስት ልጆቹ ጋር በሌላኛው የአገሪቱ ክፍል በዋሽንግተን ግዛት ይኖር ነበር።
የፎቶው ባለመብት, Reuters
ወደ አሜሪካ እንዴት መጣ?
ላካንዋል እአአ በመስከረም 2021 ወደ አሜሪካ የመጣው በጆ ባይደን ፕሬዝዳንትነት ጊዜ በነበረው "ኦፕሬሽን አላይ ዌልካም" በተሰኘው አሰራር እንደነበር ተዘግቧል።
አሜሪካ ለ20 ዓመታት ውጊያ ስታካሂድባት ከቆየችው አፍጋኒስታን በ2021 ቀውስ በተሞላበት ሁኔታ መውጣቷን ተከትሎ፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አፍጋኒስታናውያን በዚህ ልዩ የስደተኞች ጥበቃ ፕሮግራም ወደ አገሪቱ ገብተዋል።
ይህ የሆነው የአሜሪካ ወታደሮች ከአፍጋኒስታን መውጣታቸውን ተከትሎ በተከሰተው ሁከት ወቅት ነው። ታሊባን አገሪቱን መልሶ ሲቆጣጠር፣ ከአሜሪካ ጋር ሲተባበሩ በነበሩ አፍጋኒስታናውያን ላይ የበቀል እርምጃ እንደሚወሰድ ስጋት ነበር።
የኮንግረሱ የምርምር አገልግሎት 77,000 የሚሆኑ አፍጋኒስታናውያን ከአሜሪካ መውጣት በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል በልዩ የኢሚግሬሽን ጥበቃ ስር ወደ አገሪቱ እንደገቡ ገምቷል።
ላካንዋል በአፍጋኒስታን ከአሜሪካ ወታደሮች ጋር ግንኙነት እንደነበረው የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ካሽ ፓቴል ተናግረዋል። የሲአይኤ ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍ ከስለላ ድርጅቱ ጋር ሰርቷል ሲሉ ተናግረዋል።
ላካንዋል እአአ በ2024 ያቀረበው የጥገኝነት ጥያቄ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ተቀባይነት አግኝቷል ሲሉ አንድ ባለሥልጣን ለሲቢኤስ ተናግረዋል።
በምን ወንጀሎች ይከሰሳል?
የዋሽንግተን ዲሲ የአሜሪካ ጠበቃ ጄኒን ፒሮ እንደተናገሩት በተጠርጣሪው ላይ የተሰነዘሩት የመጀመሪያ የጥቃት ክሶች ወደ መጀመሪያ ደረጃ ግድያ እንደሚለወጡ ተናግረዋል።
መጀመሪያ ላይ አስተዳደሩ ላካንዋል የታጠቁ የፀጥታ ኃይሎችን ለመግደል በማሰብ በሦስት የጥቃት ክሶች እና በዓመፅ ወንጀል ወቅት የጦር መሳሪያ በመያዝ እንደሚከሰስ አስታውቋል።
"አስቀድሞ የታሰበ ግድያ ነው። ምን እንደሚመጣ የማያውቁ ሰዎችን ለማጥቃት ሽጉጥ ይዞ አድፍጦ ነበር" ሲሉ ፒሮ አርብ ዕለት ለ'ፎክስ ኤንድ ፍሬንድስ' ተናግረዋል። "ግድያ ነው፣ እና አሁን የምንመለከተው እንደ ግድያ ወንጀል ነው።"
የትራምፕ አስተዳደር እንዴት ምላሽ ሰጠ?
ጥቃቱ ከተፈጸመ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ትራምፕ በፓልም ቢች፣ ፍሎሪዳ ውስጥ ከሚገኘው ማር-አ-ላጎ የተንቀሳቃሽ ምስል መልዕክት ለቅቀዋል።
ጥቃቱን "የሽብር ተግባር" እና "በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል" ሲሉ ገልጸውታል።
ትራምፕ አሁን ካሉት ወደ 2,200 የሚጠጉ ወታደሮች በተጨማሪ፤ ሌላ 500 ብሔራዊ ዘብ አባላትን ወደ ዋሽንግተን ዲሲ እንደሚያሰማሩ ተናግረዋል።
የብሔራዊ ዘብ ወታደሮች እንደ ጦር ወታደሮች ሆነው ለማገልገል ሊሰማሩ የሚችሉ የተጠባባቂ ኃይል ናቸው፤ ነገር ግን ሕጉን ማስከበር ወይም ማሰር ስለማይችሉ የተወሰነ የሥልጣን ነጻነት ብቻ አላቸው።
ትራምፕ በነሐሴ ወር በአገሪቱ ዋና ከተማ ውስጥ "ከቁጥጥር ውጪ" ብለው የጠሩትን ወንጀል ለመዋጋት ወታደሮችን አሰማርተዋል።
ወታደሮቹ ከተላኩ በኋላ በአገሪቱ ዋና ከተማ ውስጥ ያለው አጠቃላይ ወንጀል ቀንሷል፤ ይህም ትራምፕ ወታደሮቹ በጎዳና ላይ በመሰማራታቸው እንደሆነ ይገልጻሉ።
የትራምፕ አስተዳደር የተጠርጣሪውን ማንነት አጉልቶ በማሳየት አሜሪካ ከአፍጋኒስታን እና ከሌሎች አገራት ወደ አሜሪካ የሚመጡ ስደተኞችን በተመለከተ ያለውን አካሄድ ለማጠናከር የታለሙ የተለያዩ እርምጃዎችን ይፋ አድርጓል።
ጥቃቱ በተፈጸመበት ረቡዕ ዕለት ከአፍጋኒስታን የመጡ ሁሉንም የስደተኝነት ጥያቄዎች ታግደዋል።
በማግስቱ፣ የአሜሪካ የዜግነት እና የኢሚግሬሽን አገልግሎት ከ19 አገሮች ወደ አሜሪካ ለተሰደዱ ግለሰቦች የተሰጠውን የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ እንደገና እንደሚመረምር አስታውቋል።
ትራምፕም ከዚህ በፊት ያላደጉ እና ታዳጊ አገሮችን ለመግለጽ ጥቅም ላይ የዋለውን ቃል በመጠቀም ከሁሉም "የሦስተኛ ዓለም አገሮች" ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያደርግ "ዘላቂ ዕገዳ" ለመጣል ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የዜግነት እና የኢሚግሬሽን አገልግሎት ኃላፊ ጆሴፍ ኤድሎው አርብ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ባጋሩት ጽሑፍ፤ የትራምፕ አስተዳደር "እያንዳንዱ የውጭ ዜጋ በተቻለ መጠን ከፍተኛውን ደረጃ እስኪመረመር እና እስኪጣራ ድረስ ከሁሉም አገራት ለሚመጡ የጥገኝነት ውሳኔዎችን ያቆማል" ብለዋል።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም