በዩናይትድ ኪንግደም ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት 20 ዓመት የሚያስጠብቀው አዲሱ የስደተኞች ሕግ

በሕገወጥ መንገድ ወደ ግዛቷ የሚገቡ ስደተኞችን ለመቆጣጠር የተለያዩ አርምጃዎችን ስትወስድ የቆየችው ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የተለያዩ አዲስ መንገዶችን ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድ ይዛለች።
የዚህ አዲስ ዕቅድ መሪ የሆኑት የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሻባና ማህሙድ ባለፉት ቀናት ተግባራዊ እንዲሆኑ ያቀረቧቸውን ሃሳቦች ይፋ አድርገዋል።
ሰኞ ኅዳር 8/2018 ዓ.ም. ለአገሪቱ ምክር ቤት አባላት ሚኒስትሯ በሚያሰጡት ማብራሪያ ላይ ሕገወጥ ስደተኞች ከአገር እንዲወጡ ከመደረጉ በፊት በተደጋጋሚ ይግባኝ የሚሉበት መንገድ የሚያበቃበትን ዕቅድ ይፋ ያደርጋሉ።
በሕገወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ የገቡ ስደተኞችን የሚመለከቱ ከሰብዓዊ መብቶች ጋር የተያያዙ ሕጎች ላይም ማሻሻያዎች እንዲደረጉ የሚፈልጉ ሲሆን፣ ይህም ለውይይት ቀርቧል።
ይህ የሚኒስትሯ ሃሳብ ስደተኞች ወደ ዩኬ በሕገወጥ መንገድ እንዲገቡ የሚያበረታቱ ምክንያቶችን የሚያስወግዱ ናቸው በማለት ዕቅዱ ተቀባይነት እንዲያገኝ ሚኒስትሯ እየተከራከሩ ነው።
ሻባና ማህሙድ ለዩናይትድ ኪንግደም ምክር ቤት አባላት የዕቅዳቸውን ዝርዝር የሚያቀርቡ ሲሆን፣ የሚከተሉት በዝርዝር ከሚያነሷቸው ጉዳዮች ዋነኞቹ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
በዩኬ ጥገኝነት የሚሰጣቸው ስደተኞች በዘላቂነት በአገሪቱ ውስጥ ለመኖር የሚያስችለውን ቋሚ መኖሪያ ለማግኘት ለማመልከት 20 ዓመታትን መጠበቅ የሚኖርባቸው ሲሆን፣ በቀደመው አሠራር ግን ይህንን ሂደት በአምስት ዓመት ውስጥ መጀመር ይችሉ ነበር።
ይህም ለስደተኞች የሚሰጠውን የጥገኝነት መብት ጊዜያዊ የሚደረግ ሲሆን፣ በየሁለት ዓመት ተኩል እየተመረመረ ውሳኔ ይሰጣል። ስለዚህም ስደተኞቹ የመጡባቸው አገራት አስተማማኝ ደኅንነት አለባቸው ተብሎ የሚታመን ከሆነ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ሊደረጉ ይችላሉ።
እንዲሁም ከዩኬ እንዲወጡ የሚደረጉ ስደተኛ ዜጎ��ቸውን ለመቀበል ተባባሪ በማይሆኑ የአፍሪካ አገራት ላይ የቪዛ ክልከላ የመጣል ሃሳብ በዕቅዱ ውስጥ ተካትቷል።
በዚህም መሠረት በተለይ አንጎላ፣ ናሚቢያ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ በስም ተጠቅሰው እርምጃው ተግባራዊ ሊደረግባቸው እንደሚችል ተጠቅሷል።
በሰብአዊ መብቶች ሕግ ላይ ከስደተኞች አንጻር የቤተሰብ ሕይወት መብት ትርጓሜ ጉዳይ ለውጥ ይደረግበታል ተብሏል። በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የቅርብ የቤተሰብ አባል ያላቸው ስደተኞች ብቻ በአገሪቱ ውስጥ እንዲቆዩ ሊፈቀድላቸው ይችላል።
ዕቅዱ ከእነዚህ ዋነኛ ጉዳዮች በተጨማሪ በሕገወጥ መንገድ ወደ ዩኬ የሚገቡ ስደተኞችን ፍልሰት ለማስቆም ያስችላል የተባሉ ተጨማሪ እርምጃዎችን ያካተተ ነው።
ይህ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዕቅድ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ መነጋገሪያ ከመሆኑ በተጨማሪ ከሌበር ፓርቲ የፓርላማ አባላት በኩል ተቃውሞ ገጥሞታል።
በርካታ ስደተኞች በኢንግሊሽ ቻናል በኩል በትናንሽ ጀልባዎች በመሳፈር ወደ ዩኬ የሚገቡ ሲሆን፣ ከአውሮፓውያኑ 2023 ጀምሮ በየዓመቱ ከ30 ሺህ በላይ ስደተኞች በሕገወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ እየገቡ ማሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ዩኬ ይህንን የስደተኞችን ፍልሰት ለመቆጣጠር የተለያዩ ጥረቶችን ብታደርግም ሊሳካላት አልቻለም። አሁን ደግሞ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ስደተኞችን የማያበረታታ ያሉትን ዕቅድ ለምክር ቤት አቅርበው ተቀባይነት እንዲያገኝ እየጣሩ ነው።















