አፍሪካዊቷ አገር ኢስዋቲኒ ከአሜሪካ የሚባረሩ ሰዎችን ለመቀበል ከዋሽንግተን 5.1 ሚሊዮን ዶላር እንደተሰጣት አረጋገጠች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ኢስዋቲኒ መንግሥት፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስደተኞች ላይ እየወሰዱት ባለው ጠንካራ እምርጃ ምክንያት ከአሜሪካ የሚባረሩ ሰዎችን ለመቀበል ከትራምፕ አስተዳደር 5.1 ሚሊዮን ዶላር መቀበሉን አረጋገጠ።
በንጉሥ ምስዋቲ ሦስተኛ ንጉሣዊ አገዛዝ የምትመራው ኢስዋቲኒ፤ ከአሜሪካ የሚባረሩ ስደተኞችን ለመቀበል ከትራምፕ መንግሥት ጋር ስምምነት ማሰሯ ከመብት ተሟጋች ቡድኖች ከፍተኛ ወቀሳ አስነስቷል።
ሰኞ ዕለት በአገሪቱ ፓርላማ በቀረቡበት ወቅት ይህ ጥያቄ የቀረበላቸው የፋይናንስ ሚኒስትሩ ኒል ሪክኤንበርግ መንግሥት ከአሜሪካ ገንዘብ መቀበሉን አረጋግጠዋል።
"ከአሜሪካ ለሚባረሩ [ሰዎች] እንደሆነ የተነገረን ከጠየቅን በኋላ ነው" ሲሉ የሚመሩት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ስለ ሂደቱ መረጃ እንዳልነበረው መናገራቸውን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ዘግቧል።
መስከረም ላይ፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዎች የስምምነቱን ቅጂ መመልከቱን አስታውቆ ነበር። ስምምነቱ፤ ኢስዋቲኒ 160 የሚባረሩ ሰዎች እንደምትቀበል እና በምላሹ የአሜሪካ መንግሥት "ለድንበር እና ስደት አስተዳደር አቅም" ለመገንባት የሚውል 5.1 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሰጥ ማስፈሩን ገልጾ ነበር።
ኢስዋቲኒ እስካሁን ድረስ በሁለት ዙር ሐምሌ እና ጥቅምት ላይ ስደተኞችን ተቀብላለች። ወደ አገሪቱ ከገቡት ተመላሾች ውስጥ አንዱ መነሻው ወደሆነችው ጃማይካ ተልኳል።
የኢስዋቲኒ መንግሥት ተወካይ ቃለ አቀባይ ታቢሌ ምድሉሊ፤ ሌሎች ሰዎችንም ወደ መነሻ አገራቸው ለመመለስ "ግንኙነቶች" በሂደት ላይ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"በሂደት ሁሉም [መነሻ አገራቸው] ይመለሳሉ" ብለዋል።
የፋይናንስ ሚኒስትሩ ሪክኤንበርግ፤ ከአሜሪካ የተሰጠው 5.1ሚሊዮን ዶላር በአገሪቱ የብሔራዊ አደጋ አስተዳደር ኤጀንሲ አካውንት ውስጥ እንደተቀመጠ መናገራቸውን የኤኤፍፒ ዘገባ ያመለክታል።
ይሁን እንጂ የአደጋ አስተዳደር ተቋሙ ገንዘቡ በቀጥታ ከመንግሥት የተመደበለት ባለመሆኑ መጠቀም እንደማይችል ገልጸዋል። የአሜሪካ መንግሥት ክፍያ ወደ መደበኛ መንገድ መግባት እንደሚኖርበት አስረድተዋል።
አገሪቱ መንግሥት ገንዘብ መቀበሉን ሲያረጋግጥ ይህ የመጀመሪያው ነው። ከቢቢሲ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት ምድሉሊ ግን የአሜሪካ መንግሥት ከሚያባርራቸው ሰዎች ጋር አብሮ ገንዘብ የሚያቀርብ መሆኑን በተመለከተ የኢስዋቲኒ መንግሥት "ሁሉም ግልጽ" እንደነበር ተከራክረዋል።
በቃል አቀባይዋ ገለጻ መሠረት ገንዘቡ ተባርረው የሚመጡትን ሰዎች "መሠረታዊ አቅርቦቶች እና መመለሻ ወጪዎች" እንዲሁም "በኢስዋቲኒ ከሚኖራቸው ጊዜያዊ ቆይታ ጋር የተያያዙ ሌሎች ወጪዎችን" ለመሸፈን የሚውል ነው።
በኢስዋቲኒ የሚገኙ ጠበቃዎች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ቡድኖች በበኩላቸው መንግሥት የተባረሩ ሰዎችን ለመቀበል የደረሰው ስምምነት ሕጋዊነትን በተመለከተ ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበዋል።
የአገሪቱ መንግሥት ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ የመድረስ ሥልጣን እንዳለው በመግለጽ የቀረበበትን አቤቱታ እየተከላከለ ነው።
ቃል አቀባይዋ ምድሉሊም በተመሳሳይ የተባረሩ ሰዎችን ለመቀበል የሚደረስ ስምምነት ከአሜሪካ መንግሥት ጋር የሚኖርን "ግንኙነት" እንዲሁም "የሚኖርን አቅም" እንደሚያጠናክር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኢስዋቲኒ እስር ቤት አስተዳደር የተባረሩት ሰዎች "ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እየተስተናገዱ" መሆኑን እና በሕዝብ ላይ ስጋት እንደማይጋርጡ ከዚህ ቀደም አስታውቋል።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከዚህ ቀደም ከጃማይካ፣ ኩባ፣ ላኦስ፣ ቬትናም እና የመን የሚመጡ ስደተኞችን "ነውረኛ ጭራቆች" በማለት ገልጿቸው ነበር።
በሁለቱ አገራት መካከል የተደረገው ስምምነት የኢስዋቲኒ ጎረቤት የሆነችው ደቡብ አፍሪካን አስደንግጧል። ደቡብ አፍሪካ የተባረሩት ሰዎች ድንበር አቋርጠው ወደ አገሪቱ ይገባሉ የሚል ስጋቷን ገልጻለች።
ከዚህ ቀደም ስዋዚላንድ ተብላ ትጠራ የነበረችው ኢስዋቲኒ በደቡብ አፍሪካ እና ሞዛንቢክ የተከበበች የባሕር በር አልባ አገር ነች። ከአውሮፓውያኑ 1986 ጀምሮ እየተመራች ያለችው በንጉሥ ምስዋቲ ሦስተኛ ነው።















