አሜሪካ፤ በብሔራዊ ዘብ አባላት ላይ በደረሰው ጥቃት ምክንያት የአፍጋኒስታናውያንን የስደተኝነት ጥያቄ አገደች

ተሰብስበው የቆሙ የብሔራዊ ዘብ አባላት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በትናንትናው ዕለት በዋይት ሀውስ አቅራቢያ ተሰማርተው የነበሩ ሁለት የብሔራዊ ዘብ ወታደሮች በተከፈተባቸው ተኩስ ለሕይወታቸው አስጊ በሆነ ደረጃ መጎዳታቸውን ተከትሎ፤ የአሜሪካ መንግሥት ከአፍጋኒስታናውያን የሚቀርቡ የስደተኝነት ጥያቄዎችን መቀበል አቆመ።

የአሜሪካ የዜግነት እና ስደተኝነት አገልግሎት፤ ከአፍጋን ተወላጆች የቀረቡ እና በሂደት ላይ የነበሩ የስደተኝነት ጥያቄዎች በሙሉ መታገዳቸውን አስታውቋል። ይህ እገዳ ባለሥልጣናቱ በጥያቄ አቅራቢ አፍጋኒስታናውያን ላይ የሚያካሂዳቸው "የደኅንነት እና የማጣራት" ሥራዎች እስከሚጠናቀቁ ድረስ እንደሚቆይ ተገልጿል።

መሥሪያ ቤቱ በኤክስ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ፤ "የአገራችንን እና የአሜሪካን ሕዝብ ደኅንነት መጠበቅ ብቸኛ ትኩረታችን እና ተልዕኳችን ሆኖ ይቀጥላል" ብሏል።

የአሜሪካ መንግሥት ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው፤ በዋይት ሀውስ አቅራቢያ ተሰማርተው በነበሩት የብሔራዊ ዘብ አባላት ላይ ተኩስ የከፈተው በአውሮፓውያኑ 2021 ወደ አሜሪካ የገባ አፍጋኒስታናዊ እንደሆነ ከተነገረ በኋላ ነው።

ጥቃቱን እየመረመረ ያለው ኤፍቢአይ ዳይሬክተር የሆኑት ካሽ ፓቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ወታደሮቹ "አሰቃቂ በሆነ የአመጻ ድርጊት ጥቃት" እንደደረሰባቸው ተናግረዋል። የዋሽንግተን ከተማ ሜትሮፖሊታን ፖሊስ ረዳት አዛዣ የሆኑት ጄፍ ካሮል በበኩላቸው፤ ተጠርጣሪው "ከጥግ በኩል እንደመጣ" እና "ወዲያውኑ በጦር መሣሪያ መተኮስ መጀመሩን" ገልጸዋል።

ወታደሮቹ "የደፈጣ ጥቃት" እንደደረሰባቸውም አክለዋል። በአቅራቢያ የነበሩ ሌሎች የብሔራዊ ዘብ ወታደሮች የጥይቱን ድምጽ ሰማተው ምላሽ መስጠታቸውንም አብራርተዋል።

"[ሌሎቹ ወታደሮች] ጣልቃ በመግባት፤ ተጠርጣሪው በጥይት ከተመታ በኋላ የሕግ አስከባሪ አካላት በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ እስኪደርሱ መሬት ላይ እንዳለ እንዲቆይ ለማድረግ ችለዋል" ሲሉ ግለሰቡ የተያዘበትን መንገድ አስረድተዋል።

ተጠርጣሪው አራት ጊዜ በጥይት እንደተመታ የጸጥታ አካላት ምንጮች መናገራቸውን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘግቧል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ጥቃቱን "የሽብር ድርጊት" ሲሉ ጠርተውታል። "ከየትኛውም አገር" የመጡ እና አሜሪካ ውስጥ "ሊሆኑ የማይገባቸውን" ስደተኞች በሙሉ ለማባረር እርምጃ እንደሚወስዱ አክለዋል።

አሜሪካ ለ20 ዓመታት ውጊያ ስታካሂድባት ከቆየችው አፍጋኒስታን በ2021 ቀውስ በተሞላበት ሁኔታ መውጣቷን ተከትሎ፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አፍጋኒስታናውያን በልዩ የስደተኞች ጥበቃ ፕሮግራም ወደ አገሪቱ ገብተዋል። ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር የተዘረጋው ይህ አሰራር 'ኦፕሬሽን አላይስ ዌልካም" ይባላል።

መሳሪያ ይዞ የቆመ የጸጥታ አካል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሁኑን ጥቃት በማድረስ የተጠረጠረው የ29 ዓመቱ አፍጋኒስታናዊ ራህማኑላህ ላካንዋንም በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት ወደ አሜሪካ የገባ እንደሆነ በርካታ የሕግ ማስከበር አካላት ምንጮች ለሲቢኤስ ተናግረዋል።

ትራምፕ ከጥቃቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ፤ "በባይደን [አስተዳደር] ሥር ወደ አገራችን የገባ እያንዳንዱ የውጭ አገር ዜጋ በድጋሚ መመርመር አለበት" ብለዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ወደ አሜሪካ በሚገቡ የአፍጋኒስታን ዜጎች ላይ እርምጃ ሲወስድ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ትራምፕ በተያዘው 2025፣ በ12 አገራት ዜጎች ላይ የጉዞ እገዳ በጣሉበት ወቅትም አፍጋኒስታናውያን ተካትተው ነበር።

ልዩ የስደተኝነት ቪዛ ያላቸው አፍጋኒስታናውያን ግን ከዚህ እገዳ ነጻ ተደርገው ነበር። ይህንን ቪዛ ያገኙት፤ ታሊባን በ2021 አፍጋኒስታንን በድጋሚ ሙሉ በሙሉ ከመቆጣጠሩ በፊት ከአሜሪካ ጦር ጋር በቀጥታ ሲሠሩ ለነበሩ የአገሪቱ ዜጎች ናቸው።

ትራምፕ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍጋኒስታናውያን ስደተኞች ከአሜሪካ እንዳይባረሩ ከለላ ሰጥቶ የነበረው ፕሮግራም በ2025 መጀመሪያ እንዲቋረጥ አድርገዋል።

ይህ የጊዜያዊ ከለላ ፕሮግራም፤ የአሜሪካ መንግሥት በጦርነት ምክንያት ወደ አገራቸው መመለስ የማይችሉ ብሎ የመደባቸው ስደተኞች ስራ ፈቃድ እንዲያገኙ የሚያስችል ነበር።