አሜሪካ ከየትኛውም አገር ዜጎች የሚቀርቡ የጥገኝነት ጥያቄዎችን ሙሉ በሙሉ አገደች

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በአሜሪካ የብሔራዊ ዘብ አባላት ላይ በደረሰው ጥቃት ምክንያት የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የጥገኝነት ጥያቄዎችን በአጠቃላይ ማገዱን አስታወቀ።

የአሜሪካ የዜግነት እና ስደተኝነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጆሴፍ ኤልዶው "ሁሉም ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ ተገቢው ምርመራ እስከሚካሄድ ድረስ እገዳው ይቆያል" ብለዋል።

ትራምፕ "የሦስተኛው ዓለም አገራት" ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያደርግ "ዘላቂ ዕገዳ" ለመጣል ዕቅድ እንዳላቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ የተላለፈ ውሳኔ ነው።

የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ የተሰማው ባለፈው ረቡዕ አንድ አፍጋኒስታናዊ ስደተኛ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ሁለት የብሔራዊ ዘብ አባላት ላይ ተኩሶ ክፉኛ ካቆሰላቸው እና የአንደኛዋ ሕይወት ካለፈ በኋላ ነው።

መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ መንግሥት ከአፍጋኒስታናውያን የሚቀርቡ የጥገኝነት ጥያቄዎችን መቀበል አቁሞ ነበር። አሁን ደግሞ የአገር ውስጥ ደኅንነት መስሪያ ቤት ከየትኛውም አገር የስደተኞችን ጥያቄ እንዳይቀበል ትዕዛዝ ተላልፎለታል።

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ እንደዘገበው፤ የጥገኝነት ጥያቄዎች ላይ የሚካሄደው ምርመራ የቀሚጥል ቢሆንም ውሳኔ ግን አይሰጥም።

ጥቃቱን ተከትሎ ትራምፕ ለ19 የውጭ አገር ዜጎች የተሰጡ የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃዶች እንደሚመረመሩ አዝዘዋል።

ትራምፕ የትኞቹ አገራት ላይ እገዳ እንደሚጥሉ በይፋ ባይናገሩም ከተባበሩት መንግሥታት ተቃውሞ የቀረበበት ይህ ውሳኔያቸው ሕጋዊ መሰናክሎች ይገጥሙታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ አሜሪካ የምትቀበላቸውን ስደተኞች ቁጥር ከመገደባቸውም ባሻገር የአገሪቱ ግዛቶች የሚያስተናግዷቸውን የጥገኝነት ጥያቄዎችም ውስን ማድረግ ይፈልጋሉ።

ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው፤ "አሜሪካ ሙሉ ለሙሉ እንድታገግም ከሁሉም የሦስተኛ ዓለም አገራት የሚመጡ ስደተኞች ላይ ቋሚ እገዳ እጥላለሁ" ብለዋል።

በተጨማሪም "ለአሜሪካ የማይጠቅሙ ወይም አገሪቱን መውደድ የማይችሉ" ሰዎችን ከአሜሪካ እንዲወጡ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

"ለዚህ ችግር የዳረገን የአሜሪካ ማኅበራዊ ውቅር ነው። ሚኒሶታን በሺዎች የሚቆጠሩ ሶማሌዎች ተቆጣጥረዋታል" ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

ትራምፕ የአሜሪካ ዜጋ ላልሆኑ ስደተኞች የሚሰጠውን ሁሉንም የፌደራል መንግሥት ጥቅማ ጥቅም እንደሚያስቆሙ አስታውቀዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ኤርትራን ጨምሮ ከ19 አገራት ወደ አሜሪካ ለገቡ ስደተኞች የተሰጡ የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃዶች ላይ በድጋሚ ምርመራ እንደሚያደርግ ገልጿል።

ትራምፕ 'የሦስተኛው ዓለም አገራት' የሚሉት የትኞቹን እንደሆነ በይፋ ባይገልጹም፤ ከዚህ ቀደም ታዳጊ አገራትን በዚህ ስም መጥራታቸው ይታወሳል።

በ2025 መባቻ አፍጋኒስታንን ጨምሮ በ11 የአፍሪካ እና እስያ አገራት ላይ የጉዞ እገዳ ጥለዋል።

ጥቃት አድርሷል የተባለው ተጠርጣሪ ራሕማኑላህ ላካንዋል በአውሮፓውያኑ 2021 ወደ አሜሪካ የገባው አሜሪካ ከአፍጋኒስታን መውጣቷን ተከትሎ ለአፍጋኒስታን ስደተኞች ልዩ ጥበቃ የሚሰጥ አሠራር ስትዘረጋ ነው። ግለሰቡ የአፍጋኒስታን የደኅንነት አካል የነበረው 'ዜሮ ዩኒት' አባል እንደነበረም ተገልጿል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዋይ ሀውስ የብሔራዊ ዘብ አባላት ላይ የተፈጸመው ጥቃት "ትልቅ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት" መሆኑን ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት፤ አሜሪካ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን መብት የሚያስጠብቁ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን እንድትጠብቅ አሳስቧል።

የአሜሪካ የስደተኞች ጠበቆች ማኅበር ፕሬዝዳንት ጀርሚ ማክኒ እንዳሉት፤ ትራምፕ የደረሰውን ጥቃት "እንደ ሽፋን በመጠቀም" ፀረ ስደተኞች እርምጃ እየወሰዱ ነው።

"እንዲህ ያሉ ክስተቶች የቆዳ ቀለምን ወይም ዜግነትን አይመለከቱም" ብለዋል።